Sunday, April 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚና የሚመሩት የትምህርት ጥራት ኤጀንሲ የ174.6 ሚሊዮን ብር...

የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚና የሚመሩት የትምህርት ጥራት ኤጀንሲ የ174.6 ሚሊዮን ብር ክስ ቀረበባቸው

ቀን:

ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር የትብብር ስምምነት ውል በመፈጸም እየሠራ የሚገኘው፣ ኤቢኤች (ABH) ሰርቪስስ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር፣ የኢትዮ ቴሌኮም የቀድሞ ሥራ አስፈጻሚንና በአሁኑ ጊዜ የሚመሩትን የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲን ጨምሮ ስድስት ኃላፊዎችን፣ በ174.6 ሚሊዮን ብር የስም ማጥፋት ፍትሐ ብሔር ክስ መሠረተባቸው፡፡

ማኅበሩ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፍትሐ ብሔር ቀጥታ ክስ ችሎት ያቀረበው የክስ አቤቱታ እንደሚያስረዳው፣ ማኅበሩ በሕጋዊ መንገድ የተመሠረተ ነው፡፡ ከተለያዩ የመንግሥትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ትብብር ስምምነቶችን በማድረግ እንደሚሠራ፣ በአገር ውስጥ ፕሮጀክቶችንም በውል ስምምነት እየወሰደ አገልግሎቶችን በማቅረብ እየሠራ የሚገኝ መሆኑን፣ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ክፍሎች ጋርም የሚሠራቸው ፕሮጀክቶች መኖራቸውንም ማኅበሩ በመሠረተው ክስ አብራርቷል፡፡

ማኅበሩ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋርም ታኅሳስ 23 ቀን 2005 ዓ.ም. እና ታኅሳስ 25 ቀን 2009 ዓ.ም. ውል በማድረግ፣ በመጨረሻው ውል ላይ ከዩኒቨርሲቲው ጋር እስከ ታኅሳስ 21 ቀን 2020 ዓ.ም. ድረስ አብረው ለመሥራት መስማማታቸውን ባቀረበው ክስ ዘርዝሯል፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ጋር ያደረጉት ውል ጅማ ዩኒቨርሲቲ በአዲስ አበባ ለከፈተው የሥልጠና ማዕከል፣ የመማሪያ ክፍሎች፣ ቢሮዎች፣ ቤተ መጻሕፍት፣ የኮምፒዩተር ላቦራቶሪ፣ ካፌ፣ ፋይናንስና አስተዳደርና ሌሎች ድጋፍ ሰጪ አገልግሎቶችን ለማቅረብ መሆኑንም አክሏል፡፡ ማኅበሩ ቀደም ብሎ ለስድስት ዓመታት በውሉ መሠረት አገልግሎቶችን በመስጠት ግዴታውን በብቃት በመወጣቱ፣ ውሉን በማደስ እስከ ታኅሳስ 21 ቀን 2020 ዓ.ም. ድረስ ለመቀጠል ውል ማደሱንም አስታውሷል፡፡ ይህም አሠራሩ በመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና በጅማ ዩኒቨርሲቲ ቦርድና የበላይ ኃላፊዎች የሚታወቅና ይሁንታን ያገኘ መሆኑንም ተናግሯል፡፡ ዩኒቨርሲቲው ደግሞ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 240/2003 እንደገና የተቋቋመና ዋና ግቢው በጅማ ሆኖ በሌሎች ቦታዎች ካምፓሶችን የማቋቋም ሕጋዊ መብት እንዳለው ጠቁሞ፣ ከማኅበሩም ጋር በትብብር አገልግሎት እየሰጠ የሚገኘው በዚሁ አግባብ መሆኑንም አስረድቷል፡፡ ድርጊቱ በአዋጅ ቁጥር 650/2001 አንቀጽ 93 ድንጋጌ በተፈቀደው መሠረት መሆኑንም አክሏል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

በመሆኑም ያለውን ሕጋዊ ግንኙነት ያስረዳ ዘንድ ጅማ ዩኒቨርሲቲ የክርክሩ አባሪ ሆኖ እንዲገባና ለትክክለኛ ፍትሕ አሰጣጥ ይረዳ ዘንድ፣ በፍትሐ ብሔር ሕግ አንቀጽ 40 (2) ድንገጌ መሠረት ትዕዛዝ እንዲሰጥለት ጠይቋል፡፡

ከኤጀንሲው በተጨማሪ ማኅበሩ በክሱ ያካተታቸው የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር)፣ አቶ ታምራት ሞታ፣ አቶ ታረቀኝ ገረሱ፣ አቶ ዓብይ ደባይና አቶ ሰለሞን ታደሰ ናቸው፡፡ ተከሳሾቹ ከሐምሌ ወር 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በመደበኛ መገናኛ ብዙኃንና በማኅበራዊ ድረ ገጾች ማኅበሩ ለረዥም ዓመታት ያካበተውን መልካም ስምና ዝና የሚያጎድፍ የሐሰት መግለጫዎች በመስጠት፣ የስም ማጥፋት ተግባር በይፋ መፈጸማቸውን በክሱ አስረድቷል፡፡    

ማኅበሩ መንግሥት የማያውቀው መሆኑን፣ በጅማ ዩኒቨርሲቲና በማኅበሩ መካከል ያለው ግንኙነት ሕገወጥ እንደሆነ፣ ጅማ ዩኒቨርሲቲ አዲስ አበባ በከፈተውና ከማኅበሩ የድጋፍ አገልግሎት በሚያገኝበት ካምፓስ የሚማሩ ተማሪዎች መንግሥት እንደማያውቃቸው፣ የሚሰጡ ትምህርቶች ሕገወጥ እንደሆኑ፣ ተማሪዎች የሚከፍሉት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ እንደሆነና አብዛኛውን ገንዘብ የሚወስደው ማኅበሩ መሆኑን፣ ሌሎችንም ነጥቦች በመጨማመር ስሙን እንዳጠፉት በክሱ አስረድቷል፡፡ ተማሪዎችና ወላጆች እንዳይጭበረበሩና ገንዘባቸውን አባክነው ችግር ውስጥ እንዳይወድቁ በማስጠንቀቅና በማስፈራራት መግለጫ በመስጠት ጭምር፣ ማኅበሩን መንግሥት የማያውቀውና ገንዘብ የሚዘርፍ ሕገወጥ ተቋም እንደሆነ ግንዛቤ እንዲይዝ ማድረጋቸውንም ማኅበሩ በክሱ አብራርቷል፡፡

ተከሳሾች የከፈቱበት የስም ማጥፋት ዘመቻ ሰፊ ሽፋን አግኝቶ ውጤታማ እንዲሆንም፣ ኃላፊዎቹ ነሐሴ 16 ቀን 2011 ጋዜጣዊ መግለጫ በመስጠት ጭምር የስም ማጥፋት ዘመቻውን እንደቀጠሉበትም አክሏል፡፡ ዩኒቨርሲቲው በ2012 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ካምፓስ አዲስ ተማሪዎችን ተቀብሎ ለማስተማር ማስታወቂያ ላስነገረባቸው የመገናኛ ብዙኃን፣ ተከሳሾቹ ማስታወቂያው የተሳሳተ እንደሆነና አየር ላይ ማዋላቸው ተገቢ እንዳልሆነ በመግለጽ የማስተካከያ መልዕክት እንዲያስተላልፉ የሚጠይቅ የማስፈራሪያ ደብዳቤ በመጻፍ፣ የትምህርት ፕሮግራሙ እንዲቋረጥ እየጣሩ መሆኑንም በክሱ አብራርቷል፡፡ ማኅበሩን ሕገወጥ ሥራ የሚያከናውን ሕገወጥ ድርጅት አድርገው በማቅረብ፣ ተማሪዎቹና ወላጆች አመኔታ እንዲያጡ ማድረጋቸውን ጠቁሟል፡፡ በዚህ ድርጊት ምክንያት በአዲስ አበባ ካምፓስ በመማር ላይ የሚገኙ ተማሪዎች በተፈጸመው የስም ማጥፋት ተግባር ተደናግጠው መልቀቂያ እንዲሰጣቸው ጥያቄ እያቀረቡ መሆኑን፣ ሊመዘገቡ የነበሩ በርካታ ተማሪዎች ጥርጣሬ ገብቷቸው የመመዝገብ ሐሳባቸውን እንደቀየሩ ማኅበሩ በክሱ አብራርቷል፡፡ ሌሎች የውጭና የአገር ውስጥ ተቋማትም በማኅበሩ ላይ እምነት እንዳይኖራቸው በማድረጋቸው፣ አንዱዓለም አድማሴ (ዶ/ር) ከሥልጣናቸው ውጪ በማኅበሩ ላይ ያልሆነ መረጃ በመስጠታቸው በመልካም ስሙና ዝናው ላይ ጉዳት በማድረሳቸው የሕግ ኃላፊነት እንዳለባቸው አስረድቷል፡፡ ሌሎቹም ተከሳሾች የመንግሥት ሥልጣናቸውን ያላግባብ በመጠቀም የማኅበሩን ስምና ዝና በማጥፋታቸው፣ ጥፋተኛ መሆናቸውንም ገልጿል፡፡ በአጠቃላይ ተቋሙና ኃላፊዎቹ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 2126 እና 2127 ድንጋጌዎችን በመተላለፋቸው የሕግ ኃላፊነት ስላለባቸው፣ የማኅበሩን መልካም ስም እንዲያድሱና ኪሳራ እንዲከፍሉ ክሱን ማቅረቡን ማኅበሩ በክሱ አስረድቷል፡፡

በመሆኑም ማኅበሩ ከጅማ ዩኒቨርሲቲ ጋር በገባው ውል መሠረትና ከሌሎች ድርጅቶችም ጋር ከሚያከናውናቸው የማማከር፣ የምርምርና ሌሎች ሥራዎች ያገኝ በነበረው ገቢ ላይ የደረሰበትንና ወደፊት ለሚደርስበትን ኪሳራ 174,636,893 ብር የጉዳት ካሳ እንዲከፍሉትና ጉዳቱ እንዳይከፋ የዕርምት ዕርምጃ እንዲወስዱ ዳኝነት እንዲሰጥለት ክሱን አቅርቧል፡፡

ፍርድ ቤቱ ተከሳሾች እየፈጸሙ ያለውን የስም ማጥፋት ዘመቻ እንዲያስቆምለትም ጠይቋል፡፡ ፍርድ ቤቱም በማስቆሙ ላይ ብይን ለመስጠት ለጳጉሜን 5 ቀን2011 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ ተከሳሾች የክስ መቃወሚያ ካላቸው እስከ መስከረም 26 ቀን 2012 ዓ.ም. እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቶ፣ ክሱን ለመስማት ለጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ሰው መሆን ምንድን ነው? ቅርስና ማኅበራዊ ፍትሕ (ክፍል አንድ)

በሱራፌል ወንድሙ (ዶ/ር) ዳራ ከጎራዎች፣ ከመፈራረጅ፣ ነገሮችን ከማቅለልና ከጊዜያዊ ማለባበስ ወጥተን...

ኢኮኖሚው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሳት ያሠጋል

በጌታቸው አስፋው ኢትዮጵያን እንዳያፈርሱ የሚያሠጉኝ አንድ ሁለት ብዬ ልቆጥራቸው የምችላቸው...

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል በሕግ አምላክ ይላል

በገነት ዓለሙ የአገራችንን ሰላም፣ የመላውን ዓለም ሰላም ጭምር የሚፈታተነውና አደጋ...

በሽግግር ፍትሕ እንዲታዩ የታሰቡ የወንጀል ጉዳዮች በልዩ ፍርድ ቤት ሳይሆን በልዩ ችሎት እንዲታዩ ተወሰነ

የኤርትራ ወታደሮች በሌሉበትም ቢሆን ይዳኛሉ ተብሏል በፅዮን ታደሰ የሽግግር ፍትሕ የባለሙያዎች...