በኢትዮጵያ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ በተለይ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ግንባታና ተያያዥ ሥራዎች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ስማቸው ከሚጠቀሱ ባለሀብቶች መካከል፣ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው ወይም (ታዲዮስ ኩሪፍቱ) ግንባር ቀደሙ ናቸው፡፡ በተለይ በሪዞርት ግንባታ ላይ ያኖሩት አሻራ በተመሳሳይ ሌሎችም እንዲከተሉት በር መክፈቱም ይጠቀሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት ደብረ ዘይትን ጨምሮ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በዓለም አቀፍ ደረጃ የቱሪዝም መዳረሻዎች ይጠየቃሉ የተባሉትን መሥፈርቶች ያሟሉ ሪዞርቶችን ገንብተው ለአገልግሎት አብቅተዋል፡፡ አሁንም እየገነቡ ነው፡፡ በቅርቡም በቢሾፍቱ የኢትዮጵያ ባህል ማዕከልና የዋተር ፓርክ ግንባታን አጠናቀው አስመርቀዋል፡፡ ኩሪፍቱ የሚለውን ብራንድ በመያዝ በተለይ በአፍሪካ ደረጃ ኩሪፍቱን ትልቅ ብራንድ ለማድረግ እየሠሩ ናቸው፡፡ በቅርቡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪን በተመለከተ መንግሥት ከባለድርሻ አካላት ጋር ስላደረገው ምክክር ዳዊት ታዬ ከኩሪፍቱ ሪዞርትና ስም ባለቤት ከአቶ ታዲዮስ ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል፡፡
ሪፖርተር፡- በሆቴልና ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ ከ15 ዓመታት በላይ ቆይተዋል፡፡ ኩሪፍቱና የሪዞርት ኢንቨስትመንቱ እንዴት ተጀመረ?
አቶ ታዲዮስ፡- መጀመርያ ቢዝነሱን የጀመርነው የዛሬ 20 ዓመት አካባቢ አዲስ አበባ በሚገኘው ሕንፃ ነው፡፡ ልክ የዛሬ 15 ዓመት ደግሞ የኩሪፍቱ ሪዞርትን ገነባን፡፡ ከዚያ በፊት ግን አዲስ አበባ በሚገኘው ቦስተን ስፓ ነው ሥራ የጀመርነው፡፡ በዘርፉ በአገሪቱ ውስጥ ያለውን ክፍተት በመመልከት የገባንበት ነው፡፡ በሆቴል ኢንዱስትሪ ውስጥ አፄ ኃይለ ሥላሴ ከወረዱ በኋላ አዲስ የመጣ ነገር ባለመኖሩ የመጀመርያውን ሪዞርት ለመሥራት ውኃ ዳር ቦታ ሲፈለግ ኩሪፍቱን አገኘን፡፡ ያኔ ማንም ሰው የሚፈልግው ስላልነበር እዚያ ቦታ ላይ ሥራ ለመጀመር ወሰንን፡፡ በወቅቱ ቢሾፍቱ የነበሩት የመሬት አስተዳደርና የኢንቨስትመንት ቢሮ ለእኛ ቦታ ጠቁመውን፣ ይህንን ቦታ ይዘን የመጀመርያው ኢንቨስትመንት ኩሪፍቱ ላይ ተደረገ፡፡ ይህ ከሆነ 15 ዓመታት ተቆጠሩ፡፡
ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ብዙ ክፍተቶች ያሉበት ቢሆንም፣ እናንተ በተለያዩ ቦታዎች ኢንቨስት እያደረጋችሁ ነው፡፡ እስካሁን ድረስ የት የት ኢንቨስት አድርጋችኋል? ኩሪፍቱን አፍሪካዊ ብራንድ እናደርጋለን በማለት ስትንቀሳቀሱ ነበርና ይኼ ውጥናችሁ ምን ደረጃ ላይ ደርሷል?
አቶ ታዲዮስ፡- የኩሪፍቱ ብራንድ እያደገና እየሰፋ መጥቷል፡፡ ከቢሾፍቱ ጀምሮ ባህር ዳር፣ ከዚያ ገረአልታ፣ እንደገናም ደግሞ ቡራዩ፣ ከዚያም ወደ አዳማ ደርሷል፡፡ አልፎ ተርፎ ከኢትዮጵያ ውጭ ተሻግሮ በጂቡቲ በሰፊው ኢትዮጵያዊ ብራንድ ሆኖ ለመጓዝ ችሏል፡፡ ስለዚህ ከኢትዮጵያ እየወጣም ነው፡፡ በኢትዮጵያ ቱሪዝም ኢንዱስትሪ ውስጥ በሎጅና በሪዞርት ደረጃ ፈር ቀዳጅ ሆኖ ሊታይ የሚችል ነው፡፡ ይህንን በመከተል ደግሞ ብዙዎች በተለያዩ ቦታዎች ላይ ሠርተዋል፡፡ የመዳረሻ ግንባታዎች ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ አራተኛው አልተሠራም፣ ገና ነው፡፡ ነገር ግን የኩሪፍቱን አስተዋጽኦ በተለያዩ መንገዶች መግለጽ ይችላል፡፡ አንዱና ዋናው ነገር በቀለ ሞላ ሆቴሎች ካቆሙበት በኋላ የተነሳው ኩሪፍቱ ነው፡፡ ኩሪፍቱ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በቱሪዝም ዘርፍ ብዙ ለውጥ ያመጣባቸውና በተግባር የታዩ ነገሮች አሉ፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ተሠርተው ለአገልግሎት ከበቁት ሪዞርቶች በኋላ በተመሳሳይ መንገድ ተከታዮች ማፍራቱ አንዱ ነው፡፡ ከኩሪፍቱ ሪዞርቶች ግንባታ በኋላ ብዙ ተከታዮች አፍርቶ በተለያዩ ቦታዎች ሪዞርቶች እየተገነቡ ነው፡፡ ለምሳሌ አሁን በቢሾፍቱ ከተማ ወደ 25 የሚሆኑ ሪዞርቶች ተከፍተዋል፡፡ በባህር ዳርም እንዲሁ፡፡ በየከተማው ተመሳሳይ አገልግሎት የሚውሉ ሥራዎች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- በኩሪፍቱ ሪዞርት ግንባታ ቆሞ አያውቅም ተብሎ ስማችሁ ይነሳል፡፡ ሰሞኑን እንኳን የኢትዮጵያ ባህል ማዕከልና ዋተር ፓርኩ ከተመረቀ በኋላ፣ ያደረጋችሁት ለሌላ ግንባታ የመሠረተ ድንጋይ ማኖር ነው፡፡ እስቲ እስካሁን የገነባችሁትንና አሁን የመሠረት ድንጋይ ስላኖራችሁለት ፕሮጀክት ይንገሩኝ?
አቶ ታዲዮስ፡- ከዛሬ 15 ዓመታት በፊት የመጀመርያው 18 ክፍሎች ሠራን፡፡ ከዚያ ሰባት ሌሎች ክፍሎች ጨመርን፡፡ 25 አደረስናቸው፡፡ እንደገናም ጨምረን 38 ደረሱ፡፡ 70 ጨምረን 108 ክፍሎች ደርሰናል፡፡ ሰሞኑን ደግሞ 123 ሱቆች፣ ሬስቶራንቶችና የባንክ አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎችንና ዋተር ፓርኩን አስመርቀናል፡፡ ዋተር ፓርኩ በተመረቀበት ዕለት ለሌላ ግንባታ መሠረተ ድንጋይ አኑረናል፡፡ ይህንን የመሠረተ ድንጋይ ያኖርነው 200 ተጨማሪ ክፍሎችና ሁለት ሺሕ ሰዎች የሚይዝ ኮንቬንሽን ሴንተር ለመገንባት ነው፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ በተዛማጅነት 200,000 ካሬ ሜትር ቦታ እንዲሰጠን እየተነጋገርን ነው፡፡ ቦታው ከተጨመረልን የመጀመርያው የአፍሪካ ማዕከል እናደርገዋለን፡፡ ይህንንም የምናደርገው አፍሪካውያን የሚኮሩበት ማዕከል ለመገንባት ካለን ውጥን አንፃር ነው፡፡
ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በመሆን አፍሪካ ውስጥ ያሉ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ እንዲሁም በመላው ዓለም የሚገኙ አፍሪካውያንን አኅጉራቸው በፈጠረው ቦታ ልጆቻቸውን ይዘው መጥተው የሚዝናኑበት ቦታ መፍጠር ነው፡፡ ስለዚህ ዕድገታችን ከቀን ወደ ቀን የማያቋርጥ ነው፡፡ ኩባንያችን ከተመሠረተ ሃያ ዓመታት ሊሆነው ነው፡፡ በእነዚህ ዓመታት ኮንስትራክሽን አቁመን አናውቅም፡፡ ከስድስት ወራት በኋላ ደግሞ የመጀመርያውን የአፍሪካ ቪሌጅ (መንደር) በቡራዩ እንከፍታለን፡፡ የአፍሪካ አገሮች አሻራ ያረፈበት ግንባታና ይዘቱም የአፍሪካ አገሮች ሊያመለክት በሚችል ደረጃ ግንባታው እየተካሄደ በመሆኑ፣ ከጥቂት ወራት በኋላ ተመርቆ ለአገልግሎት ይበቃል፡፡ ስለዚህ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማደግ እንጂ የመቆም ነገር የለም፡፡ በዚህ ደግሞ በጣም ደስተኛ ነን፡፡ አዳዲስ ነገሮችን ባወጣህ ቁጥር ያለህን ተቀባይነት ስታይ የበለጠ ለመሥራት ትጥራለህ፡፡ ለምሳሌ የዋተር ፓርኩን ባስመረቅንበት ጊዜ የኢትዮጵያ ሕዝብ አዳዲስ ነገር በፈጠርክ ቁጥር የሚያደርግልህን ዕገዛና ማበረታቻ ስታይ፣ መሰል ሥራዎችን ለመሥራት ትተጋለህ፡፡ ስለዚህ አዲሱ ዓመት አዳዲስ ነገሮችን እንድናስመርቅ ያብቃን እላለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ ኩሪፍቱ በዘርፉ የሚያደርገው ሌሎች ግንባታዎች ይቀጥላሉ ማለት ነው?
አቶ ታዲዮስ፡- ገና ነው አናቆምም፡፡ ብዙ መሥራት አለብን፡፡ አቅማችን እስከፈቀደ ድረስ መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡ ኢትዮጵያ እያደገች እንድትሄድና በዚህም ማፕ ላይ ማውጣት ነው የምንፈልገው፡፡ የኢትዮጵያ አየር መንገድም ስላለ የተመረጠች አገር እንድትሆን እንሠራለን፡፡ ብዙ ቱሪስቶች እንዲመጡ እንሠራለን፡፡ ሌሎች ቱሪስቶች ከሌሎች አገሮች ሲያመጡ፣ እኔ ግን ትኩረት አድርጌ እየሠራሁ ያለሁትም የአፍሪካን ዳያስፓ ራ ወደ አፍሪካ መመለስ ነው፡፡ በአገራቸውና በምርታቸው አፍሪካውያን ልዩ የሆነ ገጽታ መፍጠር እንደሚችሉ ማሳየት ነው፡፡ በአፍሪካዊነታቸው መመካት የሚችሉበት ማዕከል መፍጠር ነው፡፡ በዚህ መሠረት እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንዲህ ባለ ሁኔታ እየሠራችሁ ቢሆንም፣ በአጠቃላይ የአገሪቱ የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሲታይ እጅግ ብዙ የሚቀረው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ካላት የቱሪዝም አቅም አንፃር እየተጠቀመችበት አይደለም፡፡ እርስዎ ይህንን ሰፊ ክፍተት እንዴት ይገልጹታል?
አቶ ታዲዮስ፡- በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎቻችን አንድ አራተኛ የሚሆነውን እንኳን ሠራን ብዬ አላምንም፡፡ አንደኛ በፌዴራል መንግሥት የቱሪዝም ዘርፍ ለማሳደግ፣ እንዲሁም ያለውን የቱሪዝም ሀብት ለመጠቀም ፍላጎቱ እየተከፈተ ያለው አሁን ነው፡፡ አሁን ቅድሚያ እያገኘ እየመጣ ነው፡፡ ይህንንም በክልሎች ደረጃ ዕውን ለማድረግ እየተሠራ ያለው አሁን ነው፡፡ ታች አውርዶ መሬት ለሚሰጠው ከንቲባ፣ ቦታውን መርቶ በቶሎ ለሚያስረክበው አካል በቅልጥፍና እንዲሠሩ ያስችላል፡፡ ባንኮችም በተቀላጠፈ መንገድ ለዘርፉ ብድር ማመቻቸት ይኖርባቸዋል፡፡ እንደ እስካሁኑ ለሦትና አራት ዓመት የአጭር ጊዜ ብድር በመስጠት የሚዘልቅ አይደለም፡፡ ከውጭ የሚመጣውን ዕቃ የጉምሩክ ሰዎች በትክክለኛ መንገድ የሚያስረክቡት አሠራር ሊተገበር ይገባል፡፡ የጉምሩክ፣ የፋይናንስና የመሬት አስተዳደርና የፌዴራል መንግሥቱ ፍላጎቶች አንድ ላይ ተጣምረው የሚሠሩበት ግብረ ኃይል ቢኖር፣ እውነተኛ የቱሪዝም ለውጥ ይመጣል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁን ይኼ ሰዓት ደርሷል ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ለቱሪዝም ፈተና የሆኑ ነገሮች የሉም? ለዕድገቱ እንቅፋት የሆኑ ነገሮችን ለመቅረፍ ምን መደረግ አለበት? ሰሞኑን በቱሪዝም ዘርፍ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት መድረክ ውይይት ተደርጎ ነበር፡፡ ቀጣይ ጉዞውን እንዴት ይመለከቱታል?
አቶ ታዲዮስ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥቱን ፍላጎት ያህል የክልሎች ፍላጎት አብሮ እኩል ባለመከፈቱ፣ በዞንና በወረዳ አስተዳደር መሬት የሚሰጠው ሹም ለቱሪዝም ያለው ፍላጎትና ዓላማ አንድ ዓይነት ያለመሆን ነገር ነበር፡፡ እስከ ታች ድረስ በተዋረድ ስላልደረሰ እንጂ በኢትዮጵያ በሰሜን ሙሉ ለሙሉ፣ በምዕራብ፣ በምሥራቅ፣ በደቡብና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ገና ያልነካነው የቱሪዝም መዳረሻዎች ብዛት ልነግርህ ከምችለው በላይ ነው፡፡ እና አሁን ለመጀመርያ ጊዜ እየሰማን ያለነው ፋይናንስን በተመለከተ ትልቅ ለውጥ የሚያደርግ መሆኑን ነው፡፡ በሰሞኑ ስብሰባ ይህንን ተገንዝበናል፡፡ እስካሁን ይሰጥ የነበረው ብድር ከአምስት ዓመት ያልበለጠ፣ እንዲያውም ለሦስት ለአራት ዓመት ነው፡፡ እንዲህ ሆኖም ከፍተኛ የሆነ ወለድ የሚጠየቅበት ነበር፡፡ አሁን ግን ለዘርፉ የሚሰጠው ብድር ወደ 15 ዓመትና ሃያ ዓመት ለሚሆን ጊዜ የሚረዝምና በአነስተኛ ወለድ እንደሚሰጥ፣ ለመጀመርያ ጊዜ ሰሞኑን በተካሄደው የቱሪዝም ኮንፈረንስ ላይ ሰምተናል፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ ትስተናገዳላችሁ መባሉ ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንዲሁም የመንግሥት አቅጣጫ ቱሪዝምን ለመጀመርያ ጊዜ በቅድሚያ ዘርፍ ውስጥ አስገብቶታል፡፡ እንዲህ ያለው ነገር በተዋረድ ሄዶ ከተሠራና በመግበባት መጓዝ ከተጀመረ፣ የሚመለከታቸው አካላትም ተሳትፈው የሚሠሩ ከሆነ፣ የቱሪዝም ዘርፉ በአጭር ጊዜ ያድጋል፣ ይቀየራል፡፡ ይህ ምንም ጥያቄ የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ከሌሎች በተለየ በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎች አሏት፡፡ እንደ ኬንያና ግብፅ ያሉ አገሮች ግን በቱሪዝም የሚያገኙት ገቢ ከኢትዮጵያ እጅግ የላቀ ነው፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ምንጫቸውም ቱሪዝም ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኘው ገቢ ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፍ ገቢ እንዲህ ዝቅተኛ የመሆኑ ምክንያት ምንድነው ይላሉ?
አቶ ታዲዮስ፡- በዘርፉ ላይ በሚፈለገው ደረጃ ስላልተሠራ ነው፡፡ ምን ተሠራ? ወደ ደቡብ ብትሄድ አንድ ሁለት ሪዞርት ነው ያለው፡፡ በደቡብ ግን ያለው የቱሪዝም መዳረሻ ብዙ ነው፡፡ ገና ያልተነኩ የቱሪዝም መዳረሻ ቦታዎች አሉ፡፡ በአጠቃላይ መዳረሻ ላይ ይኼ ነው የሚባል ሆቴል አለማለት አይችልም፡፡ ቢኖርም እንኳን ዓለም አቀፍ ደረጃውን ጠብቆ ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሊመጣ የሚችለውን ቱሪስት ለማስተናገድ በሚመች ሁኔታ ተደራጅቶ እየተሠራ አይደለም፡፡ በሰሜንም ቢሆን ገና ተጀመረ እንጂ ብዙ መሻሻል ያለበት ነው፡፡ የደንበኛ አገልግሎትን አሳድጎና የምግብ አቅርቦቱን አስተካክሎ ዓለም አቀፍ ደረጃ ላይ አልደረስንም፡፡ ገና እኮ አዲስ አበባ ላይ እየተፈራገጠ ነው ያለው፡፡ ስለዚህ ይኼ ባለበት ሁኔታ የግብፅና የኬንያ ዓይነት ቱሪዝም ማምጣት በጣም ይከብደኛል፡፡ ግን ለሚቀጥሉት ዓመታት የምናያቸው ብዙ ነገሮች አሉ፡፡ በዘርፉ የሚታዩ ብርሃኖች ግን ይታዩኛል፡፡ ተስፋ ያለው ብርሃንም ይታየኛል፡፡
ሪፖርተር፡- እንዴት?
አቶ ታዲዮስ፡- ከሰሞኑ በዘርፉ ላይ የተደረገው ምክክርም ሆነ በአጠቃላይ የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ፣ በፌዴራል ደረጃ ተነሳሽነት ታያለህ፡፡ ክልሎችም በውድድር ኢንቨስተሮች እንዲመጡላቸው የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ ታያለህ፡፡ ኢትዮጵያ ሰላም እስከሆነች ድረስ መጪው ጊዜ ብሩህ መሆኑን አያለሁ፡፡ በቀደም በስብሰባው ላይ እንደሰማነው ለቱሪዝሙ ትኩረት ተሰጥቶ በፋይናንስና በሌሎች ድጋፍ በሚሹ ጉዳዮች ላይ ያደረጋል የተባለው ድጋፍ የሚቀጥል ከሆነ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም በከፍተኛ ሁኔታ ያድጋል፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን የጠቀሱልኝ መንግሥት ለዘርፉ ትኩረት መስጠቱን ነው፡፡ ይህ መልካም ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር ግን ኅብረተሰቡ ለቱሪዝም ያለውን አመለካከት በማሳደግና ቱሪስቶችን ተንከባክቦ የቆይታ ጊዜያቸውን እንዲያራዝሙ የማድረግ ችግር አለ፡፡ በአጠቃላይ ከቱሪዝም አንፃር የኅብረተሰቡ ሚና ምን መሆን አለበት ይላሉ? የባለሙያም እጥረት ያለበት ከመሆኑ አንፃር አሁንም ዘርፉ ብዙ መሻሻል ያለበት አይመስልዎትም?
አቶ ታዲዮስ፡- ሰሞኑን በተካሄደው ኮንፈረንስ ስንንጋገርበት የነበረው የሠለጠነ የሰው ኃይል እጥረት አንዱ ነው፡፡ አንዱ ከአንዱ ሠራተኛ መሰራረቅ እንጂ የራሱን ሲስተም አጎልብቶ የራሱ ራዕይ ኖሮት፣ አሠልጥኖ የከፈተበት ወቅት አለመኖሩ ይታወቃል፡፡ የቱሪዝም ኢንዱስትሪው እንጭጭ በመሆኑ እንዲያድግ ለማድረግ የአገር ውስጥ ተቋማት ብቻ ሳይሆኑ ከውጭ አገር ጋር ዝምድና ያላቸውና የውጭውን የሠለጠነ የሰው ኃይል ለማሠልጠን በሚችል ደረጃ ተቋማት መከፈት አለባቸው፡፡ አሁን ይኼም እየታሰበ ነው፡፡ እኛም በቢሾፍቱ እንዲህ ያለ ትልቅ ተቋም ለመገንባት እየተነጋገርን ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማም የሆቴል ማኅበራት በዚሁ ጉዳይ ላይ እየተነጋገሩ ነው፡፡ ይህንን በትልቁ አሳድገን፣ የዘመነ የሰው ሀብት ካፈራን፣ የመዳረሻዎች ልማት በየቦታው ከተስፋፋ ይህንን በመጠቀም ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ቱሪስት ማሳደግ ይቻላል፡፡
አሁን እኮ ዘጠኝ በዩኔስኮ የተመዘገቡ የቱሪስት መዳረሻዎች ያሉበት አገር፣ በምሥራቅ በኩል አርታኢሌ ያሉና አፋርን የመሰሉ የቱሪዝም መዳረሻዎች፣ በድሬዳዋና በሐረር ሊጎበኝ የሚችል ቦታ እያለ በቱሪስት መዳረሻ ቦታዎች ደረጃውን የጠበቀ ሆቴልና ለመሰል አገልግሎት የተዘጋጀ መሠረተ ልማት ያለ መኖር ሲያስቆጭ ይችላል፡፡ የባሌ ተራሮችን የመሰለ ቦታ አሥር ክፍል ያሉት አንድ ሪዞርት ነው ያለው፡፡ ይህንን ለመሰለ ቦታ ግን ከዚህም በላይ ያስፈልጋል፡፡ እንደ ወንጪ ያለ ቦታ፣ በጅማ በኩልም እስከ ድንበር ድረስ ያለውን የደን ሀብት በሙሉ ወደ ቱሪዝም ሊቀየር ይችላል፡፡ ለቱሪዝም የሚሆኑ የአገሪቱን ክፍሎች ቆጥረህ አትጨርስም፡፡ ብዙ ሀብት አለን፡፡ ስለዚህ የተወሰነ የመፈራገጫ ጊዜ እንጂ አንድ ጊዜ መሮጥ ከጀመርን የሚያቆመን የለም ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ቱሪዝም ሰላም ይፈልጋል፡፡ ከዚህ ቀደም እንደታየው በሆነ ምክንያት በአገር ውስጥ አንድ ነገር ሲከሰት መጀመርያ የሚጎዳው የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ምን አጥተናል ይላሉ?
አቶ ታዲዮስ፡- የኢትዮጵያ ቱሪዝምን የበለጠ ለማሳደግ የአገር ውስጥ ቱሪዝም ማደግ አለበት የምንለው ለዚህ ነው፡፡ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ማሳደግ ይኖርብናል፡፡ እንደ ውጭ አገር ቱሪዝም ትንንሽ ረብሻ ባለ ጊዜ አይደነግጥም፡፡ ስለዚህ የውስጥ ቱሪዝም ላይ ትኩረት አድርገን የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ካሳደግን በአንድ ተኩስ የሚቆሙትን መቀነስ እንችላለን፡፡ ምንም ጥርጣሬ የሌለው ንግግር የሌለው ጉዳይ ግን የቱሪዝም ኢንዱስትሪ ሰላምን ይፈልጋል፡፡ በሽግግር ወቅት ግርግሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ግን አሁን ተስተካክሎ በየቦታው ሰው ሁሉ ተመልሶ እየሠራ ነው፡፡ ሁልጊዜ ሥራ ከአገር ውስጥ ከጀመረ ጠንካራ ይሆናል፡፡ የአገር ውስጡም ቢሆን ሰላም ይፈልጋል፡፡ እርግጠኛ ነኝ ሁሉም ሰው እንደሚፈልገው አገራችን ሰላም ትሆናለች ብዬ አስባለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የቱሪዝም ኢንዱስትሪው ሰላም የሚሻ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በሰሞኑ የውይይት መድረክ ይህ ጉዳይ ተነስቷል፡፡ ከዚህ አንፃር ሰላምን በተመለከተ ከመንግሥት የተሰጠውን ሐሳብ እንዴት ገመገማችሁት?
አቶ ታዲዮስ፡- የሰሞኑ ስብሰባ ለመጀመርያ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግሥት የቱሪዝምን ዘርፍ በተለየ መንገድ ያየበት ነው፡፡ በተለየ ሁኔታ ውይይት እንዲደረግ ዕድል የተሰጠበት ነው፡፡ በፀጥታ በኩል መቶ በመቶ ምንም ሳታስቡ ሥሩ ተብሏል፡፡ ይህንን የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራሉ ራሳቸው ሲናገሩ በጣም ደስ ብሎናል፡፡ ሁለተኛ የክልል መስተዳድሮች በሽሚያ እኔ ጋ ኢንቨስት ብታደርጉ የተሻለ አደርጋለሁ ብለዋል፡፡ ሌላው ደግሞ ከዚህ የተሻለ እኔ አደርጋለሁ በማለት የመወዳደርና በዘርፉ እንዲሠራ ያሳዩት የጥሩ ስሜት በውስጣችን እንዲሰርፅ አድርገዋል፡፡ ሌላው የባንክ ኃላፊዎችም ብድር ሲሰጥ ከሚታሰበው ወለድ በአራት በመቶ የቀነሰ ወለድ የሚታሰብበት ብድር እንሰጣለን ብለዋል፡፡ እንደ ድሮ ለብድር መክፈያ ጊዜ የአራትና የአምስት ዓመት ሳይሆን፣ 15 እና 20 ዓመታት አስረዝመን እናበድራለን ማለታቸው መድረኩን የተለየ ያደርገዋል፡፡ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆኑ ሚኒስትሯ ያደረጉት ንግግር ስለዘርፉ ተስፋ እንድናገኝ የሚያበረታ ነው፡፡ በተለይ ሚኒስትሯ ቱሪዝምን ከአሁን በኋላ በሰፊው አንሄድበታለን ማለታቸው፣ ፖዘቲቭና ለወደፊት ትልቅ ራዕይ እንድናይ አድርጎናል፡፡
ሪፖርተር፡- ወቅቱ ዘመን መለወጫ በዓል ነውና እንደ ቱሪዝም ዘርፍ ባለሀብትነትዎ እንዲህ ያሉ በዓላትን እንዴት ነው የሚያሳልፉት?
አቶ ታዲዮስ፡- እኔ እኮ አሁን ሁለት ነገር ያጣሁ ሰው ነኝ፡፡
ሪፖርተር፡- ምን ማለትዎ ነው? ሁለቱ ያጧቸው ነገሮች ምንድናቸው?
አቶ ታዲዮስ፡- ያጣሁት የአባቴን ስምና የበዓል ቀንን ነው፡፡ ምክንያቱም አሁን ስሜን ሲጠሩ የአባቴን ስም ትተው ታዲዮስ ኩሪፍቱ ነው የምባለው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የበዓልን ቀን ነው፡፡ ዓመት በዓልን እሠራለሁ፡፡ ዓመት በዓሉን በየቦታው ሰው ሳስተናግድ ነው የምውለው፡፡ ትልቅ እንግዳ የማስተናግድበት ቀን ነው፡፡ የት እሄዳለሁ ብለህ ነው? ስለዚህ ዓመት በዓል ለእኔ የእንግዶች ማስተናገጃ ጊዜ ነው፡፡ ወደ ሪዞርት የሚመጡ አሉ፡፡ እነዚህን እንግዶች ልክ ቤቱ እንዳለ ሰው በሚሰማው ደረጃ ነው የምናስተናግደው፡፡ ለሁላችንም መልካም አዲስ ዓመት ይሁንልን፡፡