Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  በሃያ አንድ ዓመቱ የተቀጨው ሕንፃ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሲገለገልበት የቆየው ለገሃር አካባቢ የሚገኘው ባለ አራትና ሰባት ወለል ሕንፃ፣ እንደ ብዙዎቹ የአዲስ አበባ የዕድሜ እኩዮቹ በአገልግሎት ዘመኑ ልክ ባለበት ቦታ ለመቆየት ያልታደለ ሆኗል፡፡

  ቀድሞ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ በሚል መጠሪያ ይታወቅ በነበረው መንግሥታዊ ተቋም ባለቤትነት የተገነባው ይህ ሕንፃ፣ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ ዕድሜ ይኖረዋል ተብሎ የተገነባ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የታሰበው ረዥሙ ዕድሜው ተገቶ ለሃያ ዓመታት ብቻ ቆይቶ እንዲፈርስ ተፈርዶበታል፡፡

  እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በመዲናዋ ውስጥ ከሚገኙ በትልቅነታቸው ከሚጠቀሱት ሕንፃዎች መካከል አንዱ የሆነው ይህ ሕንፃ፣ ያለ ዕድሜው ሳይታሰብ እንዲፈርስ የተፈረደበት በለገሃር አካባቢ ይገነባል ተብሎ ከሚጠበቀው ግዙፍ የከተማዋ ኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘ ነው፡፡ ከሰሞኑ ይህ ሕንፃ ወደሚገኝበት አካባቢ ብቅ ለሚሉ ሰዎች፣ በቫርኔሮ ኩባንያ የተገነቡት ጠንካራ ምሰሶዎችና በዕምነበረድ የተለበጠው የሕንፃው አፅም ብቻ ይታያል፡፡ ውስጣዊ አካሉ ከፈራረሰ በኋላ ሕንፃውን ያቆሙትን ምሰሶዎች ማፍረስ ተጀምሯል፡፡

  ሕንፃውን ቀድሞ በዋና መሥሪያ ቤትነት ሲጠቀምበት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት፣ አሁን የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ጓዙን ጠቅልሎ በቅርብ ርቀት ወደሚገኘው የራሱ ሕንፃ ተዛውሯል፡፡

  ከመንግሥት የልማት ድርጅቶች ኤጀንሲ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ሕንፃው ያረፈበትን ቦታ ለሌላ ኢንቨስትመንት ለማዋል ሲባል ሕንፃው እንዲፈርስ በመወሰኑ፣ ድርጅቱን ወደ አዲሱ ሕንፃ ማዛወር ግድ ሆኗል፡፡

  ድርጅቱ በዋና መሥሪያ ቤትነት ይጠቀምበት የነበረውን ሕንፃ ለራሱ ብቻ ሳይሆን፣ ለሌሎች የንግድ ድርጅቶች የተወሰነውን የሕንፃ ክፍል በማከራየት ገቢ የሚያገኝበት ጭምር ስለነበረ አሁን የገቢ ምንጩም ተነክቷል፡፡ በዚህ ሕንፃ ውስጥ የተለያዩ ሥራዎቻቸውን ሲያከናውኑ የነበሩ ድርጅቶች ለቀው በየአቅጣጫው ሄደዋል፡፡ ድንገት ነው የተባለው ውሳኔ ተከራዮቹም ሌላ አማራጭ እንዲያፈላልጉ ያስገደደ በመሆኑ፣ ሁሉም ‹‹ወደዚህ ሕንፃ ተዛውረናል›› የሚል ማስታወቂያቸውን በፈራሹ ሕንፃ ላይ አኑረው ሄደዋል፡፡

  ከመንግሥት የልማት ድርጀቶች ኤጀንሲ የተገኘው ተጨማሪ መረጃ እንደሚያመልክተው ድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤቱን ከሚፈርሰው ሕንፃ ፊት ለፊት ከኢትዮጵያ መድን ድርጅት ጀርባ ወደተገነባው ሕንፃ እንዲዛወር መወሰኑን ነው፡፡

  ይህ ሕንፃ ግን ግንባታው ሳይጠናቀቅ ከ12 ዓመታት በላይ የቆየ ነበር፡፡ ድርጅቱ በዋና መሥሪያ ቤትነት የሚጠቀምበት አዲሱ ሕንፃ፣ ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ባህር ትራንዚት አገልግሎት በሚባል መጠሪያ ይታወቅ የነበረው መንግሥታዊ ተቋም ባለቤቱ የነበረ ሲሆን፣ አሁን በድርጅቱ ይዞታ ሥር በመሆኑ ቤት በማፈላለግ እንዳይደክም አግዞታል፡፡

  አዲሱ የድርጅቱ ዋና መሥሪያ ቤት መሆን የቻለውና በግንባታው መዘግየት ምክንያት መጀመርያ ይወጣበታል ተብሎ ከተያዘው የግንባታ ዋጋ በላይ ከሦስት እጥፍ በላይ ወጪ የጠየቀው ይህ ሕንፃ፣ የመጨረሻው ወለል አዲስ አበባን በአራቱም አቅጣጫ እየተሽከረከረ የሚያሳይ ሬስቶራንት እንዲኖረው ተደርጎ ዲዛይን የተሠራለት ነው፡፡ አሁንም የማጠናቀቂያ ሥራዎቹ ያላለቁለት ቢሆንም የግንባታ ሥራው እንዳለም ዋና መሥሪያ ቤት ሆኗል፡፡

  በለገሃር አካባቢ ይካሄዳል የተባለው ግዙፉ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ የሚያከናውነው ግንባታ፣ የቀድሞውን የንግድ መርከብ ሕንፃ ብቻ ሳይሆን በዕድሜ የሚልቀውንና ከጎኑ ያለውን ሕንፃ ጭምር እንዲፈርስ ያስገደደም ነው፡፡

  ይህ ሕንፃ በፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን (የቀድሞው ኪራይ ቤቶች) ሥር የሚተዳደር ሲሆን፣ ባለስምንት ፎቅ ነው፡፡ ሕንፃው ግማሽ ምዕተ ዓመት የሚደርስ ዕድሜ ሲኖረው፣ በተለያዩ ሥራዎች የሚታወቁ ድርጅቶችና መኖሪያ ቤቶችንም የያዘ ነበር፡፡ በተለይ በዚህ አካባቢ ዘመናዊ የበርገር ቤቶች ሳይታወቁ በርገንና ፈጣን ምግቦችን በማቅረብ የሚታወቀው ለገሃር ሚኒ፣ በዚህ ሕንፃ የነበረው የዓመታት አገልግሎት ትዝታውን ብቻ ትቶ ሄዷል፡፡

  የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት ሕንፃ አሁን ፈረሰ እንጂ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት መፍረስ አለበት ተብሎ ጥያቄ ይቀርብበት ነበር፡፡ ሕንፃውን የተመለከቱ አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያሳዩት፣ በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኩባንያ ግንባታ ሲባል እንዲፈርስ ውሳኔ ከመተላለፉ በፊት፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሐዲድ ዝርጋታ ዲዛይን በሚሠራበት ወቅት ማስተር ፕላኑ ሲታይ፣ ከማስተር ፕላን ውጪ የተገነባ ሕንፃ በመሆኑ እንዲፈርስ ሐሳብ ቀርቦበት ነበር፡፡ ነገር ግን ይህንን የሚያህል ሕንፃ ከማፍረስ የቀላል ባቡሩን ዲዛይን ማስተካከል ተመራጭ ሆኖ ተርፏል፡፡ ይህ ግን ዕድሜውን ያረዘመለት ለሦስት ዓመታት ብቻ ነበር፡፡

  ለቀድሞው ንግድ መርከብ ሕንፃ መፍረስ ምክንያት የሆነው የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ኤግል ሒልስ የተባለው የሪል ስቴት ኩባንያ፣ በለገሃር አካባቢ የሚገነባው ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውለው ግዙፍ ኢንቨስትመንት እስከ 50 ቢሊዮን ብር ወጪ የሚጠይቅ መሆኑ መገለጹ አይዘነጋም፡፡

  የኢትዮጵያ ባህር ትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ አገልግሎት ድርጅት በሚባል መጠሪያ የሚታወቀው ተቋም ቀደም ብሎ የኢትዮጵያ ንግድ መርከብ ድርጅት፣ የኢትዮጵያ የባህር ትራንዚት አገልግሎትና የደረቅ ወደብ አገልግሎት በሚል መጠሪያ የሚታወቁትን ተቋማት እንዲዋሀዱ በማድረግ የተመሠረተ ግዙፍ መንግሥታዊ ተቋም ነው፡፡

  spot_img
  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

  - ማስታወቂያ -

  በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች