Friday, December 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ተፈጻሚ እንዳይሆን ጠየቀ

የፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አዲሱ የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ተፈጻሚ እንዳይሆን ጠየቀ

ቀን:

ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግን ጨምሮ 107 ፈራሚ አባላትን የያዘው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በቅርቡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፀደቀው የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ የመጨረሻ አዋጅ ሆኖ እንዳይወጣ፣ የማይሆን ከሆነ ደግሞ በአስቸኳይ እንዲሻሻል የሚል ውሳኔ ማሳለፉን የምክር ቤቱ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ ለሪፖርተር አስታወቁ፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ የፀደቀውን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅን፣ እንዲሁም ሌሎች በጋራ ምክር ቤቱ አቋም ተይዞባቸው በነበሩ ጉዳዮችን አስመልክቶ ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ጽሕፈት ቤት ቅጥር ግቢ ውስጥ መግለጫ ሰጥቶ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የጋራ ምክር ቤቱ ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎችን ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ማለትም ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ ለምርጫ ቦርድ፣ እንዲሁም ለጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ማቅረቡን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ካቀረባቸው ሦስት ጥያቀዎች የመጀመርያው፣ ‹‹ከዚህ ቀደም በውይይት ወቅት ያቀረብናቸው ጥያቄዎች ለምን እንዳልተካተቱ የምንወያይበት አንድ ተጨማሪ መድረክ እንዲፈጠር፣ እኛ በተገኘንበት በጥያቄያችን መሠረት እንደገና እንዲታይና የአገሪቱ ሕግ በሚፈቅደው መሠረት እንዲሻሻል፤›› የሚል መሆኑን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም፣ እንደገና ‹‹እንዲሻሻል ወይም ሳይታወጅ በፊት የጠየቅነው ጥያቄ ምላሽ አዎንታዊ ከሆነ፣ የጋራ ምክር ቤቱ ቀርቦ የራሱን ነጥቦች በዝርዝር ለቋሚ ኮሚቴውም ሆነ ለምክር ቤቱ ለማስረዳት ዝግጁ መሆናችንን፤›› የሚል እንደሆነም አብራርተዋል፡፡

በመጨረሻም፣ ‹‹አሁን በተሄደበት መንገድና አዋጁ ባለው ይዘት ተፈጻሚ የሚሆን ከሆነ ለጋራ ምክር ቤቱም ሆነ ለፓርቲዎች በመግባቢያ ሰነዱ መሠረት የተሰጠውን ሚናና ኃላፊነት እንድንወጣ የማይፈቅድ ስለሆነ አጥብቀን እንቃወማለን፡፡ ተፈጻሚ እንዳይሆንም ከሕዝቡ ጋር በጋራ ሆነን እንታገላለን፤›› የሚል አቋማቸውን ማንፀባረቃቸውን አቶ ግርማ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ሁኔታ ውስጥ ምርጫ ማድረግም ከዚህ ቀደም ከተካሄዱ አምስት ዙር ምርጫዎች የተለየ ይሆናል የሚል እምነት እንደሌላቸውም በመግለጽ፣ ‹‹ይህ ባለበት ሁኔታ አሁን የፀደቀውን ነገር ይዘን ወደ ምርጫ እንገባለን ለማለት እቸገራለሁ፤›› በማለት፣ ከቀጣዩ ምርጫ በፊት የፖለቲካ ምኅዳሩን የማስፋትና የመጫወቻ ሜዳው ለሁሉም እኩል እንዲሆን ሊሠራ እንደሚገባ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ለዚህ እንደ መከራከሪያነት የሚያቀርቡት ነጥብ ደግሞ የጋራ ምክር ቤቱ ከዚህ ቀደም ለውይይት ካስያዛቸው ሰባት የውይይት አጀንዳዎች መካከል፣ ‹‹ምርጫ 2012 የማራዘም ጉዳይ›› የሚል መኖሩን በመጥቀስ፣ ‹‹በዚህ ላይ ተወያይተን ይራዘም አሊያም አይራዘም የሚል ውይይት ባልተደረገበትና አቋም ባልተያዘበት ሁኔታ ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ መናገር አይቻልም፤›› ሲሉ የጋራ ምክር ቤቱ ለውይይት ባቀረባቸው ሰባት አጀንዳዎች ዙሪያ አሁንም ውይይት እንዲካሄድ የጋራ ምክር ቤቱ ፍላጎት መሆኑን አስረድተዋል፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ውይይት እንዲደረግባቸው ያቀረባቸው ሰባት አጀንዳዎች ደግሞ ሕገ መንግሥት ስለማሻሻል፣ ምርጫ 2012ን የማራዘም ጉዳይ፣ ብሔራዊ መግባባት፣ ወቅታዊ ሁኔታ (የማንነትና የክልልነት ጥያቄዎችና የአዲስ አበባ ጉዳይ)፣ ስለምርጫ ቦርድ አደረጃጀትና መዋቅር፣ ለፓርቲዎች ስለሚሰጥ ድጋፍና ሌሎች ጉዳዮች የሚሉ መሆናቸውን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡

ስለሆነም፣ ‹‹እነዚህ ጥያቄዎች በአግባቡ ባልተስተናገዱበትና ስለዴሞክራሲያዊ አካሄድ ስምምነት ባልደረስንበት አካሄድ፣ እንዲሁም እነዚህ ችግሮች ይፈቱበታል ብለን የያዝናቸው አጀንዳዎች ባልተስተናገዱበት ስለዴሞክራሲያዊ ምርጫ መናገር አይቻልም፤›› በማለት አቶ ግርማ አብራርተዋል፡፡

ከላይ የቀረቡ ዝርዝር ጥያቄዎች አለመስተናገዳቸውን በመግለጽ፣ ‹‹እነዚህ ሁሉ ሁኔታዎች ባልተሟሉበት ሁኔታ ወደ ምርጫ መግባት ይቻላልን?›› በማለት አቶ ግርማ በመጠየቅ ሐሳባቸውን ቋጭተዋል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት የተቋቋመው በመጋቢት ወር 2011 ዓ.ም. ኢሕአዴግን ጨምሮ 107 ፓርቲዎች በፈረሙት የቃል ኪዳን ስምምነት መሠረት ነው፡፡ የቃል ኪዳን ሰነዱን ኢሕአዴግን በመወከል የፈረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መሆናቸው አይዘነጋም፡፡

የጋራ ምክር ቤቱ ዓላማዎች ደግሞ፣ ‹‹በአገራችን የተጀመረውን የዴሞክራሲ ግንባታ ሪፎርም ለማጠናከርና የፖለቲካ ፓርቲዎች ያለባቸውን ኃላፊነት በዚህ የቃል ኪዳን ሰነድ መሠረት ለማስፈጸም ተቋማዊ አካል ሆኖ ማገልገልና በፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንዲሁም በፖለቲካ ፓርቲዎችና በመንግሥት መካከል አለመግባባቶች ሲከሰቱ በውይይትና በመግባባት ለመፍታት የሚያስችል የውይይትና የምክክር አካል ሆኖ ማገልገል፣ እንዲሁም በፈራሚዎች መሀል የተፈጠሩ ግጭቶች በዚህ ሰነድ አግባብ ውሳኔ መስጠት፤›› የሚሉ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...