Monday, March 4, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹የመገናኛ ብዙኃንን የግለሰብ ተክለ ሰብዕና በመገንባት ላይ ያተኮሩ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ ማድረግ ለማንም...

‹‹የመገናኛ ብዙኃንን የግለሰብ ተክለ ሰብዕና በመገንባት ላይ ያተኮሩ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ ማድረግ ለማንም የማይበጅ ነው›› የአዲስ አበባ አዴፓ ኮሚቴ

ቀን:

ከነሐሴ 25 ቀን 2011 .ም. ጀምሮ ለሁለት ተከታታይ ቀናት 2011 .ም. መደበኛ የድርጅትና የፖለቲካ ሥራዎችን አፈጻጸምና በከተማዋ የፖለቲካና ኢኮኖሚ እንቅስቅሴ ላይ ግምገማ ማድረጉን ያስታወቀው የአዲስ አበባ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ኮሚቴ፣ የመገናኛ ብዙኃን መረጃ ልውውጥ ሥርዓት ከከተማው ሕዝብ ድምፅና ስሜት በላይ የግለሰብ ተክለ ሰብዕና በመገንባት ላይ ያተኮሩ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ ማድረግ ለማንም የማይበጅ ነው አለ፡፡

ኮሚቴው ሰሞኑን ባወጣው ባለ 11 ነጥብ መግለጫው የከተማውን ሕዝብና ወጣት መሠረታዊ ፍላጎቶች ለመመለስ ባከናወናቸው ተግባራት፣ የነበሩበትን ጥንካሬና ጉድለቶች በዝርዝር መገምገሙን አስታውቋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረውለውጥ ጉዞ በትክክለኛ መንገድ እንዲቀጥልና የከተማዋን ሕዝብ ትርጉም ባለው መንገድ የሚቀይር ተጠቃሚነት ከማስፈን አንፃር፣ አንድ ዓመት የለውጥ ጉዞ ውስጥ የተመዘገቡ በርካታ ስኬቶች ነበሩ ብሏል፡፡ በሌላ በኩል ግን በየደረጃው ያለ አመራር በቁርጠኝነትና በተነሳሽነት ያከናወነበት ዓመት ቢሆንም እንኳን በውስጥም በውጭም ተግዳሮቶችን ያስተናገደ ክስተት መፈጠሩን፣ የድርጅቱ ታላላቅ መሪዎች መገደልና በክልሉ ውስጥም ሆነ በውጭ በሚኖረው የአማራ ሕዝብ ላይ የደረሰው መፈናቀል ሌላኛው ችግር እንደነበር ገልጿል፡፡

በአቋም መግለጫው ከዳሰሳቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የመገናኛ ብዙኃን ጉዳይ ነው፡፡ ‹‹የመገናኛ ብዙኃን የመረጃ ልውውጥ ሥርዓቱን ለከተማዋ ዕድገት፣ ብልፅግናና ለብዝኃነት ካለው ፋይዳና የከተማዋን ሕዝብ ድምፅና ስሜት ከማስተጋባት ይልቅ፣ የግለሰብን ተክለ ሰብዕና በመገንባት ላይ ያተኮሩ አጀንዳዎች ማስተጋቢያ እንዲሆን እየተደረገ ያለው አሠራር ለማንም የማይበጅ፣ እንዲሁም ሕዝበኝነትን የሚያነግሥ፣ የከተማዋን የዘላቂ ልማትና የሰላም አጀንዳ ሁሉንም አካታች እንዳይሆን የሚያደርግ አካሄድ በመሆኑ እንዲታረም እንታገላለን፤›› ብሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ባለፈው አንድ ዓመት በከተማው ውስጥ ባከናወናቸው የፖለቲካና የድርጅት ሥራዎች የተመዘገቡት ስኬቶች የተጀመረውን አገራዊና ከተማዊ ለውጥ ወደ ላቀ ደረጃ በማሸጋገር ረገድ የራሱን መሠረት ያስቀመጠ መሆኑን መገምገሙን፣ ይሁን እንጂ ለውጡ ቀጣይና ተቋማዊ ሆኖ እንዳይቀጥል በተለያዩ ኃይሎች እየገጠመው ያለውን ተግዳሮትና የማጠልሸት ተግባር የከተማውን ሕዝቦች ሁለንተናዊና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚጎዳ በመሆኑ ከመቼውም ጊዜ በላይ አምርሮ የሚታገል መሆኑን ከሚቴው አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ሲከናወኑ የቆዩ የልማትና መልካም አስተዳደር ተግባራት ላይ አመራሩና መዋቅሩ የራሱን የማይተካ ሚና ሲጫወት እንደቆየ፣ በመሆኑም በቀጣይነት መላው የከተማው ሕዝብ በተለይም ወጣቶችና ሴቶች ፍትሐዊ ተጠቃሚነትና ተሳትፎ እንዲረጋገጥ፣ገወጥ ተግባራት እንዲወገዱ፣ የሕግ የበላይነት እንዲከበር፣ የከተማውን ሰላምና የነዋሪዎች አንድነት እንዲጠበቅ ከመቼውም በላይ ተግቶ የሚሠራ መሆኑን ኮሚቴው በመግለጫው አመልክቷል፡፡

በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት የሕዝቡን ህልውና እየተፈታተነ በመሆኑ ይህንን ችግር ሊፈታ የሚችል ሁሉን አቀፍ እንቅስቀሴ መደረግ እንዳለበት ኮሚቴው ገልጾ፣ ከዚህ ውስጥ የመኖሪያ ቤት ችግር አንዱ እንደሆነና ይህንን ለመፍታት የተዘረጋው የቤቶች ልማት ፕሮግራም በሚፈለገው ፍጥነት የሕዝቡን ተጠቃሚነት እያረጋገጠ ባለመሆኑ፣ ነባር ግንባታዎችም ሆኑ አዳዲስ ፕሮጀክቶች በተያዘላቸው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት እንዲጠናቀቁና የሕዝቡን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚታገል አስታውቋል፡፡

በከተማው የሕዝቡን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ተጠቃሚነትን ለማረጋገጥ በድርጅት አሠራርና አደረጃጀት መመርያ መሠረት ተቋማዊ አሠራርን በተከተለ ሁኔታ የአመራር ምደባ፣ ሥምሪትና ሽግሽግ የሚተገበር መሆኑ ግልጽ ነው ካለ በኋላ፣ ነገር ግን ተቋማዊ አሠራር ሳይፈርስ በግለሰብ ፍላጎት፣ ይሁንታና አድራጊ ፈጣሪነት የአመራር ምደባና ሽግሽግ እየተከናወነ፣ በተለይም አምባገነናዊ ሥርዓት እንዲሰፍን እየተሠራ ያለበት ሒደት በመኖሩ፣ ይህ ድርጊት ታርሞ በቀጣይ የሰው ኃይል ምደባና ሥምሪት የፈረሰው ተቋማዊ አሠራር ተስተካከሎ በየደረጃው ተግባራዊ እንዲደረግ እንደሚታገል ኮሚቴው አስረድቷል፡፡

‹‹የአማራዝብ ካሁን ቀደም በበሬ ወለደ የሐሰት ትርክት ግፍና በደል ሲደርስበት ቆይቷል፡፡ ይህንን ከታሪክና ከእውነት የተቃረነ የሐሰት ትርክት ከሕዝባችን ጋር ታግለን የጣልነው ቢሆንም፣ የለበሰውን አቧራ እያራገፈ የተለያዩ ተቀፅላዎችን በመለጠፍ ሕዝባችንን ለማሸማቀቅ፣ አንገት ለማስደፋትና ማንነቱን እንዲጠላ ለማድረግ የሚጥሩ ኃይሎች ከዚህ እኩይ ተግባራቸው እንዲቆጠቡና በዚህ ሰበብ ያላግባብ የታሰሩ አካላትም ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና የሕግ የበላይነት እንዲረጋገጥ እንታገላን፤›› በማለት ኮሚቴው አቋሙን አስታውቋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ውስጥ ባሉ አገልግሎት ሰጪ መሥሪያ ቤቶች ለአገልግሎት የሚመጡ ነዋሪዎች የድርጅቱ አባል ፓርቲዎች የሚወክሏቸው ሕዝቦች ብቻ ባለመሆናቸው፣ ለኅብረ ብሔራዊቷ ከተማ ያለ ማንም ያልተገባ ድጋፍና ዕርዳታ በዕውቀቱና በአቅሙ ተወዳድሮ ቦታውን የሚይዝ የሰው ኃይል እንዲኖር፣ የሲቪል ሰርቪስ ምደባ መመርያው ከሚፈቅደው ውጪ የተለየ ምደባ እንዳይሠራና በቀጣይም በተቀመጠው ሕጋዊ አሠራር መሠረት ብቻና ብቻ ተፈጻሚ እየሆነ እንዲሄድ የሚታገል መሆኑን አሳውቋል፡፡

አዲስ አበባ ውስን የሆነው የመሬት ሀብት ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ እየተወረረና ሕገወጥ ተግባራት እየተፈጸመ መሆኑን የገለጸው ኮሚቴው፣ ‹‹ይህ ድርጊት የሕዝብንም ሆነ የመንግሥትን ጥቅም የሚያሳጣና ኢፍትሐዊነትን የሚያነግሥ በመሆኑ እንዲታረም በፅኑ የምንታገል መሆኑን እናረጋግጣለን፤›› ብሏል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ የሚኖረው የአመራርና የሰው ኃይል ምደባና ሥምሪት የሕዝብን ቀመር ማዕከል ያደረገ፣ እንዲሁም የከተማዋን ሕዝቦች የሚመስል ሥርዓት በመዘርጋት አዲስ አበባችን የነዋሪዎቿና የሁሉም ኢትዮጵያዊያን መሆኗን በተግባር እንዲረጋገጥ ተቋማዊ ትግል እንደሚያደርግም ኮሚቴው አክሏል፡፡

‹‹ትናንት የገጠሙንን ውስብስብና ፈታኝ ሴራዎችንና አደጋዎችን በጋራ ትግላችን በፅናት እያለፍን እንደመጣነው ሁሉ፣ ወደፊትም የሚገጥሙንን ማናቸውንም ፈተናዎች መላ ሕዝባችንን ከጎናችን አሠልፈን በፅናት የምንታገል መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡ እኛ በአዲስ አበባ ከተማ የምንገኝ የአዴፓ አመራሮች በከተማዋ የሚኖሩ አማራዎችን በማሰባሰብና በማደራጀት ለመላው ሕዝብ ተጠቃሚነት ከምንጊዜውም በላይ የምንተጋ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን የአያት ቅድመ አያቶቻችንን ታሪክ፣ ወግ፣ ልማድና ትውፊት ለትውልድ ለማስተላለፍ የአባቶቻችን ገድል በመዘከር ትክክለኛ ታሪክንና ትውፊትን በማስረፅ ተሻጋሪ የታሪክ ክታብ በመተየብ፣ በየተግባራቱ ሁሉ እያካተቱ በማስተዋወቅ የአማራ ባህል ከሌሎች ሕዝቦች ጋር እንደ ትናንቱ የሚያስተሳስረንና የሚያጋምደን ኢትዮጵያዊ ኩራት ሆኖ እንዲቀጥል እናደርጋለን፡፡ የተጀመረውገራዊ ለውጥ እንዳይቀለበስ አዴፓ እንደ ትናንቱ ሁሉ ዛሬም በፅናት ይታገላል፤›› በማለት መግለጫውን ደምድሟል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር ሲጨምር የሚኒባስ ታክሲዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣቱ ሊታሰብበት ይገባል

በአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት አገልግሎት በመስጠት ከፍተኛ የሚባለውን ድርሻ...

ሃምሳ ዓመታት ያስቆጠረው አብዮትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውጣ ውረድ

የኢትዮጵያ ሕዝቦች የዴሞክራሲ ለውጥ ጥያቄ የሚነሳው ከፋሺስት ኢጣሊያ ወረራ...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የተፈጸመው ሕገወጥ ተግባር ምንድነው?

የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የዳይሬክተሮች ቦርድ፣...

በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ላይ ምርመራ እንዲደረግ ውሳኔ ተላለፈ

ፕሬዚዳንቷና ዋና ጸሐፊው ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ተብሏል ከአዲስ አበባ ንግድና...