Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮ ቴሌኮም የሦስት ዓመት ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ይፋ አደረገ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የንብረት ትመና እንዲሠራለት ኬፒኤምጂን ቀጠረ

ሞባይል መኒ አገልግሎት ለመጀመር ብሔራዊ ባንክን ፈቃድ ጠየቀ

ኢትዮ ቴሌኮም በመጪው ሦስት ዓመት የሚተገብረውን ስትራቴጂካዊ ዕቅድ ይፋ አደረገ፡፡

ከሐምሌ 2011 እስከ ሰኔ 2014 ዓ.ም. ተግባራዊ የሚደረገው ‹ብሪጅ› የተሰኘው ስትራቴጂካዊ ዕቅድ መንግሥት የቴሌኮም ገበያውን ለመክፈት በዝግጅት ላይ ባለበት ወቅት በመሆኑ ኩባንያውን ተወዳዳሪ፣ ብቁና ተመራጭ ሊያደርገው የሚችል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ታምሩ ዓርብ ነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. በጽሕፈት ቤታቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ እንደ ከዚህ ቀደሙ ኩባንያው ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ የሚጠይቅ ግዙፍ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩት ገልጸዋል፡፡ ‹‹አገሪቱ በገጠማት የውጭ ምንዛሪ እጥረትና በሌሎች ነባራዊ ሁኔታዎች ምክንያት የ1.2 ቢሊዮን ዶላር ማስፋፊያ ፕሮጀክት አይኖረንም፤›› ያሉት ወ/ሪት ፍሬሕይወት ቀስ በቀስ የሚካሄዱ የዕድገት ጉዞዎች እንደሚኖሩ ገልጸዋል፡፡

ያሉትን መሠረተ ልማቶች በአግባቡ በመጠቀም፣ የተወሰኑ የማስፋፊያና የማሻሻያ ሥራዎች በመከወን የድርጅቱን ዕድገት የማስቀጠል  መርሐ ግብር መነደፉን ተናግረዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም በርካታ አዳዲስ የአገር ውስጥና የውጭ አገልግሎቶች ለመጀመር ያቀደ ሲሆን ከእነዚህም መካከል ኢንተርኔት ኦፍ ቲንግስ፣ አፕሊኬሽን ፕሮግራም ኢንተርፌስ፣ ሞባይል መኒና ዳታ ክላውድ አልግሎቶች ይገኙበታል፡፡

የሞባይል መኒ አገልግሎት የቅጣት፣ የአገልግሎት የመሳሰሉትን ክፍያዎች ለመፈጸም የሚያስችል ሲሆን፣ እስከ 2025 ከሞባይል መኒ 13 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማመንጨት እንደሚቻል ወ/ሪት ፍሬሕይወት ገልጸዋል፡፡ አገልግሎቱን ለመጀመር ለብሔራዊ ባንክ የፈቃድ ጥያቄ ማቅረባቸውን ገልጸው፣ ፈቃዱን ካገኘ ኩባንያው አገልግሎቱን ለመስጠት የሚያስችል መሠረተ ልማት እንዳለው አስረድተዋል፡፡

የተጠቃሚዎች ፍላጎት ከድምፅ የበለጠ ወደ ዳታና ኢንተርኔት እየተለወጠ በመሆኑ፣ ኩባንያው የሞባይል ኔትወርክ ሽፋን በአዲስ አበባና በክልሎች እንደሚያስፋፋና እንደሚያሻሽል ገልጸዋል፡፡ በአዲስ አበባ ዳርቻ ላይ የተገነቡ ኮንዶሚኒየም ቤቶች የሞባይል ኔትወርክ ማስፋፊያ ሥራዎች ከተካሄዱ በኋላ የለሙ በመሆናቸው፣ በቂ የአገልግሎት ሽፋን ስለማያገኙ በእነዚህ አካባቢዎች የማስፋፊያ ሥራዎች እንደሚከናወኑ ገልጸዋል፡፡ የ4G ሞባይል አገልግሎት በአዲስ አበባና ዋና ዋና የክልል ከተሞች እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ የ4G ሞባይል ኔትወርክ አገልግሎት በአዲስ አበባ 332 ቦታዎች የሚገኝ ሲሆን፣ 400,000 ያህል ደንበኞች የማስተናገድ አቅም አለው፡፡

ስትራቴጂካዊ ዕቅዱ በሦስት ዓመት ተከፍሎ የሚተገበር ነው፡፡ በመጀመርያው በጀት ዓመት (2012) 5.1 ሚሊዮን ተጨማሪ ደንበኞችን ማስተናገድ የሚችል የሞባይል ኔትወርክ አቅም ለመገንባት አቅዷል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም በአጠቃላይ የደንበኞቹን ቁጥር ከ43.6 ሚሊዮን ወደ 50.4 ሚሊዮን ለማሳደግ ነው ዕቅዱ፡፡

የሞባይል ደንበኞችን ቁጥር በ15 በመቶ በማሳደግ 48.3 ሚሊዮን ለማድረስ፣ የዳታና የኢንተርኔት ደንበኞች ቁጥር በ29 በመቶ ወደ 28.7 ሚሊዮን፣ እንዲሁም የመደበኛ ብሮድባንድ ደንበኞችን በ166 በመቶ 240,000 ለማድረስ ማቀዱን አስታውቋል፡፡

ኩባንያው የቴሌ ሥርፀት ከ44.5 በመቶ ወደ 50.5 በመቶ፣ ገቢውን ከ36.3 ቢሊዮን ብር ወደ 45.4 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ አቅዷል፡፡ ከውጭ አገልግሎቶች የሚያገኘውን ገቢ ከ98.3 ሚሊዮን ዶላር ወደ 138.3 ሚሊዮን ዶላር ከፍ ለማድረግ እንዳቀደ ተገልጿል፡፡ ኩባንያው ያሉትን አከፋፋዮች ብዛት ከ168 ወደ 206፣ የቸርቻሪዎችን ቁጥር ከ167,000 ወደ 242,000 እንደሚያሳድግ ተነግሯል፡፡

ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ ስትራቴጂካዊ ዕቅዱን ለማስፈጸም የሚያስፈልገውን የኢንቨስትመንት መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል፡፡ ‹‹የቁጥሩ መጠን ሊለዋወጥ የሚችል ስለሆነ የተሳሳተ ግንዛቤ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በ2012 ዓ.ም. የባለቤትነት ለውጥ አይኖርም፡፡ በ2013 ዓ.ም. ለውጥ ሊኖር ይችላል፡፡ ሌሎች ኦፕሬተሮችም ሊመጡ ይችላሉ፡፡ እነዚህ ኩነቶች የያዝነውን ዕቅድ ሊቀይሩ ስለሚችሉ አሁን አኃዞችን መጥቀስ ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡

የፕራይቬታይዜሽን ዝግጅቱን አስመልክቶ ገንዘብ ሚኒስቴር አስፈላጊውን ጥናትና ዝግጅት በማካሄድ ላይ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ለሁለት ይከፈላል ወይ ተብሎ ለቀረበላቸው ጥያቄ መሠረተ ልማትና አገልግሎት ተብሎ ሊከፈል እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሕግ ሁለት የተለያዩ ተቋማት ይሆናሉ ማለት እንዳልሆነ አስረድተዋል፡፡

ለሒሳብ ሥራ አመቺነትና ሌሎች ኦፕሬተሮች ሲመጡ አንዳንድ የኢትዮ ቴሌኮም መሠረተ ልማቶች እንዲጠቀሙ ሲባል የታሰበ ነገር እንጂ፣ ሁለት ሕጋዊ ሰውነት ይኖራቸዋል ማለት እንዳልሆነ ገልጸው የኢትዮ ቴሌኮም ባለሙያዎች ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር እንደሚመክሩበት ገልጸዋል፡፡

በተያያዘ ዜና ኢትዮ ቴሌኮም የንብረት ቆጠራና ትመና ሥራ እንዲያከናውንለት ኬፒኤምጂ የተሰኘውን ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅት ቀጠረ፡፡ ለፕራይቬታይዜሽኑ ሒደት የንብረት ቆጠራና ንብረት ትመና ሥራ ማከናወን አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ኧርነስት ኤንድ ያንግ፣ ፕራይስ ወተር ሐውስ ኩፐርስ፣ ዲሎይት፣ ግራንት ቶርተንና ኬፒኤምጂ የተባሉ በመስኩ የዳበረ ልምድ ያላቸው ዓለም አቀፍ አማካሪ ድርጅቶችን ዕቅዳቸውን እንዲያቀርቡ ጋብዟል፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ኩባንያዎቹ ያቀረቡትን ዕቅድ ከገመገመ በኋላ፣ ኬፒኤምጂን እንደመረጠ ወ/ሪት ፍሬሕይወት ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

‹‹ኩባንያዎቹ ያቀረቡትን ዕቅድ አወዳድረን ኬፒኤምጂን ከመረጥን በኋላ ድርድር አካሂደን ተፈራርመናል፤›› ብለዋል፡፡ በውሉ መሠረት ኬፒኤምጂ በአዲስ አበባና በክልሎች ያሉትን የኢትዮ ቴሌኮም ጠቅላላ ንብረቶች ቆጠራና ትመና ሥራ በ70 የሥራ ቀናት አጠናቆ ለማስረከብ ተስማምቷል፡፡ ስምምነቱ ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. የተፈረመ ሲሆን፣ ሥራውን በሰባት ቀናት እንደሚጀምር ውሉ ያስረዳል፡፡ ኬፒኤምጂ ለሥራው 970,558 ዶላር እንደሚከፈለው ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች