Friday, June 9, 2023

የምርጫ ሥርዓት ማሻሻያን ያላካተተው አዲሱ አዋጅ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ሊቀመንበርነትን ከመረከባቸው በፊት በነበሩ ወራት አገሪቱ በተለያዩ የተቃውሞ፣ የአመፅ ድምፆችና እንቅስቃሴዎች ስትናጥ እንደነበር የሚዘነጋ አይደለም፡፡

በተለይም በ2008 ዓ.ም. እና በ2009 ዓ.ም. በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በገዥው ፓርቲና በመንግሥት ላይ ሲካሄዱ የነበሩት ተቃውሞዎችና አመፆች ገዥው ፓርቲን ያለ ባህሪው ይቅርታ እንዲጠይቅ፣ እንዲሁም ከሁሉም የአገሪቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ለውይይት ለመቀመጥ አስገድደውትም ነበር፡፡

ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመደራደርና ለመወያየት ዝግጁነቱን በወቅቱ ሲገልጽ፣ በተለይ የሥነ ምግባር ደንብ ካልፈረሙ ፓርቲዎች ጋር አልወያይም በማለት ለዓመታት ይዞት የነበረው አቋሙን መቀየሩን የሚያመላክት ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በ2009 ዓ.ም. እና በ2010 ዓ.ም. ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ዓመታዊ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የወቅቱ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ በተቃዋሚዎችና በገዥው ፓርቲ መካከል ድርድር እንደሚካሄድ፣ እንዲሁም መንግሥት የፖለቲካ ምኅዳሩን ለማስፋት በማሰብ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ እንደሚያደርግ አስታውቀው ነበር፡፡

በመንግሥት በኩል ይወሰዳሉ ተብለው ከነበሩት በርካታ ማሻሻያዎች መካከል አፋኝ የተሰኙትን የአገሪቱን ሕጎች ማሻሻልን የሚያካትት ሆኖ፣ የምርጫ ሥርዓቱንም ጭምር ለማሻሻል እንደሚቻል የሚጠቁም ንግግር አድርገው ነበር፡፡  

ከዚህ በተጨማሪም የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝም እንዲሁ፣ መንግሥታቸው ለለውጥ መዘጋጀቱንና ቁርጠኛ መሆኑን በመጥቀስ የምርጫ ሥርዓቱን እስከ ማሻሻል የሚደርስ ድርድርና ውይይት ለማካሄድ ቁርጠኛ መሆናቸውን ገልጸው ነበር፡፡

በዚህ ማዕቀፍ ውስጥ ነው እንግዲህ በ2009 ዓ.ም. በወርኃ ጥር 21 የሚሆኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ከኢሕአዴግ ጋር ለመደራደር ቅድመ ዝግጅት የጀመሩት፡፡

ቅድመ ዝግጅቱ ሲጀመር 21 የነበሩት የተቃውሞ ጎራው ፓርቲዎች ዋነኛው ድርድር ሲጀመር ወደ 17 ዝቅ ብለው የነበረ ሲሆን፣ አዲሱ የኢሕአዴግ አመራር በመጋቢት 2010 ዓ.ም. አመራሩን ሲይዝ እስከተቋረጠው ድርድር ድረስ ደግሞ 15 የሚሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎች እየተሳተፉበት ነበር፡፡

በወቅቱ በተለይ ከገለልተኛ አደራዳሪ መሰየም ጋር በተያያዘ ሰማያዊና መድረክ ፓርቲዎች ከመጀመርያው የድርድሩ ሒደት ላይ ተቃውሞ በማሰማት ራሳቸውን ከድርድሩ አግልለው ነበር፡፡

የተለያዩ ተቃውሞዎችንና ሙገሳዎችን እያስተናገደ አንዴ ሲጀመር፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ እየተቋረጠ ሲካሄድ የነበረው ይህ ድርድር ያስገኛቸው ውጤቶች በወቅቱ ከፍተኛ ትችትም ድጋፍም ያስተናገዱ ነበሩ፡፡

በድርድሩ ወቅት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ወክለው ይደራደሩ የነበሩ የተለያዩ ፓርቲ አመራሮችና አባላት በተለይም በፀረ ሽብር አዋጅ 652/2001፣ በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ 573/2003፣ እንዲሁም በተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ አዋጅ 532/99ን በተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ድርድርና ውይይት ያካሄዱ የነበረ ሲሆን፣ የፀረ ሽብር አዋጁ በይደር በእንጥልጥል እንደቀረ ነው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መምጣት አቅጣጫውን ያስቀየረው፡፡

በወቅቱ ይካሄዱ የነበሩ ድርድሮች በገዥው ፓርቲ ከፍተኛ ሥፍራ ተሰጥቶት እንደነበር ለማመሳከርም በወቅቱ ድርጅቱን ወክለው በተደራዳሪነት የሚቀርቡትን የሥራ ኃላፊዎች ማስታወስ ተገቢ ነው፡፡ በወቅቱ እንደ የውይይት አጀንዳው ዓይነት ኢሕአዴግ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ፣ አቶ ደግፌ ቡላ፣ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ እንዲሁም አቶ ፍቃዱ ተሰማን የመሳሰሉ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን በማፈራረቅ ይጠቀም ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ ሲካሄድ የሰነበተው የሁለቱ ወገን ድርድር የተፈጻሚነታቸው ሁኔታ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ቢያንስ ግን በተወሰኑት አጀንዳዎች ላይ መግባባቶችና ስምምነቶች ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በዚህም መሠረት በዚያ ማራቶን አከል የድርድር ሒደት የተቃዋሚ ፓርቲዎች ምዝገባ አዋጅ ቁጥር 573/2003 እና የተሻሻለው የኢትዮጵያ የምርጫ አዋጅ ቁጥር 532/99 ላይ አለን የሚሉትን ጥያቄዎች በማቅረብና በመደራደር፣ በዚያው መሠረትም እንዲሻሻሉ መስማማታቸውን አሳውቀው ነበር፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዋነኛነት በአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት ላይ የተወሰነው ውሳኔ እንደ ከፍተኛ ውጤት የተመዘገበ ነበር፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግና ተቃዋሚዎች ዘለግ ላለ ጊዜ ባደረጉት ድርድር፣ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት ወደ ቅይጥ ትይዩ እንዲሻሻል ስምምነት አድርገው ነበር፡፡   

በወቅቱ ምንም እንኳን የሕገ መንግሥት መሻሻል የሚጠይቅ የነበረ ቢሆንም፣ ገዥው ፓርቲ የአብላጫ ድምፅ የምርጫ ሥርዓትን ወደ ቅይጥ ትይዩ እንዲቀየር ስምምነት ላይ ደርሶ ነበር፡፡ በወቅቱ በዚህ መሠረታዊ ሐሳብ የተስማሙት ሁለቱም ወገኖች በቅይጡ የምርጫ የመቶኛ ሥርዓት የድርሻ ድርድር ላይ የተለያየ አቋም በማራመዳቸው የተነሳ ጉዳዩ ዕልባት ሳያገኝ ለሳምንታት ዘልቆ ነበር፡፡

በወቅቱ የተወሰኑ ተቃዋሚ ፓርቲዎች 50 በመቶው ለአብላጫ ድምፅ ሥርዓት፣ 50 በመቶው ደግሞ ለተመጣጣኝ ውክልና ይዋል በማለት ሐሳብ ያቀረቡ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ ራዕይ ፓርቲ (ኢራፓ) ደግሞ የምርጫ ሥርዓቱ ሙሉ በሙሉ ወደ ተመጣጣኝ ውክልና መሸጋገር አለባት በማለት ተሟግቶ ነበር፡፡ በወቅቱ ኢሕአዴግ መጀመርያ 10 በ90፣ በመቀጠል 15 በ85 እንዲሁም በመጨረሻ ደግሞ 20 በ80 በማለት 20 በመቶ ተመጣጣኝ ውክልና እንዲሆን ሲስማማ፣ 80 በመቶው ደግሞ በነበረበት አብላጫ ድምፅ እንዲቀጥል በሚለው አቋሙ በመፅናቱ የተለያዩ የመቶኛ ድርሻ ቁጥሮች ሲያቀርቡ የነበሩት ተቃዋሚ ፓርቲዎችም በዚሁ ተስማምተው ነበር፡፡

ምን ዓይነት የምርጫ ሥርዓት?

በዚህ ዙሪያ የተጻፉ በርካታ ድርሳናት እንደሚያመለክቱት ከሆነ በዋነኛነት ሦስት ዓይነት የምርጫ ሥርዓቶች አሉ፡፡ እነዚህም የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት (አሸናፊ ሁሉንም የሚወስድበት)፣ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት፣ እንዲሁም የሁለቱም ድብልቅ  ቅይጥ የሆነው የምርጫ ሥርዓት ነው፡፡

የኢትዮጵያ የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅ ሥርዓት ሲሆን፣ የአገሪቱ የዴሞክራሲ ግንባታ ከቀን ወደ ቀን እያሽቆለቆለ እንዲሄድ ካደረጉ ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ የሚገልጹ አሉ፡፡ ለዚህም መከራከሪያቸው ምንም እንኳ አንዱና ዋነኛው ባይሆንም፣ የዜጎች ሉዓላዊነት ከሚገለጽበት መንገድ አንዱ ምርጫ በመሆኑ በአብላጫ የድምፅ ሥርዓት መሠረት በርካታ ድምፆች ለብክነት የሚዳረጉ በመሆናቸው፣ የዜጎች ውክልና መብት ጥያቄ ውስጥ ይገባል በማለት ነው፡፡

ይህንን ጥያቄና አስተያየት በርካቶች የሚጋሩት ሲሆን፣ የተቃውሞ ጎራው አባላትም ይህን ጥያቄ በተደጋጋሚ ሲያቀርቡት ነበረ፡፡ በዚህ መሠረት ማሻሻያ ይደረግበታል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ወደ ሥልጣን መምጣትን ተከትሎ በነበሩ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች ምክንያት፣ ዘላቂ መፍትሔ ያገኛል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበትም ነበር፡፡

ምንም እንኳን ከዚህ ቀደም በኢሕአዴግና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባደረጉት ድርድር አማካይነት ወደ ቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓት ለመቀየር ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ ቅዳሜ ነሐሴ 18 ቀን 2011 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ የፀደቀው የኢትዮጵያ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ አሁንም የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅ ሥርዓትን እንደሚከተል ደንግጓል፡፡

ይህ አዋጅ በተቃዋሚ ፓርቲዎች አማካይነት በርካታ ጥያቄዎች እየቀረበበት ሲሆን፣ በተለይ ተቃውሞአቸውን በአንድነት ለማሰማት የተሰባሰቡት 33 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ‹በውይይታችን መሠረት ያነሳናቸው ነጥቦች ያልተካተቱበት፣ እንዲሁም ተስፋ ሰጪ የነበረውን የፖለቲካ ምኅዳር የመክፈት እንቅስቃሴ ወደ ኋላ የሚመልስ ነው› በማለት ታቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡

አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ የአገሪቱን የምርጫ ሥርዓት በተመለከተ፣ ‹‹በፌዴራል ሕገ መንግሥት መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚደረግ ምርጫ በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል አብላጫ ድምፅ ያገኘው አሸናፊ ይሆናል፤›› በማለት፣ የአገሪቱ የምርጫ ሥርዓት የአብላጫ ድምፅ ሥርዓትን እንደሚከተል ደንግጓል፡፡

ነገር ግን በአዋጁ ላይ ተቃውሞአቸውን ለማሰማት የተሰባሰቡት 33 የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ መንግሥት ለኢትዮጵያ ሕዝብም ሆነ ለፓርቲዎች በተደጋጋሚ ቃል ሲገባ ከነበረባቸው ጉዳዮች አንዱ የምርጫ ሕጉን ማሻሻል ነው፡፡ የምርጫ ሕጉን ማሻሻል ያስፈለገው ደግሞ የምርጫ ሥርዓቱን ለማሻሻል ነው በማለት፣ የምርጫ ሥርዓት መሻሻልን ሳያካትት የፀደቀው አዋጅ የተሻለ የፖለቲካ ምኅዳር ለመፍጠርና የተሻለ አሳታፊ የፖለቲካ አካሄድ ለማከናወን እንቅፋት ይሆናል በማለት ተቃውመውታል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም አሁን ባለው የአገሪቱ አለመረጋጋትና ፓርቲዎች እንዳሻቸው በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ተንቀሳቅሰው መሥራት በማይችሉበት ሁኔታ፣ በአብላጫ ድምፅ ሥርዓት መጪውን ምርጫ ለማድረግ መዘጋጀት በራሱ አስቸጋሪና አንድን ወገን የሚጠቅም ነው በማለት ይተቻሉ፡፡

በዚህ ጉዳይ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን የሰጡት የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት (መኢአድ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ ሙሉጌታ አበበ በበኩላቸው፣ ‹‹የምርጫ ሥርዓቱን ሳናሻሽል ባለበት እንዲቀጥል ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ከሁሉም  በላይ ትናንት ያሳለፍነው አመፅ ነገ ላለመምጣቱ ምንም ዋስትና የለንም፤›› በማለት፣ ከዚህ ቀደም በመረጥኩት ልተዳደርና ተመጣጣኝ ውክልናን ይስፈን የሚሉ ጥያቄዎችን መሠረት ያደረጉ የሕዝብ ጥያቄዎች፣ ዳግም አስቸጋሪና ፈታኝ ጥያቄዎች ሆነው ሊመጡ ይችላሉ የሚል ሥጋታቸውን አጋርተዋል፡፡

ለዚህ እንደ መከራከሪያ የሚያቀርቡት ሐሳብ ደግሞ ባለፉት ዓመታት በአገሪቱ የተከሰቱ አለመረጋጋቶችና አመፆች መነሻቸው ሕዝቡ አልተወከልኩም ብሎ በማመኑ እንደሆነ በማስታወስ፣ ‹‹50+1 ድምፅ ያገኘ ፓርቲ መንግሥት የሚመሠረትበት፣ 49 በመቶ ድምፅ ያገኘ ዞር በል በሚባልበት የምርጫ ሥርዓት በአገሪቱ ያደረሰውን ፈተና የምናስታውሰው ነው፡፡ አሁንም ቢሆን አዲሱ አዋጅ እንዲህ ላሉ የሕዝብ ጥያቄዎች መልስ ሰጪ አይደለም፡፡ እንዲያውም ለሌላ ችግር በር ካፋች ነው፤››  ብለዋል፡፡

ለአገሪቱ የሚበጃት የምርጫ ሥርዓት ቅይጥ ትይዩ እንደሆነ በመጥቀስ፣ የሁለቱ መቶኛ ድርሻ ደግሞ 40/60 ሊሆን እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ከተቃዋሚ ፓርቲዎች በርካታ ተቃውሞዎችን ያስተናገደው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ባለፈው ሳምንት በአስቸኳይ ስብሰባ በተወካዮች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡ ከተነሱት በርካታ የተቃውሞ ድምፆች መካከል አገር አቀፍ ፓርቲ ለመመሥረት 10,000 ፊርማዎችን ማሰባሰብ፣ ለክልል አቀፍ ፓርቲዎች ደግሞ 4,000 ፊርማዎች ማሰባሰብ፣ በመንግሥት ሥራ ላይ ሆኖ ምርጫ መወዳደር እንደማይቻልና የመሳሰሉት የሚጠቀሱ ሲሆን፣ የምርጫ ሥርዓቱ ጉዳይም ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ ከጅምሩ በተቃውሞ የፀደቀው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ በቀጣይ ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው አጠቃላይ ምርጫ ከወዲሁ እንቅፋት እንዳይሆን ሥጋታቸውን የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ሊደረግ የታሰበው ምርጫና ውጤቱም፣ አገሪቱን ወደ ከፋ አለመረጋጋት እንዳይመራት የሚሠጉም እንዲሁ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዚህ አንፃር ገዥው ፓርቲና ተቃዋሚዎቹ የሰከነ ድርድር በማድረግ እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ከአሁኑ ፈር እንዲያስይዙ የሚመክሩ ሲሆን፣ በተለይ ገዥው ፓርቲ አገር የማዳን ኃላፊነቱን ለመወጣት ካሰበ በተቃውሞ የታጀበ አዋጅ ሳይሆን፣ ቢያንስ በርካቶችን ሊያስማሙ የሚችሉና አስቻይ ሁኔታን የሚፈጥሩ አሠራሮችን መዘርጋት እንደሚኖርበት ያሳስባሉ፡፡

በተለይ ከምርጫ ሥርዓቱ ጋር በተያያዘ ከዚህ ቀደም በኢሕአዴግና በተቃዋሚ ፓርቲዎች መካከል የተደረሰውን የቅይጥ ትይዩ የምርጫ ሥርዓትን ወደ ተግባር ማስገባት እንደሚገባ አስተያየታቸውን በመስጠት፣ በቅጡ ሳይታሰብበትና ስምምነት ሳይደረግባቸው የሚፀድቁ አዋጆች ወደ ከዚህ ቀደሙ የፖለቲካ ችግሮች አዙሪት ሊመልሱ ስለሚችሉ ውይይቶች በስፋት መደረግ እንደሚኖርባቸው አስተያየት ይሰነዝራሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -