Saturday, April 20, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ገቢዎች ባለሥልጣን ለ155 ግብር ከፋዮች ዕውቅና ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ሰኞ ጳጉሜን 4 ቀን 2011 ዓ.ም. ለ155 ግብር ከፋዮች በስካይ ላይት ሆቴል ዕውቅና ሰጠ፡፡

በዕውቅና አሰጣጥ መርሐ ግብር ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር)፣ የገቢዎች ሚኒስትር ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሺሰማ ገብረ ሥላሴ፣ እንዲሁም ተጋባዥ እንግዶች በተገኙበት በብር ደረጃ 97 ግብር ከፋዮች፣ በወርቅ ደረጃ 41 ግብር ከፋዮች፣ እንዲሁም በፕላቲንየም ደረጃ 17 ግብር ከፋዮች ዕውቅና አግኝተዋል፡፡

በዚህ መርሐ ግብር የክብር እንግዳ የነበሩት ወ/ሮ አዳነች፣ ‹‹ግብር ከፋዮች አጋሮቻችን፣ ግብር ከፋዮች ባለድርሻዎች ናቸው፤›› በማለት ‹‹ለግብር አሰባሰቡ ባለቤት ናቸው ብለዋል፡፡ ‹‹ግብር ከፋዩን መደገፍ ያለብን ኃላፊነትን ለመወጣት ብቻ አይደለም፤›› በማለት፣ ‹‹ግብር መሰብሰብ የምንችለው ግብር ከፋዩን ከደገፍነው፣ ሀብታም ካደረግነው፣ እንዲሁም ትርፋማ ካደረግነው ብቻ ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ግብር ከፋዩ ሠርቶ በተሻለ ሁኔታ ገቢ ማግኘት ከቻለ የመንግሥት ገቢ፣ የአገር ገቢ፣ እንዲሁም የሕዝብ ገቢ ያድጋል፤›› ያሉት ሚኒስትሯ፣ ‹‹ይህንን ማድረግ ካልቻልን የሚቀጭጨው ግብር ከፋዩ ብቻ ሳይሆን መንግሥትም ጭምር ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መንገዳችንን ማሳለጥ የምንችለውና ተገቢውን ግብዓት ልንዘረጋ የምንችለው ግብራችንን በትክክል ከሰበሰብን ብቻ ነው፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ የተዘጋጀው ይህ መርሐ ግብር፣ ‹‹ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለታክስ ሕግ ተገዥነትና ፍትሐዊ ተጠቃሚነት›› የሚል መሪ ቃል አለው፡፡

ባለሥልጣኑ ላዘጋጀው የዕውቅና መርሐ ግብር የመረጣ መሥፈርት የሚያዘጋጅ ኮሚቴ አቋቁሟል፡፡ በዚህም መሠረት መሥፈርቱ ሦስት የመረጣ ወሰን ሲኖረው፣ የመጀመርያው ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ናቸው፡፡ በዚህም መሠረት የባለሥልጣኑ ከፍተኛ፣ መካከለኛ፣ እንዲሁም አነስተኛ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ተካተዋል፡፡ ሁለተኛው የመረጣ ወሰን ግብር ከፋዩ የተመዘገበበት ጊዜ ነው፡፡ በዚህ መምረጫ መሥፈርት የተካተቱት ለአምስት ዓመትና ከዚያ በላይ ለሆነ ጊዜ በግብር ከፋይነት የቆዩ ግብር ከፋዮች ናቸው፡፡ በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠው የግብር ከፋይ ደረጃ ሲሆን፣ በዚህ መሥፈርት የተካተቱት ደረጃ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ሆነው የሒሳብ መዝገብ የሚይዙ ግብር ከፋዮችን ብቻ እንደሆነ የኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ጥላሁን ግርማ ገልጸዋል፡፡

ከመረጣው ወሰን በተጨማሪም ሰባት የመምረጫ መሥፈርቶችም እንደተካተቱ አቶ ጥላሁን ጠቁመዋል፡፡ በዚህ የመምረጫ መሥፈርትም ሰባቱም የተለያዩ ክብደት እንደተሰጣቸውና በአጠቃላይ ከመቶ እንደተያዘ ተናግረዋል፡፡ እንደ አብነት ለመጥቀስ ያህል ከፍተኛ ክብደት ካላቸው መሥፈርቶች አንዱ በማንኛውም ሁኔታ ከጥፋት ጋር በተያያዘ የተገኘ መረጃና (የኢንተለጀንስ ኢንቨስቲጌሽን ኦዲት) ነው፡፡ ይኼም 25 በመቶ ይዟል፡፡ ሌላው የንግድ ድርጅቱ የሽያጭ (ገቢ) መጠን ሲሆን፣ ለአነስተኛ ግብር ከፋይ ከአምስት ሚሊዮን ብር በታች፣ ለመካከለኛ ከአምስት ሚሊዮን እስከ 40 ሚሊዮን ብር፣ እንዲሁም ለከፍተኛ ከፋዮች ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ነው፡፡ ይኼም አምስት በመቶ ይዟል፡፡

እነማን ተመረጡ ለሚለው ጥያቄም በመሥፈርቶቹ መሠረት ዝቅተኛ የሥጋት ደረጃ (ከፍተኛ ሕግ የሚያከብሩ) ከተመረጡ በኋላ፣ ከእነዚህ መካከል የተሻለ ገቢ ያስገቡትን በመለየት በሦስት ደረጃ ማለትም በወርቅ፣ በብርና በፕላቲኒየም ደረጃ 155 ግብር ከፋዮች እንደተለዩ አቶ ጥላሁን ገልጸዋል፡፡ በዚሁ ዕለት ከ155 ግብር ከፋዮች ጎን ለጎን ባለድርሻ አካላት፣ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች፣ እንዲሁም ልዩ ውቅና የሚገባቸው ተብለው ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል፡፡

በተዘጋጁት 16 መሥፈርቶች መሠረት ከ16 ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶች ሦስቱ ዕውቅና የተሰጣቸው ሲሆን፣ ለሥራ ማስኬጃ የሚሆን የመኪና ሽልማትም ተበርክቶላቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት በብር ደረጃ ተሸላሚ መርካቶ ቁጥር ሁለት የመካከለኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት፣ በወርቅ ደረጃ ተሸላሚ ቦሌ ክፍለ ከተማ የአነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ እንዲሁም በፕላቲኒየም ደረጃ ተሸላሚ ንፋስ ስልክ ላፍቶ አነስተኛ ግብር ከፋዮች ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ናቸው፡፡

በዚህ መርሐ ግብር ላይ ጣሃ ያሺም ለተባሉ ግለሰብ ልዩ ዕውቅና የተሰጠ ሲሆን፣ ዕውቅና የተሰጣቸው ማናቸውንም ዓይነት ግብይት በደረሰኝ ብቻ የሚያከናውኑ በመሆኑ እንደሆነ ተገልጿል፡፡ ደረሰኞቹን አደራጅተው በማስቀመጥ በአስረጂነት ማቅረብ በመቻላቸው፣ ለሌሎች በአርዓያነት የሚጠቀስ ተግባር በማከናወናቸው ዕውቅናው እንደተሰጣቸውም አቶ ጥላሁን አክለዋል፡፡ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (ኢንጂነር) ለሥራ የሚሆን ሼድ ለግለሰቡ አበርክተውላቸዋል፡፡ ሌላው ለባለድርሻ አካላት የተሰጠ ዕውቅና ሲሆን፣ ገቢዎች ሚኒስቴርም ዕውቅና ካገኙት አንዱ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ባለሥልጣን በ2011 በጀት ዓመት የዕቅዱን 93.6 በመቶ ወይም ለመሰብሰብ ካቀደው 34.5 ቢሊዮን ብር 32.57 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡ ተጠቁሟል፡፡ በዚህም ከአምናው አፈጻጸም ጋር ሲነፃፀር የ4.82 ቢሊዮን ብር ወይም የ17.57 በመቶ ብላጫ እንዳሳየ ተገልጿል፡፡                                                                                    

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች