Wednesday, June 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊየሐዋሳ ድባብ

የሐዋሳ ድባብ

ቀን:

ከተቆረቆረች ገና 60 ዓመት አልሞላትም፡፡ ከአዲስ አበባ 273 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው የደቡቧ ፈርጥ ሐዋሳ ተፈጥሮ ያደላት ውብ ከተማ ነች፡፡ 1,078 ሜትር ከባህር ጠለል ከፍ ብላ በስምጥ ሸለቆ ትገኛለች፡፡ ከአምስት አሠርታት ባልበለጠ ዕድሜዋ ዘመናዊት መሆን የቻለች፣ በአገሪቱ ከሚገኙ ጥቂት ለኑሮ ምቹ ከሆኑ ከተሞች መካከል አንደኛዋ ነች፡፡

600 ሺሕ የሚሆኑት የከተማዋ ነዋሪዎች የሚኖሩት ጥንቅቅ ተደርገው በተሠሩ ግንብ ቤቶች ነው፡፡ በከተማዋ እንደ አዲስ አበባ ወይም እንደ ሌሎቹ ከተሞች ሕገወጥ ግንባታ ያለ አይመስልም፡፡ በአውራ ጎዳናዎቿ ፊትና ኋላ፣ በውስጥ ለውስጥ መንደሮችም ከፕላን ውጪ የተገነባ ቤት አላጋጠመንም፡፡ ፅዱ ተደርገው የተሠሩት ቤቶች በመስመር የተሠለፉና በመልክ በመልኩ የተደረደሩ ናቸው፡፡ በኦሮሚያ ክልል፣ በዲላ፣ በከምባታና በአለታ ወንዶ መካከል የምትገኘው ሐዋሳ በፕላን የተገነባች መሆኗ ከፈጠረላት ውበት ባሻገር፣ ሐይቋ ልዩ መስህቧ ነው፡፡

ሐዋሳ ሐይቅ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓሳ አጥማጆች የሥራ ዕድልን ሲፈጥር፣ በከተማዋ ለሚገኙ ሬስቶራንትና ሆቴሎችም በቂ የዓሳ ምርት የሚያገኙበት የማይነጥፍ ሀብት ነው፡፡ የከተማ ኑሮ ያጨናነቃቸው እንግዶችና ጎብኚዎች የሚመርጧት የቱሪስት መዳረሻ ነች፡፡ በየዓመቱ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ የውጭ ዜጎች፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የአገር ውስጥ ጎብኚዎች የሐዋሳን ምድር ይረግጣሉ፡፡ በሐይቁ ላይ በጀልባ ይንሸራሸራሉ፣ ከደቂቃዎች በፊት ከሐይቁ የወጣ ዓሳ ፊት ለፊታቸው ተጠብሶ ይበላሉ፡፡ ከፈለጉም ጥሬ ዓሳ በዳጣ እያጣቀሱ ሊያጣጠሙ ይችላሉ፡፡

- Advertisement -

ሞቃታማ አየር ያላት ሐዋሳ ሰዎች በበጋ ልብሶች የሚዘንጡባት፣ ጎዳናዎቿ በክፍት ጫማ የሚንሸራሸሩባትና የሚናፈሱባት ነች፡፡ በቆጮ፣ አይብና ቅቤ የሚሠሩ ልዩ ልዩ የክልሉ ባህላዊ ምግቦችም ከተለመደው የምግብ ጣዕም ለየት ያሉና ትዝታ የሚያስቀሩ እጅ የሚያስቆረጥሙ ምግቦች ናቸው፡፡ ደረጃውን በጠበቀ ሬስቶራንት ውስጥ እነዚህን ባህላዊ ምግቦች ቦሌ መስመር ለአንድ በየዓይነቱ ከሚከፍሉት ያነሰ ከፍለው ሊመገቡ ይችላሉ፡፡

በትምህርትና በሥራ አጋጣሚ ወደ ሐዋሳ የሄዱ ከተማዋን ለቅቆ መውጣት እስኪቸገሩ ሐዋሳ ታባብላለች፡፡ ብዙዎችም በሰበብ አስባቡ ከተማዋን ሳይለቁ እዚያው ኑሯቸውን ሲያደርጉ ይታያል፡፡ ኑሮ እንደሆነ ርካሽ ነው፣ የሚከራዩ ተጨማሪ ሁለት ሰርቪሶች ያሉት ጥንቅቅ ተደርጎ የተሠራ ቪላ ቤት 7,000 ብር፣ ፅዱ ተደርጎ በሸክላ ወይም በግንብ የተሠራ አንድ ክፍል 1,500 ብር ተከራይተው መኖር ይችላሉ፡፡ በአጠቃላይ በመኖሪያ ቤት ረገድ ሐዋሳ ዝቅተኛ ደመወዝ የሚከፈለው የመንግሥት ሠራተኛ ጥሩ ቪላ ገንብቶ የሚኖርባት ጉደኛ ከተማ ነች፡፡

የከተማዋ የቱሪዝም መስህብ ልማትና ጥናት ባለሙያ አቶ እያሱ ቀሬሶ፣ ሐዋሳ ስሟን ያገኘችው ከሐይቁ እንደሆነ ይናገራሉ፡፡ የከተማዋም ኢኮኖሚ በቱሪዝም ላይ የተመሠረተ፣ ከመንግሥት ብዙም ድጎማ ሳይደረግላት በራሷ በውስጥ ገቢ ብቻ የምትንቀሳቀስ ከተማ ነች ይሏታል፡፡ ከሁለት መቶ የሚበልጡ መለስተኛ ሆቴሎችና 15 በላይ ባለኮከብ ሆቴሎች አሏት፡፡ ፍል ውኃና ሌሎች መዝናኛ ቦታዎችም አሏት፡፡ በአጭሩ ሐዋሳ ያላትን የተፈጥሮ ፀጋ በአግባቡ የተጠቀመች ለሌሎች ከተሞች አርዓያ መሆን የምትችል ቦታ ነች፡፡ ሚሊዮኖች የሚጎርፉባት፣ ሺዎች ለመኖሪያነት የሚያጯት ፅዱና የምታዝናና ቦታ ስለመሆኗ ብዙዎችም ይመሰክሩ ነበር፡፡

ከሐምሌ 11 ቀን 2011 .. ጥቃት በኋላ ግን፣ ብዙ ነገሮች እንዳሉ ቢሆንም የሰላሟ ሁኔታ አሥጊ በመሆኑ በርካቶች እንዳልተመላለሱባት ርቀዋታል፡፡ በአጭሩ ሐዋሳ ከቱሪዝም መዳረሻነት ቦታዋ ተፍቃለች፡፡ ጎብኚዎች እግራቸውን ወደ ሐዋሳ ማንሳት ሲያቆሙ ነዋሪዎችም በራሳቸውን ዘግተው መዋል የመረጡ ይመስል ደማቋ ከተማ ጭር ብላለች፡፡ ማንኛውም ንግግር ፖለቲካዊ መዘዝ ሊያስከትል፣ አልያም እንደዋዛ ግጭት እንዳያነሳሳ በጓደኛሞች መካከል የሚደረግ ውይይትም ይሁን ጨዋታ በጥንቃቄ ነው፡፡ ብዙዎች ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚንሾካሾኩባት ትመስላለች፡፡  ጎዳናዎቿ፣ ሆቴሎቿ ምግብ ቤቶቿ ቅዝቅዝ ብለዋል፡፡

የከተማዋ ቱሪዝም ፍሰት መቀዛቀዝ ያሳሰባቸው የክልሉ የቱሪዝም ቢሮና ሌሎች ባለድርሻዎች ከተማዋ ወደ ነበረችበት ሰላም መመለሷን ለማስነገር ከቀናት በፊት የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎችን ወደሐ ወስደው ነባራዊውን ሁኔታ እንዲመለከቱ አድርገው ነበር፡፡ ሐዋሳን ለመጎብኘት ዕድሉን ካገኙ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት መካከል አንዱ የነበረው ሪፖርተርም ከተማዋ ያለችበትን ሁኔታ ተዘዋውሮ ታዝቧል፡፡  

በከተማው ታዋቂ የሚባል ትልቅ ሬስቶራንት ቢሆንም በምሳ ሰዓት ጭር እንዳለ ነው፡፡ ከመስተንግዶ ሠራተኞችና አንዳንድ ደንበኞች በቀር መመገቢያ ክፍሉ እንደወትሮው በሰዎች የተጨናነቀ አልነበረም፡፡ ሬስቶራንቱ ስም ያተረፈበትን የደቡብ ክልል ባህላዊ ምግብና የፆም ፍርፍር አዘን ተቀመጥን፡፡ ምግቡ እስኪመጣም የተለያዩ ጉዳዮችን እያነሳን መጫወታችንን ቀጥለናል፡፡ በዙሪያችን የነበሩ ሁሉ ጋዜጠኞች ነበሩና የምናወራባቸው ጉዳዮች በሽ ነበሩ፡፡ ከቀናት በፊት የክልሉን ሁኔታ አስመልክቶ በአንደኛው የመገናኛ ብዙኃን የወጣውን ዜና በተመለከተ የክልሉ ጋዜጠኞች ዜናው በክልሉ ካለው የፀጥታ ጉዳይ አንፃር ጥንቃቄ የጎደለው እንደሆነ ቅሬታቸውን ገለጹልንና ጨዋታው በአካባቢው ሰላም ላይ ያተኮረ ሆነ፡፡

የደቡብ ክልል መናገሻና በመቶሺዎች የሚቆጠሩ የክልሉና ሌሎች የአገሪቱ ዜጎች የሚኖሩባት ሞቅ ያለችው ሐዋሳ እንደ ሬስቶራንቱ ጭር ያለችበትን ምክንያት አወጉን፡፡ በአገሪቱ ያለው ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውጥረት ያነገሰባት ከሆነች ሰነባብታለች፡፡ ከዚህ ቀደም ብዙም ትኩረት የማይስቡ በመገናኛ ብዙኃን የሚለቀቁ መረጃዎች በአሁኑ ወቅት የከተማዋን ሰላም ሊያናጉ ይችላሉ፡፡ እንደዋዛ ይሳቅባቸው የነበሩ ቀልድና ተረቦች ፖለቲካዊ አንድምታቸው የከፋ መዘዝ የሚያስከትል ይሆናል፡፡ በአጠቃላይ ሐዋሳ የመዝናኛ ከተማ መሆኗ ቀርቶ ውጥረት ነግሶባታል፡፡

ከሲዳማ የክልልነት ጥያቄ ጋር በተያያዘ ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. በከተማዋ በተከፈተ ጥቃት ሦስት ሰዎች ሕይወታቸውን አጡ፡፡ በሌሎች የክልሉ አካባቢዎችም ተመሳሳይ ጥቃቶች ተፈጸሙ፡፡ ጥቃቱ ከመፈጸሙ አስቀድሞ የተለያዩ አካላት በ‹‹11 11›› ጥቃት እንደሚፈፅሙ ሲዝቱ ነበረና፣ ክስተቱ ፈጽሞ ያልተጠበቀ አልነበረም፡፡ አስቀድሞ አስፈላጊውን ጥንቃቄ ማድረግ ሲቻል የሆነው እንዲሆን መፍቀድ እንደሆነ የተሰማቸው አብዛኞች በሆነው ነገር መንግሥትን ከመውቀስ አልቦዘኑም፡፡

ጥቃቱ በተፈጸመ በቀናት ውስጥ ከተማዋ በኮማንድ ፖስት ቁጥጥር ሥር ሆናለች፡፡ ወደ ቀድሞ ሰላሟ መመለስ እንደቻለች፣ በኮማንድ ፖስቱ ሥር በዋለችባቸው ጊዜያት ውስጥም አንድም የጥቃት ሙከራ አለመመዝገቡን የከተማዋ ኮማንድ ፖስት ኃላፊ ኮሎኔል ተክለብርሃን ገብረመድህን አስረድተዋል፡፡ ከተማዋ ወደ ቀድሞዋ ሰላም ተመልሳለች ቢባልም፣ ነዋሪው በሙሉ ልቡ የተቀበለው አይመስልም፣ አልያም ከድንጋጤው ማገገም አልቻለም፡፡

የከተማዋ ጎዳናዎች እንደ ቀድሞው ሞቅ ያሉ አይደሉም፡፡ በተለያዩ የከተማዋ ክፍሎች የሚገኙ ንግድ ቤቶችም ተዘግተው ይውላሉ፣ ተዘግተው ያድራሉ፡፡ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ነዋሪው በሙሉ ልቡ አምኖ መቀበል አለመቻሉን የታዘቡት አንዳንድ የክልሉ ጋዜጠኞችም፣ የተፈጠረውን ሰላምና መረጋጋት ሕዝቡ አምኖ እንዲቀበል ሰላም ላይ አተኩረው እየሠሩ እንደሚገኙ ነግረውናል፡፡ ተከስቶ ከነበረው ጥፋት ይልቅ፣ አሁን ያለው ሰላም ትልቅ መሆኑን ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ ሌሎች መገናኛ ብዙኃንም ለሰፊው ሕዝብ ጥቅም ሲባል አንዳንድ መረጃዎችን ከመልቀቃቸው በፊት ሁለቴ ማሰብ እንዳለባቸው ምሣ እየበላን አውርተናል፡፡

ነዋሪው ግን አሁንም ሥጋት ውስጥ ነው፡፡ አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች እንደሚሉት፣ ብዙዎች ቤት ንብረታቸውን ሸጠው ከተማዋን እየለቀቁ እየወጡ ነው፡፡ በሐዋሳ የቤት ዋጋ ቀድሞ ከነበረው አንፃር በአሁኑ ወቅት በወረደ ዋጋ እየተሸጠ ይገኛል፡፡ አንዳንዶች እንዲያውም ከገዙበት ዋጋ እየቀነሱ በኪሳራ ለመሸጥ እንደሚጣጣሩ ነዋሪዎች የታዘቡትን ይናገራሉ፡፡ አሁን የተፈጠረውን ሰላም ዘለቄታዊነት አጥብቀው የሚጠራጠሩም በርካቶች ናቸው፡፡ ‹‹ኮማንድ ፖስቱ ቢወጣ ሰላሙ እንደሚቀጥል ዋስትና የለንም›› የሚሉ ብዙዎች መሆናቸውንም ሪፖርተር ታዝቧል፡፡ በአንፃሩም በከተማው ከተከሰተው ችግር ይልቅ ወሬው መግነኑን በመግለጽ በተባለው መጠን ሐዋሳ ሰላሟ አለመድፍረሱን፣ ኮማንድ ፖስቱም ቢወጣ ያለው ሰላም እንደሚቀጥል የሚናገሩ አሉ፡፡

የኮማንድ ፖስቱ ዋና ሥራ የከተማዋን ሰላም ማስጠበቅ ነው የሚሉት ኮሎኔሉ፣ ለከተማው የፀጥታ ኃይል አጋዥ ሆኖ ኮማንድ ፖስቱ እንደሚሠራ ይናገራሉ፡፡ እንደ ዋዛ የአካባቢው ሰላም እንዳይደፈርስም ነዋሪው የሰላምን ዋጋ እንዲያውቅ የተለያዩ ሕዝባዊ ስብሰባዎችን በማድረግ የማስተማር ሥራ እንደሚሠራም ገልጸዋል፡፡ በየክፍለ ከተማውና በየቀበሌው ኮማንድ ፖስት በመመሥረትም የሕዝብን ሰላም ለማረጋገጥ እንዲሁም ችግር ፈጣሪዎች ለሕግ የማቅረብ ሥራ እየተሠራ ይገኛልም ብለዋል፡፡ የከተማዋን ድባብ ወደ ነበረበት የሚመልሱ የልማትና የንግድ እንቅስቃሴዎች እንደ ቀድሞው ሞቅ ደመቅ እንዲሉም ኮማንድ ፖስቱ ኃላፊነት ወስዶ ይሠራል፡፡

‹‹የሰላም ዋናው ምንጭ ሕዝቡ ነው፤›› የሚሉት ኮሎኔል ተክለ ብርሃን፣ ያለውን የፀጥታ ችግር ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ ከፀጥታ ኃይሉ የበለጠ ነዋሪው ትልቅ ተሳትፎ እንደነበረውና፣ ኮማንድ ፖስቱ በየትኛውም ሰዓት ከተማውን ለቆ ቢወጣ የሚያሠጋ የፀጥታ ችግር አለመኖሩን አስረግጠዋል፡፡ ለከተማዋ ሰላም ጠንቅ የሆኑ ግለሰቦችን ነዋሪው እያጋለጠ መሆኑን በመግለጽ፣ ለሰላም መረጋገጥ አስፈላጊውን ጥረት እንደሚያደርግ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡ በየክፍለ ከተማውና ቀጣናው ሕዝቡ ዋርዲያ በመውጣት የፀጥታ ችግር እንዳይከሰት ዘብ እስከመቆም ደርሷል፡፡ ይህ በከተማው ብቻ ሳይሆን በገጠራማ አካባቢዎችም የሚታይ ነው የሚሉት ኮሎኔል ተክለ ብርሃን፣ በወቅቱ በደረሰ የፀጥታ ችግር በንብረታቸው ላይ ጉዳት የደረሰባቸውን የገጠር ነዋሪዎች ሀብት ተባብሮ የመተካት ሥራ ሲሠሩም እየታየ ነው ብለዋል፡፡ በአጠቃላይ በአሁኑ ወቅት ሐዋሳ ከተማ ብዙ ችግር የለባትም ሲሉ ደምድመዋል፡፡

በወቅቱ ተከስቶ የነበረው የፀጥታ ችግር ግን በሐዋሳ ስምና ዝና ላይ ያሳደረው ተፅዕኖ በቀላሉ የማይሻር ሆኗል፡፡ ሰላሟ ወደነበረበት ተመልሷል ቢባልም የነበራትን ድባብ ግን አጥታለች፡፡ የአገር ውስጥና የውጭ ቱሪስቶች መዳረሻዋ ሐዋሳ፣ ነዋሪዎቿ እንደ ልብ የማይንቀሳቀሱባት ውጥረት የነገሠባት ከተማ ሆናለች፡፡ ሰላሟ ተመልሷል ቢባልም፣ ለወትሮው ተጨናንቀው ያድሩ የነበሩ ናይት ክለቦችም እንደ ከተማዋ የቀን ውሎ ጭር ያሉ እንደሆኑ በሥራ ምክንያት ወደ ከተማዋ ያቀኑ እንግዶች ነግረውናል፡፡ ከሐምሌ 11 ጥቃት በኋላ አንዳችም የተቃጣ መሰል ጥቃት አለመኖሩን ኮሎኔሉ ቢናገሩም፣ የነዋሪው ሥነ ልቦና ግን በቀላሉ የሚባለውን ነገር መቀበል የቻለ አይመስልም፡፡

ቅዳሜና እሑድን በአሞራ ገደል፣ በሐዋሳ ሐይቅ ለማሳለፍ ከአዲስ አበባና ሌሎች ቅርብ ቦታዎች ወደ ሐዋሳ ነድተው የሚሄዱ ጎብኚዎች ቁጥር በአስገራሚ ሁኔታ ቀንሷል፡፡ በከተማዋ በቆየንባቸው ሦስት ቀናትም አንድም የውጭ አገር ጎብኚ አልተመለከትንም፡፡ የከተማዋ የቱሪዝም ገቢም በአስደናቂ ፍጥነት ቁልቁል ወርዷል፡፡

የደቡብ ክልል የባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ / ሰብለፀጋ አየለ እንደሚሉት፣ ካለፈው 2019 መጨረሻ ጀምሮ አልፎ አልፎ በሚከሰቱ አገራዊና ክልላዊ የፀጥታ ችግሮች ምክንያት በቱሪዝም ፍሰቱ ላይ ተፅዕኖ ተፈጥሯል፡፡ 2010 .. አንፃር 2011 .. የክልሉ የቱሪስት ፍሰት ሲታይ ቀላል የማይባል መቀነስን አሳይቷል፡፡ 2011 .. የውጭ አገር ጎብኚዎች ቁጥር 49 ሺሕ ቀንሷል፡፡ 274,572 የውጭ ቱሪስቶች በዚህ ዓመት ሐዋሳን ጎብኝተዋል፡፡ ሐዋሳ ዓምና በቱሪዝም ዘርፍ ካገኘችው አጠቃላይ ገቢ 2011 .. 15.3 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል፡፡ በሐምሌ ወር ላይ ዜሮ ማለት በሚያስችል ሁኔታ አሽቆልቁሎ የነበረው የቱሪዝም ፍሰቱ፣ ከነሐሴ 2011 ዓ.ም. ወዲህ ግን መነቃቃትን እያሳየ መጥቷል፡፡ ሐምሌ 11 በሐዋሳ ከተማ ተከስቶ በነበረው ጥቃት ሳቢያ በሐምሌ ወር ላይ ምንም ዓይነት የቱሪስት ፍሰትም አልነበረም ብለዋል፡፡

ሐዋሳ ከፍተኛ የቱሪስት ፍሰት የምታስመዘግብባቸው ክበረ በዓላት እንኳን ጭር ብለው እንደነበር ኃላፊዋ አስታውሰዋል፡፡ በተለይም በከተማዋ በድምቀት በሚከበረው የሐምሌ ገብርኤል የንግሥ በዓል በተለመደው መጠን ሳይከበር ቀርቷል፡፡ በገብርኤል የንግሥ በዓል የመኪና ማቆሚያ ቦታ እስኪቸግር በጎብኚዎች ተጨናንቃ የምትውለው ሐዋሳ ለሆቴሎች፣ ለአስጎብኚዎችና ለሌሎችም የከተማዋ ነዋሪዎች የሚተርፍ የንግድ እንቅስቃሴና የገንዘብ ፍሰት ይኖር ነበር፡፡

ባህላዊና ዘመናዊ ሬስቶራንቶች በተስተናጋጅ ተሞልተው፣ ሆቴሎች ሙሉ ለሙሉ አልጋቸው ተይዞ፣ መዝናኛ ሥፍራዎች በጎብኚዎች ተጨናንቆ፣ ሐዋሳ ሐይቅ ገበያ መስሎ ይከርም ነበር፡፡ ተፈጥሮ ያደላት ደማቋ ሐዋሳ የነበራት የቱሪስት ፍሰት ለበርካቶች የሥራ ዕድል የፈጠረም ነበር፡፡ የከተማዋ ቱሪዝም ሕፃንና አዋቂ ሳይል ገንዘብ የሚያገኝበት፣ የዕለት ጉርሱን የሚያበስልበት ነበር፡፡

በሐይቁ ዙሪያ ዓሳ በማጥመድ ሥራ ከተሰማሩ፣ ሬስቶራንት ከፍተው ከሚሠሩ ነዋሪዎች በተጨማሪ ለእንግዶች እጅ የሚያስታጥቡ፣ የሚጨፍሩና ሌሎችም ጥቃቅን ሥራዎች ሠርተው የሚያድሩ ሕፃናት ቀላል የማይባል ገንዘብ ከጎብኚዎች የሚሰበስቡ ናቸው፡፡ ከሐምሌ 11 በኋላ ግን በተለይ ሙሉውን ሐምሌ ወር የቱሪስት ፍሰት ባለመኖሩ ብዙዎች ገበያቸው ቀንሷል፡፡ አንዳንድ በከተማዋ የሚገኙ ሆቴሎችም ሠራተኞችን እስከመቀነስ ደርሰው እንደነበር / ሰብለፀጋ ገልጸዋል፡፡ የንግድ እንቅስቃሴውም ወድቆ እንደነበር አውስተዋል፡፡

በሐዋሳ ከሚገኙ ትልልቅ ሪዞርቶች አንዱ  ኃይሌ ሪዞርት በተፈጠረው ችግር ደንበኞቻቸውን ካጡ ሆቴሎች መካከል ነው፡፡ ጥቃቱ በተከሰተበት ሐምሌ ወር ላይ ገበያው ዜሮ በሚባል ደረጃ ወርዶ እንደነበር ተወካዩ ገልጸዋል፡፡ ለወትሮው ሙሉ ለሙሉ ይያዙ የነበሩት መኝታ ክፍሎቹ ቀስ እያለ እስከ 30 እስካለፈው ሳምንት ድረስ ግን እስከ 40 በመቶ ብቻ ይያዝ እንደነበር አስረድተዋል፡፡ ይህም በሐምሌ ወር ከነበረው አንፃር ሲታይ ይበል የሚያሰኝ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የደቡብ ክልል የሆቴሎች ኅብረት ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንቱ አቶ ደጀኔ ጌታቸው፣ በከተማው የነበረው የአገር ውስጥና የውጭ የቱሪስት ፍሰት እስከመቆም ደርሶ ነበር ይላሉ፡፡ በከተማዋ 16 ባኮከብ ሆቴሎች ይገኛሉ፡፡ 200 የሚበልጡ የኮከብ ደረጃ የሌላቸው ነገር ግን ደረጃቸውን የጠበቁ ሆቴሎች ለሐዋሳ እንግዶች የመስተንግዶ አገልግሎት ይሰጣሉ ይላሉ፡፡ ነገር ግን የሐምሌው ጥቃት ‹‹ያሳደረው ጉዳት አንድና ሁለት የለውም፡፡ ገበያ ተቀዛቅዟል፣ ሠራተኞች ተሰደዋል፤›› የሚሉት አቶ ደጀኔ፣ ጎብኚ ሰላም ይፈልጋል፣ እኛም አገልግሎት ሰጪዎችገልግሎት በምንሰጥባቸው ቦታዎች ሰላም እንፈልጋለን ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

የተፈጠረው ክስተት በሆቴሎች ላይ ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ሥራ የሚሠሩ፣ በተለያዩ ንግዶችም ላይ በተሰማሩ ሁሉ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳሳረፈም ገልጸዋል፡፡ ‹‹ገበያው በአንድ ቀን አይመለስም፡፡ ቀጥሎ በምንሠራቸው ሥራዎች ይመለሳል የሚል እምነትና ምኞት ነው ያለን፤›› ብለዋል፡፡ ሐዋሳ የነበራትን ስም ወደ ነበረበት ለመመለስ ከከተማው መስተዳድርና ሌሎች ባለድርሻዎች ጋር አብረን እንሠራለንም ብለዋል፡፡

የከተማዋ ምክትል ከንቲባና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ገለታ ገረመው፣ በከተማዋ በተለያዩ ወቅቶች የራሳቸው አጀንዳ ያላቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በሚፈጥሩት የፀጥታ ችግር የከተማዋ ሰላም ሲናጋ ቆይቷል ብለዋል፡፡ በተለይም የሐምሌ 11 ጥቃት የከተማዋን የፀጥታ ሁኔታ አደጋ ውስጥ የከተተ እንደነበር፣ ክስተቱ በተለይም ሐምሌ 12 እና 13 ድረስ የከተማዋ እንቅስቃሴ የመቆም አዝማሚያ እንዲያሳይ አድርጎ እንደነበር አስታውሰዋል፡፡ የነበረውን የፀጥታ ችግር በቀናት ውስጥ ማስተካከል ቢቻልም ግን ‹‹ስለ ሐዋሳ የሚነገረውና የሐዋሳ ስም ሲነሳ በሕዝቡ አዕምሮ ውስጥ የሚመጣው ነገር አሁን በከተማዋ ያለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማይመሳሰል ነው፤›› ሲሉ የከተማዋ ሰላም ከሚወራው የፀጥታ ችግር ጋር የማይገናኝ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተለይም በማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚለቀቁ ጽሑፎች ከተማዋን የማይወክሉ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡.

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...