Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

ሚዳቋ

ቀን:

ሚዳቋዎች Common duiker sylvicapra grimmia  በብዙ የአገራችን ክፍሎች ይገኛሉ፡፡ መጠናቸው ከሥፍራ ሥፍራ ቢለያይም፣ ሴቶቹ ከወንዶቹ ይልቅ ተለቅ ይላሉ፡፡ የወንዶቹ ከፍታ በአማካይ 50 ሴ.ሜ ደገማ ይሆናል፡፡ የሴቶቹ አማካይ ቁመት ከወንዶቹ በለጥ ይላል፡፡ ክብደታቸውም ከአንድ ኪሎ ግራም ይበልጣል፡፡ ቀንድ ያላቸው ወንዶቹ ብቻ ናቸው፡፡ ቀንዳቸው ከ 7 ሴ.ሜ እስከ 18 ሴ.ሚ ርዝመት አለው፡፡ የፀጉራቸው ቀለም ቡናማ ግራጫ ነው፡፡ የፊት እግሮቻቸው ፊት ለፊት ቡናማ ቀለም አላቸው፡፡ ደረትና ሆዳቸው ነጭ ነው፡፡ ወጠጤዎቹ ጠቆር ይላሉ፡፡

ሚዳቋ የምትገኘው ረጠብ ባለ ገሶ፣ የምትደበቅበት ያህል ቅጠላ ቅጠልና ቁጥቋጦ ባለበት፣ እናም ሰዎች በሰፈሩበት አካባቢ ነው፡፡ በተረፈ፣ ከዝናብ ደኖችና ከበረሃዎች በስተቀር፣ አፍሪቃ ውስጥ የማትገኝበት የለም፡፡

ሚዳቋዎች የተሳካላቸው እንስሶች ናቸው ማለት ይቻላል፡፡ ለዚህም ምክንያቱ በማናቸውም ሥፍራ መኖር መቻላቸውና ብዙ የተለያዩ ዕፅዋትን መብላታቸው ነው፡፡ ለመደበቂያ የሚሆን የዕፅዋት ሽፋን ባለበት በማንኛውም ሥፍራ ይኖራሉ፡፡ በየመንደሩ ጥግ ይገኛሉ፡፡ ሰው የተከለውን ማንኛውንም ነገር ይበላሉ፡፡ ለጋ ቅጠላ ቅጠል እስካገኙ ድረስ ውኃ አይጠጡም፡፡ በኢትዮጵያ ተራሮች የሚገኙት ሚዳቋዎች የሚበሉት ሃመልማል ነው፡፡ በተጨማሪ የቁጥቋጦውን፣ የችፍርጉን ቅጠላ ቅጠል ይበላሉ፡፡ በጥቂቱም ቢሆን ጨሌ ሣርም ይበላሉ፡፡ ከሞቱ በኋላ ጨጓራቸው ውስጥ የሚገኙ እንግዳ ነገሮች፣ ሙጫ፣ ቅርፊት፣ ሦስት አፅቄዎች፣ አባ ጨጓሬና ጉንዳን የመሳሰሉትን፣ አሻንጉሊት፣ አይጦችና ወፎችን ያጠቃልላሉ፡፡

ማኅበራዊ አደረጃጀታቸው ክልልተኛና አንድ ወንድና አንድ ሴት ሆነው የሚኖሩበት ነው፡፡ በሚዳቋዎች ላይ የተደረጉ ጥናቶች በቂ አይደሉም፡፡ ምናልባት እንደየ አካባቢው ጥንድ የሆኑት ወንድና ሴት ብዛት ሳይለያይ አይቀርም፡፡ የዓይን እማኞች እንደሚሉት የሴቶቹና የወንዶቹ ክልል ስፋት ተመጣጣኝ ነው፡፡ የተለያዩ ፆታዎች፣ አንዳንዴ ክልላቸው ይደራረባል፡፡ የአንዱ ወንድ ክልል ከ 2 ሴቶች ሊደራረብ ይችላል፡፡ እናም ከሁለቱ አንደኛዋ ክልሉ ስትመጣ ያገኛታል፡፡ ስለዚህም ሚዳቋ ጋ አለ የሚባለው የአንድ ወንድና አንድ ሴት ትስስር ትክክል ላይሆን ይችላል፡፡

ሚዳቋዎች የሌትም የቀንም እንስሶች ናቸው፡፡ አደን በሚበዛበት አካባቢ ከሞላ ጎደል ሌሊት ብቻ ይንቀሳቀሳሉ፡፡ ሴቶቹ ዝቅ ያለ፣ በቂ የሚደብቃቸው የዕፅዋት ከለላ ያለው ሥፍራ ለማረፍ፣ ለመተኛትና ለማመንዢክ ሲመርጡ፣ ወንዶቹ ደግሞ ገላጣና ከፍ ያሉ ሥፍራዎችን፣ ለምሳሌ፣ ኩይሳን የመሰለ ይመርጣሉ፡፡ በምሽት እስከ ሁለት ሰዓት፣ ኪዚያም ከሌሊቱ አስር ሰዓት ጀምሮ ሲመገቡና ሲንቀሳቀሱ፣ በቀን ደግሞ ተግባሮቻቸውን የሚያቀላጠፉት በጣም በጠዋትና፣ ከሰዓት በኋላም ምሽቱ ሲጠጋ ነው፡፡ በሞቃት ሰዓት፣ ጥላ ይፈልጋሉ፡፡

ክልልተኛው ወንድ፣ ድንበሩ የሚጥስ ወንድ ሲመጣበት፣ አዘናግቶ ያጠቃል፡፡ በኃይል ሊያባርረውና ሊወጋውም ይችላል፡፡ መሸሽ ያልቻል ወንድ፣ በመንጋለል መሸነፍን ያረጋግጣል፡፡

ሚዳቋዎች የተወሰነ የመራቢያ ወቅት የላቸውም፡፡ በማንኛውም ወራት ሊያረግዙና ሊወልዱ ይችላሉ፡፡ የሚዳቋ የርግዝና ጊዜ ርዝመት በደንብ ላለመጠናታቸው ምስክር ነው፡፡ 3 ወር፣ 5 ወር፣ እና 7 ወር የሚሉ አሉ፡፡ ሚዳቋዎች ከመውለዳቸው ቀደም ብለው ስለሚሸሸጉ፣ ሲወልዱ መመልከት ከባድ ነው፡፡ ሆኖም በቁጥጥር ስር ያሉ ሚዳቋዎች አወላለድ ይታወቃል፡፡

ግልገሏ በተወለደች በ15 ደቂቃ እናቷ በመላስ ካፀዳቻት በኋላ ራሷን ቀና ታደርጋለች፡፡ በ35 ደቂቃ ትቆማለች፡፡ በ50 ደቂቃ መራመድ ትጀምራለች፡፡ 80 ደቂቃ ሲሞላት የእናቷን ጡት ብታገኝም አትጠባም፡፡ የሚዳቋ ግልገሎች በ24 ሰዓቶች ውስጥ መሮጥ ይጀምራሉ፡፡ 3 ቀን ከሞላቸው ለመያዝ ያስቸግራሉ፡፡ ይህም ሆኖ ግን ለጥቂት ሳምንታት ተደብቀው ይተኛሉ፡፡ እናቶቻቸው በ24 ሰዓት ሁለት ወይም ሦስት ጊዜ አግኝተው ያጠቧቸዋል፡፡

ሚዳቋዎች 6 ወር ሲሞላቸው በመጠን ወላጆቻቸውን ያህላሉ፡፡ አንዳንድ ሴቶች ደግሞ በአንድ ዓመታቸው ይወልዳሉ፡፡

  • ሰሎሞን ይርጋ (ዶ.ር) “አጥቢያዎች” (2000)
spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የመቃወም ነፃነት ውዝግብ በኢትዮጵያ

ስሟ እንዳይገለጽ የጠየቀችው በአዲስ አበባ ከተማ በተለምዶ የሾላ አካባቢ...

የሲሚንቶን እጥረትና ችግር ታሪክ ለማድረግ የተጀመረው አጓጊ ጥረት

በኢትዮጵያ በገበያ ውስጥ ለዓመታት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆን ከሚጠቀሱ ምርቶች...

የብሔር ፖለቲካው ጡዘት የእርስ በርስ ግጭት እንዳያባብስ ጥንቃቄ ይደረግ

በያሲን ባህሩ በሪፖርተር የኅዳር 9 ቀን 2016 ዓ.ም. ዕትም “እኔ...