Tuesday, October 4, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisement -
  - Advertisement -
  ማኅበራዊየበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊዎች

  የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊዎች

  ቀን:

  ‹‹ሽልማቱ ከማንም በላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ ውጤት ነው››

  አቶ አማረ አረጋዊ

  እሑድ ነሐሴ 26 ቀን 2011 ዓ.ም. ለሰባተኛ ጊዜ በተካሄደው የበጎ ሰው ሽልማት ሥነ ሥርዓት የጋሞ ሽማግሌዎች በልዩ ተሸላሚነት፣ በዘጠኝ ዘርፎች ደግሞ የተለያዩ ግለሰቦች ተሸልመዋል፡፡ በኢንተርኮንቲኔንታል ሆቴል በተካሄደው የሽልማት ሥነ ሥርዓት እንደተገለጸው፣ በዘጠኝ ዘርፎች 291 ዕጩዎች ተጠቁመው 27 ግለሰቦች  ዕጩ ሆነው ቀርበዋል፡፡

  በየዘርፉ ከቀረቡ ሦስት ዕጩ ተወዳዳሪዎች መካከል የመጨረሻዎቹ አሸናፊዎች በመምህርነት ዘርፍ ወ/ሮ ሕይወት ወልደ መስቀል፣ በቅርስና ባህል ጥበቃ ዘርፍ አቶ አብዱልፈታህ አብደላ፣ በሳይንስ ዘርፍ ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በንግድ ሥራ ፈጠራ ዘርፍ አቶ ነጋ ቦንገር፣ በመንግሥታዊ ሥራ ተቋማት ዘርፍ አቶ ግርማ ወንዳፍራሽ፣ በበጎ አድራጎት ዘርፍ አብዱላዚዝ አብራሂም (ዶ/ር)፣ በኪነ ጥበብ  (ፎቶ ግራፍ) ዘርፍ አቶ በዛብህ አብተው፣ በሚዲያና ጋዜጠኝነት ዘርፍ አቶ አማረ አረጋዊ፣ እንዲሁም በዳያስፖራዎች ዘርፍ አቶ ኦቦንግ ሜቶ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

  የበጎ ሰው ሽልማት ድርጅት የቦርድ አባል አቶ ዮናስ ታደሰ የዕጩዎች አመራረጥ እንዴት እንደተከናወነ ለሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች አስረድተዋል፡፡

  ተሸላሚዎቹ ሽልማቶቻቸውን ከፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እጅ ከተቀበሉ በኋላ አጫጭር ንግግሮች አድርገዋል፡፡ ለተበረከተላቸው ሽልማትም ምሥጋና አቅርበዋል፡፡

  የሚዲያ ኮሙዩኒኬሽን ሴንተር (የአማርኛውና የእንግሊዝኛው ሪፖርተር ጋዜጦች አሳታሚ ድርጅት) ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አማረ አረጋዊ ባደረገው ንግግር፣ ‹‹በመጀመርያ ለአዘጋጁ አካል ምሥጋናዬን አቀርባለሁ፡፡ በመሸለሜም ደስታዬን እገልጻለሁ፡፡ ነገር ግን የዛሬውን ቀን የማስታውሰው የተሸለምኩበት ቀን ነው በሚል ብቻ ሳይሆን፣ ይበልጥ ለአገሬ ኢትዮጵያ አንድነት እንድሠራ የኢትዮጵያ ሕዝብ ኃላፊነት የሰጠኝና እኔም ደግሞ ሕይወቴን ሙሉ እስከ መስዋዕትነት ድረስ ለአገር አንድነት፣ ፍቅርና ሰላም ለመሥራት ቃል የምገባበት ቀን መሆኑን እገልጻለሁ፤›› ብሏል፡፡

  ሽልማቱን አስመልክቶ ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ በሰጠው ምላሽም፣ ‹‹ሽልማቱን እኔ ልቀበለው እንጂ ሃያ አምስተኛ ዓመቱን ለማክበር እየተዘጋጀ ያለው የሪፖርተር ጋዜጣ ሠራተኞች በሙሉ ውጤት ነው፡፡ እንዲሁም ከጎኔ ያልተለዩት ቤተሰቦቼም ውጤት ነው፡፡ ከምንም ነገር በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ ድጋፍ እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል፤›› ሲል አስረድቷል፡፡

  የአቶ አማረን መሸለም በተመለከተ በማኅበራዊ ትስስሮችም ሆነ በአካል ለሪፖርተር አስተያየት የሰጡ የቀድሞ ጋዜጠኞችና የሥራ ባልደረቦች፣ ሽልማቱ ተገቢ መሆኑን ገልጸው እንዲያውም የዘገየ ነው ብለዋል፡፡ ሪፖርተርም እስካሁን ድረስ ተግባራዊ ሲያደርግ የቆየውን በኃላፊነት ስሜትና በነፃነት የመሥራት ልምዱን አጠናክሮ በመቀጠል፣ ለጋዜጠኝነት ሙያ ዕድገት የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ በአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡

  - Advertisement -

  ይመዝገቡ

  spot_img
  spot_img