Friday, June 21, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያን ተግባራዊ ለማድረግ አሥር ቢሊዮን ዶላር ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአገሪቱ ጠቅላላ ዕዳ 52.2 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል

መንግሥት ዕዳ ለማቃለል እንዲሠራ ተጠይቋል

ኢትዮጵያ በሦስት ዓመታት ውስጥ ተግባራዊ እንዲሆን ይፋ ያደረገችው አገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ ከለጋሾች የአሥር ቢሊዮን ዶላር ድጋፍን እንደሚሻ፣ የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን ዋና ጸሐፊ ቬራ ሶንግዌ አስታወቁ፡፡ ዋና ጸሐፊዋ ይኼንን ያሉት በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዳራሽ ማሻሻያውን በማስመልከት ከለጋሾችና ከተለያዩ አገሮች ተወካዮች ጋር በተደረገ ውይይት ላይ ነው፡፡

ኢትዮጵያ የያዘችው ዕቅድ የተለጠጠ ቢሆንም ሊሳካ የሚችል መሆኑ ከአሁን ቀደም በቻይናና በቬትናም ከታዩ ተሞክሮዎች ማወቅ ይቻላል ያሉት ዋና ጸሐፊዋ፣ ኢትዮጵያ ግን የመካከለኛ ገቢ አገሮች ተርታ ለመሠለፍ በየዓመቱ የስድስት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንት ዕድገት፣ እንዲሁም የመንግሥት ገቢ ከአጠቃላይ አገራዊ ምርት እስከ 20 በመቶ ድረስ እንዲያድግ ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ወደ መካከለኛ ገቢ አገር በሚደረግ ጉዞ ይኼ ነው የሚባል ቀጥተኛ የዕድገት መንገድ እንደሌለ በመጠቆም፣ የኢትዮጵያ ብድር እያደገ ስለሚሄድ ያንን መቆጣጠርና ከመክፈል አቅም ጋር ማጣጣም እንደሚያስፈልግም አስረድተዋል፡፡

መንግሥት ጥብቅና ማዕከላዊ የሆነ የበጀት ፖሊሲ በመከተል ገቢው ከጠቅላላ አገራዊ ሀብቱ ከ12 እስከ 20 በመቶ ማደግ እንደሚችል በመግለጽ፣ መዋቅራዊ ማሻሻያዎችን ማድረግ ደግሞ ለታቀደው የሁለት ሚሊዮን የሥራ ዕድል ፈጠራ እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያን የነፍስ ወከፍ ጠቅላላ አገራዊ ምርት በሁለት ወይም በሦስት እጥፍ ማሳደግ እንደሚቻል የጠቆሙት ሶንግዌ፣ የሪፎርም አጀንዳው አፈጻጸምና በፍጥነቱ መቀጠል ለስኬቱ ወሳኝ ናቸው ብለዋል፡፡

ነገር ግን ለጋሾችም ሆኑ ኢንቨስተሮች ወደ አገሪቱ እንዲሳቡ፣ በተለይ በንግድ እንቅስቃሴ ማነቆዎች ላይና በፋይናንስ ዘርፉ ማሻሻያዎች ላይ ትኩረት በማድረግ ፈጣን ድሎችን ማስመዝገብ ያስፈልጋል ሲሉም አክለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የውጭ የብድር ዕዳዋን መቆጣጠር እንዳለባት፣ የውጭ ዕዳዋ አሁን ባለበት ሁኔታ ከቀጠለ ዕዳዋ ጭንቀት ውስጥ ይከታታል ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያ ዕዳዋን ለማቃለል መሥራት ይኖርባታል ብለው፣ በብዙ አገሮችም እንደተሠራበት አስታውቀዋል፡፡ አገሮች ኢኮኖሚያቸውን ከምንም ተነስተው መገንባት መቻላቸውንም ጠቁመዋል፡፡

በዓለም ባንክ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ካሮሊን ተርክ በበኩላቸው የኢትዮጵያን መንግሥት ለግልጽነቱና ለዕቅዱ አመሥግነውና አድንቀው፣ ዕቅዱ ይሳካል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል፡፡ የማሻሻያውን ዋና ዋና ምሰሶዎች በተመለከተ ከመንግሥት ጋር ተመሳሳይ ዕይታ እንዳላቸው በመግለጽና ለድጋፍ እንዲያመች የበለጠ ዘርዘር ያለ ዕቅድ ተሠርቶ እንዲቀርብላቸው በመጠየቅ፣ መንግሥት መረጃ አያያዝና ቁጥር ነክ መረጃዎች ላይ ከፍተኛ ትኩረት በማድረግ ሪፎርሙን ለመደገፍ እንዲያውል አሳስበዋል፡፡

የዓለም የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) የኢትዮጵያ ተወካይ ጁልስ ሌቸር በበኩላቸው ማሻሻያው ችግሮችን በመለየትና ነቅሶ በማውጣት ረገድ እንደተሳካለት በመጠቆም፣ ትልቁ ትኩረት ግን ተቋማት ላይ ተሰጥቶ መሥራት እንደሆነ አሳስበዋል፡፡ ወደ ቀደመው የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባት ላለመመለስም አስፈላጊ የሆኑ ዕርምጃዎች መወሰድ አለባቸው ያሉት ሌቸር፣ የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር ጥብቅ የገንዘብ ፖሊሲ መተግበር ግድ ይላል ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ከእያንዳንዱ የማሻሻያ ዕቅድ ምን ያህል ገቢ ለማግኘት አቅዷል? እንዲሁም ለዋጋ ንረትና የዕዳ ጫና የታቀዱ ዝርዝር ግቦች ምንድናቸው? ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በስዊድን ኤምባሲ የባለ ብዙ ወገን ግንኙነት የልማት ድጋፍ ትብብር ክፍል ኃላፊ አኒካ ጃያዋርዴና የኢኮኖሚ ሪፎርም ሲሠራ ለብቻው ሳይሆን ከሌሎች ዘርፎች ጋር መቀናጀት እንዳለበት በመጠቆም፣ የግል ዘርፉ ተሳትፎ ላይ ማተኮር የሕዝብን ተጠቀሚነት ያመጣልም ሲሉ ጠቁመዋል፡፡

እንደ ጃያዋርዴና ገለጻ ለጋሾች የተግባር ነጥቦችን፣ አመለካከቶችን፣ እንዲሁም ዕቅዶቹ አገሪቱን የት ሊያደርሱ እንደሚችሉ አቅጣጫ ተቀምጦ ማየት ይፈልጋሉ ብለዋል፡፡ መንግሥት ዕቅዱን በዝርዝር እንዲያስቀምጥም ጠይቀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም መንግሥት ተከታታይና መጠነኛ ጥናቶችን በማድረግ፣ የለውጦችን ሒደት ዓይቶ ማሻሻያ ካስፈለገም በድጋሚ ለማስተካከል መዘጋጀት አለበት ሲሉም አሳስበዋል፡፡

መድረኩን በንግግር የከፈቱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ዓመት ውስጥ በተደረጉ ለውጦች በርካታ ነገሮችን መለወጣቸውን በመጠቆም፣ እ.ኤ.አ. በ2030 ኢትዮጵያን የአፍሪካ ልማት ምልክት ለማድረግ እንደሚሠራ ገልጸዋል፡፡ ቀጣዩ የኢትዮጵያ የዕድገት ምዕራፍም የግል ዘርፉን ተሳትፎ በእጅጉ ያስተናግዳል በማለት፣ ‹‹ይኼ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ለልቤ ቅርብ ነው፤›› ሲሉ አስምረውበታል፡፡

ኢኮኖሚው በሚችለው አቅም መጠን እንዲያድግ የእሳቸው አስተዳደር ያለ ድካም እየሠራ እንደሚገኝ በመግለጽ በሥራ ፈጠራ፣ በዕድገትና ዕድሎችን በማመቻቸት ላይ ያተኮረ ኢኮኖሚ እንደሚገነባም ገልጸዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ እንደሚያሳየው እ.ኤ.አ. እስከ መጋቢት ወር 2019 ድረስ የአገሪቱ ጠቅላላ የብድር ዕዳ 52.27 ቢሊዮን ዶላር ነው፡፡ ከዚህ ዕዳ ውስጥ 26.93 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ዕዳ ነው፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ባደረጉት ገለጻ የአገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት የሚፈታተኑት የዕዳ ጫና፣ የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዋጋ ግሽበት ናቸው፡፡ ነገር ግን ከፊት ለፊት ያሉትን ግዙፍ ተራራዎች ገለል ማድረግ እንደሚቻል ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያ ኢኮኖሚዋን ክፍት በማድረግ ዋነኛ የሚባሉ ዘርፎችን ፕራይቬታይዝ በማድረግ የመንግሥትን ሞኖፖሊ ከቴሌ ዘርፍ ታስወግዳለች ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች