Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርግራ የተጋቡ ገበያተኞችና ግራ አጋቢ ገበያዎች

ግራ የተጋቡ ገበያተኞችና ግራ አጋቢ ገበያዎች

ቀን:

በጌታቸው አስፋው

ሰማኒያ በመቶ ገበሬና ሃያ በመቶ የከተማ ሥራ ሠራተኛ በሆነባት ኢትዮጵያ ቀይና ነጭ ሽንኩርት፣ ኮረሪማ፣ ጤፍ፣ ቅቤ፣ ሥጋ፣ ዶሮ፣ እንቁላል፣ ወተት፣ ዳቦ ወዘተ. ሸቀጦች ዋጋዎች እየተወደዱ መሄድ ሕዝቡን እያስመረረ ነው፡፡ የአጠቃላይ ዋጋዎች አመልካችም እስከ ሃያ በመቶ በመድረስ በሁሉም ሸቀጦች ላይ ያለው የዋጋ ንረት ምሬት ተባብሷል፡፡ በአንፃሩ ደግሞ የውጭ ሸቀጦቻችን ዋጋዎች በውጭ ገበያ እየወደቁ ኤክስፖርተሮችን አማረዋል፡፡ አገሪቱ ከወጪ ንግድ የምታገኘው ገቢ በጥቅሉም ሆነ በእያንዳንዱ የሸቀጥ ዓይነት ሲታይ አሽቆልቁሏል፡፡ በዋጋ ንረት፣ በሥራ ቅጥርና በውጭ ምንዛሪ ግኝት ብሔራዊ ኢኮኖሚው አልረጋጋ ብሏል፡፡

ከሁለቱ የገበያ ኢኮኖሚ የጥናት መስኮች አንዱ ማይክሮ ኢኮኖሚክስ በእጅ ያለው የምርት ማምረቻ የተፈጥሮ ሀብት፣ የሰው ኃይልና ካፒታል የሰዎችን ፍላጎቶች ለማሟላት እንዴት በተለያዩ የምርት ዓይነቶች ይደለደላሉ የሚል የተናጠል ገበያዎች በውድድር የዋጋ አወሳሰን ጥናት ሲሆን፣ ሁለተኛው ማክሮ ኢኮኖሚክስ ግን በአገር ያለውን የምርት ማምረቻ የሰው ኃይልና ቁሳዊ ሀብት ሁሉ በአግባቡ ተጠቅሞ ገበያዎችን በማረጋጋት፣ እንዴት ያለ አቅምን አሟጦ መጠቀምና ማሳደግ ይቻላል የሚል የጥቅል ኢኮኖሚ ጥናት ነው፡፡

የማይክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት መስኮች ፍላጎት፣ አቅርቦትና የገበያ እኩልነት (Market Equilibrium) ሲሆኑ፣ ጥናቶቹ የሚመሠረቱት በሸማቾችና በአምራቾች ባህሪያት ታሳቢነት ነው፡፡ እነዚህ ታሳቢዎችም ሸማቾች ከሸቀጦች የሚያገኙትን ጥቅም ከፍተኛ ለማድረግ፣ አምራቾችም ከምርቶቻቸው የሚያገኙትን ትርፍ ከፍተኛ ለማድረግ ይጥራሉ ነው፡፡ እነዚህ ታሳቢዎች ሁሌም ትክክል ባይሆኑም፣ ኢኮኖሚስቶች በጥናታቸው የተሟላ ግምት መስጠት ያስችሏቸዋል፡፡

የማክሮ ኢኮኖሚክስ ጥናት አጠቃላይ ኢኮኖሚውን የተረጋጋ ለማድረግ የሦስት ገበያ ዓይነቶችን የምርት ገበያውን (Product Market)፣ የጥሬ ገንዘብ ገበያውን (Money Market) የሠራተኛ ገበያውን (Labor Market) ጣምራ እኩልነት በአንድ የሒሳብ ሥሌት ሞዴል ወይም በአንድ ዲያግራም ላይ በማመልከት፣ አጠቃላይ እኩልነትን (General Equilibrium) መፍጠር ማለት ነው፡፡ ቢያንስ ለሁለቱ ለምርት ገበያውና ለገንዘብ ገበያው ጣምራ እኩልነት ሳይፈጥሩ ማክሮ ኢኮኖሚውን ማረጋጋት ዘበት ነው፡፡

በ1987 ዓ.ም. ‹‹የኢትዮጵያን ትኩረት የሚሹ ሦስት የኢኮኖሚ ጥያቄዎች›› በሚል ርዕስና በ2007 ዓ.ም. ‹‹ግላዊና ብሔራዊ ኢኮኖሚያችን›› በሚል ርዕስ ባሳተምኳቸው ሁለት መጻሕፍት፣ ገና ያኔ የኢትዮጵያ ገበያዎች ዛሬ ስላሉበት ሁኔታ ጽፌአለሁ፡፡ በተለይም በግላዊ ኢኮኖሚው መጽሐፌ ክፍል አንድ ስለፍላጎት፣ ስለአቅርቦትና ስለገበያ መስተጋብር የማይክሮ ኢኮኖሚ ሁኔታዎች ተንትኜአለሁ፡፡ በክፍል ሁለት የማክሮ ኢኮኖሚ ክፍልም ስለጥቅል ኢኮኖሚው የነበሩትን ሁኔታዎች ገልጬአለሁ፡፡ ለማየትና ለመስማት ዓይኑንና ጆሮውን የሰጠ ሰው አልነበረም፡፡ ‹‹ምከረው ካልሰማህ መከራ ይምከረው›› የተባለው ዓይነት እየሆነ ነው፡፡ አሁን ካለው የገበያተኛው ግራ መጋባትና የገበያው ግራ አጋቢነት ጋር አነፃፅሬ ከ25 ዓመትና ከአምስት ዓመት በፊት ከጻፍኳቸው መጻሕፍት ውስጥ፣ ምንም ሳልቀይር እንደነበሩት ወስጄ አንዳንድ ነጥቦች ልጠቃቅስ፡፡

የገበያ ትርጉም

ገብይቼ እመለሳለሁ፣ ገበያ እሄዳለሁ፣ ዛሬ ገበያ ነውና ዕቃው ገበያ የለውም ይላሉ ሰዎች አንዱን ቃል በተለያየ ትርጉም አጠቃቀም፡፡ ምናልባት ግን ብዙ ሰዎች ስለገበያ ሲወሳ የሚገምቱት የቁሳዊ ዕቃዎችን ግዥና ሽያጭ ብቻ ወይም በአንድ እንደ መርካቶ ባለ የታወቀ የገበያ ቦታ የሚከናወንን የግብይት ሥርዓት ብቻ ይሆናል፡፡ ሆኖም  በኢኮኖሚክስ በማንኛውም ቦታ በማናቸውም ጊዜ ማንኛውም ዓይነት የምርት ግብረ ኃይሎች አገልግሎቶች ወይም የዕቃም ሆነ የአገልግሎት የሸቀጥ ልውውጥ የሚካሄድበት ቦታ ወቅትና ሥርዓት ሁሉ ገበያ ይባላል፡፡

በማንኛውም ገዥና ሻጭ ባለበት ቦታና ወቅት ሁሉ ገበያ አለ፡፡ በቤታችን ውስጥ እንኳን ውኃ እንገዛለን፣ የመብራት አገልግሎት እንገዛለን፣ የስልክ አገልግሎት እንገዛለን፣ የቤት ሠራተኛ ካለንም የሠራተኛውን አገልግሎት እንገዛለን፡፡ ፒያሳ ወይም አራት ኪሎ ሄደን የሕክምና ምርመራ ስናደርግ፣ ልብሳችንን ለላውንደሪ ስንሰጥ፣ ጫማ ስናስጠርግ፣ የሐኪሙን አገልግሎት፣ የልብስ አጣቢውን አገልግሎትና የጫማ አሳማሪውን አገልግሎት ከገበያ መግዛታችን ነው፡፡

አንድ ድርጅት ሠራተኛ ሲቀጥር የሠራተኛውን አገልግሎት ከገበያ መግዛቱ ሲሆን፣ ሠራተኛው አገልግሎቱን በገበያ ውስጥ ሻጭ ነው፡፡ በመንግሥት መሥሪያ ቤትም ሠራተኛ ሲቀጠር መንግሥት የሠራተኛውን አገልግሎት ከገበያ ገዥ ሲሆን፣ ሠራተኛው አገልግሎቱን በገበያ ውስጥ ሻጭ ነው፡፡ ብር ከባንክ ስንበደርና የብሩን አገልግሎት ከባንኩ ወይም ከገንዘብ ገበያው መግዛታችን ሲሆን፣ ባንኩ የብሩን አገልግሎት ለእኛ በገንዘብ ገበያው ውስጥ ሻጭ ነው፡፡ እኛ በጊዜ ወይም በቁጠባ ተቀማጭ ባንክ ገንዘብ ስናስቀምጥ ባንኩ የብሩን አገልግሎት ከእኛ መግዛቱ ነው፡፡ ለባንኩ የምንከፍለው ወይም ባንኩ የሚከፍለን የግብይት ዋጋም ወለዱ ነው፡፡ እንዲሁም ደግሞ አንድ ግለሰብ ወይም ድርጅት የከተማ ቦታ ወይም የእርሻ ቦታ ከመንግሥትም ሆነ ከግለሰብ ሲከራይ የቦታውን አገልግሎት ከመሬት አገልግሎት ገበያ መግዛቱ ሲሆን፣ የሚከፍለውም ዋጋ የቦታው ኪራይ ነው፡፡

የገበያ ዓይነቶች

የሸቀጦች ዋጋ በገበያ ውስጥ በፍላጎትና በአቅርቦት መስተጋብር የሚወሰንበት ሥርዓት ነፃ ገበያ ይባላል፡፡ ተመሳሳይ ምርቶች በሚያመርቱ አምራች ድርጅቶች ቁጥር ማነስና መብዛት ምክንያት፣ የሸቀጦች ዋጋ በተለያዩ መንገዶች የሚወሰንባቸው የተለያዩ የነፃ ገበያ ዓይነቶችም አሉ፡፡ የገበያዎች ዓይነት በሻጮች ብዛት፣ በሸማቾች ብዛት፣ በሸቀጦች የዓይነትና የጥራት ተመሳሳይነትና ልዩነት፣ በገበያተኞች ስለሸቀጡ በቂ መረጃና ዕውቀት መኖርና አለመኖር ሁኔታዎች ላይ ተመሥርቶ በሁለት ዋና ዋና ምድቦች ይከፈላሉ፡፡ እነሱም የጠራ ገበያና ያልጠራ ገበያ ተብለው ይጠራሉ፡፡ ያልጠራ ገበያም በውስጡ ሦስት ንዑሳን ክፍሎች አሉት፡፡

የጠራ ገበያ (Perfect Market) ባህሪ

ገበያው ሞቋል ይላሉ በገጠር በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ ሰዎች፣ በከተማዋ የገበያ ቀን ገበያተኛው የገበያውን ሥፍራ ጢም ብሎ ሲሞላው፡፡ ይኸኔ ነው የከተማዋ ሰዎች ወደ ገበያ የሚወጡት፡፡ ጠዋት ገበያተኞች በሙሉ ሳይሰባሰቡና ወደ ማታ ገበያተኞች ወደ መበተን ደረጃ ሲደርሱ ዕቃዎች ወይ ይወደዳሉ፣ ወይ ይረክሳሉ ወይ ደግሞ ይታጣሉ፡፡  በስድስት ሰባትና ስምንት ሰዓት ላይ ገበያው ሲሞላ ወይም ሲሞቅ፣ ብዙ ሸማቾችና ብዙ ሻጮች ስለሚሰባሰቡ ረጋ ብሎ ገበያውን አጥንቶና አማርጦ የመግዛትና የመሸጥ ሁኔታ ይታያል፡፡ ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ የሆኑ ሸቀጦች በብዛት ወደ ገበያው የሚገቡበትና ገበያው በመጠኑም ቢሆን ካለመጥራት ወደ መጥራት የሚቃረብበት ጊዜ ነው፡፡

በከተሞችም ረቡዕ ወይም ሐሙስ ወይም ቅዳሜ የገበያ ቀን ተመርጦ ወደ ገበያ ይወጣል፡፡ ገበያው በሚሞላበት ወይም በሚሞቅበት ቀን ተመርጦ ገበያው በመጠኑም ቢሆን ካለመጥራት ወደ መጥራት ሲቃረብ፣ የጠራ የሚለው ቃል ከገበያ ጋር ቢያያዝም ትርጉሙ እንከን የለሽ ያልጎደፈ ወይም አንድ ገፀ ባህሪ ያለው ማለት ነው፡፡ ስለዚህም ንፁህ ውኃ የጠራ ውኃ ይባላል፣ ያልጎሸ ጠላ የጠራ ጠላ ይባላል፣ ጥሩ ዕቃ ጥራት ያለው ዕቃ ይባላል፣ ፀሐያማ የሆነ ቀን የጠራ ቀን ይባላል፡፡  የሸቀጥ ፍላጎትና የሸቀጥ አቅርቦት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የገበያ ጥናትም ቢያንስ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ቢሆን ኖሮ በሚል ታሳቢ በጠራ ገበያ ውስጥ ሊኖር የሚችለውን የግብይት ሁኔታ በማመልከት ይጠናል፡፡ ቢሆን ኖሮ የሚባለውም በተግባራዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ሙሉ በሙሉ የጠራ ገበያ በዓለም ውስጥ በየትኛውም አገር ስለማያጋጥም ነው፡፡

የጠራ ገበያ የሚፈጠረው ለገበያ የቀረበው ሸቀጥ በዓይነትና በጥራት ደረጃ ተመሳሳይ ሆኖ፣ የገበያ ኃይሎች የሆኑት ፍላጎትና አቅርቦት የሸቀጡን ዋጋ በጋራ ለመወሰን የሚያስችላቸውን ተመጣጣኝ አቅም እንዲያገኙ በሚያስችል መጠን በገበያው ውስጥ ሸቀጡን  የሚያቀርቡ ሻጮች ብዛትና ሸቀጡን የሚፈልጉ ሸማቾች ብዛት በርካታ ሲሆኑ ነው፡፡ የአንድ ነጋዴ ሸቀጥ ለገበያው ከቀረበው ተመሳሳይ ሸቀጥ ጋር ሲነፃፀር እጅግ አነስተኛ ስለሚሆን፣ ነጋዴው ዋጋ በማስወደድ በገበያው ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ አይችልም፡፡ በሸማቾች በኩልም ለገበያ የቀረበው ሸቀጥ ሁሉም ነጋዴዎች ዘንድ በጥራት ደረጃና በዓይነት ተመሳሳይ ስለሆነና ዋጋው ሁሉም ጋር እኩል መሆኑን ስለሚያውቁ ነጋዴ ሳያማርጡ መግዛት ይችላሉ፡፡

ያልጠሩ ገበያዎች (Imperfect Markets) ባህሪ

በፋሲካ ዋዜማ አመሻሽተው ገበያ ወጥተው ያውቃሉ? ከሁለት አማራጮች አንዱ ያጋጥምዎታል፡፡ ብዙ ዶሮና በግ ሻጮች ሸማች አጥተው ዋጋ ሰብረው ለመሸጥ ሲጣደፉ፣ ወይም ደግሞ ጥቂት ዶሮና በግ ሻጮች በብዙ ሸማቾች ተከበው ዋጋውን አስወድደው አንቀንስም ሲሉ ንትርኩ ሲበዛ፡፡ እነዚህ ናቸው ያልጠሩ ገበያዎች የሸቀጦች ዋጋ በቀንስ ጨምር ንትርክና ጭቅጭቅ የሚወሰንባቸው የገበያ ቦታዎች፣ የገበያ ወቅቶችና የገበያ ሥርዓቶች፡፡ የተለያዩ ሰዎች ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ለሆኑ ሸቀጦች የተለያዩ ዋጋዎች የሚከፍሉባቸው የገበያ ቦታዎች፣ የገበያ ወቅቶችና የገበያ ሥርዓቶች፡፡ ያልጠሩ ገበያዎች እንደ የሸቀጡ ዓይነትና የሸቀጡ አምራች ድርጅቶች ብዛት የተለያዩና በርካታ ዓይነቶች ሊሆኑ ቢችሉም፣ በኢኮኖሚ ጥናት ውስጥ በሦስት ዋና ዋና ምድቦች ተከፍለው ይገለጻሉ፡፡

አንድ ድርጅት ብቻውን አንድ ዓይነት ሸቀጥ ለገበያ የሚያቀርብ ከሆነ የአሀዳዊ (Monopoly) ገበያ ይባላል፡፡ በኢትዮጵያ የዚህን ዓይነት ገበያ ያላቸው ድርጅቶች በአገር አቀፍ ደረጃ ሲታይ እንደ የኢትዮጵያ አየር መንገድ በአገር ውስጥ በረራ፣ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎትና ኢትዮ ቴሌኮም፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ በተለያዩ የገበያ ቦታዎች ሲታይ ግን በአንድ የገጠር ከተማ አንድ መድኃኒት ቤት ወይም አንድ መጠጥ ቤት ወይም አንድ የሸቀጣ ሸቀጥ ሱቅ ብቻ ቢኖሩ፣ ለአካባቢው ገበያ አሀዳዊ ገበያዎች ናቸው፡፡ ሁለተኛው ያልጠራ ገበያ ዓይነት የአናሳ (Oligopoly) ገበያ በመባል የሚታወቅ ነው፡፡ በዚህ ገበያ ጥቂት ምርት አምራችና አቅራቢ ድርጅቶች እርስ በርሳቸው ስለሚተዋወቁ፣ አንዱ ሌላውን ሊጫረት የሚችልበት ወይም የዋጋ ስምምነት የሚያደርጉበት፣ ወይም ከመካከላቸው አንዱ ግዙፍ ሆኖ የዋጋ አወሳሰኑን ሲመራ ሌሎች ፋናውን የሚከተሉበት የገበያ ዓይነት ነው፡፡

በኢትዮጵያ በዚህ የገበያ ዓይነት የሚመደቡ ድርጅቶች የምርታቸውን ዋጋ ራሳቸው የሚወስኑ የግል አምራች ድርጅቶች፣ የውጭ አገር ሸቀጦች ነጋዴዎች፣ ወዘተ. ናቸው፡፡ በተለያዩ አካባቢዎችም ለአካባቢው ኅብረተሰብ ተመሳሳይ ሸቀጦች የሚያቀርቡ ጥቂት አምራችና ጥቂት አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች በዚህ የገበያ ዓይነት ይመደባሉ፡፡ ሦስተኛው ያልጠራ ገበያ ዓይነት የአሀዳዊነት ውድድር (Monopolistic Compitition) የሚባለው ገበያ ነው፡፡ በእያንዳንዱ ነጋዴ እጅ ያሉት ሸቀጦች በዓይነትና በጥራት ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ሆነው የነጋዴዎቹና የሸማቾቹ ቁጥርም በጣም ብዙ ቢሆንም፣ በሸማቹ ዓይን ድርጅቶቹ ለሸማቹ የመኖሪያ አካባቢ ቅርብ በመሆናቸው ወይም ሸማቾች ደንበኛ በመያዛቸው ወይም ሸማቾቹ በሸቀጡ ጥራት ጣዕምና የቀለም ወይም የቅርፅ፣ ወይም የእሽግ ዓይነት ምርጫ የግል ግምት በመውሰዳቸው፣ ወይም በሁሉም ምክንያቶች ነጋዴውን የሚመርጡበት ነጋዴውም ራሱን ከሌሎች የተለየ አድርጎ ለማቅረብ የሚጥርበት የገበያ ዓይነት ነው፡፡

ገበያዎች በመጥራትና ባለመጥራት ቀረቤታ

የጠራ ገበያ የግብይት ሥርዓት መሠረተ ነጥቦችን በሙሉ የሚያሟላ ገበያ በየትኛውም አገር አልነበረም፣ የለም፡፡ ወደፊትም ላይኖር ይችላል፡፡ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ ብቻ ሊታሰብ የሚችል ነው፡፡ የግብይት ሥርዓት ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴን ለመተንተን የሚረዳ የእንከን የለሽ ግብይት ትርጓሜ ሆኖ የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ግን ከፍተኛ ነው፡፡ ገበያዎችን ወደ ጠራ ገበያ ሥርዓት የተቃረቡ ወይም ከጠራ ገበያ ሥርዓት የራቁ በማለት ለመፈረጅ ማነፃፀሪያ ሆኖም ያገለግላል፡፡

በበለፀጉት አገሮች ውስጥ በአብዛኛው የጠራ ገበያ የግብይት ሥርዓት ሁኔታዎች ከሞላ ጎደል የተሟሉ ስለሆነና የዕቃዎች ዋጋም የሚወሰነው በቀንስ ጨምር ንትርክ ስላልሆነ፣ ገበያዎች ወደ ጠራ ገበያ የግብይት ሥርዓት የተቃረቡ ናቸው፡፡ በአገራችን ብዙ ሻጮችና ብዙ ሸማቾች ያሉባቸው የእርሻ ምርት ውጤቶች የሆኑ የእህል ዘሮች፣ ጥራጥሬዎች፣ አትክልቶች በዓይነታቸው በሁሉም ሻጮች ዘንድ ተመሳሳይና የጥራት ደረጃቸውም በመጠኑ ተቀራራቢ ከመሆናቸውም በላይ፣ ሸማቾችም ሆኑ ሻጮች ስለዕቃዎቹ ዓይነትና ዋጋ ስለገበያው ሁኔታ በቂ ዕውቀት ስለሚኖራቸው የእነዚህ ሸቀጦች ገበያዎች ወደ ጠራ ገበያ የግብይት ሥርዓት የተቃረቡ ናቸው፡፡  በጅምላ ንግድ የጅምላ ሻጮችና የጅምላ ሸማቾች ቁጥር ተመጣጣኝ፣ ሻጮቹም ሆኑ ሸማቾቹ ሸቀጦቹን በብዙ መጠን ስለሚሸጡና ስለሚገዙ ስለገበያው ሁኔታ፣ ስለሸቀጡ ዓይነትና ስለሸቀጡ ዋጋ አስቀድመው አጥንተውና አውቀው ስለሚገበያዩ ገበያዎቹ ወደ ጠራ ገበያ የግብይት ሥርዓት የሚያደሉ ናቸው፡፡

በሌላ በኩል መጠናቸው እጅግ አነስተኛ የሆኑ በጥቂት ነጋዴዎች እጅ የሚገኙ የውጭ አገርና የአገር ውስጥ ምርቶች ከሸቀጦቹ በመጠን ማነስም ባሻገር፣ በዓይነትና በጥራት ተመሳሳይ ባለመሆናቸውና ሸማቹም ሆነ ሻጮቹ ስለዕቃዎቹና ስለገበያው በቂ ዕውቀት ስለሌላቸው፣ ግብይቱም በቀንስ ጨምር ንትርክ ስለሚፈጸም የእነዚህ ሸቀጦች ገበያዎች ከጠራ ገበያ የግብይይት ሥርዓት የራቁ ናቸው፡፡ መርካቶ ያሉ የልብስና የሌሎች ሸቀጦች ዋጋቸው ጎን ለጎን ባሉ ሱቆች እንኳ በጣም የተለያዩ ስለሆኑ፣ የጨምር ቀንስ ንትርኩም የጦፈ ስለሆነ እነዚህ የአናሳ ገበያ መገለጫዎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ የዋጋ ለውጦች ታሪክ (1966 እስከ 1985)

ከ1966 እስከ 1985 ዓ.ም. በነበሩት ሃያ ዓመታት ውስጥ በኢትዮጵያ የሸቀጦች ዋጋ ጭማሪና ዕድገት ሁኔታን አስተውለን ለማስታወስ ብንሞክር፣ ጉራማይሌ መልክ ያለው የዋጋ ዕድገት ታሪክ እንዳሳለፍን እንገነዘባለን፡፡ የብዙዎቹ ሸቀጦች ዋጋ በሃያ ዓመቱ ውስጥ እስከ አሥር እጥፍ በሆነ መጠን ጨምሯል ብለን በጥቅሉ ልንናገር ብንችልም፣ የዋጋ ጭማሪና ዕድገት ሁኔታን በዝርዝር ስንመለከት ግን የጭማሪውና የዕድገቱ መጠን በእያንዳንዱ ሸቀጥ ላይ የተለያየ እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ የጥቂት ሸቀጦችን ዋጋ ጭማሪና ዕድገት ሁኔታ ወስደን መመልከትና ማነፃፀር እንችላለን፡፡

ክብሪት ከነበረበት የአምስት ሣንቲም ዋጋ በስምንት እጥፍ በማደግ የችርቻሮ ዋጋው አርባ ሳንቲም ደርሷል፡፡ ከሃያ ዓመት በፊት ከአምስት ኪሎ ግራም በላይ ክብደት ያለው ሽንጥ ሥጋ ዋጋው ከአሥር ብር አይበልጥም ነበር፡፡ ዛሬ በ1985 ዓ.ም. የአንድ ኪሎ ግራም ሥጋ ዋጋ 12 ብር ደርሷል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የበሰሉ የሆቴል ምግቦች የሽሮና የምስር ክክ ወጥ ወይም የሥጋ ወጥ ዋጋቸው በአማካይ በአሥር እጥፍ እንዳደገ ይገመታል፡፡ በ1965 ዓ.ም. 15 ሣንቲም የነበረው የሽሮና የምስር ክክ ወጥ በ1985 ዓ.ም.  አንድ ብር ከሃምሳ ሣንቲም ሲደርስ፣ ሃምሳ ሣንቲም የነበረው የሥጋ ወጥ ወደ አምስት ብር አድጓል፡፡

ያልበሰሉ የምግብ ሸቀጦች እህሎችም ሆኑ ጥራ ጥሬዎች ወይም የእንስሳት ተዋጽኦዎችና አትክልቶች ግን በዝርዝር ቢጠኑ የተለያየ የዋጋ ዕድገት መጠኖች ታሪክ ቢኖራቸውም ሁሉም በጥቅል ሲወሰዱ ከአምስት እጥፍ በታች የሆነ የዋጋ ዕድገት እንዳሳዩ ይገመታል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ የመኖሪያ ቤትና የማንኛውም ሕንፃ የወር ኪራይ እስከ አሥር እጥፍ አድጓል፡፡ ሃያ ብር ይከራይ የነበረው ቤት ወደ ሁለት መቶ ብር፣ ሃምሳ ብር ይከራይ የነበረው ቤት ወደ 500 ብር እንዳደገ ይገመታል፡፡ የቤት ሽያጭም ከሃያ በላይ እጥፍ በሆነ መጠን አድጓል፡፡ በብዙ ዓይነት የፋብሪካ ምርት ውጤቶች የታየው ዋጋ ለውጥም ጉራማይሌ ነው፡፡ ለምሳሌ ከቤትና ከሕንፃ ግንባታ መሣሪያዎች መካከል የቤት ክዳን ቆርቆሮ በ1965 ዓ.ም. ከነበረበት 2.50 ብር ዋጋ ሃምሳ ብር የችርቻሮ ዋጋ ሲደርስ የሃያ ጊዜ እጥፍ ዕድገት አሳይቷል፡፡

እንደ ስኳር፣ ቢራና ለስላሳ መጠጥ ወዘተ. የመሳሰሉት የፋብሪካ ምርቶች የችርቻሮ ዋጋቸው ከአምስት እስከ አሥር እጥፍ ሲያድግ የአገር ውስጥ ልብስ፣ የአገር ውስጥ ጫማዎችና እንደ ድስት፣ ሳህን፣ ብርጭቆ፣ ሲኒ፣ ሳሙና፣ ወዘተ. የመሳሰሉ የቤት ውስጥ ቁሳቁሶች በአጠቃላይ ከሦስት እጥፍ በማይበልጥ ጭማሪ ዕድገት እንዳሳዩ ይገመታል፡፡ የብዙ አገልግሎቶች የአልቤርጎ፣ የላውንደሪ፣ የፀጉር ማስተካካያና የጫማ ማሳመሪያ ወዘተ. የመሳሰሉት ዋጋ በጥቅሉ ከሦስት እጥፍ በታች እንዳደጉ ሲገመት ሌሎች አገልግሎቶች ለምሳሌ በአዲስ አበባ ከተማ የታክሲ መጓጓዣ ትራንስፖርት የአንድ ጊዜ እጥፍ እንኳን ዕድገት አላሳዩም፡፡

በመንግሥት ባለቤትነት ተይዘው ለሕዝብ አገልግሎት የሚሰጡ ዋጋቸውም በመንግሥት በሚወሰነው የመብራት፣ የስልክ፣ የውኃና የሌሎች አገልግሎቶችም ዋጋቸው ብዙ አልጨመረም፡፡ የሠራተኛ አገልግሎት ክፍያ ዋጋ ደመወዝ በተለይም የመንግሥት ሠራተኛ ደመወዝ በጥሬ ገንዘብ በጣም ዝቅተኛ ጭማሪ ቢያሳይም፣ ጥሬ ገንዘቡ ሸቀጥን በመግዛት አቅሙ ወይም የሠራተኛው እርግጠኛ ገቢ (Real Income) እስከ አምስትና ስድስት እጥፍ አሽቆልቁሏል፡፡

ከዚህ በላይ በተጠቀሱት ሸቀጦች ሁሉ ዋጋ ምን ያህል እንደተወደደ እንጂ፣ ፍላጎትና አቅርቦት መጨመራቸውን ወይም መቀነሳቸውን በምን ያህል እንደጨመሩና እንደቀነሱም አናውቅም፡፡ ሆኖም ዋጋቸው በጣም የጨመረ ሸቀጦች በዚያ ዋጋ ተፈላጊነታቸው ከፍተኛና አቅርቦታቸው ውስን እንደነበረና ዋጋቸው በጥቂቱ የጨመረ ሸቀጦች በዚያ ዋጋ ተፈላጊነታቸው ዝቅተኛና አቅርቦታቸው በቂ እንደነበረ በስሜትና በግምት መረዳት እንችላለን፡፡

በ2005 ዓ.ም. የዋጋዎች ሁኔታ ከሃያ ዓመት በፊት ከነበረው ጋር ሲነፃፀር ምግብ ሸቀጦች ገበያ ውስጥ

ዚህ ገበያ ውስጥ በቅርብ ዓመታት ሸማቹን ኅብረተሰብ ግራ የሚያጋቡ በርካታ ክስተቶች ተስተውለዋል፡፡ ሽንኩርት፣ ጎመን፣ ሰላጣ፣ ቲማቲም፣ ቃሪያና ሎሚ የመሳሰሉ አትክልቶች ቀናት ውስጥ በኪሎ ከሁለት ብር እስከ ሃያ ብር፣ ከሃያ ብር እስከ ሁለት ብር ከፍና ዝቅ ሲሉ ወይም ዋጋቸው ሲዋዥቅ በዓይናችን አየን፡፡ ምክንያቱን የነገረን ግን አንድም ሰው አልተገኘም፡፡  ጤፍና ጥራ ጥሬዎች በጥቂት ዓመታት ውስጥ በኩንታል ከሁለትና ሦስት መቶ ብር ተነስተው ወደ ሺሕ አምስት መቶና ሦስት ሺሕ ብር አሻቅበዋል፡፡ ሥጋ ከአሥር እጥፍ በላይ ጨምሮሯል፡፡ በሌሎችም ዕቃዎች ላይ ተመሳሳይ ጭማሪና የተዘበራረቀ ሁኔታ ታይቷል፡፡ ማንም ምክንያቱ ይህ ነው ያለን ሰው ግን የለም፡፡

አንድ ኢትዮጵያዊ ምስር፣ አተር፣ ሽምብራ ባቄላ፣ ሥጋ ወይም የቅባት እህል ለመመገብ ከቻይናና ከተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ሸማች ጋር በመግዛት አቅም ወይም በገቢው መጠን መወዳደር ያለበት ጊዜ ላይ ደርሰናል፡፡ የአትክልቶቹ ዋጋ መዋዠቅ ምክንያት ዋጋቸው ወደ ላይ የሚወጣበት ምክንያት የምግብ ሸቀጦች ስለሆኑ በዋጋ ለውጥ ፍላጎት ኢተለጣጭ (Inelastic) ስለሆነ ሲሆን ዋጋቸው ወደ ታች የሚወርደው የሚበላሹ ምርቶች ስለሆኑ አቅራቢው ወደ ገበያ ያወጣቸው ሸቀጦች ሳይበላሹበት ቶሎ መሸጥ ስላለበት ነው፡፡ የጥራ ጥሬዎቹ ዋጋ መናር ምክንያት ገር ውስጥ ብቻ ተብለው ይመረቱ የነበሩ በአቅማችን ልክ ዋጋቸው ይወሰን የነበረ ጥራ የቅባት እህሎች ሥጋን የመሳሰሉ የግብርና ምርቶቻችን ዓለም ገበያ ተነጋጅ (Internationally Tradable) ሆነው ዋጋቸው በዓለም ዓቀፍ ገበያ ፍላጎትና አቅርቦት መስተጋብር ሲወሰን ነፍስ ወከፍ ዓመታዊ ገቢያቸው ሰላሳና 40 ዶላር ከሆነ ሰዎች ጋር በስትና አራት መቶ ዶላር ዓመታዊ ነፍስ ወከፍ ገቢያችን መወዳደር ስላቃተን ነው፡፡ 

ከጠባብ አገር አቀፍ ግብይት ሥርዓት ውስጥ ወጥተን ወደ ዓለም አቀፍ ግብይት ሥርዓት ውስጥ ስንገባ ሊገጥሙን ከሚችሉት ችግሮች፣ ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሁኔታዎች በቂ ማስረጃዎች ናቸው፡፡ በዓለም ውስጥ እስከኖርን ድረስ ወደድንም ጠላንም ወደ ዓለም አቀፍ የግብይይት ሥርዓት ውስጥ መግባታችንና በሸመታና በማምረት ባህሪያት ቀሪውን ዓለም መቀላቀላችን አይቀርም፡፡ ለዚህም መቼ ዝግጁ እንደምንሆን የእስካሁኑ አካሄዳችን ድንግዝግዝ ነው፡፡ 

በአጠቃላይ ሸቀጦች ገበያ ውስጥ ግብርናውንም ጨምሮ ለአጠቃላይ ሸቀጦች ዋጋ መናር እንደ ዋና ምክንያት ሊጠቀስ የሚችል ነገር መንግት ዋጋን በማናር ግብር (Inflationary Taxing) የኢኮኖሚና ማኅበራዊ መሠረተ ልማት ወጪውን መሸፈኑ ነው፡፡ የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትና ሥርጭት ጭማሪ ከጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት መጠን ጭማሪ በላይ ሆነ ማለት በምሳሌያዊ አነጋገር ወተትን በውኃ አቅጥኖ ለመንግሥት የሚያስገኘውን የጥሬ ገንዘ ገቢና ይህ ገቢ ሊገዛ የሚችለውን ቁሳዊ ሀብት መጨመር ማለት ነው፡፡

የጥሬ ገንዘብ አቅርቦትን በማሳደግ የዋጋ ንረት ግብር እንዴት እንደሚፈጠር በሌላ ምሳሌ እንመልከት፡፡ አንድ ኩንታል ጤፍ በ1,000 ብር ይገዙ ከነበረና ዋጋው ተወዶ 2,000 ብር በመግባቱ እርስዎ በአንድ ሺሕ ብር ግማሽ ኩንታል ጤፍ ብቻ የሚገዙት፣ ብቸኛ የብር ማተም ሥልጣን ያለው መንግሥት አንድ ሺሕ ብሯን አትሞ ግማሿን ኩንታል ጤፍ ወደ ጎተራው ስላስገባ ነው፡፡ ይህ ዓይነት ግብር የሚከፈለው በአምራችና አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ሳይሆን፣ ሕፃንና አዋቂ ሳይል በእያንዳንዱ ሸማች ስለሆነ ገቢው ለመንግሥት ቀላል አይደለም፡፡ ግብር ሰብሳቢ ስለማያስፈልገውም ወጪ የሌለበት ገቢ ነው፡፡ የገቢው ተጋሪ በአጋጣሚው ተጠቃሚና መረቡ ውስጥ የገቡ ታላላቅ ነጋዴዎችም ናቸው፡፡ 

ባለፉት ዓመታት ያየነው የኢኮኖሚ ዕድገትና የብሔራዊ ሀብት መጨመር እያንዳንዱ ሰው የኑሮውን ውድነት አሜን ብሎ ተቀብሎ አንጀቱን አስሮ ያመጣው ለውጥ ነው፡፡ የመንግሥት ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ እንቅስቃሴና መሠረተ ልማቶቻችን በፍጥነት ያደጉትም በዚህ ፎርሙላ ነው፡፡ አንድ ሰው ለምሳው ሽሮ ወጥ እንጀራ 45  ብር ለሆቴል ቤት ሲከፍል 4.50 ሳንቲሙ የቀድሞው የሽሮው ዋጋ ሲሆን፣ 40.50 ሳንቲም ግን በዋጋ ንረት አማካይነት ለመንግሥት መንገድና ሕንፃ ግንባታ ወይም የጥቅም መረብ ውስጥ ለገባ ለማያውቀው ሰው ሕንፃ ግንባታ፣ በብሔራዊ ኢኮኖሚ አተረጓገም በአስገዳጅነት ለብሔራዊ ቁጠባ የተከፈለ ነው፡፡  የአንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም ሽሮአችን ላይ 40.50 ሳንቲም ጨምረን እየከፈልን ነው አዲስ አበባችንን በአውቶሞቢልና በአሳንሰር ብቻ ለሚጓዙ ሰዎች ያሳመርንላቸው፡፡

በብሔራዊ ኢኮኖሚ ትርጉም ቁጠባ ማለት እንደ ግል ቁጠባ የገንዘብ ቁጠባ ማለት ሳይሆን፣ ዛሬ ከተመረተው ምርት ቆጥቦ ለነገ ማሳደር፣ ዘንድሮ ከተመረተው ምርት ቆጥቦ ለከርሞ ማቆየት ማለት ነውና ሽሮው የዛሬ ፍጆታ ሲሆን፣ መንገዱና ሕንፃው በመንግሥትም ይሠራ በግለሰብ ለአገር የዛሬ ቁጠባም መዋዕለ ንዋይም ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው g[email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...