Saturday, December 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርፖለቲካን እንደ ቤተሰብ

ፖለቲካን እንደ ቤተሰብ

ቀን:

(ክፍል ሁለት – እናት)

በሰለሞን መለሰ ታምራት

እናቱ ያሳደገችውን ልጅ “የሴት ልጅ” ብሎ መጥራት እንደ ስድብ መቆጠሩን ለመረዳት፣ በራሳችን ላይ እስከ ሚደርስብን መጠበቅ የሚያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ በአንፃሩ የቤተ ክርስቲያን መምህራን (እኔ የምከታተለው የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንን መሆኑ ይታወቅልኝና) “ሴት” የሚለው ቃል ከፆታ መጠሪያነትም ከፍ ብሎ የከበረ ትርጉም እንዳለው ሲያብራሩ አዳምጫለሁ፡፡ የመጀመርያው ሰው አዳም ብቻውን እንዳይሆን ከፈጣሪው የተሰጠችው ውብ ስጦታውን እንደተመለከታት፣ በሥጋም በአጥንትም አንድ መሆናቸውን ተረድቶ ሔዋን በሚለው ስም ሳይጠራት በፊት ቀድሞ ያገኘላት ገላጭ ቃል “ሴት” የሚለውን ነበር፡፡ ሴት እናት ስለሆነች ሁላችንም የተገኘነው ከእርሷ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ ሚስትም፣ እህትም፣ ደግሞም ልጃችን ሆና ታስደምመናለች፡፡ አገርም በሴት መመሰሉ እንዲያው የተፈጠረ አይመስለኝም፡፡ ለምንሳሳለት፣ ለምንወደውና የእኛ ለምንለው ጉዳይ ሁሉ የምናወጣለት ፆታ አንስታይ መሆኑን ያሳየናል፡፡ እናም የሴት ልጅ መባል እንደ ምርቃት መቆጠር ሲኖርበት፣ ለስድብ የሚበቃበቱ ምክንያት ምን ሊሆን እንደሚችል እኔን በገባኝ መንገድ ላቀርበው ፈልጌያለሁ፡፡

እናት ሆዷ ዥንጉርጉር ነውና የተለያዩ ልጆችን ትወልዳለች፣ በመልክም በፀባይም፡፡ አንዱ አመሥጋኝ ይሆናል፣ እርሱ ያገኘው ነገር ከሌሎች ጋር ሲወዳደር ምንም ልዩነት የሌለው፣ እንዲያውም ያነሰ እንኳን ቢሆን ለምሥጋናው ወደር አይኖረውም፡፡ ሌላው ደግሞ የእርሱ ተቃራኒ ሆኖ ይፈጠራል፣ እጅግ ብዙ ተደርጎለት ፈጽሞ ምሥጋና ቢስ ከመሆኑም በላይ መልካም ላደረገችለት እናቱ ክፉ የሚመኝም ሞልቷል (መሸጥ የለመደ እናቱን ያስማማል እንደሚባለው)፡፡ ኢትዮጵያን ለ17 ዓመታት ያስተዳደሩት “ጓድ” መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ተናግረውታል እንደተባለው፣ ‹‹ወርቅ ሲያነጥፉለት ፋንዲያ ነው›› የሚል ሰውም ይኖራል፡፡ ምን ያህል በሚመሩት ሕዝብ ተማረው ይህንን ሊናገሩ እንደቻሉ የሚያውቁት እርሳቸው ብቻ ናቸው (ላለፉት 28 ዓመታት ከባለቤታቸው ጋር ተንደላቀው ለመኖርና ልጆቻቸውን ለወግና ለማዕረግ አብቅተው፣ የልጅ ልጅ ለማየት የመታደላቸውን ሚስጥር ለጊዜው እንለፈውና)፡፡ እናም ዛሬ በአገራችን ምድር የምናየውና የምንሰማው የፖለቲካ ጫጫታ ወርቅ ላበደረ ጠጠር ከሚባለውም በላይ ደርሷል ሊባል ይችላል፡፡

እናት ያሳደገችው ልጅ ባለጌ ይሆናል ተብሎ እንዲቆጠር ያበቃው ከዱላ ይልቅ፣ በምክርና በልመና ሲብስባትም በዕንባ ልጆቿን ለማሳደግ ከመፈለጓ ጋር የተያያዘ ሳይሆን አይቀርም፡፡ በግልጽ እንደሚታወቀው እናት ከፍቅሯ ብዛትም ይሁን፣ ከአቅሟ ማነስ ጉልበትን ለልጆች ሥነ ሥርዓት ማስያዣነት የምትጠቀመው አማራጮቿ ሁሉ ከተሟጠጡባት ይሆናል፡፡ በአገራችን ከአባታቸው ይልቅ በእናታቸው ስም የሚጠሩና መጠሪያቸውን እንዲሁ እንዲሆን የፈቀዱ ሰዎች እየበዙ የመምጣታቸው አንዱ ምክንያት፣ ለእናት ያላቸውን ጥልቅ አክብሮት ሊገልጹ የሄዱበትን ርቀት የሚያሳይ ነው፡፡

ይኼንን ሁሉ መንደርደሪያ ያነሳሁበት የጽሑፌ ግብ የእናትና የአባት ጉዳይ ሆኖ አይደለም፡፡ ነገር ግን አገር በእናት መመሰሏ እንዳለ ሆኖ ዛሬ ላይ  ሥልጣን  የያዘው                                                                                                                የዶ/ር ዓብይ አህመድ አስተዳደር ማንም ሊገምተው ያልቻለ መልካም ነገር አድርጎላቸው ሲያበቃ፣ ባለና በሌለ ጉልበታቸው ያንኑ ያጎረሳቸውን እጅ ለመንከስ በእጅጉ በመገዳደር ላይ ያሉት ግለሰቦች የጥላቻቸው ልክ ቢበረታብኝ፣ ምናልባት መልስ የሚሰጠኝ ሰው ይኖር እንደሆነ ብዬ ነው ብዕር ከወረቀት ያዋደድኩት፡፡

በቅድሚያ ልክ አሁን እኔ እያደረግኩ እንዳለሁት መቼምና በምንም ሁኔታ ቢሆን ሰዎች ሐሳባቸውን ያለ ምንም ገደብ እንዲገልጹ እሻለሁኝ፡፡ ሲጀመር ይህ ሐሳብን የመግለጽ ነፃነት ባይኖር ኖሮ ዛሬ እንዴት እንደዚህ ሊሆን ቻለ ብዬ የምጠይቅበትንም ርዕስ አላገኝም ነበር፡፡ የወደቀው የሕወሓት አስተዳደር (በቤተሰብ እንደ ፖለቲካ ክፍል አንድ መጣጥፌ የገለጽኩት የኢሕአዴግና የሕወሓት ጉዳይ ግልጽ ከሆነ፣ ኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን የመጣው በታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. ከዶ/ር ዓብይ አህመድ መመረጥ በኋላ መሆኑን መረዳት ይቻላል) አንዳችም የፖለቲካና የህሊና እስረኛ በአገሪቱ ውስጥ የለም በማለት ደጋግሞ ቢናገርም፣ ኢትዮጵያ በትክክልም የብሔርና ብሔረሰቦች እስር ቤት ሆና እንደነበር የተረጋገጠው ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሥልጣን በያዙ መንፈቅ እንኳን ሳይሞላቸው ከእስር በተለቀቁት ሰዎች ብዛት ነበር፡፡

በወቅቱ የነበረው መንግሥት በሰበብና በአስባቡ አስሯቸው የነበሩና መቼም እንደሚፈቱ የማያውቁትን፣ በፍርድ ቤት የተወሰነባቸውን እስር ጨርሰው ሲወጡ በድጋሚ ሰበብ ተፈልጎላቸው የታሰሩትን፣ ለዝንተ ዓለም ፍርድ ቤት በመመላለስ ወይ የማይፈረድባቸው አለያም ነፃ የማይወጡትን የታወቁ እስረኞችን እንዲያው ‘በሕግ ጥላ ሥር የሚገኙ’ ናቸው ብለን ብናልፋቸው እንኳን፣ እንደ ማዕከላዊና ‹ጄል ኦጋዴን›ን በመሳሰሉት የማሰቃያ ቦታዎች ታጉረው ፍዳቸውን ሲያዩ የነበሩ ግፉዓን ቀን የወጣላቸው፣ አዲሱ የኢሕአዴግ አስተዳደር ወደ ሥልጣን በመምጣቱ ነው፡፡ ከዚህ ውጪ እንኳንስ በሰው ልጆች በማንም ፍጥረት ላይ ሊፈጸም የሚከብድ አሰቃቂ ግፍ የደረሰባቸውና በይፋ በማይታወቁ የተለያዩ የማሰቃያ ቦታዎች ታጉረው ስለነበሩ ሰዎችም የሰማነውና ያየነው በዚሁ በተለወጠው አመራር ዘመን ነው፡፡ ምንም እንኳን አጀንዳው ተለውጦ በአንድ ዘር ላይ የተነጣጠረ ጥቃት እንዲመስል መደረጉ ጉዳዩን ተለባብሶ እንዲቀር አደረገው እንጂ፣ በዓለም አቀፉ የፍርድ ችሎት ሊታይ የሚገባው በሰው ልጆች ላይ የተፈጸመ አሰቃቂ ወንጀል ሊሆን ይገባ ነበር፡፡

ከ2008 ዓ.ም. መጀመርያ አንስቶ ለውጡ በይፋ ታውቆ መንግሥት የኃይል ዕርምጃ መውሰድ እስካቆመበት መጋቢት 2010 ዓ.ም. ድረስ በየዕለቱ ሊባል በሚችል ሁኔታ ለተቃውሞ በወጡ ኢትዮጵያውያን ላይ በየአቅጣጫው ይወሰድባቸውም የነበረው ወታደራዊ ዕርምጃ፣ ደርግ አውጆት ከነበረው የቀይ ሽብር ዕርምጃ ጋር የሚተናነስ አልነበረም፡፡ የዓለም አቀፍ መገናኛ ብዙኃን የዕለት ተዕለት ሽፋን ለማግኘት ያልቻለበት አንድና ዋነኛ ምክንያቱ፣ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ ውስጥ ባለመከሰቱ ብቻ ነው፡፡ በሱዳን ለሦስት ወራት የዘለቀው የሕዝቡ ተቃውሞ የቀጠፈው የሰው ብዛት በኢትዮጵያ ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከፈሰሰው ደም ጋር ሲተያይ ከቁጥር የሚገባም አልነበረም፡፡ ነገር ግን የሱዳን የሕዝብ ተቃውሞ በዋና ከተማዋ ካርቱም የሚካሄድ በመሆኑና የጦር ኃይሉም ሕዝባዊ አመፁን መቀላቀሉን ተከትሎ ዓለም አቀፍ ሽፋን በሰፊው ከማግኘቱም በላይ፣ የተፈራው የፀደይ አብዮት ክስተት (የፀደይ አብዮትን ተከትሎ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ አገሮች እንዳልነበሩ ሆነው የመቀጠላቸው ሁኔታ) ሰለባ ሳይሆኑ በአጭሩ ሊቋጭ ችሏል (የኢትዮጵያን በተለይም የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)  ድርሻ በራሳቸው በሱዳኖቹ በሰፊው የተባለለት በመሆኑ የእኔ ተጨማሪ ምስክርነት አስፈላጊነቱ አይታየኝም)፡፡ በኢትዮጵያ የተነሳው ሕዝባዊ አመፅ የተቃውሞው ወላፈን አዲስ አበባን ዙሪያዋን ሲለበልባት ከርሞ ማንም ባልጠበቀው መንገድ የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ፣ “የመፍትሔው አካል ልሁን” ብለው በወሰዱት ዕርምጃና እሱንም ተከትሎ የለውጥ ኃይሉ (ቲም ለማ) በፓርቲው የውስጥ ድርድር ወቅት ባደረገው ብርቱ ፍልሚያ፣ ያለ አንዳች ኮሽታ ይኼ ለውጥ ተከስቷል፡፡ ምንም እንኳን ዛሬ እንዲህ እንደ ተራ ጉዳይ አቃለነው ከህሊና ማኅደራችን እንደ ዋዛ እየጠፋ መምጣቱ ከፋ እንጂ፡፡

ቀደም ሲል የጠቀስኳቸው የተለያዩ “በሕግ ጥላ ሥር” የነበሩና የነበሩበትም የማይታወቁ የሥርዓቱ ሰለባዎች አንድ በአንድ ነፃ ሲወጡ፣ ሥርዓቱን በመሸሽ በውጭ አገር ለተሰደዱትና በአገር ውስጥም በየስርቻው ተደብቀው ለሚገኙ ፍርደኞች፣ ተከሳሾችና በጥብቅ ተፈላጊዎች አጠቃላይ ምሕረት ተደረገላቸው፡፡ አሸባሪ የሚለው ስም የሚገባው መንበሩን ተቆጣጥሮ ሥልጣን ከእጁ እንዳይወጣ በንፁኃን ላይ ጭፍጨፋ ሲያካሂድ የነበረው አካል እንጂ፣ ወገኖቻቸውን ከስቃይ ለመታደግ አማራጭ በማጣት ተገደው ወደ ትግል ለገቡ ዜጎች አለመሆኑን አዲሱ የኢሕአዴግ ሊቀመንበር አስታወቁ፡፡ ከቶውንስ ይኼንን የለውጥ ዕርምጃ አለማድነቅ እንዴት ይቻላል? ይኼንን በህልማችንም ሆነ በዕውናችን የማናስበው ፍፁም ሰላማዊ ለውጥ በምን ፍጥነት ተረስቶ ነው ዛሬ ለዚህ የለውጥ ኃይል የጎን ውጋት ለመሆን የበቃነው? እውነቱን እንነጋገርና ኢትዮጵያውያን ስንባል የምንፈልገውን በትክክል እናውቀዋለን ወይ?

ሕወሓት በሚመራው የ27 ዓመት አስተዳደር ዘመን ካሳደዳቸው ኢትዮጵያውያን መካከል በከፍተኛ ሁኔታ የሥርዓቱ በትር ያረፈባቸው የግሉ ፕሬስ አባላት ናቸው ብል የተሳሳትኩ አይመስለኝም፡፡ የግሉ ፕሬስ አባላት ከሙያውም ሆነ ከሥነ ምግባር ጋር የተያያዙ በርካታ ችግሮች የነበሩባቸው ቢሆንም፣ በአንድ ወቅት እንደ እንጉዳይ ከከፈሉበት ዘመን አንስቶ በሚከፍሉት ዋጋ እየተመናመኑ በመሄድ በአንድ እጅ ጣቶቻችን ልንቆጥራቸው ደርሰን እንደነበር አይረሳም፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም ስማችንን ተደጋግሞ እንደሚነሳው የፕሬስ ነፃነትን በማፈን በዓለም ላይ ከሚገኙት አገሮች በመጨረሻው ደረጃዎች ላይ የመቀመጣችን እውነታ የሚናገረው ሀቅ ይህንኑ ነው፡፡ ዛሬ በለውጡ አስተዳደር ከአካልና ከህሊና እስረኝነት ሙሉ በሙሉ በመፈታታቸው ደስታቸው ጣራ ይነካል ብለን ስንጠብቅ፣ ከማንኛውም የለውጡ ተቃዋሚ ነኝ ከሚል ኢትዮጵያዊ በላይ ባለፈው አንድ ዓመት በለውጡ አመራሮች ላይ የጭቃ ጅራፋቸውን ሲያሳርፉ ከርመዋል፡፡

ፕሬሱ ለመጣው መንግሥት እንዲያጎበድድ አይጠበቅበትም፣ ፈጽሞ፡፡ ነገር ግን  በሚታዩት ተጨባጭ እውነታዎች ላይ ተመሥርቶ መልካሙን ነገር ማበረታታት፣ ክፉ ሁኔታ ሲፈጠርም እርምት እንዲወሰድ ማንቃት ድርሻው ሊሆን ይገባል፡፡ በአንፃሩ  ለዓይን ክፉ የሚመስሉ ጉዳዮችን ብቻ እየመዘዙ ማጥላላት፣ በተለይ ለዘመናት ስንናፍቀው የነበረውን ነፃነትና ተስፋ ባሳየን ሥርዓት ላይ ሲሆን፣ የበሉበትን ወጪት መስበር እንጂ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?

ዛሬ በዚህ ጽሑፌ የምዳስሳቸው የፕሬስ ውጤቶች የለውጡ ምልክት ተደርገው የሚቆጠሩትን ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድን (ዶ/ር) ለማጥላላት የሚሄዱበት ርቀት ከማሳዘንም አልፎ አስቂኝ ይሆናል፡፡ ለምሳሌ “ኮሎኔል ዓብይ” ብሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩን መጥራት ዛሬም በወታደራዊ አገዛዝ ሥር እንገኛለን የሚለውን መልዕክት ከማስተላለፉም በላይ፣ ከደርጉ ዘመን መሪ ከኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር በማነፃፀር የሚፈጥረው አሉታዊ ገጽታ ቀላል አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ጥላሸት መቀባቱ ለባለቤታቸውም ተርፏል፡፡ በአንዱ የዚሁ የነፃነት ገፈት ቀማሽ በሆነ “ጋዜጠኛ” የኅትመት ውጤት ላይ ቀዳማዊቷ እመቤት በዚህ ሁኔታ ተገልጸዋል፣ ‹‹በወታደራዊ የሙዚቃ ባንድ ውስጥ ያለፉት ድምፀ መረዋዋ ባለቤታቸው ዝናሽም፣ በሕይወታቸው በዶ/ር ዓብይ ላይ ዛሬም ድረስ ተፅዕኖአቸው የጎላ ነው፡፡ ዶ/ር ዓብይ ከሌሎች አምባገነን መሪዎች የሚወስዱት ክፉ ትምህርት ካለ፣ ከእርሳቸው በኋላ ይህች መከረኛ አገር በወይዘሮዋ ትመራ ይሆናል፤›› ተብለዋል፡፡ በዚሁ ጉደኛ የኅትመት ውጤት ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የአስትሮሎጂ ኮከብ ምልክት ሳይቀር በመተንተን ‘ጀብደኝነት’ የሚያጠቃቸው እንደሆኑና ተቺዎቻቸውንም በበጎ ጎን እንደማያዩ በማስጠንቀቅ ሊያስፈራራን ይሞክራል፡፡ የትውልድ ከተማቸው በሻሻም ሳትቀር በኦነግ ምሽግነት ተፈርጃለች፡፡ ምናልባት የኦነግ ምልምል ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት እንድንይዝ ለማስቻል ይመስላል፡፡ ይኼው ላለፉት ጥቂት ወራት በየሳምንቱ የሚቀርብ የኅትመት ውጤት በፊት ሽፋኑ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩን የተለያዩ አሉታዊ ጎኖች ሊያሳዩ በተፈለጉ የፎቶ ሾፕ ምሥሎች በመድመቅ ዛሬም ድረስ ገበያውን አጨናንቆ ይዞታል፡፡

ሌላኛው የዚሁ የሴራ ፖለቲካ (Conspiracy Theory) ቡድን ፊታውራሪ እንዲሁ በዚሁ የለውጥ ዕርምጃ ነፃ ከወጡት መካከል አንዱ ነው፡፡ ለአንድ የፖለቲካ ድርጅትና ለግለሰቦች ያለውን የመረረ ጥላቻ በየሳምንቱ በሚወጣው የኅትመት ውጤቱ አማካይነት ማሠራጨቱ አንሶት፣ በአንድ ስብሰባ ላይ አምስት ሺሕ የሚጠጉ የከተማው ነዋሪዎች በጭብጨባ መርጠውኛል በማለት የከተማችሁ ባለ አደራ አመራር ሆኛለሁ ሊለን የሚቃጣው “ጋዜጠኛም” ነው፡፡ እስክንድር ነጋ በኦነግም ሆነ በኦዴፓ ላይ ያለውን ሥር የሰደደ ጥላቻም ይሁን የኦነግን ዓላማ ከሚደግፉ ግለሰቦች ጋር የገባውን የእልህ እሰጥ አገባ በሺሕ ለሚቆጠሩ የጋዜጣው አንባቢያን ያለገደብ የሚያቀርብበት የኅትመት ውጤቱን በተመለከተ፣ ይህንኑ አማራጭ (Platform) ያገኘው እንዲህ አምርሮ ከሚጠላው ኦዴፓ/ኢሕአዴግ መሆኑን በመርሳት ዳግም ወደ ፖለቲካው እንዳይመጡ (እንዳይመረጡ) በትጋት እሠራለሁ ሲል በተደጋጋሚ ሲገልጽ ያሳዝነኛል፡፡ ያጎረሰኝን እጅ ለመቁረጥ ወደ ኋላ አልልም የሚል ፉከራ ማንን ያዝናናል?

ይኼው ባለብዙ ሥልጣን አብዮተኛ (ጋዜጠኛ፣ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና፣ የባለ አደራ ምክር ቤት ሰብሳቢ በነገራችሁ ላይ የአዲስ አበባ ባለአደራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ ዋና መቀመጫው ዋሽንግተን ዲሲ መሆኑን ልብ በሉልኝ) ሰኔ 15 ቀን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ተካሂዶባታል ወደተባለችው የባኅር ዳር ከተማ በጥይት እየተናጠች በምትገኝበት ሰዓት እግር ጥሎት እዚያው መገኘቱ አንሶት፣ ከአውሮፕላን ማረፊያው ወጥቼ ወደ ከተማው እንዳልገባ ተከልክያለሁ በማለት ከፍተኛ ወቀሳውን በመንግሥት ላይ ሲያቀርብ የሰማሁኝ ዕለት፣ ሕፃን ልጅ እሳት ውስጥ አጄን ካላስገባሁ ብሎ እንደሚያለቅሰው ዓይነት ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ፈጥሮብኝ እንደነበር መሸሸግ ያለብኝ አይመስለኝም፡፡ እንዲያው ወደ ከተማው እንዲገባ ፈቅደውለት ቢሆንና አንድ ጉዳት ደርሶበት ቢሆን ምን ሊባል ነበር? እሱ እንደሚያስበው በዚህ የለውጥ ኃይል ጥርስ የተነከሰበት ሰው ቢሆን ኖሮ ይኼ አጋጣሚ መቼም መቼም የማይገኝ ዕድል ነበር፡፡ ‹ገዳይ ሲያረፋፍድ ሟች ይገሰግሳል› እንደሚባለው፡፡ በአካል ሊታደምበት አገጣጥሞት ከነበረው የባህር ዳሩ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ጋር በተያያዘ የተወሰኑት የባላደራ ምክር ቤት “አመራሮች” በተጠርጣሪነት መቅረባቸው በራሱ፣ ብዙ ጥያቄን የሚያስነሳ ጉዳይ ቢሆንም ለአሁኑ እንዝለለው፡፡

ከላይ የጠቀስኳቸውን ሁለቱን ጋዜጠኞች ፈጽሞ ከሚያስማማቸው ጉዳይ አንደኛው በሰኔ 15 ቀን የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ ላይ ያላቸው አተያይ ነው፡፡ በዕለቱ የተፈጸመው መፈንቅለ መንግሥት አልነበረም ከሚለው አመለካከታቸውም ባሻገር፣ በተለይም አንዱ ጋዜጠኛ ባለፈው የሕወሓት ዘመን የመፈንቅለ መንግሥቱ ዋነኛ ጠንሳሽ ከነበሩት ጄነራል አሳምነው ጽጌ ጋር በአንድ ላይ ታስረው በነበሩበት ወቅት፣ የታዘበውን ሃይማኖታዊ ፅናት በማድነቅ እንዲህ ዓይነቱን እርኩስ ተግባር ሊፈጽሙት እንደማይችሉ በመከራከሪያነት የሚያቀርበው በዚሁ ለውጡን በሚያብጠለጥልበት የኅትመት ውጤቱ ላይ ነው፡፡ ስፍር ቁጥር ከሌላቸው የሴራ ትንተናዎቻቸውም ባሻገር ሁለቱም ጋዜጠኞች የጄኔራሉን የቅርብ ቤተሰቦች በየኅትመት ውጤቶቻቸው ላይ በማቅረብ፣ ‹‹በእርግጥ ጄኔራሉ ይህንን ክፉ ተግባር ፈጽመውታል?›› ዓይነት ጥያቄ እያቀረቡላቸው በሚሰጡት የተረጋገጠ መልስ የተፈጠረውን ጉዳይ ለማጣጣል የተቻላቸውን ሁሉ ጥረት በማቅረብ ብዙ ደክመዋል፡፡

እነዚህን ዓይነት “ጋዜጠኞች” እና መሰል ለውጡ ያመጣውን የነፃነት ትሩፋት እያጣጣሙ፣ ለውጡ ግን ያልተመቻቸው ወገኖች በእናታቸው እጅ ያደጉ ቅምጥሎች ሆነው መኖርን ቀጥለዋል፡፡ ‹የማይመቱት ልጅ ሲቆጡት ያለቅሳል› እንደሚባለው አንዳንድ ፅንፍ የወጡ ዕርምጃዎቻቸው (በመከላከያ ሠራዊቱ መካከል ክፍፍል እንዲፈጠር የሚቀርቡ ዘገባዎችና አሁንም የአንድ ብሔር የበላይነት አለ ዓይነት ትርክቶች) አግባብ እንዳልሆኑ በሚነገራቸው ወቅት የሚያሳዩት የ‘ምን ታመጣላችሁ’ ንቀት፣ በአገራችን በየትኛውም አስተዳደር ያልታየ ሆደ ሰፊነት በመንግሥት በኩል መኖሩን የሚያመለክት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ፀብ የለሽ በዳቦ አካሄድ አባት ባለበት ቤተሰብ ውስጥ ቁንጥጫ እንደሚያስከትል ይታወቃልና የሚታሰብ አይሆንም፡፡ እነርሱም ኖረውበትና ደርሶባቸው አጣጥመውታል፡፡

ከጋዜጠኞቹና “አክቲቪስቶቹ” ባልተናነሰ ሁኔታ ለዚህ የለውጥ ዘመን ከፍተኛ ፈተና ከመሆንም በላይ በየደረሱበት ክብሪት በመጫር የብሔር ፅንፈኝነትን የሚያራግቡ ፖለቲከኞችም እንዲሁ፣ አዲሱ የለውጥ አመራር ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ነፃነታቸውን ያረጋገጠላቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ የክልላችሁ ቋንቋ እንዳያድግ የሚሆነው ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችሁ ጋር በምትፈጽሙት ጋብቻ ምክንያት ነው እያሉ በአደባባይ ለመስበክ ዕድሉን የሰጣቸውን ሕዝብና መንግሥት ለመከፋፈል የሚያደርጉት ጥረት በወንጀል ባያስጠይቃቸውም፣ ከፍተኛ ትዝብት ላይ ሳይጥላቸው ግን አይቀርም፡፡ ጥሩነቱ ለዘመናት በጋብቻና በጉርብትና የኖረውን ሕዝብ እንዲህ በአንድ ጀንበር ጋብቻ አትመሥርትና አትገበያይ በመባሉ ግራ የሚጋባ አለመኖሩ በጀን እንጂ፣ እንደ አጀማመራቸው እስከ ዛሬም ድረስ አንድ ላይ አንዘልቅም ነበር፡፡ ይኼ ማለት ግን በእነዚህ ፅንፍ የወጡ ንግግሮች የተወናበደ ሰው አይኖርም ማለት አይደለም፡፡ ሁሉንም ነገር የእኛ ነው የሚሉ ጥቂት ተከታዮችን ለማፍራት እንደሚችሉና በአንፃሩም እነርሱን ለመቃወም ፅንፍ ይዘው ለሚነሱ “አክቲቪስቶች” የሥራ ዕድል መክፈታቸውን ለመታዘብ ችለናል፡፡

የእነዚህኛዎቹ የብሔር ፀንፈኞች የተቃውሞ ዘይቤን ለየት የሚያደርገው ሌላው ጉዳይ ደግሞ፣ የመጣውን ለውጥ በፅኑ ይቃወመዋል ከሚባለውና እነርሱንም ለዓመታት በእስርና በስደት ፍዳቸውን ሲያስቆጥራቸው ከሰነበተው አካል ጋር ለመተባበር ዓይናቸውን የማያሹ የመሆናቸው ጉዳይ ነው፡፡ ምን ችግር አለው ማንዴላስ ቢሆኑ ለ27 ዓመታት በግፍ ካሰራቸው የነጭ ዘረኛ ቡድን ጋር ተባብረው የለም ወይ? ብሎ ለሚጠይቀኝ አንባቢ የምሰጠው መልስ ማንዴላ ከነጮች አገዛዝ ጋር ተባብሮ ሲሠራ የነበረው ለዘመናት ተንሰራፍቶ የነበረውን ኢፍትሐዊ ሥርዓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማስወገድ እንጂ፣ በእስር ሲያንገላታው ከነበረው አገዛዝ ጋር ተሞዳሙዶ በሌላው የጋራ ጠላታችን ነው በሚለው ማኅበረሰብ ላይ ለመነሳት እንዳልነበር አስረግጬ በመንገር ነው፡፡

በመግቢያዬ ላይ እንደጠቀስኩት ማንኛችንም ቢሆን፣ ከዘመናት በኋላ ያገኘነውን ሐሳባችንን በነፃነት የመግለጽ መብታችንን ፈጽሞ ልናጣው አይገባም፡፡ ለዚህ መሠረታዊ የሰብዓዊ መብታችን ዘውግ ብዙዎች ለዘመናት ብዙ ዋጋ ከፍለውበታል፡፡ ይህንኑ ብዙዎች ተመኝተው ያላገኙትንና በእጃችን የገባውን አጋጣሚ ያላግባብ ተጠቅመንበት፣ እስከ መጨረሻው እንዳናጣው ሥጋቴን ለመግለጽ ያህል ነው የጽሑፌ ዋነኛ መነሻ፡፡ ማንም ማገናዘብ የሚችል ሰው እንደሚረዳው የተሰጡን መብቶች የሚያስከትሏቸው ግዴታዎች አሏቸው፡፡ ግዴታዎቻችንን መወጣት ብቻም ሳይሆን፣ ልዩነቶቻችንን አቻችለን ተከባብረን ልንኖር የሚያስፈልጉ የሥነ ምግባር መርሆችም ሊጠበቁ ይገባል፡፡ ለምሳሌም ያህል አገራችንን እንድንወድ የሚያስገድድ ሕግ ባይኖርም ሞራላዊ ግዴታ እንዳለብን ግን ልንዘነጋ አይገባም፡፡ ጊዜ ሰጠኝ ተብሎም እርስ በርሱ የሚጋጭና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ የማያንፀባርቁ ትርክቶችን እየቆሰቆሱ አንዱን ማኅበረሰብ በአንዱ ላይ ማነሳሳትም አግባብ አይደለም፡፡ ይህች አገር ቀውስ ውስጥ ብትገባና ብትበጠበጥ ማነው የሚጠቀመው? ማንን አስጥለን ማን ወደ ሥልጣን እንዲመጣልን ነው የምንመኘው?

ዛሬ ያለው መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣበት የመጀመርያ ቀን አንስቶ በተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱበትን ዘርፈ ብዙ እንቅስቃሴዎች ታግሶና በእጁ የገባውን አቅምና አጋጣሚ ተጠቅሞ ወደ ኃይል ዕርምጃ ላለመግባት ያደረገውን ትዕግሥት በጽሑፌ መግቢያ ላይ እንደገለጽኩት፣ የእናትነትን ለውሳኔ ከመቸገር ልምድ ጋር አመሳስዬዋለሁ፡፡ በተለይም በአንድ እጃቸው የለውጡን ትሩፋቶች እያጣጣሙ ሥራ በፈታው እጃቸው ቦክስ ሊሰነዝሩ የሚቃጡትን ውለታ ቢሶች ዓይቶ እንዳላየ የሄደበት ርቀት የሚያስመሰግነው ቢሆንም፣ እነዚሁ ግለሰቦች የሚፈጥሩትን ወጀብ ግን በጥንቃቄ እያየ ከልኩ አልፎ የማይወጣበትን መንገድ ቢፈልግ መልካም እንደሆነ ለማስመዝገብ እወዳለሁ፡፡

ማጠቃለያ

ሁላችንም እንደምንረዳው አንድ ቤተሰብ ምሉዕነቱ የሚገለጸው እናት፣ አባትና ልጅ (ልጆች)ን በአባልነት ሲያቅፍ ነው፡፡ ቤተሰቡ ሰላም እንዲሆንም እነዚህ አባላቱ ተሳስበውና ተከባብረው መኖራቸውን ግድ ይላል፡፡ አባትም ሆነ እናት በየራሳቸው ባላቸው የባህሪ ልዩነት የተነሳ ሁለቱም አዋቂዎች ሚዛናቸውን ጠብቀው ለመጓዝ መቻላቸው፣ ከልጆቻቸውም አልፎ ለቤተሰባቸውም ሆነ ለአካባቢያቸው ሰላም የግድ አስፈላጊ ነው፡፡ የካሮትና የዱላው ምጣኔ አግባብነት ሊጠበቅ የሚችለው ሁለቱም ተጣማሪዎች በጋራና በፍቅር ሊጓዙ በሚፈቅዱበት መጠን ይሆናል፡፡ ምንም ያህል በተናጠል ጠንካራ ሰብዕና ቢኖራቸውም አባት ብቻውን ያሳደጋቸውም ሆነ እናት ብቻዋን ያሳደገቻቸው ልጆች በማኅበራዊም ሆነ በአዕምሮዋዊ ጤናቸው ላይ ጎዶሎ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ መንግሥትም ለሚያስተዳድራቸው ዜጎቹ የአባትነት ቁጣንና የእናትነት ርህራሔን አጣምሮ ማስተዳደሩ እንደ ቤተሰብ አባላት ለዜጎቹም ሆነ ለመላው አገሪቱ ህልውና፣ ከዚያም ከፍ ሲል ለቀጣናውና ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡም ሰላምና መረጋጋት የራሱን ድርሻ እንዲወጣ ያስችለዋል፡፡

 በሁለት ክፍሎች አማካይነት ላስተላልፍ የሞከርኩትም ቁምነገር መንግሥትን እንደ አንድ የቤተሰብ አባወራ በመውሰድ በውስጡ የሚፈጠር መከፋፈል፣ በቤተሰቡም ሆነ እኔ እንደ ልጆች በቆጠርኳቸው የአገሪቱ ዜጎች ግንኙነት ላይ ምን ሊፈጥር እንደሚችል የራሴን አባባል የገለጽኩበት ሆኖ ይቆጠርልኝ ዘንድ በትህትና አሳስባለሁ፡፡ ዕድሜና ጤና ይስጥልኝ፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...