Wednesday, December 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማቆም መቀመጫን ማደላደል ይቅደም!

አምስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አራተኛው የሥራ ዘመን፣ በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት ውስጥ ለአስቸኳይ ስብሰባ ካልተጠራ በስተቀር ሥራውን አጠናቋል፡፡ በሚቀጥለው አዲሱ ዓመት በመስከረም ወር የመጨረሻው ሰኞ አምስተኛውን የሥራ ዘመኑን ይጀምራል፡፡ አምስተኛው የሥራ ዘመን ደግሞ የምክር ቤቱ የመጨረሻው የሥራ ዘመን ይሆናል ማለት ነው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአምስት ዓመት የሥራ ዘመን ከማብቃቱ በፊት አንድም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥያቄና በራሱ በምክር ቤቱ ፈቃድ፣ ወይም በፖለቲካ ፓርቲዎች ጣምራነት አለመቀጠል ምክንያት ተበትኖ አዲስ ምርጫ ሊካሄድ ይችላል፡፡ ነገር ግን ከዚህ በፊት በዚህ ዓይነት ሁኔታ ምርጫ ተካሂዶ አያውቅም፡፡ የምክር ቤቱ አምስተኛ ዘመን ግን እስካሁን ድረስ የምርጫ ዓመት ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዚህ መሠረት 2012 ዓ.ም. ስድስተኛው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚመረጥበት የምርጫ ዘመን ይሆናል ማለት ነው፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ ተከብሮ አያውቅም እንጂ 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ 25ኛ ዓመት ጭምር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አለ ሲባል ኢሕአዴግ የመጀመርያው አይደለም፡፡ ደርግም ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አቋቁሜያለሁ ብሎ ነበር፡፡ ደርግም ኢሕአዴግም አቋቁመናል ቢሉም፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ግን በነፃና ባልተጭበረበረ ምርጫ ድምፁና ፍላጎቱ ተገናኝቶ የፈቃዱ ውጤት የሆነ መንግሥት ዓይቶ አያውቅም፡፡ አሁን የተገባበትን ለውጥ ያመጣውም ይኼ ፅኑ ፍላጎት ነው፡፡

ኢትዮጵያ ዕውን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ናት ወይ ተብሎ ሲጠየቅ፣ ሕዝብ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ ነው ወይ? መንግሥታዊ ሥልጣን ከሕዝብ ሿሚነትና ጠያቂነት ጋር ተገናኝቷል ወይ? ምክር ቤቶች የሕዝብ ጥያቄዎችና ብሶቶች የሚስተጋቡባቸውና የሚመከርባቸው ናቸው ወይ? ሪፐብሊክነት ከስያሜና ከወግ ያለፈ ነው ወይ? ሕዝብ ተወካዮቹን፣ ተወካዮቹ ደግሞ ሥራ አስፈጻሚውን መንግሥት መግራትና መቆጣጠር ይችላሉ ወይ? ሕዝብስ በእርግጥ ተወካዮች አሉት ወይ? ሕዝብ፣ በየደረጃው ያሉ ምክር ቤቶችና አባሎቻቸው ለሥራ አስፈጻሚው አካል አጎንብሶ አዳሪ መሆናቸው ለምን በየጊዜው እየባሰበት መጣ? ወዘተ. ማለት ነው፡፡ ለውጡ እንዲመጣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ምክንያት የሆኑትን እነዚህን ጥያቄዎች የተሸከሙ ቅሬታዎች፣ ቅያሜዎች፣ ብሶቶችና ተቃውሞዎች መሆናቸው ይታወቃል፡፡ የለውጡ መነሻና መድረሻ ተብሎ የሚታሰበው ደግሞ፣ እውነኛ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መመሥረት ነው፡፡ ለዚህ ፍላጎት ዕውን መሆን መቀመጫን ማደላደል የግድ ይሆናል፡፡

  የሕዝብ ሉዓላዊነትን የመጎናፀፍ ወይም ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የመገንባት ጉዳይ የመንግሥት አውታራትን (የአስተዳደር፣ የጦር፣ የፀጥታና የደኅንነት ተቋማትን፣ ወዘተ.) ከፓርቲ ወገናዊነት ነፃ ማውጣትና ገለልተኛ ማድረግ፣ እውነተኛ የሆነ የፓርቲ ውድድር ወይም ፉክክር ዕውን ማድረግ፣ ባልተጭበረበረ ምርጫ የሕዝብ ምክር ቤቶችን ማደራጀትና ከዚያም በላይ ይጠይቃል፡፡ ዴሞክራሲን የማንኛውም ፓርቲ ተቀፅላ ባልሆኑ ተቋማት ላይ መገንባት ይገባል፡፡ የለውጡ ተዋናዮች ዋና ዓላማ በፍትሐዊና በእኩልነት ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር ውስጥ መኖር እንደሆነ ስለሚጠበቅ፣ መጀመርያ በመረባረብ ለውጡን የማይቀለበስበት ደረጃ ላይ ማድረስ ለነገ የሚባል መሆን የለበትም፡፡ በዚህ እሳቤ ላይ በመመሥረት የኢትዮጵያን የሥልጣንና የመንግሥት አውታራት ከየትኛውም ፖለቲካዊ ቡድን ታማኝነትና ተፅዕኖ ማላቀቅ፣ ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የማድረግ የመጀመርያው የመነሻ ዕርምጃ ይሆናል፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ አምባገነንነትንና የፓርቲ ወገናዊነትን እንዲያገለግሉ የተቀናበሩ መንግሥታዊ አውታራት፣ ለሕዝብና ለሕግ ብቻ ታምነው ሊያገለግሉ ስለማይችሉ ነው፡፡ ይህ ትልቅ ትኩረት የሚያስፈልገው መሠረታዊ ጉዳይ ነው፡፡

ከዚህም በተጨማሪ ለምሳሌ የአገሪቱ የጦርና የፀጥታ ኃይሎች ከየትኛውም የፖለቲካ ቡድን ወገናዊነትና መከፋፈል ርቀው መቆየት የሚችሉት፣ የታሰበው ዓላማ እንዲሳካ አስፈላጊዎቹ ነገሮች ሲደረጉ ብቻ ነው፡፡ በሕዝብ መካከል የመከፋፈልና የመጠፋፋት ሥጋትና አደጋን ማምለጥ ወይም መከላከል የሚቻለውም፣ ዴሞክራሲን ወገንተኛ ባልሆኑ አውታራት ላይ የመገንባት ግዳጅን ቀዳሚ የማድረግ ፍላጎት ሲኖር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ እንደሚታወቀው በለውጡ ተዋንያን መካከል ዓይነተ ብዙ የአቋም ወይም የዝንባሌ ልዩነቶች አሉ፡፡ የትኛውም ዓይነት ልዩነት በጭራሽ ሊያጣላ አይገባም፡፡ ልዩነቶች የሚያጣሉት የተለያየ አቋምና ግብ ስላለ ሳይሆን፣ በዴሞክራሲያዊ ቅፅር ውስጥ ማሰብና መኖር ባለመለመዱ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ኖረም አልኖረ፣ ሕገ መንግሥቱ ተሻሻለም አልተሻሻለ፣ ለኢትዮጵያ የሚበጃት ፌዴራሊዝም ወይም አሀዳዊነት፣ ወዘተ. ልዩነቶች ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን በዴሞክራሲያዊ አስተሳሰብና ማዕቀፍ ውስጥ መንቀሳቀስ እስካልተፈለገና እስካልተቻለ ድረስ ልዩነቶች ያጣላሉ፡፡ ልዩነቶች ማጣላት የለባቸውም የሚባለው፣ የልዩነት ባለቤቶች ለሕዝብ ፍላጎት የመገዛትና በሕዝብ እውነኛ ድምፅ መሠረት መወሰን ይችላሉ በሚል ነው፡፡ ይህንን ተግባራዊ ለማድረግ ገለልተኛ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈልጋል፡፡ ይህንን ማድረግ ሲቻል ልዩነትን ይዞ ለጋራ ዓላማ በአንድነት መቆም ይቻላል ማለት ነው፡፡

ዴሞክራሲን ፅኑ መሠረት ለማስያዝ መሠረቱ ሕዝብ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ካሁን በኋላ እንደ ትልቅ ድል የሚቆጥረው የዚህኛው ወይም የዚያኛው አማራጭ ወይም አቋም ማሸነፍን ሳይሆን፣ አማራጮች በእርጋታ ተገላብጠውና በሚገባ ተመክሮባቸው በራሱ ድምፅ በነፃነት ሲወስንባቸው ነው፡፡ ይህም አሠራር ዘለቄታዊ የሚሆነው መሠረቱ ሲጠብቅ ነው፡፡ በመሆኑም የሁሉም ኢትዮጵያውያንና የፖለቲካ ተዋንያን ርብርብ መሆን ያለበት ከዚህ ቀደም አይጥና ድመት የነበሩ ቡድኖችም ሆኑ፣ ከአንድ ዓመት ተኩል ወዲህ ግልብጥብጣቸው የወጣው የኢሕአዴግ አባል ድርጀቶች፣ በሕግ ማዕቀፍ ውስጥ ሆነው ዴሞክራሲያዊ አገር ለመገንባት መሰባሰብ ላይ ሲያተኩሩ ነው፡፡ ነፃ ማኅበራት ነፃ የሕዝብ ተሳትፎዎች እንዲናኙና ነፃ የፖለቲካ አየር እንዲፈጠር መጠናከር ይኖርባቸዋል፡፡ በዚህ አየር ውስጥ የፖለቲካ ወገንተኝነት የሌላቸው የዴሞክራሲ ተቋማትና አውታራት መብቀል አለባቸው፡፡ በቀጣዩ ምርጫም ከቡድኖች የፖለቲካና የድምፅ ትርፍ ይልቅ፣ ጤናማ የሆነ የምርጫ ዘመቻና ያልተጭበረበረ የድምፅ ሥርዓት ሥር ማስያዝ ማስጨነቅ ይኖርበታል፡፡ ለዚህም የፓርቲዎች፣ የአባሎቻቸውና የሕዝብ ንቃተ ህሊና መጎልበት አለበት፡፡ በአሸናፊ ፓርቲ መመራት ማለት የሕዝብ ነፃ ምርጫን ማደላደል ማለት ነው፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ተቀባይነት፣ አሸናፊነትና ገዥነት በፕሮግራሙ ፋይዳና በፍትሐዊና በነፃ ምርጫ ላይ የተንጠላጠለ የሚያደርገው፣ ፓርቲው ከሌሎች ፓርቲዎች አቋሞች ጋር ገጥሞ ሐሳብን በሐሳብ መርታቱን በሕዝብ ድምፅ ሲያረጋግጥ ብቻ ነው፡፡ ለዚህ ለሚያበቃ ሥርዓት ሳይታገሉና ጥረት ሳያደርጉ፣ እኔ ብቻ ልክ ስለሆንኩ ላሸንፍ ማለት ጨዋታውን አለማወቅ ነው፡፡ መቀመጫን ማደላደል የሚያስፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ለማቆም ነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...