Tuesday, May 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በኬሚካል ማዳበሪያ ምትክ በደቂቅ አካላት ዘር ማብቀል እንደሚቻል ተገለጸ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

ደቂቅ አካላት (Micro Organisms) በየትኛውም በዓለም ክፍል፣ በየትኛውም ሥርዓተ ምኅዳርና ሥፍራ ስለሚገኙ፣ የኬሚካል ማዳበሪያን በመተካት ዘር ለማብቀል እንደሚያስችሉ የኢትዮጵያ ብዝኃ ሕይወት ኢንስቲትዩት ተመራማሪ አስታወቁ፡፡

በኢንስቲትዩቱ የደቂቅ አካላት ብዝኃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ተመራማሪ አቶ ዘሪሁን ፀጋዬ፣ የጤፍ ምርታማነትን ለመጨመር የሚረዳ የምርምር ሥራ ማቅረባቸውን ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡ ተመራማሪው፣ ‹‹ደቂቅ አካላትን እንደ ማዳበሪያ ብንጠቀም ምርታማነትን በማሳደግ፣ ለኬሚካል ማዳበሪያዎች የሚወጣውን ወጪና የኬሚካል ማዳበሪያዎች የሚያደርሱትን የጎንዮሽ ጉዳት መቀነስ እንችንላለን፤›› ማለታቸው ተመልክቷል፡፡

ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ለፅዕዋት ዕድገት ማፋጠኛ የሚሆኑ ደቂቅ አካላትን ለመለየት፣ በአጠቃላይ 1,375 የጤፍ አፈርና የጤፍ ሥር ናሙናዎች መሰብሰባቸውን ተመራማሪው አስረድተዋል፡፡ ከተሰበሰቡት ናሙናዎች በላቦራቶሪ ግምገማ 38 የባክቴሪያና 17 የፈንገስ በድምሩ 55 ከፍተኛ አቅም ያሳዩ ዝርያዎች መለየታቸውን ገልጸዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት በቤተ ሙከራና በመስክ በማሳ ላይ ለሚያካሂዱት የምርምር ሥራቸው፣ አራት የባክቴሪያና ሁለት የፈንገስ ዝርያዎች በድምሩ ስድስት የደቂቅ አካላት ዝርያዎች እንደተጠቀሙ አቶ ዘሪሁን ጠቁመዋል፡፡ ኢትዮጵያ በጤፍ ሰብል የምትታወቅ እንደ መሆኗ፣ ምርምራቸውን አርሶ አደሮች እየተጠቀሙባቸው ያሉ ሁለት የጤፍ ዝርያዎችን መጠቀማቸውን አክለዋል፡፡

ተመራማሪው በቤተ ሙከራ (ግሪን ሐውስ) እና በመስክ ማሳ ላይ ደቂቅ አካላትን ብቻ በመጠቀም፣ ደቂቅ አካላትን ከኬሚካል ማዳበሪያ ጋር አደባልቆ በመጠቀምና ደቂቅ አካላትንና ኬሚካል ማዳበሪያን ሳይጠቀሙ ጤፍ በመዝራት ሙከራ ማድረጋቸው ተገልጿል፡፡

በውጤቱም ደቂቅ አካላትን በመጠቀም የተዘሩት የጤፍ ዝርያዎች እጅግ በተሻለ ሁኔታ መብቀላቸውንና ግንዳቸው ወፍራም፣ ቅጠላቸው ሰፋፊ፣ ዛላቸው ረዣዥምና ቁመታቸው ከሰው ቁመት ርዝመት እኩል በሚባል ደረጃ እስከ 1.73 ሜትር እንደሆናቸው ተመራማሪው አስታውቀዋል፡፡ ‹‹በዚህ መሠረት በአንድ ዘለላ ብዙ ዘሮችን በመያዝ ከፍተኛ ምርት ሊሰጡ እንደሚችሉ ማሳያ ነው፤›› ሲሉ ተመራማሪው ገልጸዋል፡፡

በኢንስቲትዩቱ የደቂቅ አካላት ብዝኃ ሕይወት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ገነነ ተፈራ (ዶ/ር) እንደ ባክቴሪያ፣ ፈንገስና ሌሎች ደቂቅ አካላት በሽታ አምጪ ብቻ ተደርገው መወሰድ እንደሌለባቸው፣ በአግባቡ ጥቅም ላይ ከዋሉ የሚሰጡት አገልግሎት ከፍተኛ ነው ብለዋል፡፡ ‹‹ደቂቅ አካላት በብዛት አፈር ውስጥ የሚገኙ ቢሆንም፣ በተገቢው ቦታ ጥቅም ላይ ብናውላቸው ዕፅዋት የሚያስፈልጋቸውን የተሟላ ንጥረ ነገር እንዲያገኙ በማድረግ ያለ ችግር እንዲበቅሉና ራሳቸውን ከበሽታ መከላከል እንዲችሉ የማድረግ ባህሪ አላቸው፤›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በሦስት ዓመት ለማጠናቀቅ የታቀደው ይህ የምርምር ፕሮጀክት፣ ከኢኖቬሽንና ከቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በተገኘ ድጋፍ ለሁለት ዓመታት እየተከናወነ መሆኑ ተገልጿል፡፡

የኢንስቲትዩቱ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ፈለቀ ወልደየስ (ዶ/ር)፣ በዚህ የምርምር ሥራ የታየው ውጤት የአገር በቀል የዛፍ ዝርያዎችን ብቅለት ለማፋጠን የሚውል መሆኑ ጭምር ጠቃሚ ጎን መሆኑን ጠቁመው፣ ኢንስቲትዩቱ ተመሳሳይ ምርምሮችን በማከናወን ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ለማድረግ በትኩረት ይሠራል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች