Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየፍትሕ ወር ሲታሰብ ለፍትሕ ማስፈኛ የተገነባው ሽንጣሙ ሕንፃ ትውስታ

የፍትሕ ወር ሲታሰብ ለፍትሕ ማስፈኛ የተገነባው ሽንጣሙ ሕንፃ ትውስታ

ቀን:

በኤልያስ እሸቱ

የፍትሕ አካላት ተብለው የሚጠሩት (የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት፣ የፌዴራል ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ፣ የፌዴራልና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር) ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ በየዓመቱ በግንቦት ወር የፍትሕ ሳምንት በሚል በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብሩ የቆዩ ሲሆን፣ በዚህ ዓመት ግን ጊዜውን ወደ አንድ ወር በማራዘም ‹‹የሕግ ተገዥ ነኝ!›› በሚል መሪ ቃል ማክበር ተጀምሯል፡፡ በብዙዎች ዘንድ ስለፍትሕ ሲነሳ ጎልቶ የሚታየው የፍርድ ቤት ድርሻ ነው፡፡ ግራ ቀኙ ወገኖች የሚከራከሩበት ፍርድ ቤት ለሁሉም ወገኖች አመቺ ሊሆን ይገባል፡፡ በዚህ አጋጣሚ በአዲስ አበባ ከተማ ልደታ አካባቢ የሚገኘውን ከ50 ዓመታት በፊት ለፍርድ ቤት ተብሎ የተገነባውና አሁንም እያገለገለ የሚገኘው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃን በተመለከተ ጥቂት ለማለት ወደድኩ፡፡

     መዲናችን አዲስ አበባ እንዲህ እንደአሁኑ በርካታ ሕንፃዎች ሳይኖሯት በፊት እዚህና እዚያ  አልፎ አልፎ ይታዩ የነበሩት ሕንፃዎች እንደ ብርቅ ይታዩ ነበር፡፡ የዛሬ ሃምሳ አራት ዓመት ከተገነቡት ሕንፃዎች አንዱ የሆነው አሁን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የሚያገለግለው ሕንፃ ነው፡፡

ጥቂት ወደኋላ

ኅዳር 7 ቀን 1958 ዓ.ም. ከቀትር በኋላ ለአገሪቱም ለከተማዋም የዕድገት መገለጫ ከሆኑት ሕንፃዎች የአሁኑን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋናው መሥሪያ ቤትንና ልደታ ምድብ ችሎትንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ክቡን ሕንፃ (ኢትዮጵያ ቴሌቪዥን አጠገብ የሚገኘውን) ለማስመረቅ የአሠሪዎቹ ሹማምንት ወዲያ ወዲህ እያሉ ነው፡፡

በወቅቱ በብር አንድ ሚሊዮን ስምንት መቶ ሃምሳ ሺሕ ብር የተሠራው የጠቅላይ ንጉሠ ነገሥት ፍርድ ቤትና የከፍተኛ ፍርድ ቤት ሕንፃ (የአሁኑ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ) ሊመረቅ ዝግጅቱ ተጠናቋል፡፡ የፍርድ ሚኒስቴር የሥራ ኃላፊዎች ሕንፃውን መርቀው የሚከፍቱትን ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴን እየጠበቁ ነው፡፡ ከዚያም ንጉሠ ነገሥቱ ልዑል መርዕድ አዝማች አስፋወሰን፣ ንጉሣውያን ቤተሰብ፣ ጸሐፌ ትዕዛዝ አክሊሉ ሀብተ ወልድን አስከትለው ዘጠኝ ሰዓት ተኩል ላይ በዓሉ የሚፈጸምበት (የሽንጣሙ ሕንፃ ምርቃት) ቦታ ተገኙ፡፡

ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል የሥራና መገናኛ ሚኒስትር ሚኒስትር፣ ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል የፍርድ ሚኒስትር ስለሕንፃዎቹ አሠራርና ስለሚሰጠው አገልግሎት ማብራሪያ ሰጡ፡፡ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ንግግር ካደረጉ በኋላ የተዘጋጀውን ሪባን በመቀስ ቆርጠው የፍርድ ቤቱን ሕንፃ መርቀው ከፈቱ፡፡ እየተዘዋወሩም ጎበኙ፡፡ የሻምፓኙ ግብዣም ቀጠለ፡፡ ሚኒስትሮች ከፍተኛ የመንግሥት ሹማምንት፣ የፍርድ ቤት ዳኞች፣ ነጋዴዎችና የውጭ አገር መንግሥታት እንደራሴዎች በምርቃቱ ላይ ተገኝተዋል፡፡

የቦታው አመራረጥ

ለፍርድ ቤቱ ሕንፃ መሥሪያ መጀመርያ ተመድቦ የነበረው ሥፍራ የካቲት 12 አደባባይ አቅራቢያ በኪንግ ጆርጅ ስድስተኛ መንገድ ግራና ቀኝ (ከአምስት ኪሎ እስከ ስድስት ኪሎ ያለው ቦታ) ነበር፡፡ ነገር ግን የፍርድ ቤት ሕንፃዎች ከዩኒቨርሲቲው አካባቢ ራቅ ብለውና ለባለጉዳዮቹም አማካይ በሆነ ሥፍራ ቢሠሩ የተሻለ ነው በማለት ይህ የአሁኑ ሥፍራ ተመረጠ፡፡

ቅድመ ግንባታ

ቀደም ብሎ ታስቦ የነበረው ዕቅድ ከሕንፃዎቹ በተጨማሪ ሌሎች የሥራ ክፍሎችን ይዞ ሒሳቡ 3.8 ሚሊየን ብር ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ከጠቅላላ ፕሮጄክት በቅድሚያ ሊደራጁ ለሚገባቸው ሕንፃዎች ለጥናትና ለመሥሪያ 2,151,000 ብር ስለተመደበ ተገቢው ዝርዝር ጥናት በኖር ኮንሰልት ተደርጎ በጨረታ አሸናፊ ከሆነው ሥራ ተቋራጭ አሌክሳንድ ሚሪያሊስ ጋር በሰኔ 1955 ዓ.ም. ውል ተፈረመ፡፡ የመቆጣጠሩን ተግባር በሥራና መገናኛ ሚኒስቴር የቴክኒክ ክፍልና ኖር ኮንሰልት ያከናውኑ ነበር፡፡

የፍርድ ቤቱ ሕንፃና ምድረ ግቢ

የሕንፃው ግንባታ ተቆጣጣሪ መሐንዲስ የነበሩት አቶ ዘገየ በቀለ ዋናው ሕንፃ ለጠቅላይ ንጉሠ ነገሥቱ ፍርድ ቤት ከኋላ ያሉት ሦስቱ ሕንፃዎች ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ችሎት ማስቻያና ጽሕፈት ቤቶች የተሠሩ መሆናቸውን የተናገሩ ሲሆን፣ ባላምባራስ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል ደግሞ የዋናው ሕንፃ ርዝማኔው ሽንጡ እስከዚያ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተሠሩት ሁሉ የበለጠ መልካም ለከተማችንም ውበት የሚሰጥ ነው ብለው ነበር፡፡

ለፍርድ ቤቶቹ ከተመደበው 38,420 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ ሕንፃዎቹ (አሁን የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ዋናው ሕንፃና ሦስቱ ከጀርባ የሚገኙት ሕንፃዎች) የያዙት 3,684 ሜትር ካሬ ነው፡፡

ዋናው ሕንፃ

በወቅቱ እንደተገለጸው ምድር ቤቱ ውስጥ ያሉት ክፍሎች ለዕቃ ቤት፣ ለኤሌክትሪክ ማከፋፈያ ለእስረኞች ማከፋፈያና ለባለጉዳዮች የሚያገለግሉ የንፅህና ክፍሎች የተመደቡ ናቸው፡፡ በምድር ቤቱ ደግሞ ሰፊ የሆነ ዋና መግቢያ፣ የባለጉዳዮች ማረፊያ፣ እያንዳንዳቸው 55 ባለጉዳዮችን የሚይዙ ስድስት ችሎቶች፣ እያንዳንዳቸው 45 ባለጉዳዮችን የሚይዙ ሁለት ችሎቶች፣ 110 ባለጉዳዮችን የሚይዝ አንድ ሰፊ የሆነ ችሎት የዳኞችና የጸሐፊዎች ቢሮዎች እንዲኖሩት ተደርጓል፡፡

የመጀመርያው ፎቅ በወቅቱ (በ1958 ዓ.ም.) ለጠቅላይና ለከፍተኛ ፍርድ ቤቶች ፕሬዚዳንቶች፣ ለጸሐፊዎችና ለጠበቆች ቢሮዎች፣ ሁለተኛው ፎቅ ለጠቅላይ ንጉሠ ነገሥትና ለከፍተኛው ፍርድ ቤት ጸሐፊዎች ለመዝገብ ቤቶች ለግምጃ ቤቶች ለሒሳብ ክፍሎች አገልግሎት የተሠራ ነው፡፡ ሦስተኛው ፎቅ ሃያ አራት ባለጉዳዮችን የሚይዝ አንድ የሰበር ሰሚ ችሎት ነበረው፡፡

ከዋናው ሕንፃ ጀርባ ያሉ ሦስት ሕንፃዎችን

ከዋናው ሕንፃ ጀርባ ያሉት ሦስት ሕንፃዎች እያንዳንዳቸው 50 ባለጉዳዮችን የሚይዙ 12 ችሎቶች አሏቸው፡፡ በሁለቱ ሕንፃዎች በመጀመርያ ፎቅ እንዳንዳቸው 25 ባለጉዳዮችን የሚይዙ ሁለት ችሎቶች የነበሩ ሲሆን፣ በሦስተኛው ሕንፃ ደግሞ የስብሰባ አዳራሽ ነበረው፡፡

ምድር ቤቱ

ምድር ቤቱ ለተዘጉ መዝገቦች እስከ 2003 ዓ.ም. ማስቀመጫ ያገለግል የነበረ ሲሆን፣ እነዚሁ መዝገቦች ወደ ቃሊቲና ቦሌ ምድብ ችሎቶች ተወስደው የተከማቹ በመሆናቸው በአሁኑ ወቅት ግን ከተወሰኑት ክፍሎች በቀር ምድር ቤቱ አብዛኛው ክፍል ባዶ ነው፡፡

የሽንጣሙ ሕንፃ ዕድሳት

ለፍርድ ቤቱ ባለፉት በርካታ ዓመታት ዕድሳት ቢደረግለትም ተገቢው ሙያዊ ጥንቃቄ ያልተደረገለት በመሆኑ ጉዳቱ ከፍ ያለ ነበር፡፡ ከአምስት ዓመታት በፊት የተደረገለት ዕድሳት ግን የተሻለ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ሆኖም በዕድሳቱ ወቅት ከቢሮ ጥበት አኳያ መተላለፊያዎች ላይ የተሠሩ ጊዜያዊ ቢሮዎች ፈርሰው የነበረ ቢሆንም፣ በድጋሚ አሁን ተሠርተው መታየታቸው የሕንፃውን የውስጥ ውበት እንዲበላሽ አድርጎታል፡፡ 

የአሁኑ ገጽታ

በአሁኑ ወቅት ዋናውንና ከኋላ የሚገኙትን ሦስት ሕንፃዎች የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት እየተጠቀመበት ሲሆን በዋናው ሕንፃ ያሉት ዘጠኝ የችሎት አዳራሾች እንዲሁም በጀርባ ካሉት  ሦስቱ ባለ አንድ ወለል ሕንፃዎች ላይ ካሉት 12 የችሎት አዳራሾች ውስጥ አሁን አገልግሎት እየሰጡ ያሉት ሰባቱ ብቻ ሲሆኑ ሌሎቹ በደረሰባቸው ጉዳት አገልግሎት እየሰጡ አይደለም፡፡ በአገራችን በዘመናዊ መልክ ለፍርድ ቤት ተብሎ የተሠራ ሕንፃ ነውና በዕድሳት ወቅት ተገቢው ጥንቃቄ ሊደረግለት በመስኩ ያሉ ባለሙያዎችም በዚሁ ላይ ሊሳተፉ ይገባል፡፡

በሕንፃው ምርቃት ወቅት ምን ተብሎ ነበር?

ግርማዊ ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ

‹‹. . .አገራችሁንና ወገኖቻችሁን ለማገልገል ዳኞችና ጠበቆችም ከባድ ኃላፊነት ተጥሎባችኋል፡፡ እውነትንና ትክክለኝነትን ብቻ ፈላጊዎች መሆን አለባችሁ፡፡ ከመደለልና ከርካሽ የግል ጥቅሞች ፍለጋ የራቃችሁ ፈተና የማያሸንፋችሁ መሆን አለባችሁ፡፡

ዛሬ ይህን አዲስና የተዋበ ሕንፃ የምናበረክተው በውስጡ ተቀምጠው ለሚፈርዱት ዳኞችና በዚህ የፍርድ ሸንጎ እየቀረቡ ለሚከራከሩት ጠበቆች ይበልጡንም ለመላው ሕዝባችን ነው፡፡ ፍትሕና ፍርድ ነፃ ለሆነ ሕዝብ ጽኑ ምሽጎች ናቸው፡፡ እንዲሁም ጉዳያቸውን በሕግ መሠረት ለማከናወን ኑሮአቸውን ለማሳካትና አከራካሪ ጉዳዮችን ክርክራቸውንም በዚሁ መስመር ለመፈጸም ለሚሹ ሁሉ ለትልቁም ለትንሹም አገልጋይና ደጋፊ ናቸው፡፡

‹‹ይህን ሕንፃ ያሠራነው እጅግ ከፍ ያሉ ጠቃሚ ነገሮችን በሚገባ ለማስፈጸሚያ ነው እንጂ፣ ለውበትና ለምቾት ተብሎ አይደለም፡፡ ስለዚህ ለተባለውና ለተመረቀበት ዓላማ መፈጸሚያ ብቻ እንዲውል አድርጉት. . .››

ቢትወደድ አስፍሐ ወልደ ሚካኤል (የወቅቱ የፍርድ ሚኒስትር)

‹‹ሐሳብ ቦታንና ሥራን ይቀድሳል እንደተባለው ለዚሁ የተቀደሰው የዳኝነት ተግባር የዋለው የግርማዊነትዎ ሐሳብና ድካም ሁሉ በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋ አግኝቶ፣ ይህን ሕንፃ የፍትሕ ምንጭ የዳኝነት ትእምርት እንዲያደርገው እመኛለሁ፡፡›› 

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ባልደረባ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...