ባለፈው ሳምንት በፕሪቶሪያ በሚኖሩ የውጭ ዜጎች ላይ የተጀመረው ጥቃት በተያዘው ሳምንት በጆሃንስበርግ በመቀጠል ለብዙዎች ንብረት መዘረፍ ምክንያት ሆኗል፡፡
በኢኪሩሂዊሊኒ፣ በችዋኔና በማዕከላዊ ጆሃንስበርግ በውጭ ዜጎች ላይ የተፈጸመው ጥቃት፣ በተለይም የንግድ ተቋማት ላይ ባነጣጠረው ዘረፋ የተሳተፉ ናቸው የተባሉ ከ90 በላይ ዜጎች መታሰራቸውንም አፍሪካን ኒውስ ኤጀንሲ ዘግቧል፡፡
የውጭ ዜጎች ንብረት የሆኑ ተሽከርካሪዎችንና ሕንፃዎችን በማቃጠልና በመዝረፍ ላይ ባተኮረው ጥቃት ተሳትፈዋል የተባሉ በርካታ ደቡብ አፍሪካውያንን እያሰረና እያደነ መሆኑንም የአገሪቱ ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የውጭ ዜጎችን መፍራት፣ መጥላትና በተለያዩ ጊዜያት ጥቃት መፈጸም በደቡብ አፍሪካ የተለመደ ቢሆንም፣ የአሁኑ ጥላቻን ሳይሆን ዝርፊያን የሚያሳይ ወንጀል መሆኑን የአገሪቱ ፖሊስ ሚኒስትር ቤኪ ሲሌ መግለጻቸውን ቢቢሲ አስፍሯል፡፡
የጆሃንስበርግ የንግድ ማዕከል የሆኑ ሥፍራዎችን የጎበኙት ሚኒስትሩ ሲሌ፣ የዘረፋ ወንጀል ቢፈጸምም፣ በውጭ ዜጎችና በደቡብ አፍሪካውያን መካከል ግጭት አለመፈጠሩን ገልጸዋል፡፡
ፖሊስ ዘራፊዎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ፣ እውነተኛ ያልሆነ ጥይትና ገዳይ ያልሆነ ፈንጂ መጠቀሙም ታውቋል፡፡
ደቡብ አፍሪካ ከቅርብ ወራት ወዲህ ተከታታይ የጥላቻ ጥቃቶችን እያስተናገደች ሲሆን፣ በዚህም ሳቢያ ከሳምንት በፊት የታክሲ አሽከርካሪ፣ በመጋቢት ደግሞ በደርባን በሚገኙ የውጭ ዜጎች ሱቆች ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሦስት ሰዎች ተገድለዋል፡፡
እሑድ በጆሃንስበርግ በተቀሰቀሰ ጥቃትም፣ በከተማዋ ማዕከላዊ የንግድ ቀጣና በሚገኝ ሕንፃ ላይ እሳት በመነሳቱና ሕንፃው በመደርመሱ ሦስት ሰዎች ሞተዋል፡፡
በጆሃንስበርግ በሚገኙት በዴንቨር፣ ማልቨርን እንዲሁም በቴምባሲ አካባቢዎች ባለፈው ሰኞ ጥቃቱ የተስፋፋ ሲሆን፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችም በየሱቆች በመግባት ሲዘርፉ፣ መኪናና ሕንፃ ሲያቃጥሉ ተስተውለዋል፡፡
ጥላቻና ጥቃት በጆሃንስበርግ
በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ የውጭ ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸምና ሱቆችን መዝረፍ የዕለት ተዕለት ገጠመኝ መሆኑን የቢቢሲው ተንታኝ ሚልዮን ኒኮሲ ይገልጻል፡፡ ዘረፋው የዕለት ተዕለት በመሆኑም ተግባሩን በቅርቡ ማስወገድ ይቻላል ብሎ ማሰብ ይከብዳል ብሏል፡፡
በደቡብ አፍሪካ በተለይ በጆሃንስበርግ በተደጋጋሚ በውጭ ዜጎች በተለይም በአፍሪካውያን ላይ ጥቃት ይደርሳል፡፡ በተለይ በናይጄሪያውያን ላይ ጥቃቱ ያይላል ሲሉ የናይጄሪያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ይገልጻሉ፡፡
በርካታ አፍሪካውያን ስደተኞች በሚገኙባት ደቡብ አፍሪካ ኢትዮጵያውያን ስደተኞችም ቢሆኑ ከጥቃት ያመለጡ አይደሉም፡፡ በርካቶቹ የአፍሪካ ስደተኞች በደቡብ አፍሪካ ሠርተው አዳሪ ሲሆኑ፣ በተለይ በአነስተኛ ንግድ በመሰማራት ራሳቸውን የለወጡና የሚለውጡም ናቸው፡፡
ሆኖም ይህ ሥራቸው የአገሪቱን 79 በመቶ ሕዝብ ከሚሸፍኑት ጥቁር ደቡብ አፍሪካውያኑ በተወሰኑት ተቀባይነት የለውም፡፡ በአገሪቱ በተለይ በጥቁሮች ዘንድ ያለው ሥራ አጥነት አገሪቷ በስደተኞች ከመወረሯ ጋር የተያያዘ እንደሆነም ይታመናል፡፡ በመሆኑም በተገኘው አጋጣሚ ሁሉ ከአፍሪካውያን ወንድሞቻቸው ጋር ጠብ መፍጠራቸው አልቀረም፡፡ አንዳንዴም አንዱን በማጥቃት የሚጀመር እንቅስቃሴ፣ ወደ ግጭት ያመራል፡፡ የቻለ ራሱን አስከብሮ ሲኖር፣ ያልቻለ ይዘረፋል፣ ንብረቱ ይቃጠላል ብሎም ይገደላል፡፡
28 በመቶ ያህል ሕዝቧ ሥራ አጥ የሆነባት ደቡብ አፍሪካ፣ ከአፓርታይድ አገዛዝ ነፃ ከወጣች ከሁለት አሠርት በላይ ብታስቆጥርም፣ በነጭና ጥቁር መሀል ያለው የኢኮኖሚ ልዩነትም ዛሬም አልጠበበም፡፡ ትምህርት የማግኘት ዕድልም ቢሆን ለጥቁር ደሃ ደቡብ አፍሪካውያን ብርቅ ነው፡፡ በተሻሻለ ቤት መኖር፣ የተሻሻለ መፀዳጃ ማግኘትም ሆነ መሠረታዊ ፍላጎትን ማሟላት ሩቅ የሆነባቸው ደቡብ አፍሪካውያን በብሶት እንደሚኖሩ ይነገራል፡፡
ደቡብ አፍሪካውያኑ ከፖሊስ ጋር ግጭት ለመፍጠር አንዱ ምክንያታቸውም ድንገት ተደራጅተው የንግድ ተቋማትን መዝረፋቸውና ማውደማቸው ነው፡፡