Saturday, December 9, 2023

የ2011 ዓበይት ፖለቲካዊ ክስተቶች

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ኢትዮጵያውያን በመልካም ምኞት የተቀበሉት 2011 ዓ.ም. የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ዓበይት ክስተቶችን አስተናግዶ አሮጌው ዓመት ተብሎ ለመሸኘት የቀሩት ጥቂት ቀናት ናቸው፡፡ በዚህ ባለፈው አንድ ዓመት በአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን የተለያዩ መረጃዎች ለሕዝብ ሲቀርቡ ነበር፡፡ የባህር ኃይል ሊቋቋም እንደሚገባና ይህንንም ተፈጻሚ የሚያደርግ ረቂቅ ሕግ ለተወካዮች ምክር ቤት መቅረቡ፣ የመንግሥት ተቋማትን በከፊል ወደ ግል ለማዛወር መወሰኑ፣ እንዲሁም በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ሲቀሰቀሱ የነበሩ ግጭቶችንና አለመረጋጋቶችን የተመለከቱ ዜናዎችና ዘገባዎች ዋና ዋናዎቹ ነበሩ፡፡

ከዚህ በተለየ ደግሞ ለሳምንታት የአገሪቱ የመገናኛ ብዙኃን የዜና ርዕስ ሆኖ የሰነበተው በረራ ከጀመረ ስድስት ደቂቃዎች በኋላ የወደቀው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነው አውሮፕላን አደጋ ነበር፡፡ መዳረሻውን ኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ አድርጎ የነበረው ቦይንግ 737-800 ማክስ አውሮፕላን 149 መንገደኞችን አሳፍሮ ነበር፡፡ ይህ አውሮፕላን በደረሰበት አደጋ 149 ተሳፋሪዎችና ስምንት የአውሮፕላኑ ሠራተኞች ሕይወት ማለፉ፣ በዚህ ዓመት አገሪቱ ካጋጠማት አሳዛኝ ክስተት አንዱና ዋነኛው ነበር፡፡

እነዚህንና የመሳሰሉ ክስተቶችን ያስተናገደው አሮጌው 2011 ዓ.ም. ለ2012 ዓ.ም. ቦታውን ሊለቅ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተውታል፡፡ በዚህ ዘገባም በአገሪቱ የተከሰቱ ዓበይት ፖለቲካዊ ክንዋኔዎች ይቃኛሉ፡፡

2011 ዓ.ም. ሲጀመር ከወደ ሰሜን የአገሪቱ ክፍል የተሰማው ዜና የብዙዎችን ልብ ያሞቀ ነበር፡፡ ማክሰኞ ዕለት ውሎ የነበረው መስከረም አንድ ቀን እንደ ከዚህ ቀደም ማክሰኞዎች፣ እንዲሁም በየዓመቱ እንደሚመጣው የአዲስ ዓመት መጀመርያ ቀን ብቻ አልነበረም፡፡ ዕለቱ ለሃያ ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ዳግም የተከፈተበት እንጂ፡፡

በዕለቱ የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ከተካሄደባቸው ሥፍራዎች መካከል የቡሬና የዛላንበሳ ግንባሮች፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) እና የኤርትራ ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ በተገኙበት ምሽጎቹ ፈርሰው የየብስ ትራንስፖርት በይፋ መጀመሩ ተበስሮ ነበር፡፡ በወቅቱ በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን የቀጥታ ሥርጭት መከታተል እንደተቻለው በቡሬም ሆነ በዛላምበሳ ለሃያ ዓመታት ያህል የተዘጉት ድንበሮች ሲከፈቱ፣ የሁለቱም አገሮች የአካባቢው ነዋሪዎችና ፍጥጫ ውስጥ የነበሩት ወታደሮች የሁለቱን አገሮች ሰንደቅ ዓላማዎች በማውለብለብ በሆታና በጭፈራ የአዲሱን ዓመት በዓል በጋራ አክብረዋል፡፡

ምንም እንኳን በአካባቢው የሚገኙ የሁለቱም አገር ዜጎች በሆታና በደስታ አዲሱን ዓመት ቢቀበሉም፣ የድንበር አካባቢ ንግድ ቢጧጧፍም፣ እንዲሁም በርካታ ኤርትራውያን ወደ ኢትዮጵያ ቢገቡም እስካሁን ድረስ ከሁለቱም ወገን ግልጽ የሆነ ማብራሪያ ሳይሰጥበት ድንበሩ በታኅሳስ አጋማሽ 2011 ዓ.ም. ዳግም ተዘግቷል፡፡ ዳግም ተከፍቶ ዳግም የተዘጋው የሁለቱ አገሮች ድንበር በመጪው አዲስ ዓመት ዳግም ይከፈት ይሆን? መልሱ የቀናት ጉዳይ ነው፡፡

በዚሁ ዓመት የመጀመርያ ሳምንት ላይ የመነጋገሪያ ርዕስ፣ እንዲሁም በአዲስ አበባና ዙሪያዋ በሚገኙ ከተሞች መሀል ለተቀሰቀሰው ግጭት መንስዔ የሆነው የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ወደ አገር ቤት መመለስ ነበር፡፡ መስከረም 5 ቀን 2011 ዓ.ም. ከ26 ዓመታት የስደትና የትግል ሕይወት በኋላ ወደ አዲስ አበባ የተመለሰው በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግ፣ በመስቀል አደባባይ በሺዎች የሚቆጠሩ አባላቱ አቀባበል አድርገውለት እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡

ምንም እንኳን በመስቀል አደባባይ የነበረው የአቀባበል ሥነ ሥርዓት ሰላማዊ የነበረ ቢሆንም፣ ከዕለቱ አስቀድሞ የኦነግ ዓርማና ባንዲራ ለመስቀልና በተለያዩ ሥፍራዎች ለመቀባት በተደረገ እንቅስቃሴ ምክንያት በተፈጠረ ግጭትና አለመረጋጋት በርካቶች የአካል ጉዳት የደረሰባቸው ሲሆን፣ የተወሰኑ የሞቱ ግለሰቦች እንደነበሩም መዘገቡ የሚታወስ ነው፡፡ አደጋው ጥሎት ያለፈው ጠባሳ አይረሴ ነው፡፡

ኦነግ ወደ አገር ቤት የገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይን ጥሪ ተቀብሎ የነበረ ቢሆንም፣ ከጥቂት ቆይታ በኋላ ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሊቀመንበርነት ከሚመሩት የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ኦዴፓ) እና ከመንግሥት ጋር እሰጥ አገባ ውስጥ ገብቶ እንዲሁ መነጋገሪያ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ በተለይ ከታጠቁ የግንባሩ አባላት ዕጣ ፈንታ ጋር በተያያዘ የተፈጠረው አለመግባባት ተካሮ በምዕራብ ኦሮሚያ ከፍተኛ ግጭት ተፈጥሮ ነበር፡፡

በዚህ መሀል የግንባሩ የጦርና የፖለቲካ ቡድን መለያየታቸውን በመግለጽ ጦሩ በትግሉ እንደሚቀጥልና ከፖለቲካው ቡድን ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው ገልጿል፡፡ ይህ ልዩነት የተፈጠረበት ዓመት በጉዳዩ ላይ ዘላቂ መቋጫና መፍትሔ ሳይገኝለት ሊጠናቀቅ ነው፡፡

የ2011 ዓ.ም. መስከረም ወር በርካታ የፖለቲካ ክስተቶችን ያስተናገደ ወር ነበር፡፡ ወሩ ከመጠናቀቁና ጥቅምት ከመባቱ አንድ ቀን በፊት ነበር፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ ጋር ካልተወያየን ያሉ ወታደሮች ወደ ቤተ መንግሥት ያቀኑት፡፡

ከኦነግ አቀባበል ጋር በተያያዘ በቡራዩ የተፈጠረውን አለመረጋጋትና ፀጥታ የማስከበር ግዳጃቸውን የፈጸሙት ወታደሮች፣ ከጥቅማ ጥቅም ጋር በተገናኘና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ጠቅላይ ሚኒስትሩን ማነጋገር እንፈልጋለን ማለታቸው አይዘነጋም፡፡

በዕለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፑሽአፕ ከወታደሮቹ ጋር ሠርተውና እራት አብልተው በመሸኘት በመንግሥት የመገናኛ ብዙኃን ጉዳዩ ቀላል ነገር እንደሆነ በመግለጽ ሕዝቡን ለማረጋጋት የሞከሩ ቢሆንም፣ ከጉዳዩ መረጋጋት በኋላ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በወቅቱ ‹‹እርር ድብን›› ማለታቸውን ገልጸው ነበር፡፡

በዚህ ዓመት ዋነኛ የፖለቲካ ርዕስ ከሆኑ ጉዳዮችና የአገር ውስጥንም ሆነ ሌሎችን ታላላቅ ዓለም አቀፍ የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ የሳበው ጉዳይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ አዲስ የካቢኔ አደረጃጀት ነበር፡፡ በዚህ አዲስ ካቢኔ ውስጥ ሴቶች ግማሽ ያህሉን ሥፍራ የያዙ ሲሆን፣ ይህ ክስተትም ለጠቅላይ ሚኒስትሩ የተለያዩ ሙገሳዎች ማስገኘት ችሎ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ከጥቂት ወራት በኋላ የተወሰኑት ከነበሩበት ቢነሱም፣ ይህ ፆታን የማመጣጠን ጉዳይ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፍተኛ ድጋፍ አስገኝቶላቸው ነበር፡፡

ከሹመትና ፆታን ከማመጣጠን አንፃር ሌላው በዚህ ዓመት የተከሰተው ክስተት ደግሞ አራተኛዋ የሪፐብሊኩ ፕሬዚዳንት ሳህለ ወርቅ ዘውዴ፣ የወይዘሮ መዓዛ አሸናፊ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት መሆን፣ እንዲሁም በተቃውሞ የፖለቲካ እንቅስቃሴያቸው የሚታወቁት ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሆነው መሾማቸው ነበር፡፡

ቀዝቃዛው የጥቅምት ወር ተገባዶ የሰብል ምርት የሚሰበሰብበት ኅዳር ወር ሲገባ፣ መንግሥትም ያላግባብ በባለሥልጣናትና በሥራ ኃላፊዎች ተበትኖብኛል ያለውን የአገሪቱ ሀብት መሰብሰብ መጀመሩን ይፋ በማድረግ፣ በአገሪቱ ከፍተኛ ብክነት እንዲስፋፋና በሙስና ተሳትፈው ነበር ያላቸውን ግለሰቦች ማሰር የጀመረበት ወቅት ነበር፡፡

በዚህም መሠረት በርካቶች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ በተለይ የቀድሞው የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ዋና ዳይሬክተር ሜጄር ጄኔራል ክንፈ ዳኘው በቁጥጥር ሥር የዋሉት በዚህ ጊዜ ነበር፡፡ ዋና ዳይሬክተሩ በትግራይ ልዩ ፖሊስ በቁጥጥር ሥር ውለው ለፌዴራል መንግሥት ተላልፈው የተሰጡ ሲሆን፣ የመያዛቸው ዜና በሰበርነት መቅረቡ፣ እንዲሁም በካቴና ታስረው በቴሌቪዥን መስኮት መታየታቸው፣ በሕወሓት በኩል ከፍተኛ ተቃውሞ ቀስቅሶ ነበር፡፡

በዚሁ ወር ሌላው ተጠርጥረው ሲፈለጉ የነበሩት የደኅንነት መሥሪያ ቤቱ ባልደረባ የነበሩት አቶ ያሬድ ዘሪሁን፣ በኦሮሚያ ክልል በዱከም ከተማ በአንድ ሆቴል ውስጥ በሚገኝ መኝታ ቤት ውስጥ ተገኝተው በቁጥጥር ሥር መዋላቸው እንዲሁ ከዘንድሮ ዓበይት ፖለቲካዊ ክስተቶች አንዱ ነው፡፡

በርካታ የአገሪቱ ጎምቱ ፖለቲከኞችን ወደ ማረፊያ ቤት እንዲገቡ ምክንያት በሆነው የሙስና ችግር ምክንያት፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) ነባርና ከፍተኛ አመራር የነበሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ከጥረት ኮርፖሬት ኩባንያዎች ገንዘብ ያላግባብ በማባከንና ማጥፋት የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው፣ እስካሁን መቋጫ ሳያገኝ ወደሚቀጥለው ዓመት የተሸጋገረ ክስተት ነው፡፡

በየካቲት ወር መጀመርያ ላይ በአዲስ አበባ ከተማ የተከናወነው 32ኛው የአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ቀደም ሲል ሲደረጉ እንደነበሩት የኅብረቱ ስብሰባዎች በኢትዮጵያውያን ዘንድ ስሜት ያልሰጠ አልነበረም፡፡ ኢትዮጵያውያኑ ይህንን ስብሰባ አስመልክቶ የተለየ ነገር እንዳለ በማወቃቸው፣ የስብሰባውን መጠናቀቅ በጉጉት ሲጠብቁ ነበር፡፡ የዚህ ጉጉት ምንጭ ደግሞ በስብሰባው ማጠናቀቂያ ወቅት የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መታሰቢያ ሐውልት በኅብረቱ ቅጥር ግቢ ውስጥ በይፋ እንደሚመረቅ በመገለጹ ነው፡፡

ሐውልቱ በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና በሌሎች መሪዎች በይፋ እንደተመረቀ በደቂቃዎች ውስጥ ነበር በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያ በስፋት የመነጋገሪያ አጀንዳ የሆነው፡፡ የንጉሡን ሐውልቱ ምሥል፣ ክብርና ዝና አይመጥንም በማለት የተለያዩ የተቃውሞ ድምፆች የተሰሙ ሲሆን፣ ሐውልቱ መሠራቱ በራሱ አንድ ትልቅ ውለታ ነው በማለት አስተያየት የሰጡም ነበሩ፡፡

አቶ ገዱ አንዳርጋቸው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድርነት ሥልጣናቸውን የለቀቁት በየካቲት ወር ሲሆን፣ በሰኔ 15 ቀን ግድያ ሕይወታቸው ያለፈው ኢኮኖሚስቱ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) የክልሉን የርዕሰ መስተዳድርነት ሥልጣን የተቆናጠጡት በዚህ ወር ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በዚህ ወር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በመሆን ሲያገለግሉ የነበሩት ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የኬንያ ቢሮ ዳይሬክተር በመሆን የተሾሙበት ወርም ነበር፡፡

ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣውን የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች በመካከላቸው የሚኖረውን ግንኙነትና በተናጠል የሚያደርጓቸውን እንቅስቃሴዎች የሚገዛ የአሠራር በማስፈለጉ፣ አዲስ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ለማድረግ መሻገራቸውን የሚያሳይ ነው የተባለለት የቃል ኪዳን ሰነድ ተፈራርመው ነበር፡፡ ነገር ግን ቃል ኪዳኑን መሠረት አድርጎ የተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ እንደከዚህ ቀደሙ አደረጃጀቶች ሁሉ የፀደቀውን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጅን ተቃውሞታል፡፡

የፖለቲካ ፓርቲዎች ቁጥር ማሻቀቡን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተለያዩ መድረኮች በአገሪቱ የሚገኙ የተቃዋሚ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ሰብሰብ ብለው ቢመጡ መልካም እንደሆነ ሲመክሩ ነበር፡፡ የዚህ ምክር ውጤት በሚመስል ሁኔታ ሰባት የተለያዩ ፓርቲዎችንና ታዋቂ ፖለቲከኞችን ያሰባሰበው ኢዜማ ምሥረታውን ይፋ ያደረገው፣ በዚህ ለመሸኘት ጥቂት ቀናት በቀሩት ዓመት ነው፡፡

በዋነኛነት የዜግነት ፖለቲካን እንደሚያራምድ የገለጸው የኢትዮጵያ ዜጎች ማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ ከምሥረታው ባለፈ በመጀመርያ ጉባዔው የፓርቲውን መሪዎችና ሊቃነ መናብርት መርጧል፡፡

በፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ ማካሄድና ሌሎች የምርጫ ጉዳዮች ጋር በተያያዘ ሥራ የበዛበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ፣ በመጪው ዓመት ይካሄዳል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርጫ ማስፈጸሚያ ይሆን ዘንድ 3.7 ቢሊዮን ብር በጀት መጠየቁም ዓብይ የመነጋገሪያ አጀንዳ ነበር፡፡

ቦርዱ ያቀረበው የበጀት ጥያቄ ባለፉት የምርጫ ወቅቶች ከነበሩት በጀቶች ከፍተኛ ጭማሪ ያለው ሲሆን፣ ይህም የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ከዚህ ቀደም ጥቅም ላይ የነበሩትን ኮሮጆዎች በግልጽ በሚያሳዩ ኮሮጆዎች ለመቀየር፣ በአንድ የምርጫ ጣቢያ አንድ የነበረውን የምርጫ ኮሮጆ ሁለት ለማድረግ በመታቀዱና በመሳሰሉት ምክንያቶች መሆኑን በመግለጽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ አየር መንገድ አደጋ የፈጠረው ድንጋጤና ሐዘን ሳይደበዝዝ፣ በሰኔ ወር እንዲሁ ሌላ አስደንጋጭና አሳዛኝ ክስተት በአገሪቱ ርዕሰ መዲና አዲስ አበባና በአማራ ክልል ዋና ከተማ ባህር ዳር ላይ ተከሰተ፡፡

ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከወደ ባህር ዳርና ከአዲስ አበባ ከተማ የተሰማው ይህ አሳዛኝ ዜና፣ የአገሪቱን ከፍተኛ የጦርና የሲቪል ባለሥልጣናትን ሕይወት የነጠቀ ነበር፡፡

በዚህም ምክንያት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ሜጄር ጄኔራል ገዛዒ አበራ፣ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ የእሳቸው የአደረጃጀት አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ፣ እንዲሁም አቶ ምግባሩ ከበደ ግድያ ተፈጽሞባቸው ሕይወታቸው ማለፉን አገርን ማቅ ያለበሰ ሐዘን ውስጥ ከቷት ነበር፡፡

ከዚህ ጋር በተያያዘ በርካቶች በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሲሆን፣ እስካሁን ድረስ መረጃዎችና ማስረጃዎች ተጠናቅረው በአዲስ አበባና በባህር ዳር ግድያዎች መካከል ስላለው ግንኙነት፣ እንዲሁም መንግሥት ‹መፈንቅለ መንግሥት› ብሎ በሰየመው እንቅስቀሴ ዙሪያ የተወሰዱ ዝርዝር ዕርምጃዎች ለሕዝብ ይፋ አልሆኑም፡፡ በዚህ ዘግናኝ ግድያ አደጋ ሳቢያ የተጠረጠሩ ግለሰቦች ጉዳይ በፍርድ ቤት እየታየ ዓመቱ ተገባዶ ወደ አዲስ ዓመት እየተሸጋገረ በመሆኑ፣ በመጪው ዓመት ይህ ጉዳይ በፍርድ ቤት ውሎ ዋነኛ አጀንዳ ከሚሆኑ ጉዳዮች አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ከእነዚህ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች መገደል ቀናት በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ አዳዲስ ሹመቶችን የሰጡ ሲሆን፣ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር የነበሩት ጄኔራል አደም መሐመድን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም፣ ሌተና ጄኔራል ሞላ ኃይለ ማርያም የምድር ኃይል ዋና አዛዥ፣ እንዲሁም አቶ ደመላሽ ገብረ ሚካኤልን ደግሞ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አድርገው ሾመዋል፡፡

በሰኔ ወር የተከናወነ ሌላው ዓብይ ሹመት ደግሞ ታዋቂው የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር)፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው የመሾማቸው ዜና ነበር፡፡

በተለይ የ1997 ዓ.ም. ምርጫን ተከትሎ በተፈጠረው ቀውስ ሳቢያ በቁጥጥር ሥር ከዋሉት በርካታ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች ጋር ታስረው የነበሩ ሲሆን፣ ከዓመታት በኋላ ግን ኮሚሽነር በመሆን ተሹመው ከቀድሞ ኮሚሽነርና በአሁኑ ወቅት በዚምባቡዌ የኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑትን አዲሱ ገብረ እግዚአብሔር (ዶ/ር) ተክተው እየሠሩ ነው፡፡

በደቡብ ክልል በሲዳማ ዞን የክልልነት ጥያቄ ጋር ተያይዞ ተከስቶ የነበረው ውጥረት በዚህ ዓመት ከተከሰቱ አሳሳቢ ፖለቲካዊ ጉዳዮች አንዱ ነበር፡፡ በዚህ የክልልነት ጥያቄ የተነሳ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ነዋሪዎች ክልልነትን እንመሠርታለን ባሉበት ሐምሌ 11 ቀን 2011 ዓ.ም. አንድ ቀን ሲቀረው በአምስት ወራት ውስጥ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ሥራዎች መጀመሩን ቢገልጽም፣ የዞኑ ነዋሪዎች ግን ለተቃውሞ አደባባይ በመውጣት የተለያዩ ጉዳቶች አድርሰዋል፡፡ በዚህም ምክንያት የሰው ሕይወት ጠፍቷል፣ የግልና የመንግሥት ንብረት ወድሟል፡፡ ጥያቄው እንዲህ በኃይል ቢጠናቀቅም ለጉዳዩ መፍትሔ ለመስጠት ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ የሚመለከተው ምርጫ ቦርድ፣ ኅዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ሕዝበ ውሳኔ እንዲካሄድ ወስኗል፡፡ ይህ ጉዳይ ከዘንድሮ ጀምሮ ወደሚቀጥለው ዓመት የተንከባለለ ዓብይ ፖለቲካዊ ትኩሳት ነው፡፡

ቀጣይ የአገሪቱን የምርጫ ሁኔታና ሥርዓት ይመራል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ አዋጅ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከዕረፍት ተመልሶ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የፀደቀው፣ በነሐሴ አጋማሽ ነው፡፡ አዋጁ ግን ከፍተኛ ተቃውሞ ቀርቦበታል፡፡

በተለይ የቃል ኪዳን ሰነዱን የፈረሙ 107 ፓርቲዎች ያቋቋሙት የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት አባላት አዋጁ ተፈጻሚ እንዳይሆን የጠየቁ ሲሆን፣ ከዚህ ማዕቀፍ ውጪም 57 የሚሆኑ ፓርቲዎች በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውመውታል፡፡

እነዚህንና የመሳሰሉ ዓበይት የፖለቲካ ጉዳዮችን ያስተናገደው 2011 ዓ.ም. ሊሸኝ ነው፡፡ በርካቶች በዚህ ዓመት የተከሰቱ አለመግባባቶችና ፈተናዎችም ከዓመቱ ጋር አብረው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እንዲሸኙ ምኞታቸው እንደሆነ ከወዲሁ እየገለጹ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -