Friday, December 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርበቋንቋ ውዝግቡ የባለሙያ ምሁራን ዝምታ ይሰበር

በቋንቋ ውዝግቡ የባለሙያ ምሁራን ዝምታ ይሰበር

ቀን:

በአገራችን ኢትዮጵያ በሚከሰቱ ጉዳዮች በመግባባት በማስረጃዎች ቅን ውይይት ከማድረግ ይልቅ፣ አንዱ ወገን የማይቀበለውን በማኅበራዊ ሚዲያ ማውገዝ ሌላኛው ወገን ደግሞ አፀፋው ያልተገባ ምላሽ መስጠት ለሚቀጥለው ትውልድ ምን ክፉ ነገር እንደሚያወርስ ሁሉም መረዳት ይኖርበታል፡፡ በነገራችን ላይ የሥነ ቋንቋ ልሳን የሚለው ቃል ራሱ የመጀመርያዎች የጽሑፍ የታሪክ ባለቤቶች የሱሜራዊያን ጥሬ ቃል ትርጉሙ፣ በአማርኛም ሆነ በሌሎቹ ሴማዊ ቋንቋዎች ተመሳሳይ ትርጉምና ድምፅ ያለው ነው፡፡

በአገራችን የአማርኛና የኦሮሚኛ ቃላት በተለይ አማርኛ ብዙዎችን የውጭ ቋንቋዎች ሳይቀር በመዋስ በማስገባት ማደጉ የተረጋገጠ ነው:: በአማርኛ ቋንቋ ቢገለጹ የሚያረካ ትርጉም የሌላቸውን በሁሉም ያደጉ ቋንቋዎች እንደሚደረገው አማርኛ በመዋስ የበለጠ ዳብሯል፡፡ አማርኛ የመንግሥትና የትምህርት ይፋ ቋንቋ በመሆኑ፣ ከሌሎቹ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የበለጠ ማደጉና መግባቢያ መሆኑ ሊካድ አይቻልም፡፡

ሰዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ የመማር መብታቸው በፍጹም ሳይጣስ ሌሎች ያደጉ የመግባቢያ ቋንቋዎችን ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር መጠቀም በመላው ዓለም የተለመደ ሲሆን፣ በህንድ 41 በመቶ የሚናገሩት የሂንዲ ቋንቋን በሁሉም ግዛቶች የሚማሩትና የሚጠቀሙት ትምህርት ይሁነን፡፡ በአገራችን የሥራ ቋንቋ አማርኛም ሆነ ሌሎቹ ቋንቋዎች የሚገባውን ያህል እንዳያድጉ የብሔርና  የዘር ፍጥጫና ፉክክሩ እንቅፋት መሆኑን፣ ባለሙያው ፕሮፌሰር ፈቃደ አዘዘ ብዙ ጊዜ የመከሩት ሰሚ  በማግኘት  ሁሉን  በሚጠቅም መንገድ በሚዛናዊነት ሁሉም ቋንቋዎች በተለይ ብዙዎችን በማግባባት፣ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ነው ተብሎ የዓለም የቋንቋ  ምርምር ያፀደቀው  የአማርኛው  ጥናት  መስፋፋት በበጎ  መታየት ይኖርበታል፡፡  አማርኛን  የሚናገሩ  ሁሉም የአማራ ብሔር (ዘር) ያለ መሆናቸው ሊታወቅ  ይገባል፡፡                                                                                                                                         

በዓለማችን የማንነት ጥያቄ  በሰፊው በተነሳበት በመካከለኛው ዘመን  ጀርመኖቹ በዋናነት የመንግሥትና የሃይማኖት  ቋንቋ  ከሆነው የዳበረው ላቲን በተጨማሪ የየራሳቸውን ቋንቋ መጠቀም ሲጀምሩ፣ የላቲን ቋንቋን በተጓዳኝነት በሉም የትምህርት ደረጃ ይጠቀሙ እንደነበር ከታሪክ ብንማር በጎ ነው፡፡ ይህ ጸሐፊ የተመረቀበት የድኅረ ምረቃ ዲፕሎማ በአሜሪካ ሳይቀር በላቲን ቋንቋ መጻፉን መመስከር ይፈልጋል፡፡ ሌሎቹም ከፍተኛ የአሜሪካና የአውሮፓ ተቋማት ላቲንን ዛሬም መጠቀማቸው ይስተዋል፡፡ በዓለም የጥንት ታሪኮች ከተዘገቡበት አንዱ የትግርኛና የአማርኛ አባት ግዕዝ በዚሁ መልክ  ለበጎ ዋቢነት የሚረዳ ቅርሳችን ነው፡፡

በዓለም ላይ ያሉ የቋንቋ ምሁራን በቅርቡ መጠቀም የጀመሩት የአማርኛው ቋንቋ ተተኪ መጠሪያ ኢትዮፒክ (Ethiopic) የሚያግባባ፣ ሁሉንም የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የሚያካትት መጠሪያ መጠቀሙ ጥሩ አማራጭ ይሆናል፡፡ ወቅቱ የአማርኛ ቋንቋም ሆነ ሌሎቹ ቋንቋዎች በመዋዋስ ማደጋቸው የታመነበት ሀቅ ነው፡፡ ከውጭ የፋብሪካ ሞተር ዕቃዎች ወደ አማርኛ ሲመለሱ ከሚሰጡት ትርጉም ይልቅ፣ ከውጭ የተወሰዱት የተሻለ መልዕክት አላቸው፡፡

ስለዚህ በአገራችን በቋንቋዎች ጉዳይ የሚሰጡ አባባሎችና መረዳቶች ሁሉንም በሚያካትት ለሁሉም በሚጠቅም መንገድ ይሆኑ ዘንድ፣ የሙያ ሰዎች በተለይ የሥነ ቋንቋ ምሁራንን አልሰማ ያልንበት ዘመን ሊያቆምና ማለቂያ በሌለው የአገራችን ፖለቲካ ባለመጠመድ የትምህርት ብቃትና ዕድገታችን እንዲሻሻል መደማመጥ፣ በቀና መንፈስ መወያየት ይጎለብት ዘንድ ምክሬን እሰጣለሁ፡፡ በዚህ ብርቱ ጉዳይ የመከሩንና ያስተማሩንን ያልሰማናቸውን ታላላቆች ይቅርታ በመጠየቅ ዛሬም ሳይታክቱ ይመክሩን ዘንድ ዝምታቸው ይሰበር እላለሁ፡፡

(ኤዲ (አደፍርስ) ሀብቴ መካሻ፣ ኦማሃ ነብራስካ፣ አሜሪካ)

***

በራሳችን ችግር አጉል መደናገር

ሕይወት ልዩ የተፈጥሮ ፀጋ ናት፡፡ በምድር ላይ የተጠነሰሰችው የዛሬ አራት ቢሊዮን ዓመት ገደማ እንደሆነ ይገመታል፡፡ ይኸውም በአልትራ ቫዮሌት ጨረርና በመብረቅ ተፅዕኖ የሕይወት ፀብ የሆኑት (Amino Acid) እና (Nucleic Acid) ስለሰረፁ እንደሆነ ይታሰባል፡፡ አሁንም ብዙ ዓይነት ዕፅዋትና እንስሳት በምድር ላይ ይኖራሉ፡፡ ድሮ ግን እጅግ ብዙ እንደነበሩና አብዛኞቹም እንደከሰሙ ይታወቃል፡፡ ዕውቀትና ፍቅር የሕይወት ዋና ፀጋዎች ናቸው ይባላል፡፡ በዕውቀት ነገር መለየት ይቻላል፡፡ ፍቅር እርስ በርስ ለመግባባትና በሥራ ለመተባበር ይጠቅማል፡፡ የዘመኑ ሥልጣኔ የሰረፀው በዕውቀትና ፍቅር እንደሆነ ይታሰባል፡፡ የእኛ ፀሐይ ለሕይወት መፍለቅ ትልቅ አስተዋጽኦ አድርጋለች ይባላል፡፡ ሙቀትና ብርሃን በዘላቂነት ትሰጣለች፡፡ ከፀሐይ ያነሰ ለሕይወት በቂ ሙቀትና ብርሃን አይሰጥም፡፡ ግዙፍ ፀሐይ ደግሞ በጥድፊያ ስለሚቃጠል ነዳጁን (Hydrogen) ቶሎ ይጨርሳል ይባላል፡፡ ለሕይወት ግን ልዩ ጥቅም አበርክቷል፡፡ ይኸውም ፀሐይና መሬት ላይ ያለው አተም ሁሉ የተገኘው ከእርሱ ቃጠሎና ፍንዳታ (Supemova) እንደሆነ ይታሰባል፡፡

ነፃነት የሕይወት ልዩ ፀጋ ናት፡፡ ሰው ራሱን ካልገለጸ በቀር ምን እንደሚያስብ ማንም አያውቅም፡፡ ይህ የሰው ቀዳማዊ ነፃነት ነው ማለት ይቻላል፡፡ ሰው በአኗኗሩ ማኅበረሰባዊ እንደ መሆኑ እርስ በርስ ይግባባል፣ ይዋለዳል፡፡ ለሥራና ለችግር ጊዜም ይተባበራል፡፡ ግንኙነቱ ውጤታማ የሚሆነው ግን የእኩልነትና የነፃነት ሥርዓት (ዴሞክራሲ) ሲኖር ነው፡፡ ሥርዓቱ አንድነትና ምርታማነትን ያበለፅጋል፡፡ እንደ ልብ በመንቀሳቀስ የበለጠ ለማወቅና ህልውናን ለማዝለቅ ይረዳል፡፡ እኛ ኢትዮጵያውያን የለመድነው ሥርዓት ግን የበላይነትና የበታችነት፣ ወይም የጌታና የአሽከር ግንኙነት ነው፡፡ እንደ አገር ስንኖር የምንደናገርበት አንዱ ችግር ይህ ነው፡፡

ሰው በዚህ ምድር ሲኖር ሁለት ቁም ነገሮች ያደርጋል ይባላል፡፡ አንዱ ማምረት ሲሆን፣ ሌላው መዋለድ ነው፡፡ ማምረት ምግብን፣ ልብስን፣ ዕቃን፣ በአጠቃላይ ለኑሮ የሚያስፈልጉ ነገሮችን ሁሉ ያካትታል፡፡ መዋለድ ዘር ለመተካት ይጠቅማል፡፡ የሚፋቀሩ ባልና ሚስት ረጅም እንክብካቤ የሚፈልገውን ሕፃን ልጃቸውን ለአቅመ አዳም/ሄዋን ያደርሳሉ፡፡ ማምረትና መዋለድ ግን እኩል አይሄዱም ይባላል፡፡ መዋለድ ፈጣን ማምረት ግን ዘገምተኛ መሆኑ ይታወቃል፡፡ ስለሕዝብ ብዛት የተደረጉ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት ሰው ሲበዛ ትርፉ ድህነት፣ የተፈጥሮ ሀብት መባከንና የእርስ በርስ ግጭት መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ ስለሆነም ራስን መተካት የተሻለ አማራጭ መሆኑ ይታወቃል፡፡

ነጮች ብዙ ሀብት እያላቸው መዋለዳቸውን ይመጥናሉ፡፡ እኛ ደግሞ ‹‹ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሏት››፣ ‹‹እስከ አራት እስከ ሰባት ሚስት ማግባት ይቻላል›› ተብለናል እያልን ብዙ ልጆች እንወልዳለን፡፡ አንዳንዴም በዕድሉ ያድጋል እያልን እዚህም እዚያም ጽንስ እየለኮስን ፍሬውን ሳናይ እንጠፋለን፡፡ በዕድሉ ያደገ ልጅ ሲንከራተት ይኖራል፡፡ ማጅራት መቺ፣ ነገር ጫሪ አክቲቪስት ወይም ባለጌ ይሆናል፡፡ እናም እንደ አገር ስንኖር ሁለተኛ የምንደናገርበት ችግር አለመጠን መዋለድ ነው ማለት ይቻላል፡፡

ምርታማነታችን ዝቅተኛ ነው፡፡ በዓለም ደረጃ ከሌሎች አገሮች ስንነፃፀር ለረዥም ጊዜ ግርጌ ሆነን ቆይተናል፡፡ የውጭ ዕርዳታ ግን ጠቅሞናል፡፡ ስለምርታማነት አምላክ አዳምን ጥሮ ግሮ እንዲኖር መርቆታል ይባላል፡፡ እኛ ምርቃቱን እንደ ዕርግማን የምንቆጥረው ይመስለኛል፡፡ እናም የምናተኩረው ማምረት ላይ ሳይሆን ምርቱን መነጣጠቅ ላይ ነው፡፡ አምላክ ለሰው ልጅ አልብጦ የሰጠው ፀጋ፣ ዕውቀትና ፍቅር መሆኑን ባለመገንዘባችንም በሥልጣኔ ኋላ ቀር ሆነናል፡፡ እንደ አገር ስንኖር ዝቅተኛ ምርታማነት የምንደናገርበት ሦስተኛው ችግር ነው ማለት ይቻላል፡፡

እነኚህን እንቅፋቶች ለማቃናት ብንንቀሳቀስ የተሻለ ኑሮ መቋደስ እንችላለን፡፡ ስለዕውቀትና ፍቅር የበለጠ ስናውቅ ደግሞ ወደ ሥልጣኔ እየገባን ሕይወትን ልናጣጥማት እንችላለን፡፡ ሕወሓትና ሻዕቢያ ስለሰላማዊ ንቅናቄ እንደእነ ጋንዲ ቢያውቁ ኖሮ ፍሬያቸው እያደር ይጎመራ ነበር፡፡ በተለይ ሕወሓት ወደ ትግል ቤቱ አይመለስም ነበር፡፡ ዕውቀትና ፍቅር ቢኖርማ ኖሮ አካባቢው ስለማይቆረቁዝ ወደ ትግልም አይገባም ነበር፡፡

ትኩረት የሚፈልጉ ሌሎች ጉዳዮችም አሉ፡፡ አንደኛው ጉዳይ ሕይወት የሰፀረው ዘለዓለማዊ ከሆኑ ቁስ አካልና ኢነርጂ እንደ መሆኑ፣ ህልውናን የበለጠ ማዝለቅ ይቻል ይሆን የሚል ጥያቄ ነው፡፡ ዘመናዊ ኑሮ መልካም ግንኙነት፣ የተሟላ ምግብ፣ ፍትሕና ሕክም፣ ወዘተ. ዕድሜ እንደሚጨምር ይታወቃል፡፡ በዚህ አቅጣጫ የቱን ያህል መጓዝ እንችል ይሆን?

የመሬት ስበት (Gravitation) እንደ እስር ቤት ህልውና ላይ ተፅዕኖ ያለው ይመስለኛል፡፡ ቀና ቢሉ ሰማይ ዘወትር ስለሆነ ኑሮ ይሰለቻል፡፡ ሞትንም ያፋጥን ይሆናል፡፡ ችግሩ እንዴት ይቀረፋል? በመንኮራኩር 100 ኪሎ ሜትር ወደ ሕዋው መመንጠቅ ከስበት ነፃ ያደርጋል፡፡ ብቃትና ወጪው ግን ሊገታን ይችላል፡፡ ምድር ላይ ወደ ጎን በመንቀሳቀስ ችግሩን መቅረፍ ይቻል ይሆን? በግልጽ የምናውቀው ነገር ሲደብረን ስንናፈስ መታደሳችንን ነው፡፡ ምድር ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ትሾራለች፡፡ ንፋስም ያጅባታል፡፡ እኛም በዚሁ አቅጣጫ ብንንቀሳቀስ የበለጠ እንታደስ ይሆን?

እንቅስቃሴ ተፈጥሯዊ ፀጋ ነው፡፡ በምድር ላይ ከሞላ ጎደል ከዕፅዋት በቀር አብዛኛው ፍጡር ይንቀሳቀሳል፡፡ የዕፅዋት ሥርና አገዳ ማደግ ምናልባት እንቅስቃሴ ይሆን? የሆነ ሆኖ ፍጡር ክልላዊነት (ዘረኝነት) ባህሪ ስላለው እንቅስቃሴን ይገድባል፡፡ ቋንቋ ካወቅንና ቀና ልቦና ካለን ግን ችግሩን እንፈታዋለን፡፡ በቀና ልቦና እንኳን ከሰው ጋር ከአውሬም መግባባት ይቻላል ይባላል፡፡ ለማንኛውም ዘረኝነትን እርግፍ አድርጎ መተው ግን ለሁላችንም ይጠቅማል፡፡ ዘረኝነት ማለት ራስን በራስ ከርቸሌ እንደ ማስገባት ይቆጠራል፡፡

የሰውም ሆነ የሌላ ፍጡር የዘር ምንጩ ‹‹Bacteria Achaea›› እንደሆነ ይነገራል፡፡ ይህም ማለት በዓለም ላይ ያለው ፍጡር ሁሉ ይዛመዳል ማለት ነው፡፡ ስለአምላክ ስንናገር እኛን ይበልጥ ይወደናል፣ በአምሳሉ ሠርቶናል ስንል ትክክል እንሆን ይሆን? በፍጡር ዘንድ ልዩነት የሚንፀባረቀው በተፈጥሯዊ ለውጥ (Evolution) ነው ይባላል፡፡ ለውጡ ግን የት እንደሚያደርስ ግልጽ አይደለም፡፡ ግልጽ የሆነውን ነገር ባለፈው አራት ቢሊዮን የሕይወት ዘመን ብዙ ዓይነት ፍጡር ፈልቋል፣ አብዛኛው ግን ወድሟል ይባላል፡፡

ድንቅና ሚስጥር የሆነችውን ተፈጥሮ በዕውቀትና ፍቅር ስንገላልጣት ልዩና ብሩህ የሆነችውን ሕይወት በአግባቡ እንድንቋደሳት ትጋብዘናለች፡፡ ግብዣውን ካከበርን አምላክን እያደር እናውቀው ይሆናል፡፡ አሁን የምናውቀው ግን የቁስ አካልና ኢነርጂ ልዩ ውህድ መሆናችንን ነው፡፡ ዕድሜአችን አጭር ስለሆነ እንግዳ መሆናችንን እንገነዘባለን፡፡ በዚህች ምድር እንደ ልባችን እንድንኖር ግን እንመኛለን፡፡

(ፍቅሩ አማረ፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...