Sunday, June 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰኔ 15 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ተጠርጣሪዎች ላይ የተፈቀደው...

ጠቅላይ ፍርድ ቤት በሰኔ 15 ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ተጠርጣሪዎች ላይ የተፈቀደው የምርመራ ጊዜ ሕገወጥ ነው አለ

ቀን:

የፀረ ሽብር አዋጁን የሚቃረን ትዕዛዝ መሰጠቱን ገልጿል

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በተቀራራቢ ሰዓታት በተፈጸመው ከፍተኛ የመንግሥትና የወታደራዊ አመራሮች ግድያ ተጠርጥረው እስር ላይ በሚገኙ ተጠርጣሪዎች ላይ፣ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት የተፈቀደው 48 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ሕገወጥ መሆኑን፣ የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት አስታወቀ፡፡

ይግባኝ ሰሚ ችሎቱ በእነ አቶ አስጠራው ከበደ የምርመራ መዝገብ በተካተቱ 24 ተጠርጣሪዎች ላይ በሰጠው ፍርድ እንዳብራራው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ይግባኝ ሰሚ ችሎት የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት በተጠርጣሪዎች ላይ በፖሊስ የቀረበውን የምርመራ መዝገብ መርምሮ ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በሰጠው ብይን ምክንያት በቀረበለት የይግባኝ አቤቱታ ላይ ብይን መስጠቱን አስታውሷል፡፡

- Advertisement -

የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ለተጠርጣሪዎቹ የፈቀደውን የዋስትና መብት ተቃውሞ፣ መርማሪ ፖሊስ ያቀረበለትን የይግባኝ አቤቱታ የተመለከተው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት፣ የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተጠርጣሪዎቹ በዋስ እንዲለቀቁ ትዕዛዝ የሰጠበትን ምክንያት ሳይገልጽ፣ ‹‹የመጀመርያ ፍርድ ቤት የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል፤›› ማለቱ ተገቢ አለመሆኑን በፍርዱ ገልጿል፡፡

ይግባኝ ሰሚው ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሌላው የሰጠው ሕገወጥ ውሳኔ የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (20) አንድ በሽብር ተጠርጥሮ በምርመራ ላይ የሚገኝ ተጠርጣሪ ለተጨማሪ ምርመራ 28 ቀናት ለፖሊስ እየተፈቀደለት እስከ አራት ወራት ድረስ መሄድ እንደሚቻል ደንግጎ ቢገኝም፣ ይግባኝ ሰሚው የከፍተኛ ፍርድ ቤት ግን በአንድ ቀጠሮ 48 ቀናት መፍቀዱን ነው፡፡ ይግባኝ ሰሚው የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት በአዋጁ መሠረት 28 ቀናትን ቢፈቅድ እንኳን፣ ከሐምሌ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ የሚሆን ቢሆንም፣ ችሎቱ ግን እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ቀጠሮ መስጠቱን ፍርዱ ያስረዳል፡፡ ይኼ ማለት ተጠርጣሪዎቹ ከነሐሴ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ያለ ምንም ትዕዛዝ ወይም ሕጋዊ መሠረት፣ በሕገወጥ ሁኔታ መታሰራቸውን አመልክቷል፡፡

በፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ተጠርጣሪዎችን በዋስ እንዲለቀቁ ብይን የሰጠው፣ ፖሊስ መጀመርያውኑ በሽብር ተግባር ሲጠረጥራቸው 28 ቀናት የምርመራ ጊዜ ተሰጥቶት የነበረ ቢሆንም፣ ፍርድ ቤቱ በአዋጁ አንቀጽ 19(1) ድንጋጌ መሠረት ለመጠርጠር የሚያስችል ምንም ዓይነት ምክንያት እንደሌለው ከምርመራ መዝገቡ መረዳት መቻሉን አስታውቋል፡፡

በመሆኑም የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ከመረመረና ከእያንዳንዱ ተጠርጣሪ አኳያ፣ ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ፈጽመዋል›› ተብለው በመነሻነት የቀረበውን ድርጊት መርምሮና የእያንዳንዱን ተሳትፎ ገልጾ መሆኑን ጠቅላይ ፍርድ ቤት በፍርዱ አረጋግጧል፡፡ የመጀመርያ ፍርድ ቤትን ብይን የሻረው ከፍተኛው ፍርድ ቤት፣ የፖሊስን የምርመራ መዝገብ ከአዋጁ አንቀጽ 19 (1) ድንጋጌ አኳያ የወንጀል ድርጊቱን በሚገባ ለመጠርጠር የሚያስችል ከእያንዳንዱ ተጠርጣሪ አኳያ በቂ መነሻ ስለመኖሩና አለመኖሩ አጣርቶ፣ የግራ ቀኙን ክርክር ከሰማ በኋላ በምክንያት ላይ በመመርኮዝ ድምዳሜ ላይ መድረስ ይገባው እንደነበር ይግባኝ ሰሚው ፍርድ ቤት ገልጿል፡፡ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ግን በቂ ምክንያትና ትንታኔ ሳይሰጥ፣ ‹‹የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠው ትዕዛዝ ተሽሯል፤›› በማለት የሰጠው ትዕዛዝ፣ ሥነ ሥርዓታዊ አለመሆኑንም አስታውቋል፡፡ መርማሪ ፖሊስ ያልጠየቀውንና አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ (20) ድንጋጌ ከሚፈቅደው በላይ 20 ቀናት ጨምሮ 48 ቀናት አድርጎ መፍቀዱ፣ የሕጉን ድንጋጌ የጣሰ መሆኑን እንደሚያሳይ አክሏል፡፡ በተጠረጠሩት ግለሰቦች ላይ፣ ‹‹በቂ መነሻ ቀርቧል? ወይስ አልቀረበም? የሽብር ወንጀል ድርጊት ነው? ወይስ አይደለም?›› የሚለው በአግባቡ ታይቶና ተመርምሮ ከዋስትና መብታቸው አኳያ ተገቢውን ምላሽ መስጠት ሲገባው አለማድረጉ፣ ‹‹መሠረታዊ የሕግ ስህተት ነው›› ብሏል፡፡

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚው ችሎት በከፍተኛ ፍርድ ቤት ብይንና ትዕዛዝ ግራ መጋባቱን ጠቁሞ፣ ምክንያቱ ደግሞ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ያላግባብ የሰጠው የምርመራ ጊዜ እያለቀ ከመሆኑ አንፃር፣ በቀሪውና ባልተፈጸመው ጊዜ ላይ መታየት ያለበት ከመሆኑ በስተቀር፣ ያላግባብ ከታሰሩት ጊዜ አኳያ የተለየ ነገር ማለቱ፣ ጉዳዩ የጊዜ ቀጠሮ ከመሆኑ አንፃር ትርጉም እንደሌለው ገልጿል፡፡

በመሆኑም ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሐምሌ 25 ቀን 2011 ዓ.ም. የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት ትዕዛዝን በመሻር 48 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ መፍቀዱ ሕግን የጣሰ በመሆኑ፣ ከነሐሴ 15 እስከ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. (ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፍርድ እስከሰጠበት ቀን) ያለው ጊዜ ላይ ትዕዛዝ መስጠቱ ትርጉም እንደሌለው ጠቁሞ፣ ከነሐሴ 27 ቀን እስከ ጳጉሜን 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ድረስ ባሉ ቀናት የተሰጠው ትዕዛዝ መሻሩን በውሳኔው አስታውቋል፡፡ የታሰሩ ሰዎች መሠረታዊ መብቶች አንዱ ዋስትና መሆኑ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 19(6) ከመደንገጉ አንፃር፣ የመፈታት መብት ሊነፈግበትና ሊገደብ ከሚቻልበት አግባብ ውጪ መብታቸው ተነፍጎ በእስር ላይ መሆናቸው፣ የሕግ መሠረት የሌለውና ሕገወጥ መሆኑንም ይግባኝ ሰሚው ችሎት በውሳኔው ገልጿል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት በመጨረሻም በውሳኔው እንዳሳወቀው፣ ‹‹ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የሚጠየቅ ቢሆን›› (ማን ይግባኝ እንደሚጠይቅ ግልጽ አይደለም) የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሰጠውን ብይን ተመልክቶ፣ ተጠርጣሪዎቹና መርማሪ ፖሊስ በሚከራከሩበት ወንጀል ጉዳይ ‹‹በሕግ አግባብ መነሻ አለ ወይስ የለም?›› በሚለው ላይ፣ ‹‹በሌላ ችሎት ወይም ዳኛ›› አገናዝቦና በቂ ትንታኔና ምክንያት በመስጠት፣ እንዲወስን ትዕዛዝ ሰጥቶ መዝገቡን ወደ ታች በመመለስ ዘግቶታል፡፡

በሌሎች ተመሳሳይ ሁለት የምርመራ መዝገቦች ማለትም በእነ አቶ ሲያምር ጌጤ ሦስት ሰዎችና በእነ አቶ ወዳጅ ማሞ የምርመራ መዝገብ ሦስት ሰዎች በድምሩ ስድስት ተጠርጣሪዎች ላይ፣ ችሎቱ ተመሳሳይ ትዕዛዝ ሰጥቶ መዝገቡን ዘግቷል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ከስምንት ጠበቆች አንዱ የሆኑት አቶ መስኡድ ገበየሁ፣ ደንበኞቻቸው ሕግን መሠረት ያላደረገ እስር ውስጥ መሆናቸውንና ከሕግ ውጪ በሕገወጥ ሁኔታ መታሰራቸውን የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማረጋገጡን ጠቁመው፣ አካልን ነፃ የማውጣት (Habeas Corpus) የፍትሐ ብሔር ክስ እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የምግብ ዋጋ ንረት አጣዳፊ ዕርምጃ ያስፈልገዋል!

መንግሥት የሚቀጥለውን ዓመት በጀት ይዞ ሲቀርብ በአንገብጋቢነት ከሚነሱ ጉዳዮች...

ከባለአንድ ዋልታ ወደ ባለብዙ ዋልታ የዓለም ሥርዓት የመሸጋገራችን እውነታ

በአብዱ ሻሎ አንገት ማስገቢያ እ.ኤ.አ. በፌብሩዋሪ 2022 የሩሲያ መንግሥት በዩክሬን ‹‹ልዩ...

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የውጭ ግንኙነት የሺሕ ዘመናት ታሪኳና እሴቶቿን የሚመጥን መሆን ይኖርበታል

(ክፍል አንድ) በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን) እንደ መንደርደሪያ ለዛሬው የግል ትዝብቴንና ታሪክን ላዛነቀው...

ከአገር ግንባታ ጋር የተያያዙ ወሳኝ የቅርብ ታሪካችን አንጓዎች

በታደሰ ሻንቆ በአያሌው የተመረጡና ልጥ የሌላቸው ነጥቦች የተደራጁበት ይህ ታሪክ...