ኤቢኤች ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ ደርሶብኛል ባለውና ወደፊትም ይደርስብኛል ላለው የስም ማጥፋት ጉዳት፣ የ174,634,893 ብር የፍትሐ ብሔር ክስ መሠረተ፡፡
ማኅበሩ ክስ የመሠረተው በኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አንዷለም አድማሴ (ዶ/ር)፣ አቶ ታምራት ማሞ፣ አቶ ታረቀኝ ገረሱ፣ አቶ ዓብይ ዲባይና አቶ ሰሎሞን ታደሰ ላይ ነው፡፡
ድርጅቱ ሕጋዊ ሆኖ በተለያዩ የሥራ ዘርፎች የተሰማራ መሆኑንና ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጋር በመተባበር እየሠራ እንዳለ በመግለጽ፣ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ደግሞ እ.ኤ.አ. ከ2013 እስከ 2017 ድረስ በፈጸመው ውል አዲስ አበባ ባለው ቅርንጫፉ የትምህርት አገልግሎት ሲሰጥ መቆየቱን በክሱ አስረድቷል፡፡
ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር የሚያከናውነው ሥራ እስከ ታኅሳስ 21 ቀን 2020 ዓ.ም. ድረስ መሆኑን ጠቁሞ፣ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናትና የቦርድ አባላት የሚያውቁት መሆኑን ገልጿል፡፡
በተጨማሪም ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ በከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ የተጣለው ዕግድ እንዲነሳለት ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም ለጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ለብይን ቀጥሯል፡፡
ኤጀንሲው በክሱ ላይ ተቃውሞ ካለው ለመስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲያቀርብና ክሱን ለመስማት ለጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ተሰጥቷል፡፡
ክሱ የቀረበው በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ተረኛ ችሎት ነው፡፡