Thursday, December 7, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ከ1924-2019

ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ከ1924-2019

ቀን:

እኚህ ሰው ከአልገዛም ባይነታቸውና ፖለቲከኛነታቸው ጎን ለጎን በንግግራቸው ሁሉ ጣል በሚያርጉት ቀልድ አዘልና አነጋጋሪ መልዕክት ይታወቃሉ፡፡ በተገኙበት መድረክ ሁሉ ምዕራባውያንን ሳያወግዙ የቀሩበት ጊዜ የለም፡፡ ሁሌም የመገናኛ ብዙኃንን ትኩረት የሚስቡት የቀድሞው የዚምባቡዌ ፕሬዚዳንት ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ፣ እንደ ጥቅስ ተከትበው በቀሩ ንግግሮቻቸውም የሚታወሱ ናቸው፡፡ በተለይ ለነጮች ባላቸው አሉታዊ አመለካከትም ይታወቃሉ፡፡ በአገራቸው ብቻ ሳይሆን በአፍሪካ ለሚታየው ሥር የሰደደ ድህነት የነጮች ሸፍጥ አለበት ሲሉም በተደጋጋሚ ተደምጠዋል፡፡

ዚምባቡዌ ከብሪታንያ አገዛዝ ነፃ ከወጣችበት እ.ኤ.አ. ከ1980 ጀምሮ እስከ 2017 ድረስ አገሪቱን የመሩት ሙጋቤ፣ ጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸውን የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ኤመርሰን ማናንጋጋዋ አስታውቀዋል፡፡

‹‹የነፃነት ፈርጥ›› በሚል የሚታወቁት ሙጋቤ፣ የአዲሷ ዚምባቡዌም መሥራች ናቸው፡፡ በሥልጣን ላይ በነበሩበት ዘመን በዓለም ካሉ መሪዎች ሁሉ፣ የዕድሜ ባለፀጋውና አዛውንቱ ሙጋቤ፣ በ95 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ቢለዩም፣ በአብዛኛው የዚምባቡዌ ሕዝብ ዘንድ የሚታወሱ ናቸው፡፡

ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ከ1924-2019

 

የዚምባቡዌ አባት በሚሏቸው ሕዝባቸው ዘንድ ተወዳጅነትን አትርፈዋል፡፡ ሕዝባቸው በሌላ መሪ እንዲመራ ዕድል ባለመስጠታቸው፣ ዚምባቡዌያውያን ከነፃነት በኋላ አብዝተው የሚያውቁት እሳቸውን ነው፡፡ የኋላ ኋላ ተቃዋሚዎች ብቅ ያሉባቸው ሙጋቤ፣ ከሕዝባቸውም የይብቃዎት ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር፡፡ በተለይ 2017 የገጠማቸው ተቃውሞ ሥልጣን እንዲለቁ ምክንያት ሆኗል፡፡

‹‹ሥልጣን የሾመኝ እግዚአብሔር ነው፣ ሥልጣኔን የሚነጥቀኝም እርሱ ብቻ ነው፡፡ ሙቨመንት ፎር ዴሞክራቲክ ቼንጅ (ኤምዲሲ) [በወቅቱ በኔልሰን ቻሚሳ ይመራ የነበረና ሙጋቤን የሚቃወም የፖለቲካ ፓርቲ] ሆነ ብሪታንያ እኔን ከሥልጣን አያወርዱኝም›› በማለት በአገሪቱ የ2008 ምርጫን ለማካሄድ በነበረ ቅስቀሳ ላይ የተናገሩት ሙጋቤ፣ ለሚቃወማቸውም ሆነ ለነጮች ሐሳብ እጅ የሚሰጡ አልነበሩም፡፡

ኢምፔሪያሊስቶች የከፋፈሏት አፍሪካ ወደቀደመ ማንነቷ መመለስ እንዳለባትና የፓን አፍሪካ ውጥን የሚሳካውም ይህ ሲሆን እንደሆነ የሚያምኑት እኚህ ሰው፣ በነጮች ላይ እምነት የላቸውም፡፡ ‹‹አንድን ነጭ የምታምነው ከሞተ ብቻ ነው፣ በነጮች ልብ ውስጥ ፍርሃትን መጫር አለብን፣ ነጮች ዋና ጠላቶቻችን ናቸው፤›› ሲሉም የነጮችን ኢፍትሐዊ አሠራር አበክረው ይቃወሙ ነበር፡፡

ከአወዛጋቢ ግን ጠንካራ መልዕክት አዘል ንግግራቸው ‹‹እኔ የዘመኑ ሂትለር ነኝ፡፡ ይህ ሂትለር አንድ ዓላማ አለው፡፡ ለሕዝቦቹ ፍትሕ፣ ሉዓላዊነት፣ ሕዝቦቹ ከቅኝ ነፃ መውጣታቸው ተቀባይነት እንዲያገኝ፣ ባላቸው ሀብት የመጠቀም መብታቸው እንዲከበር ይፈልጋል፡፡ ይህ ሂትለር ከሆነ እኔ አሥር አጥፍ ሂትለር ልሁን፡፡ እኛ የቆምነው ለሕዝባችን ነው›› ብለው እ.ኤ.አ. በ2003 የተናገሩት ይገኝበታል፡፡ ሙጋቤ በየመድረኩ ስለሕዝባቸው ሳይከራከሩም አላለፉም፡፡

አፍሪካዊነትን የሚያቀነቅኑትና ‹‹ሙጋቤይዝም›› በተባለ ፖሊሲዎቻቸው የሚታወቁት ሙጋቤ፣ አፍሪካን ከቅኝ ግዛት ለማላቀቅ የታገሉ፣ አገራቸውን ከቅኝ ነፃ ለማውጣት በነበራቸው አብዮታዊ ጉዞም በሮዲዥያ (የአሁኗ ዚምባቡዌ) መንግሥት ለእስር የተዳረጉ ነበሩ፡፡  

እ.ኤ.አ. በ1924 በደቡባዊ ሮዲዥያ በምትገኘው ኩታማ ከዝቅተኛ ቤተሰብ ስለመወለዳቸው የታሪክ ማኅደራቸው ያስረዳል፡፡ ታዲያ እኚህ ሰው ትምህርታቸውን በኩታማ ኮሌጀ በኋላም በፎርት ሃሪ ዩኒቨርሲቲ ተምረዋል፡፡ በአገራቸውና በጋና መምህርም ነበሩ፡፡ አገራቸው በብሪታንያ ቅኝ አገዛር መውደቋና አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ነጮች መተዳደሯ ቁጭታቸው ነበር፡፡

አገራቸው ነፃ ትወጣ ዘንድ ‹‹የአፍሪካ ናሽናሊስት ፕሮቴስት››ን የተቀላቀሉት ሙጋቤ፣ ገዥውን መንግሥት የሚያጣጥል ንግርር አድርገዋል በሚልም እ.ኤ.አ. ከ1964 እስከ 1974 ዘብጥያ ወርደው ነበር፡፡

ሮበርት ጋብሬል ሙጋቤ ከ1924-2019

 

ከእሥር ሲፈቱ ሞዛምቢክን ቤቴ በማለት፣ ዛኑ ፕርቲን መሠረቱ፡፡ የሽምቅ ውጊያም ጀመሩ፡፡ ይህ ብሪታንያ ወደስምምነት እንድትመጣ ያደረገ ክስተት ነበር፡፡ ጦርነቱ እንዲያበቃ፣ በ1980ም አጠቃላይ ምርጫ እንዲደረግ የተጫወቱት ሚና በዚምባቡዌ ‹‹የዚምባቡዌ አባት›› አስብሏቸዋል፡፡

በ1980 በተደረገው ምርጫም በሙጋቤ የሚመራው ዛኑ ፒኤፍ ሥልጣኑን ተረከበ፡፡ እሳቸውም ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኑ፡፡ ሁለት የሥልጣን ዘመን ካገለገሉ በኋላ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት ሙጋቤ፣ እ.ኤ.አ. ከ2000 ጀምሮ ነበር ተግዳሮት የገጠማቸው፡፡

በሞርጋን ሻቫንጋሪ የሚመራው ኤምዲሲ ውጤታማ መሆንና፣ በነጮች የእርሻ መሬት ላይ ሙጋቤ የወሰዱት ዕርምጃ፣ ሙጋቤን ያስተቻቸው፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽመዋል ያስባለ ነበር፡፡

ከነጭ አርሶ አደሮች መሬት ቀምተው ለጥቁሮች ከማከፋፈላቸው ባለፈ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት ላይ ዕርምጃ አስወስደዋል መባሉ፣ ምዕራባውያን በዚምባቡዌ ላይ ማዕቀብ እንዲጥሉ ምክንያት ነበር፡፡ ይህም በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ ጠባሳ ጥሏል፡፡

በ2000 በአገሪቱ ከሁለት ሚሊዮን ቶን በላይ በቆሎ የተመረተ ሲሆን፣ ይህ በ2008 ወደ 450 ሺሕ ቶን አሽቆልቁሎ ነበር፡፡ የሙጋቤ የግብርና መሬት ፖሊሲ የአገሪቱን ግብርና እንደጎዳም ይነገራል፡፡

የአገሪቱ ኢኮኖሚ ማሽቆልቆል፣ የዋጋ ግሽበት፣ ከጤና፣ ከትምህርት ጋር የተያያዙ ችግሮች እየተባባሱ የመጡት ከ2008 በኋላ ነው፡፡ በተለይ በአገሪቱ ሙጋቤን የሚቃወም የፖለቲካ ፓርቲ ብቅ ማለቱ፣ ሙጋቤን ከገጠሙ ፈተናዎች ይጠቀሳሉ፡፡ ከተቃዋሚዎቻቸው ጋር ባለመግባባታቸው በሚፈጠሩ ግጭቶች ሰብዓዊ መብት ጥሰት ይፈጸማል በሚልም ይወቀሳሉ፡፡ በሕዝባዊ አመፅና በወታደሩ ጣልቃ ገብነት ከሥልጣን እስከለቀቁበት እስከ 2017 ድረስ አገራቸውን ከመመሥረት ጀምሮ በርካታ አዎንታዊ ለውጦችን ለአገራቸው ያመጡ አብዮታዊ መሪ ነበሩ፡፡

ከመጀመርያ ባለቤታቸው ሳሊ ሙጋቤ አንድ ልጅ ወልደው ባይባረክላቸውም፣ ከሁለተኛ ባለቤታቸው ግሬስ ሙጋቤ ሦስት ወንዶችና አንድ ሴት ልጅ አፍርተዋል፡፡

በአንባቢነታቸውና በትምህርት ጉብዝናቸው የሚታወቁት ሙጋቤ፣ ከለንደን ዩኒቨርሲቲ በኢኮኖሚክስ ማስተርስ፣ በአስተዳደር ዲግሪ እንዲሁም በሕግ ሁለት ዲግሪዎች አግኝተዋል፡፡ ወግ አጥባቂ እንደሆኑ የሚነገርላቸው ሲሆን፣ ለጠላት የማይንበረከኩና አልኮል መጠጥ የማይቀምሱ ነበሩ፡፡

በተለይ ከስድስት ወራት በፊት በገጠማቸው ሕመም ሲንጋፖር ሲታከሙ ቆይተው በተወለዱ በ95 ዓመታቸው ማረፋቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...