ቀሪዎቹ ትምህርቶች የተተውት የውጤት ግነት ስለታየባቸው ነው
የ2012 ዓ.ም. የመንግሥት ዩኒቨርስቲዎች መግቢያ የሚወሰነው በአራት መሠረታዊ የትምህርት ዓይነቶች ውጤት መሆኑ ተገለጸ፡፡ ቀሪዎቹ ትምህርቶች የተተውት የውጤት ግሽበት ወይም ግነት ስለታየባቸው ነው፡፡
በዚህም መሠረት የ2012 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት ምደባ የሚከናወነው ከእንግሊዝኛ፣ ከሒሳብና ከስኮላስቲክስ አፕቲትዩድ ትምህርቶች ጋር የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪዎች ፊዚክስን፤ የማኅበራዊ ሳይንስ ተማሪዎች ደግሞ ጂኦግራፊን በማከል መሆኑን ተጠቁሟል፡፡
ትምህርት ሚኒስቴር፣ አገር አቀፍ ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲና የክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጡት መግለጫ፣ የ2012 ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ በአራት የትምህርት ዓይነቶች ብቻ እንዲወሰን የተደረገው፣ የጋሸበና የተጋነነ የፈተና ውጤት በመታየቱ ነው፡፡
የአገር አቀፍ ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሸን ጉዳዮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ረዲ ሺፋ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ (12ኛ ክፍል) ብሔራዊ ፈተና ሰኔ 6 እና 7 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡት ትምህርቶች ሒሳብ፣ እንግሊዝኛ፣ ስኮላስቲከስ አፕቲትዩድ፣ ፊዚክስና ጂኦግራፊ ሲሆኑ፣ ቅዳሜና እሑድን ታርፎ በሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡት ሲቪክስ፣ ባዮሎጂና ኬሚስትሪ ነበሩ፡፡
ሰኔ 10 እና 11 ቀን 2011 ዓ.ም. የተሰጡት ሲቪክስ፣ ባዮሎጂና ኬሚስትሪ ፈተናዎች ውጤት ከዚህ ቀደም ከነበሩ ዓመታት በተለየ የተጋነነ ወይም ትልቅ ውጤት ስለተመዘገበባቸው፣ ለ2012ቱ ዓ.ም. የከፍተኛ ትምህርት መግቢያ እንደማይደመሩ፣ ውጤቱም እንደከዚህ ቀደሙ ከ700 ሳይሆን ከ400 እንደሚሰላ ተናግረዋል፡፡ ይህ የተደረገውም ዘንድሮ የተፈጠረውን ችግር ለመፍታት ነው ብለዋል፡፡
ተማሪዎች የተጋነነ ውጤት ስላመጡ የለፉበትን ውጤት ማስቀረት ተገቢ ነው ወይ? ለሚለው ጥያቄም፣ ውጤቱ ከተለመደው ውጭ ስለሆነ እንጂ ትልቅ ውጤት ከዚህ ቀደም አልተመዘገበም ማለት አይደለም፣ ሆኖም በርካታ ተማሪዎች ውጤቱን እንደ ዘንድሮው ባልተለመደ አያመጡም ነበር ብለዋል፡፡
ከዚህ ውሳኔ ለመድረስ ዳሰሳ መደረጉን፣ በዳሰሳውም ከክልል ክልል ውጤቱ ቢለያይም በአገር አቀፍ ደረጃ በሲቪክስ፣ ኬሚስትሪና ባዮሎጂ ፈተናዎች ላይ የተመዘገበው ውጤት ግሽበት (ግነት) ስለታየበት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ምክንያቱ ፈተናው ተሰርቆ ነው ወይም እርማት ላይ ስህተት ተፈጥሮ? በሚል ላነሳነው ጥያቄ፣ በእርማት ላይ ስህተት አለመኖሩን፣ ግን በቡድን ተሠርቶ ሊሆን ይችላል የሚል ነገር እንዳለ አክለዋል፡፡
ይህ ውሳኔ በተሰረዙት ትምህርቶች፣ ጎበዝ የሆኑ እንዲሁም በጥረታቸው ውጤት ያገኙ ተማሪዎችን የሚጨፈልቅ አይሆንም ወይ? በሌላ በኩል መሠረታዊ ወይም በግዴታ የሚያዙት ትምህርቶች ካላቸው ክብደት አንፃር ተማሪዎቹ በቀሪዎቹ እንዳያካክሱ ዕድል አያሳጣም ወይ? የሚል ጥያቄም አንስተናል፡፡
አቶ ረዲ እንደሚሉት፣ ውሳኔው አብዛኛውን ተማሪ ሊጠቅም የሚችል ነው፡፡ ሆኖም የተወሰነ ጉዳት ሊኖረው እንደሚችል በመግለጫው ላይ ተነስቷል ብለዋል፡፡
ውጤቱ ወደ መንግሥት ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ለመግባት ብቻ የሚያገለግል ሲሆን፣ ወደ ከፍተኛ ትምህርት የሚመደቡ ተማሪዎችም በአንደኛ ዓመት የሚሰጡ የፍሬሽማን ኮርሶችን ከተማሩ በኋላ በሚያስመዘግቡት ውጤት መሠረት፣ በሚመርጡት የትምህርት መስክ የሚመደቡ መሆኑም ተነግሯል፡፡