በደቡብ ክልል የሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ በክልሉ ምክር ቤት ተቀባይነት አግኝቶ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሕዝበ ውሳኔ ጥያቄ በአፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ሔለን ደበበ ከቀረበ በኋላ፣ በርካታ የክልሉ ዞኖች በተከታታይ የክልልነት ጥያቄ በየምክር ቤታቸው አፅድቀው ለክልሉ ምክር ቤት አሳውቀዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 47(2) መሠረት የአገሪቱ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የየራሳቸውን ክልል የመመሥረት መብትን የሚያጎናፅፉ ሲሆን፣ አሁን ይኼንን ሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ ተከትለው በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄዎች 11 ደርሰዋል፡፡
በጥቅም ወር 2011 ዓ.ም. በሐዋሳ ከተማ በተካሄደው የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ ተቀባይነት ያገኘው የሲዳማ የክልልነት ጥያቄን ተከትሎ እየመጡ ያሉ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ግን፣ በመጡበት አግባብ መስተናገድ የሚችሉ እንዳልሆኑና ቢስተናገዱም ለአስተዳደር ከባድ እንደሚሆን በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ ምክር ቤቱም የእነዚህን ጥያቄዎች በአጀንዳነት መቅረብን ለማራቅ በሚመስል ሁኔታ ነው ጉባዔ ከማድረግ የተቆጠበው የሚሉ ትችቶች በተደጋጋሚ ሲቀርቡበት ተደምጧል፡፡
ምንም እንኳን እነዚህ ጥያቄዎች በምክር ቤት ደረጃ ተይዘው ውይይት ተደረገባቸው እንጂ፣ በተለያዩ መድረኮች ግን በርካታ ግጭቶ የተስተዋሉባቸው ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ከእነዚህ ስብሰባዎች ሁለቱና ከፍተኛ ልዩነቶችን አስተናግደው የተጠናቀቁት በአዲስ አበባ ከሁለት ወራት በፊት የተደረገው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ማዕከላዊ ኮሚቴ ስብሰባ፣ እንዲሁም በሐዋሳ ከተማ የማዕከላዊ ኮሚቴውን ስብሰባ ምክረ ሐሳብ በመያዝ የተደረገው የከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ነበሩ፡፡
በአዲስ አበባ የተካሄደው የደኢሕዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ይደረጋል የሚል ዕቅድ ቢወጣለትም፣ በተለይ በፓርቲውና በክልሉ መንግሥት የተጠናው የክልልነት ጥያቄ ውጤት በፈጠረው አለመግባባት ሳቢያ ለዘጠኝ ቀናት ዘልቋል፡፡
ጥናቱ የተካሄደው በሃያ የዩኒቨርሰቲ መምህራን፣ የክልሉና የፌዴራል መንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ሲሆን፣ ሦስት ምክረ ሐሳቦችን አቅርቦ ነበር፡፡ የመጀመርያው ክልሉን ባለበት ማስቀጠል፣ ሁለተኛው ክልሉን ከሁለት ወይም ከአምስት ባልበለጡ የተለያዩ ክልሎች መክፈል፣ ወይም በሦስተኛነት የክልልነት ጥያቄዎችን ለጊዜ ማቆየት የሚሉ ምክረ ሐሳብ ተቀብሎ የሲዳማ ክልልነት በመፍቀድ፣ ሌሎች ባሉበት እንዲቀጥሉ የሚል ውሳኔ በአብላጫ ድምፅ አሳልፎ ነበር ስብሰባውን ያጠናቀቀው፡፡
የዚህ ውሳኔ ተከታይ የሆነውና በሐዋሳ ከተማ የተደረገው የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች ስብሰባ ለሰባት ቀናት የዘለቀ ሲሆን፣ ማዕከላዊ ኮሚቴው የሲዳማን ክልልነት ተቀብሎ ሌሎቹን እንዲሁ በማስቀጠል ክልሉን ‹55 ለአንድ› ማደራጀት በማለት ሰፊ ውይይት አድርጎበት ነበር፡፡ ሆኖም በወላይታና በካፋ ዞን አመራሮች ሐሳቡ ተቀባይነት ሳያገኝ በልዩነት ሊጠናቀቅ ችሏል፡፡
ከእነዚህ ስብሰባዎች በመቀጠል በጉዳዩ ላይ ሕዝባዊ ስብሰባ እንዲደረግና በክልሉ እየተነሱ ባሉ የክልል እንሁን ጥያቄዎች ላይ ተከታታይ ውይይቶች እንዲካሄድ መርሐ ግብር ወጥቶ፣ በተለያዩ አካባቢዎች ውይይት ማድረግ ተጀምሮ ነበር፡፡
ነገር ግን ክልል እንሁን ሲሉ የጠየቁ ዞኖች ውስጥ ያሉ ፖለቲከኞችና ሌሎች የመብት ተሟጋቾች፣ ጥያቄዎቹ ሕገ መንግሥታዊ ናቸው እንጂ በጥናት የሚመለሱ አይደሉም፣ እንዲሁም ሕገ መንግሥታዊ መንገድ ብቻ በመከተል ብቻ መስተናገድ አለባቸው የሚሉ ችግሮችንና ተቃውሞዎችን ሲያስተጋቡ ነበር፡፡
በተጨማሪም እነዚህ የክልልነት ጥያቄዎች ከምክንያታዊ ውይይትና መፍትሔ መሻት ባሻገር ለአመፅና ለብጥብጥ ምክንያት በመሆናቸው፣ በተለይ በሐዋሳና አካባቢው ለበርካቶች መሞት፣ መጎዳት፣ መፈናቀልና የንብረት ውድመት ምክንያት ሲሆኑ ተስተውሏል፡፡ በዚህ ሳቢያም ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ የሲዳማ ክልልነት ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ዝግጅት እንደሚገኝ ሊሟሉለት የሚገባቸውን ቅድመ ሁኔታዎች ካስቀመጠ ወዲህ በተነሳ አመፅ፣ ክልሉ ሙሉ በሙሉ በፀጥታ ኮማንድ ፖስት እንዲተዳደር ተደርጓል፡፡
ሰኞ ነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መግለጫ የሰጠው የዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የክልሉ ሕዝብ ያነሳው ሕገ መንግሥታዊ ጥያቄ በአስቸኳይ ሕገ መንግሥታዊ ምላሽ እንዲሰጠው ሲል የጠየቀ ሲሆን፣ ‹‹የዎላይታ በክልል ደረጃ መደራጀት ጥያቄ ማለት ዎላይታ በህልውና የመቀጠል ጥያቄ ነው፤›› ሲል አስታውቋል፡፡
በእነዚህ ጊዜያት ውስጥ አንዴም ያልተደረገው የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔ የ2011 ዓ.ም. አጠናቆ የበጀት ዓመቱን አፈጻጸም ሳይገመግም፣ ሐምሌ 1 ቀን 2011 ዓ.ም. የተጀመረውን በጀት ዓመት ያለ አዲስ በጀት ጀምሯል፡፡
ለምክር ቤቱ አለመሰብሰብ በዋና ምክንያት የሚነሳው እየተነሱ ያሉ የክልልነት ጥያቄዎች ፖለቲካዊ መፍትሔ ሳያገኙና የጋራ አቋም ሳይያዝባቸው መቅረታቸው ሲሆን፣ ምክር ቤቱ መደበኛ ስብሰባ ካደረገ እነዚህ ጉዳዮች በአጀንዳነት መያዛቸው አይቀሬ ስለሆነ ነው የሚሉ አሉ፡፡ ይኼ ከሆነ ደግሞ በጥያቄዎች ላይ ምክር ቤቱ ድምፅ የመስጠት ሕጋዊ መብትና ሥልጣን ስለሌለው ለምርጫ ቦርድ እንዲመራ ብቻ ይወስናል፡፡ ጥያቄዎቹ ከተመለሱ ለአስተዳደር ያስቸግራል የሚለውም ሥጋት ዕውን ሊሆን ይችላል፡፡
ስለዚህ እነዚህን ጥያቄዎች ተከትሎ የበጀት ዓመቱን ሁለተኛ ወር ያለ በጀት ሊያገባድድ የተቃረበው የደቡብ ክልል ምክር ቤት፣ ቅዳሜ ነሐሴ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. የግማሽ ቀን ጉባዔ አድርጓል፡፡ ሆኖም በምክር ቤቱ እነዚህ የሚነሱት የክልልነት ጥያቄዎች በአጀንዳነት ያልቀረቡ ሲሆን፣ አንገብጋቢ የነበረው በጀት የማፅደቅ ጥያቄና ከሥልጣናቸው በተነሱት የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ሚሊዮን ማቴዎስ ምትክ አዲሱ ሹመት ብቻ አጀንዳ በማድረግ ተጠናቋል፡፡ የክልሉ የ2012 በጀት ዓመት 40.6 ቢሊዮን ብር እንዲሆን በማፅደቅ፣ የስፖርት ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩት አቶ እርስቱ ይርዳው በምክትል ርዕሰ መስተዳድርነት ክልሉን እንዲያስተዳድሩ ሾሟቸዋል፡፡ ምክር ቤቱም ስብሰባ ሳያደርግ በመቅረቱ አፈ ጉባዔዋ ወ/ሮ ሔለን አባላቱን ይቅርታ ጠይቀዋል ሲሉም ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ይሁንና ሰብሳበው አስቸኳይ ይሁን መደበኛ ሳይጠቀስ የተጠሩት የክልሉ ምክር ቤት አባላት ከስብሰባው ቀደም ብሎ በአቶ መለስ ዓለሙ መሪነት የሁለት ቀናት የምክክር ውይይት አድርገውም ነበር፡፡ የዚህ ስብሰባ ዋናው ትኩረት አገራዊና ክልላዊ ጉዳዮች ቢሆኑም፣ በዋናነት ግን የክልልነት ጥያቄዎች ሰፊ ጊዜ ወስደው ውይይት እንደተደረገባቸው ለማወቅ ተችሏል፡፡
ምክር ቤቱም በጀት አፅድቆና አዲስ የክልል አስተዳዳሪ ከመረጠ በኋላ ባደረገው ዝግ ስብሰባም የክልልነት ጥያቄዎችን በጉልህ እንደተወያየባቸው የታወቀ ሲሆን፣ በተለይ የክልልነት ጥያቄን በምክር ቤታቸው አፅድቀው ለምክር ቤቱ ያቀረቡት አሥራ አንዱ ዞኖች ቅሬታቸውን በከፍተኛ ደረጃ እንዳስተጋቡ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለክልሉ የራስ ምታት የሆነው የክልልነት ጥያቄን አሁንም ቢያንስ ለስድስት ወራት ከምክር ቤቱ አጀንዳነት ያራቀው፣ ክልሉ በተጠናው ጥናት ላይ ሕዝብን የሚያወያዩ የአሠልጣኞች ሥልጠና እየተሰጠ እንደሚገኝም ለማወቅ ተችሏለ፡፡
የክልሉ ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄዎችን ባለማየቱ በርካታ ፖለቲከኞችና በማኅበራዊ ትስስሮች በጉዳዩ ላይ አስተያየት ያሰፈሩ አቀንቃኞች ምክር ቤቱን የወቀሱ ሲሆን፣ ‹ሕገ መንግሥታዊ መብታችን ተደፈጠጠ› ሲሉም ተሰምተዋል፡፡
ከዚህ ወዲያም በክልሉ የተጣለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ በርካታ ጥያቄዎች እየቀረቡ ሲሆን፣ ደኢሕዴንን ጨምሮ ሌሎች የፖለቲካ ቡድኖች መነሳት አለበት የሚሉ አቋሞችን አንፀባርቀዋል፡፡
ፌዴራሊዝምና ሕግ ያጠኑ ባለሙያዎች እየተነሱ ያሉ የክልልነት ጥያቄዎችን ሕገ መንግሥታዊ መሠረት እንዳላቸው እንደሚያምኑና በዚያው አግባብ መመለስ እንዳለበት የሚያወሱ ቢሆንም፣ የክልልነት ጥያቄዎች ምላሽ ብቻ ግን እየታዩ ላሉ ችግሮች መፍትሔ ይሆናሉ ብለው እንደማያምኑ ያመለክታሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም ሕዝበ ውሳኔ መደረጉ ወዲያውኑ ክልልነትን የሚያጎናፅፍ እንዳልሆነ በመግለጽ፣ በተለይ የንብረት ክፍፍልን የሚገዙ ሕጎች በሌሉበትና የድንበር ጥያቄዎች በጉልህ በሚነሱት አካባቢ እነዚህ መፍትሔ ሳይሰጣቸው ክልልነትን ብቻ መፈለግ ያልተጠበቀ ውጤት ሊያስገኝ ይችላል ሲሉ የሚያስጠነቅቁ አሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ ለሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ ለማድረግ ኅዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ቁርጥ ቀን ያስቀመጠ ሲሆን፣ ክልሉ ለዚህ ሕዝበ ውሳኔ መሳካት አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎችን እንደሚያሟላ በዝርዝር ጠይቋል፡፡ ለሕዝበ ውሳኔው ማካሄጃ ከ75 ሚሊዮን ብር በላይ በጀት እንደሚያስፈልገውም አስታውቋል፡፡