Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
የሳምንቱ ገጠመኝየሳምንቱ ገጠመኝ

የሳምንቱ ገጠመኝ

ቀን:

ከመሥሪያ ቤቴ ፊት ለፊት በከተማዋ በተለያዩ ቦታዎች ከሚገኘውና በኅብረተሰቡ በሰፊው ከሚታወቀው የሸዋ ዳቦ መካከል አንዱ ቅርንጫፍ ይገኛል፡፡ ምሽት ምሽት ወጣ ብለን ከእዛች ዳቦ ቤት ዳቦ መግዛት የተለመደ ተግባሬ ነው፡፡ በወጣሁ ቁጥር ታዲያ በርከት ያለ ሠልፍ መመልከቴ አይቀሬ ሆኖ ቆይቷል፡፡ በዕድሜ የገፉ አዛውንቶችና አሮጊቶች ወጣት ሴቶችና ወንዶች ታዳጊ ልጆች ሠልፍ ይዘው የዳቦ ወረፋ ሲጠብቁ ማየቴም የተለመደ ነው፡፡ እየመሸ በሄደ ቁጥር ሠልፉ እየተመናመነ ስለሚሄድ በአብዛኛው ገዝቼ እሄዳለሁ፡፡ አልፎ አልፎ ግን ያልቅና በባዶ እበራለሁ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲያ ያ ይሰለቸኝ የነበረው ሠልፍ በአንዴ ጠፋ፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የዳቦ ዋጋ መጨመር እንደሆነ ተረዳሁ፣ ልቤን ባር ባር አለው፡፡ ያስጠላኝ የነበረው ያ ሠልፍ ዳቦ መብላት እየፈለገ ዳቦ ለመግዛት ያልቻለው ወገኔ ትዝ ሲለኝ አዘንኩ፡፡ አሁን ታድያ ያ! ሠልፍ ናፈቀኝ ውስጤ ዳቦ ለመብላት ይሠለፍ የነበረው ወገኔ በአካባቢው የለም፡፡ “ሠልፉ” የመግዛት ፍላጎትን ያሳይ እንደነበር፣ “መጥፋቱ” ደግሞ የመግዛት አቅም ማጣቱን ልቦናዬ ይነግረኛል፡፡

ከጥቂት ዓመታት በፊት የዳቦ መጠን እያነሰ መጥቶ አሮጊት እናቶችና ባልቴቶች  ‹ምነዋ! ኪኒና አሳከላችኋት› ይሉ ነበር፡፡ የዘመኑ ወጣቶች ደግሞ ዳቦ ሲገዙ ዳቦውን ለሸጠላቸው ነጋዴ፣ ‹‹ከምግብ በኋላ ነው ከምግብ በፊት!›› እያሉ መሳለቃቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡ ዳቦን ለመንደርደሪያ ብቻ አይደለም ያነሳሁት፡፡ በአሁኑ ወቅት በገበያ ውስጥ ከፍተኛ ጭማሪ ከሚታይባቸው የምግብና የሸቀጥ ዕቃዎች መካከል አንዱ በመሆኑ እንጂ፡፡

ዳቦ የሱዳንን መንግሥት ነቅንቆ ጣለው ከሚሉት የዋሆች ተርታ ባልሠለፍም ምክንያት ሊሆን ግን አይቻለሁ ሰምቻለሁ፡፡ በከተማችን በተለይ ዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል በስፋት የሚጠቀምባቸው የሚሠራባቸውና ራሱን የሚያስተዳድርባቸው ከሆኑት ሸቀጦችና የምግብ እህሎች መካካል አንዳንዶቹ ሊታመን በማይችል መጠን ሲጨምሩ ተስተውሏል፡፡

ለአብነት ሽንኩርት፣ ካሮት፣ ምስር፣ ጤፍ፣ ዳቦ፣ ድንችና መሰል ሸቀጦች ምክንያታቸው በማይታወቅ ሁኔታ ጨምሯል፡፡ ፓስችራይዝድ ወተት ሳይቀር!! በአትክልት ተራ ያገኘኋት በአትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ የተሰማራችው ወጣት ስለገበያው አወራኋት፡፡ ምላሿ እንዲህ ነበር፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ ራሷን በሽንኩርት አቅም መቻል አቅቷት ከሱዳን ስታስመጣ አይገርምም!!›› ግብፅና ሱዳን እኮ የሚያመርቱት ከእኛው አገር በሚጓዘው ዓባይ ይመስለኛል፡፡ ‹‹ታዲያ ከእናት ምድሯ የሚፈልቀው ዓባይ ሽንኩርት እንኳን ማልማት ይሳነው! ያስገርማል!!›› ብላኝ ልትነግድ ወዳስቀመጠቻቸው አትክልትና ፍራፍሬዎቿ ሄዳ ማስተካከል ያዘች፡፡ ተከተልኳት፡፡ ከሱዳን የሚመጣው ሽንኩርት በኪሎ ሃያ ብር ይሸጣል፣ እያየህም አይደል! በዕድሜዬ እንኳን ከአምስት ብር ዘሎ የማያውቀው ድንች አሥራ አምስት ብር ሲገባ ምን ትለዋለህ! ሽሮ እንኳን በአቅሟ አሥራ አምስት ብር ትግባ አይገርምም!! በቃህ እባክህ ሁሉንም ካወሩት ሆድ ባዶ ይቀራል ይባል የለ!!›› አለችኝ፡፡

ብዙም ላስጨንቃት ስላልፈለግኩ ወደ ውስጥ ዘለቅሁ፡፡ ‹‹አንድ ሜትር በማትሞላ ግድግዳ ላይ ከፍተኛ ግብር እየከፈልኩ እየሠራሁ ነው፤›› የሚለውን ወጣት የገበያው ሁኔታ እንዴት ነው አልኩት፡፡ ‹‹ይኸው እንደምታየኝ ቲማቲም እየነገድኩ ነው ሸማች እኔ ጋር ለመድረስ ስንትና ስንት ሕገወጥ የቲማቲም ነጋዴዎችን አልፎ እንደሚመጣ ልነግርህ አልችልም አይተኸዋልና. . .›› አለኝ፡፡

‹‹ኑሮ ላይ ሽንኩርት ብቻ መሰለህ ላያችን ላይ የወጣው ጤፉስ ብትል የዳቦውን ነገር እርሳው፡፡ ከሚዛን ሚዛን የለው ከዋጋ ዋጋውን አትችለው፡፡ ምናለፋህ የሚሸጥ እንጀራ አሁን ወደ ሰባት ብር እየተጠጋ ነው፡፡ ሦስት ልጆች ያሉት እንዴት ነው ልጆቹን የሚያኖረው. . .›› አለኝ፡፡ ምላሽ የለኝምና አለፍኩት፡፡ በአቦካዶ፣ በማንጎና በፓፓዬ የፍራፍሬ ምርቶች ተከባ መሀል ላይ ወደተቀመጠችው ወጣት ተጠጋሁ፡፡ እዚያው በአትክልት ተራ አትክልትና ፍራፍሬ ንግድ ላይ እንደተሰማራች ትናገራለች፡፡

‹‹የሽንኩርት፣ የድንችና የካሮት ዋጋ መናር ለፍራፍሬ ገበያው መቀነስ ምክንያት አለው፡፡ ሰው እነዚያን አስፈላጊ የሆኑ የምግብ ሸቀጦችን ከገዛ በኋላ ነው ወደ ፍራፍሬው የሚመጣው፤›› ትላለች፡፡ ‹‹እኔም እዚህ ጋር ስነግድ ብታየኝም ቤቴ ስሄድ ሸማች ነኝ፡፡ በርካታ የምግብ እህሎች ጭማሪ አሳይተዋል፡፡ አንድ ጊዜም አይደለ በተከታታይ ይህን ማን ሃይ ይለዋል፡፡ ምነው ስትል ‹ነፃ ገበያ ነው› ይሉሃል. . .›› ብላኝ ሸማች ስለመጣባት ወደእዚው ሄደች፡፡

እኔም የፒያሳን የውስጥ አትክልት ተራ ተሰናብቼ ወደ ፊለፊት ወጣ አልኩ፡፡ ከፊት ለፊት ሰፋፊ ባነሮች ከተለጠፉባቸው መጋዘኖች መካከል ወደ አንዱ ጎራ አልኩ፡፡ ከሱዳን የሽንኩርትናድንች ምርቶች በማስመጣት ሥራ ላይ የተሰማራው የቪፋት አትክልትና ፍራፍሬ አክሲዮን ማኅበር ወኪል አግኝቼ አነጋገርኩ፡፡ በተለይ ከሱዳን የሚገባው ሽንኩርት ባይኖር በአገር ውስጥ ሽንኩርት ገበያውን መቋቋም አዳጋች እንደሆነ ነገሩኝ፡፡ በአገር ውስጥ ምርት ፍጆታውን መሸፈን የማይታሰብ መሆኑን በመግለጽ፡፡ አሁን አንድ ኪሎ ሽንኩርት ከ20 እስከ 22 ደርሷል፡፡ ከሱዳን የሚመጣው ሽንኩርት በጅምላ አንድ ኪሎው በ12 ብር ከሃምሳ ሳንቲም እየተከፋፈለ መሆኑን ማየት ትችላላችሁ አሉኝ፡፡ ከዚህ ቀደም ከመቂናዝዋይ ይቀርብ የነበረው የሽንኩርት ምርት  በሚፈለገው ደረጃ እየቀረበ እንዳልሆነ የሚናገሩት ወኪሉ፣ የምርት አቅርቦት እጥረቱ የዋጋ ጭማሪ  አስከትሏል ባይ ናቸው፡፡

ነጋዴውና አምራቹ በቀጥታ እየተገናኙ አለመሆኑንና በመሀል ደላላዎች የዋጋ ንረት እያስከተሉ በመሆኑ፣ የግብይት ሥርዓቱ ሊስተካከል እንደሚገባም ጠቆሙኝ፡፡ የዋጋ ጭማሪው ምን አመጣው የሚለውን ለመጠየቅ ወደ አዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ዘለቅሁ፡፡ በተነሳው ነጥብ ላይ በተመሳሳይ ለጋዜጠኞች መረጃ ለመስጠት በዝግጅት ላይ የነበሩትን የቢሮው አንድ ኃላፊ አገኘሁ፡፡

ኃላፊው ጭማሪው ፈፅሞ ምክንያታዊ ያልሆነ መሆኑን ይናገራሉ፡፡ የዋጋ ጭማሪ ያደረጉ ነጋዴዎችና ግለሰቦች ሕዝብ እንዲማረር እያደረጉ መሆኑን ገለጹ፡፡ ያልተገባ ጥቅም ማግኘት የሚፈልጉ አካላት የምርት እጥረት እንዳለ በማስመሰል የዋጋ ጭማሪ እያደረጉ፣ ሸማቹንና ማኅበረሰቡን ሥጋት ውስጥ እየከተቱ መሆኑንምተናገሩት ኃላፊው፣ ይህን ለማስተካከልም ቢሮው ዕርምጃ እየወሰደ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡ የነዳጅ ዋጋ ማስተካከያን ተከትሎም ቢሆን በትራንስፖርት ታሪፍ ላይ የተደረገ ጭማሪ አለመኖሩንም አክለዋል፡፡

እስከ ሚያዚያ መጨረሻ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ በማድረግ ሲነግዱ የተደረሰባቸው 6,163 ድርጅቶች መታሸጋቸውን፣ 271 ድርጅቶች የንግድ ፈቃድ መሰረዙንና 80 የሚሆኑ ድርጅቶች ንግድ ፈቃዳቸው መታገዱንም ነው ያስረዱት፡፡ በተለይ መንግሥት የታችኛውን ኅብረተሰብ ለመደጎም በሚያቀርባቸው የዳቦ ስንዴና የመሳሰሉ የምግብ እህሎችን ለኅብረተሰቡ እንዲያዳርሱ ትስስር ከተፈጠረላቸው ድርጅቶች መካከል 263 የሚሆኑትን ድርጅቶች ከትስስሩ እንዲወጡ ማድረጉንም አብራርተዋል፡፡

(ሚስባህ አወል፣ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...