Friday, July 12, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየምርጫውን ቀን መርጠናል?

የምርጫውን ቀን መርጠናል?

ቀን:

በሳሙኤል ረጋሳ

እንኳን ለአዲሱ ዘመን በሰላም አደረሳችሁ ማለት በአሁን ጊዜ የወቅቱ መልካም ምኞት መግለጫ ነው፡፡ እኔ ደግሞ ሌላ ልጨምርበት፡፡ አዲሱን ዘመን የሰላምና የደስታ ያድርግላችሁ፡፡ ተጨማሪው ምርቃት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ የምርጫ ወቅት ከሚገባው በላይ እየፈጠነ ቀርቧል፡፡ እኛ ደግሞ ስለምርጫው ደንታ የሌለን ይመስል ያለ ምንም ተጨባጭ ተስፋ እየተንቀረፈፍን ነው፡፡ በሌላው ዓለም ‹‹ጊዜው ያልፋልና ዛሬን እንሥራበት›› የሚሉ ሲሆን፣ እኛ ደግሞ ‹‹ጊዜ ይመጣልና ቀስ ብለን እንሠራለን፤›› የሚል ነው ልምዳችን፡፡ ይኼ በጊዜ ያልፋልና በጊዜ ይመጣል አትቸኩሉ በሚለው መሀል ያለው ልዩነት አንዱ ሲጎዳን የኖረ ነው፡፡

መቼም ምርጫ የምናደርገው ለበጎና ለብሩህ ተስፋ መሆኑ በተግባር ባናየውም፣ በንድፈ ሐሳብ ደረጃ እስኪበቃን ዘምረንለታል፡፡ በእኛ አገር ታሪክ እስከ ዛሬ አንድም ጊዜ ምርጫ ተስፋ አልሆነንም፡፡ አንድም ጊዜ በመረጥነው ክፍል አልተደሰትንም፡፡ ይልቁንስ አሁን አሁን ምርጫ በተቃረበ ቁጥር ከተስፋው ይልቅ ሥጋቱ ነው የሚተርፈን፡፡ የዘንድሮው ምርጫም ከሌላው ጊዜ የበለጠ ሥጋትን ይዞልን እየመጣ ነው፡፡ የአሁኑ ሥጋታችን ከሁሉ በፊት ምርጫው ይካሄዳል ወይስ አይካሄድም የሚለው በራሱ ገና ያልለየለት መሆኑ ነው፡፡ እንኳን ምርጫ ማካሄድ ወቅቱን ለመወሰን እንኳን ባልደፈርንበትና ባልቻልንበት ሁኔታ ላይ ነን፡፡ ይኼ ውሳኔ በራሱ የሚያስከትለው ችግር እንዳለ የሚገመት ነው፡፡ የጋራ መግባባትም የለም፡፡ ምርጫው ይካሄድ የሚሉትም ሆነ አይካሄድ የሚሉት የየራሳቸውን ምክንያት እያቀረቡ ነው፡፡

ምርጫው ካልተካሄደ እስከ ዛሬ ለሺሕ ዘመናትም ሆነ ለመቶ ዓመታት የቆየችው አገር ትፈርሳለች ከሚለው ውጤት ጀምሮ፣ በተቃራኒው አገሪቱ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫን ማስተናገድ የማትችል በመሆኑ የማይሞከር ነው የሚሉ ተፃራሪ ሐሳቦች እስካሁን ሸምጋይ አላገኙም፡፡ አሁን አሳሳቢው ጉዳይ እነዚህ ሁለት ዋልታ ረገጥ ጽንፎች በመወያየት ለምን የጋራ የሆነ መፍትሔ አይቀመጥላቸውም የሚለው ነው፡፡ ይኼ መፍትሔ በጋራ መተማመን ሳይቀመጥ ምርጫውን በታቀደው መሠረት መፈጸም ቀርቶ መጀመርስ ይቻላል ወይ ሌላው ጥያቄ ነው፡፡ ነገሩን ፈታ እናድርገው፡፡

ምርጫው በወቅቱ መካሄድ አለበት የሚሉት ወገኖች መከራከሪያ ነጥባቸው በሕገ መንግሥቱ ላይ የተቀመጠ ድንጋጌ በመሆኑ፣ በምንም መመዘኛና ምክንያት መራዘም እንደማይቻል ነው የሚጠቅሱት፡፡ በእርግጥ ማንኛውም ዜጋ የአገሪቱን ሕግ የማክበር ግዴታ አለበት፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ከእነ ጉድለቶቹም ቢሆን ዘመኑ የሚፈልገውን መሠረታዊ የሕገ መንግሥት ይዘቶችን ያሟላ ነው፡፡ የሚገርመው ጉዳይ ግን እስከ ዛሬ ድረስ ማንኛውም ባለሥልጣን (አመጣሁት የሚለው ኢሕአዴግን ጭምር) እንደፈለገው ሲጥሰው የኖረ ነው፡፡ ተራው ዜጋ ግን ትንሽ እንኳን ዝንፍ ቢል ሕይወቱን ጭምር የሚያጣበት ነው የነበረው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ዋናው ጠንካራ ጎኑ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ለማስከበር የሄደበት ርቀት ነው፡፡ ይህንን ጠንካራ ጎኑን ያልጣሰ ባለሥልጣን በግለሰብም ደረጃ ሆነ በፓርቲ ብዙ አልታየም፡፡ የሕገ መንግሥቱ በርካታ አንቀጾች ደግሞ እነዚህን መብቶች ለማስጠበቅ የተቀመጡ ናቸው፡፡ እነዚህ በርካታ መሠረታዊ የሰው ልጆች መብቶች ሲጣሱ በመንግሥት በኩል ትንፍሽ ያለ የለም፡፡ አሁን ግን አንድ አንቀጽ 58/3 ብቻ ማሻሻያ ቢደረግበት ወይም እንደ ችግሩ ሁኔታ መፍትሔ ቢቀመጥ የሚያስከትለውን አደጋ ሲነግሩን ይዘገንናል፡፡

በመሠረቱ ይኼ አንቀጽ ዲክታተሮች ለመቆጣጠር የሚያስችል ተገቢና አሳሪ አንቀጽ ነው፡፡ ይኼንን አንቀጽ ለማስፈጸም በምንሞክርበት ጊዜ ደግሞ ሌሎች በርካታ አንቀጾች ከቁጥጥራችን ውጭ በሆነ ሁኔታ እንዳይጣሱ መጠንቀቅ አለብን፡፡ የአገራችን ተጨባጭ ሁኔታ ደግሞ የሚያሳየን ይኼንን ነው፡፡ አሁን ባለንበት ሁኔታ በመጪው ዓመት ምርጫውን ማካሄድ አለብን ብለን ብንገፋበት እንዘልቀዋለን ወይ? ይቻላል ወይ? ነው ጥያቄው፡፡ የሚቻል ከሆነ እንሂድበት፡፡ ግን ስምምነት መኖሩ የግድ ነው፡፡ የማይቻል መሆኑን ካመንን ግን በሕገ መንግሥቱ ስለተደነገገ ብቻ ምርጫ ወይም ሞት የሚል የጅል ድምዳሜ ላይ መድረስ ይገባናል? አብዮታዊ እናት አገር ወይም ሞት ብለው የተሰው ደርጋውያን እነሱ ሞቱ እንጂ አብዮታዊ አገር አልዘለቀችም፡፡ እንዲያውም ዛሬ ዛሬ አብዮት አላስፈላጊ የትግል አቅጣጫ መሆኑ እየታመነ መጥቷል፡፡

ምርጫን ለማስፈጸም ሦስት ደረጃዎች አሉ፡፡ ቅድመ ምርጫና ድኅረ ምርጫ፡፡ ሦስቱም የየራሳቸው ምቹ ሁኔታን የሚጠይቁ ናቸው፡፡ ምቹ ሁኔታ ከሌለ ግን እጅግ ዋጋ የሚያስከፍሉ መሆናቸውን በዓለም ላይ ከበቂ በላይ ተሞክሮዎች አሉ፡፡ የ1997 ዓ.ም. የእኛ ምርጫም ሩቅ ከመሄድ የሚያድን ማሳያ ነው፡፡ ለዋናው ምርጫ የሚረዳን የቀድሞ ምርጫ መሰናዶ በአግባቡ መከናወን አለበት፡፡ በዚህ ወቅት ሰፋፊ የሎጂስቲክስ አቅርቦቶችን ከመወሰን በተጨማሪ፣ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በየክልሉና በየከተማው እየተዘዋወሩ የምዝገባ፣ የቅስቀሳና አጠቃላይ የዝግጅት ተግባራቸውን የሚከውኑበት ጊዜ ነው፡፡

አሁን ባለው ሁኔታ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና ግለሰቦች በሁሉም የአገሪቱ ክፍሎች እንደ ልብ ተዘዋውረው ያለ ምንም ጫናና ወከባ አባሎቻቸውን፣ ደጋፊዎቻቸውንና ሕዝብን ጭምር ሰብስበው የመቀስቀስ፣ የማደራጀትና የማዘጋጀት ሥራ ያለ ሥጋት ሊሠሩ ይችላሉ? ምርጫ ቦርድስ ይኼንን ለማስፈጸም በቂ ዝግጅትና አቅም፣ እንዲሁም እስከ ምርጫ ጣቢያ ዘልቆ የሚሠራ የሠለጠነ የሰው ኃይል ይኖረዋል? መንግሥት እንደ መንግሥት ሁሉንም በእኩል ሜዳ ላይ አወዳድሮ ሕግን በማስከበር ለምርጫው ቀን ለማብቃት የሚያበቃ ዝግጅትና አቅም አለኝ ብሎ ያምናል? ሕዝቡስ በላም ወጥቶ ለመሳተፍና በሕጋዊ መንገድ መብቱን በሰላማዊ መንገድ ተጠቅሞ ለመምረጥ የሚያስችለው ሥነ ልቦናዊ ብቃት አለው? የፖለቲካ ፓርቲዎችስ ከመጠላለፍና ከመወነጃጀል ተላቀው አንዱን በማጥፋት ወይም በማዳከም ለመመረጥ ያላቸውና የነበራቸው አቋም ተለውጧል? በምርጫው ዕለትም ተመሳሳይ ጥያቄዎች መመለስ አለባቸው፡፡ በድኅረ ምርጫ ወቅትም ቢሆን በዕለቱ በየጣቢያው ድምፅ ማስቆጠርና ተማምኖ መለያየት፣ የምርጫ ኮሮጆውን ከምርጫ ጣቢያዎቹ በእግርና በከብት ጭምር አጓጉዞ ወደሚፈለገው ሥፍራ ከማድረስ ጀምሮ ቆጠራውና ሥሌቱ በሰላም ይጠናቀቃል ወይ? በመጨረሻም ፓርቲዎች ውጤቱን በሰላም ተቀብለው በሰላማዊ መንገድ ተጨባብጠው ይለያያሉ? ምርጫ በሚካሄድበት በየትም አገር ቢሆን እነዚህ ችግሮች አልፎ አልፎ ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

ግን ክፉ አደጋን የሚያስከትሉ አለመሆናቸው ታውቆ ነው የሚገባበት፡፡ አሁን በምናየው የአገራችን ሁኔታ ግን እነዚህን ሒደቶች በሰላም እናከናውናለን ወይ? ለሚለው ጥያቄ የአብዛኛዎቻችን ወይም የሁላችንም መልስ ብዙ የሚለያይ አይመስለኝም፡፡ እንደ አያያዛችን ከሆነ የእኛ ሁኔታ ለየት ያለና አደጋው በቀላሉ ሊቆም የማይችል መሆኑን መገመት ቀላል ነው፡፡ ለምርጫ ቅስቀሳ ሳይሆን ራሳቸውን ለሕዝብ ለማስተዋወቅ ጎጃም ደርሰው እንዳይንቀሳቀሱ ታግተው ተመልሰው የመጡ አሉ፡፡  በዚህ ሁኔታ ውስጥ ነው ምርጫው ከተያዘለት ቀነ ገደብ መተላለፍ የአገሪቱን ሕገ መንግሥት መጣስ ስለሚሆን፣ የሕገ መንግሥት ጥሰት ውጤት ደግሞ አገሪቱን ሊያፈራርስ ወደሚችል አደጋ እንደሚወስደን እየነገሩን ያሉ አሉ፡፡

አገሪቱን በማንኛውም ጥቃቅን ምክንያት እንደ እንቧይ ካብ ልናፈርሳት የምንችል ከሆነ፣ ቆም ብለን ማየት የሚገባን ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ ለምናቀርባቸው ጥያቄዎችም ሆነ ለምንፈልጋቸው ግቦች ማስፈጸሚያ የአገርን መፍረስ እንደ ቅድመ ሁኔታ ማስቀመጥ የለብንም፡፡ ይኼ አስተሳሰብ አገርን አስይዘን ቁማር የምንጫወት ያስመስልብናል፡፡ ከመንግሥት ጀምሮ ድብርት በተጫናቸው ቁጥር ስለአገር መፍረስና ማፍረስ የሚያስቡ፣ ከኢትዮጵያውያን ውጭ ሌላ ሕዝብ ያለ አይመስልም፡፡ የአገራችንን ድንበር አናስነካም ብለው አያቶቻችን በየጠረፉ ላይ ተሰውተው እንዳልቀሩ፣ ዛሬ እኛው ራሳችን እናፈራርሳታለን የምንል ሰዎች መኖራችን እንዴት የሚያስገርም ነው? ለትልቁም ለትንሹም እኔ ያልኩት ካልሆነ አገር ትፈርሳለች የሚለው አደንቋሪ ጩኸትና ማስፈራሪያ በሕግ ገደብ ሊበጅለት ይገባል፡፡ እኛው ራሳችን አገራችንን እናፈርሳለን የሚል አስተሳሰብ ከሞራል አንፃር ዝቅጠት፣ ከሕይወት አንፃር ውርደትንና ከንቱነት የት ድረስ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡

ሕገ መንግሥትንና አገርን በእኩል ሚዛን ላይ አስቀምጠን ለምርጫ የምናቀርብ ከሆነ ጤነኝነታችን ያጠራጥራል፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለአገር ተፈጠረ እንጂ፣ አገር ለሕገ መንግሥት ህልውና አልተፈጠረም፡፡ ሕገ መንግሥቱ ለአገር እንዲሆን ተብሎ ከጊዜ በኋላ ተፈጠረ እንጂ፣ አገር ሕገ መንግሥትን ለመፍጠር አልተመሠረተም፡፡ ሊለወጥ የሚችል ሕግንና ሊለወጥ የማይችል አገርን አናወዳድር፡፡ ቆም ብለን ካሰብን የተለያዩ ጥያቄዎችን ማንሳት እንችላለን፡፡ እንዲያው ለነገሩ የሲዳማን የክልልነት ጥያቄ ወይም ምርጫን በተመለከተ ሕገ መንግሥቱ ተጣሰ ብለው ለአስገዳጅነቱ የሚከራከሩት፣ በእውነት ሕገ መንግሥቱን ወደውና ፈቅደው ከልብ ደግፈውት ነው? ወይስ ከበስተጀርባው ልናገኘው የምንችለው ጥቅም ይኖራል ብለን አስበው ነው? አንዳንዶች የመጨረሻውን ውጤት ሳያገናዝቡ እኛ በርካታ ደጋፊዎች አሉንና ሌሎች ጊዜ አግኝተው ሳይገዳደሩን ምርጫው የግድ አሁን መሆን አለበት ከሚል እሳቤ የተነሱ ለመሆናቸው ብዙ እየተባለለት ነው፡፡

በእርግጥ ሕገ መንግሥት እንደ ሌሎች ሕጎች በቀላሉ የሚለወጥ መሆን የለበትም፡፡ ይኼ በመርህ ደረጃ ትክልል ነው፡፡ ነገር ግን ተጨባጭ ሁኔታው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለመፈጸም ካላስቻለ ምን ሊሆን ነው? የዚህ ዓይነት አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙ የግድ አንድ መፍትሔ ሊኖረን ይገባል፡፡ በሕገ መንግሥቱ መሠረት ለማሻሻል ቢፈለግ ደግሞ ሁሉም ክልሎች ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ጭምር ስላላቸው ለጊዜው ይኼ መንገድ ዝግ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ምርጫው ከወቅቱ ማለፍ እንደሌለበት ፈራ ተባ እያለም ቢሆን ነግሮናል፡፡ ይኼ የራሱ የድርጅቱ አቋም ነው፡፡ ነገር ግን በሒደት ውስጥ ከላይ የተጠቀሱት ችግሮች እንዳይፈጠሩ፣ ቢፈጠሩም ሁኔታዎችን የመቆጣጠር ግዴታ ያለበት እሱ የሚመራው መንግሥት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡ ሒደቶችን ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው በተገቢ መንገድ ከውኖ የምንፈልገውን መንግሥት ካቋቋመልን የሁላችንም ምርጫ ነው፡፡ ምርጫው ሁሉን አቀፍ፣ ነፃ፣ ቀጥተኛና ትክክለኛ መሆን እንዳለበት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 54/1 ደንግጓል፡፡ ስለዚህ ትጠቅመናለች ብለን ላሰብናት አንቀጽ ብቻ እየታገልን ሌሎችን እንዳናፈርስ መጠንቀቅ አለብን፡፡ በአሁን ወቅት ኢሕአዴግ ውስጥ ከፍተኛ ቅራኔዎች እንዳሉ የአደባባይ ሚስጥር ነው፡፡

ታዲያ እንኳን እንደ መንግሥት እንደ ቤተሰብ እንኳን የተከፋፈለ ቡድን ያለበትን መምራት ይቸግራል፡፡ አንድ የኦሮምኛ አባባል አለ፡፡ ‹‹ልጅቷ በአፏ ሙሉ ውኃ እንድትይዝ ተደረገች፡፡ ከዚያ ውኃውን ወደ ውስጥ ብትውጭው አባትሽ ይሞታል፣ ወደ ውጭ ብትተፊው እናትሽ ትሞታለች ስለተባለች፣ ሁለቱንም ለማድረግ ድፍረቱን ስላጣች እስከተቻለኝ እሞክራለሁ ብላ ውኃውን በአፏ ይዛ ቀረች፡፡››

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድም (ዶ/ር) እንደዚህ ዓይነት ቅርቃር ውስጥ ገብተው መውጫ እንዳያጡ የብልሆችና የብልጦች ምክር፣ ከዚህ በተጨማሪም ከሁሉም ጋር በቂና ሰፊ ውይይት ማድረግና የሚያዋጣውን መንገድ መቀየስ ተገቢው ነው፡፡ በመጨረሻ ደግሞ ጠንካራ አቋም ይዞ የሚከፈለውን መስዋዕትነት ከፍለው ሕዝቡን ከጭንቅና ከመከራ ውስጥ ጎትተው ማውጣት አለባቸው፡፡ በእርግጥ በእኛ አገር ታሪክ ለመሥራት የምንሞክረው ሕዝብን በማወያየት አሳምኖ የጋራ አቋም በማስያዝ አይደለም፡፡ እስካሁን አገሪቱ በመጣችበት ታሪክ የሚሠራው ጦርቱን በማሸነፍ መሆኑ ሲነገረን የኖረ ነው፡፡ አሁንም በተመሳሳይ መንገድ ሌላ ታሪክ ለመሥራት ብዙዎች የአገራችን ክልሎች ሠራዊት በመመልመልና በማሠልጠን በአክሳሪው የቁማር ጨዋታ የተጠመድን በርካቶች ነን፡፡ እውነተኛውንና የዘመኑን ሥልጡን ታሪክ ለመሥራት ደግሞ በመወያየትና በመደራደር ጦርነትን ማስቆም ስንችልና ያለ አግባብ ለጦርነት ያዘጋጀናቸውን ወጣቶች፣ ወደ ትምህርታቸውና መደበኛ ሥራቸው ስንመልሳቸው ነው ታሪክ ተሠራ የምንለው፡፡ ሁሉም ብሔረሰቦች ማንነታቸው ታውቆና ተከብሮ አንዱ ሌላውን እንደ ራሱ ብሔር መብቱ እንዳይነካበት ተቆርቋሪነቱን ከልብ ሲያይ ነው፡፡ ለዚህ ሁሉ ደግሞ የሚያበቃን አሁን በሽግግሩ ሒደት የሚመራን ድርጅት ጥንካሬና ሕዝቡ ለሥልጣን ሲሉ በሕዝብ መሀል ልዩነት ለመፍጠር ሌት ተቀን የሚባዝኑትን ለይቶ ሲያውቅ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት አገራችን ካችለበት ምስቅልቅል ሁኔታ ለመውጣትና ነገሮችን መልክ ለማስያዝ በመጀመርያ ሥልጣኑን የያዘው ኢሕአዴግ፣ በመጠኑም ቢሆን ከያዘው ፅኑ ደዌ ተላቆ ወደ ሕዝባዊነት መመለስ አለበት፡፡ በመካከላቸው ያለውን ያለ መግባባት ፈትተው በንፁህ ልቦና አገራዊ ጉዳይ ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባቸዋል፡፡ ኢሕአዴግ አሁን ከሕዝቡ ጋር ብቻ ሳይሆን ከራሱም ጋር ነው ቅራኔ ውስጥ የገባው፡፡ በተለይ ሕወሓት ካለው ሰፊ የፖለቲካ ተሞክሮና የአንጋፋ አባላት ስብስብ አንፃር፣ ኢሕአዴግ ውስጥ የሚፈጠረውን ቅራኔ በማለዘብና በመፍታት ከፖለቲካዊ ግምገማ አሳልፎ በሽምግልና ጭምር የመገሰጽና የማስማማት ኃላፊነት ነበረበት፡፡ ነገር ግን ሕወሓት እንኳን ሊገላግልና ነገሮችን ሊያለዝብ እሱ ራሱ የዕብድ ገላጋይ ሆኖ ዱላ ከማቀበል በማለፍ፣ የጠቡ መሪ ተዋናይ በመሆኑ ድርጅቱ በአጠቃላይ ከፍተኛ የፖለቲካ ኪሳራ ውስጥ ገብቷል፡፡ ሥልጣን የማይጠገብ ቢመስልም በዚህ ዘመን ለማንኛውም መንግሥት 27 ዓመታት መግዛት የዲክታተርነት መገለጫ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ራሱን በሰፊው ትዝብት ላይ ጥሏል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ በተለይ ሕወሓት ይኼን ያህል ዘመን ሥልጣን ላይ ቆይቶ ኢትዮጵያን ያልመራ ይመስል፣ ክፉ ቀን ሲመጣ ተጠቃሎ ወደ ክልሉ መመለሱና የሚከራከረው ለትግራይና ለትግራውያን ብቻ ሆኖ ሲታይ ለካስ በእነዚህ ነበረ ወይ ስንመራ የኖርነው የሚል ሂሳዊ ጥያቄ እያቀረበ ነው፡፡ አብሮአቸው ሲሠራ የኖረውም ከእነዚህ ጋር ነው ወይ የሠራሁት ይላል፡፡

አሁን ኢሕአዴግ በጥቅሉ ሕወሓት ደግሞ በተለይ ምርጫን በተመለከተ እንደገና ተመልሰው ሥልጣን ለመቆናጠጥ ካላቸው ፍላጎት ብቻ በመነሳት፣ አገርን ወደ አደጋ ሊያመራ የሚችል ተግባር ለመፈጸም መሞከር እስከ ዛሬ የሠሩዋቸውን በጎ ሥራዎች ሁሉ በዜሮ በማባዛት ታሪክም ሕዝብም ይቅር የማይላቸው ተጠያቂዎች መሆን የለባቸውም፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ምርጫውን እናስፈጽም የሚለው ሐሳብ የግድ ከሆነ፣ ገና ከጅምሩ በቅድመ ምርጫ ሒደት የሚገጥመን ችግር ለምርጫው ቀን የማያበቃን መሆኑንም ከግንዛቤ ማስገባት ተገቢ ነው፡፡ በቅድመ ምርጫው የሚነሳው ሁከት ምርጫውን ለማስፈጸም ስለማያስችለን ምርጫው ራሱን በራሱ ጊዜውን የሚያራዝምበት ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይኼ አስገዳጅ መራዘም ግን የሚመጣው የበርካቶችን ሕይወት በልቶ፣ ብዙ ሀብትና ንብረት አውድሞ፣ ሰፊ የፖለቲካና የማኅበራዊ ቀውስ ከፈጠረ በኋላ ነው፡፡

በመተላለቅ መፍትሔ ይመጣል ብለን ከጥንት ጀምሮ ተላልቀናል፡፡ ግን መፍትሔው እንደተደከመለት አልመጣም፡፡ ጦርነት መፍትሔ የሚሆነው አገርን ለመውረር ከሚመጣ የውጭ ጠላት ጋር ብቻ ነው፡፡ እርስ በርሳችን ለሥልጣንና ለፖለቲካ የበላይነት ብለን በፖለቲካው ውስጥ እጁ የሌለበትን ወጣትና አርሶ አደር እጁን ጎትተን ወደ ጦርነት መማገድ የለብንም፡፡ የውስጣችንን የፖለቲካ ልዩነት የመፍቻው ቁልፍ ውይይትና ድርድር ብቻ መሆን እንደሚገባው ካለፈው ታሪካችን እንማር፡፡ ዋናው ችግር ምርጫው እኛ እንደምናስበው የምርጫ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ አገሪቱን አደጋ ላይ ጥለው የራሳቸውን ጥቅም ለማስከበር የሚጥሩት ወገኖች ሁሉ ምርጫው በዋናነት የሚጠቀሙበት የማስፈንጠሪያ ቦርድ መሆኑ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...