Saturday, July 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአዲሱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት መግለጫ ቀመር ተገቢነት እስከምን ድረስ ነው?

አዲሱ የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ውጤት መግለጫ ቀመር ተገቢነት እስከምን ድረስ ነው?

ቀን:

የ2011 ዓ.ም. የኮሌጅ መግቢያ ውጤት ከታወቀበት ሐምሌ መጨረሻ ቀናት ጀምሮ እስካሁን ለአንድ ወር ያህል እንዳወዛገበ ቆይቷል፡፡ ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ለውዝግቡ መቋጫ የሚሆን መግለጫ የአገር አቀፍ የትምህርት ምዘናና ፈተናዎች ኤጀንሲ፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የክልላዊ መንግሥታት ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች በተገኙበት ይፋ አድርጓል፡፡

 በዚህም ለኅብረተሰብ ሳይንስ (Social Science) መስክ ተፈታኞች ጂኦግራፊ፣ ለተፈጥሮ ሳይንስ (Natural Science) መስክ ተፈታኞች ደግሞ የፊዚክስ የትምህርት ዓይነቶች ብቻ በልኬት ሥሌት ውስጥ እንደሚገቡ፣ በመሆኑም ለሁለቱም የሳይንስ መስኮች እንግሊዝኛ፣ ሒሳብና ጠቅላላ ዕውቀት (Scholastic Aptitude Test) የትምህርት ዓይነቶች ይወሰዱና በጠቅላላው ከአራት መቶ (400) ተደምሮ የሚገኘው አዲሱ የውጤት ልኬት ነው፡፡

የመንግሥት የትምህርት አካላቱ በሰጡት መግለጫ ይህ ቀመር ያስፈለገው በሌሎቹ የትምህርት መስኮች የታየው የተጋነነ ውጤት ማስተዋል ነው ቢሉም፣ ይህ ለተፈታኝ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው ምክንያትም ሆነ መልስ የሚሆን አይመስልም፡፡ ከዚህ ይልቅ የተደረገው የውጤት መግለጫ ለውጥ ተፈታኝ ተማሪዎቹ በቀድሞው ሥሌት ያገኙት ነጥብ ከአዲሱ ቀመር ሥሌት ውጤታቸው አንፃር በማነፃፀር የሚያነሱት ጥያቄ ሊኖር እንደሚችል ይገመታል፡፡ ይህም ‘አዲሱ ሥሌት ከቀድሞው አንፃር ትርጉም ያለው ተፈታኝ ቁጥር ኮሌጅ የመግባት/አለመግባት የመቀያየር ሁኔታን ይፈጥር ይሆን?’ የሚል እንደሚሆን ጥርጥር የለውም፡፡ ነገር ግን ለዚህ እርግጠኛ መልስ ለማፈላለግ ቢያንስ የሁሉም ተፈታኞች ውጤትን ማወቅ ይጠይቃል፡፡

ይሁንና በግርድፉም ቢሆን እያንዳንዱ ተማሪ ከራሱ አንፃር በአዲሱ ሥሌት (ከ400 የታረመው ለማለት ነው) እና በቀደመው ሥሌት (ከ700 የታረመው ለማለት ነው) መሠረት የሚኖርን የውጤት ልዩነት በማየት ተቀራራቢ መልስ ማግኘት ይችላል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ይህም ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸው ከአዲሱ አንፃር አቻ ግምት በመቀመር ነው፡፡

ለዚህ ቀመር የሥነ ልኬት (Measurement) ባለሙያዎች የራሳቸው ስታትስቲካዊ ሥሌት እንደሚኖራቸው ዕሙን ነው፡፡ በዚህ መጣጥፍ ከላይ የተነሳው ጉዳይ ምላሽ የሚያገኝበት፣ ቤት ያፈራውን ቀመር ለመጠቆም እሞክራለሁ፡፡

ተፈታኝ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው በዚህ ወቅት ሊኖሩበት የሚችለውን ውጥረት (Tension) በመገመት፣ ይህ አጭር ጽ ለሚከተሉት ጥያቄዎች መልስ ያፈላልጋል፡፡

  1. ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸው ከአዲሱ ቀመር ሥሌት ውጤታቸው አንር የሚኖረው አቻ ግምት ምን ያህል ነው?
  2. አዲሱ ቀመር የተማሪዎችን ውጤት ምን ያህል ይቀይረዋል?
  3. በአዲሱ ሥሌት መሠረት የኮሌጅ የመግቢያ መቁረጫ ነጥብን መገመት ይቻላል?

አንባቢያንም ሆኑ ተፈታኝ ተማሪዎች ልብ ሊሉት የሚገባ ነገር……

በቅድሚያ አንባቢያን እንዲገነዘቡት የምፈለገው ከዚህ በታች በጽሑፌ ያስቀመጥኩት ግርድፍ ሒሳባዊ ሥሌት እንጂ ስታስቲካዊ አይደለም፡፡ የተሻለ እርግጠኝነት ያለው ሥሌት በስታትስቲካዊ መሣሪያ (Statistical Tool) ይገኛል፡፡ ይህ ሲባል ግን ሒሳባዊ ስሌቱ (Mathematical Result) ከስታትስቲካዊ ስሌቱ እምብዛም ይርቃል ማለት አይደለም፡፡

ተማሪዎች ሊገነዘቡ የሚገባው ነገር የፈተናውን ጉዳይ ፖለቲካዊ ቅርፅ ሰጥተው ድብቅ የፖለቲካ አጀንዳቸውን ለማሳካት የሚጥሩ አካላት (ቡድኖች) ሊኖሩ እንደሚችሉ አውቀው፣ የፖለቲካ መጠቀሚያ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የፈተና ውጤት መግለጫ ቀመር መለየቱ ውጤታቸው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ አምጥቷል ወይ የሚለው ቁልፍ ጉዳይ ይዘው በምክንያት መመርመር ነው ያለባቸው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማም ተማሪዎች ይህን ግንዛቤ ወስደው ነገሩን በምክንያት እንዲመረምሩ መነሻ ይሆን ዘንድ ነው፡፡

ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸው ከአዲሱ ቀመር ሥሌት አንፃር የሚኖረው አቻ ውጤት ምን ያህል ነው?

ለዚህ ጥያቄ መልስ ለማግኘት የቀደመው ውጤታቸውን ወደ አራት መቶ መቀየር አለባቸው፡፡ ለዚህም የመቀየሪያ ክፋይ (Conversion Factor) 400/700 (0.5714) ነው፡፡ በመሆኑም ተማሪዎች የቀደመው ውጤታቸውን በ0.571 ማብዛት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ቀድሞ ከ700 በታረመው መሠረት 356 ውጤት ያስመዘገበ ተማሪ ከ400 የታረመው አቻ ውጤት (Equivalent Result) 203 ገደማ ነው፡፡

በመሆኑም ሰባቱም ትምህርቶች ቢያዙ ወይም በአዲሱ ውጤት አለካክ ልዩነቱ ምን ያህል ነው? አዲሱ ቀመር ያገኙት ውጤት ታሳቢ የሚሆነው ከላይ የተገለጹት የአራት ትምህርቶች ውጤት ድምር ከአቻ ውጤት ውጤት አንፃር የቁጥር (Absolute) ልዩነት ወይም ፐርሰንታዊ (percentile) ልዩነት ማሥላት ይችላሉ፡፡

አዲሱ ቀመር የተማሪዎችን ውጤት ምን ያህል ይቀይረዋል?

ለምሳሌ ከ700 በታረመው መሠረት 356 ውጤት ያመጣ/ች ተማሪ አዲሱ ቀመር ውጤቱን ምን ያህል ቀይሮታል? ለሚለው መልሱ፣ በቅድሚያ ከአራት መቶ (400) የታረመው አቻ ውጤት (Equivalent Result) ማግኘት፡፡ ለዚህ ደግሞ 356 በ0.571 ማብዛት፡፡ ውጤቱም 203 ገደማ ይሆናል፡፡

እንበልና ይህ/ች ተማሪ በአዲሱ ልኬት መሠረት በአራቱም የትምህርት ዓይነቶች ያስመዘገበው 196 ነው፡፡ ስለዚህ አዲሱ ልኬት ከአቻ ውጤቱ አንፃር ያለው የውጤት ልዩነት (በፐርሰንት) ሲሰላ -3.5 በመቶ ነው። በመሆኑም ይህ ተማሪ አዲሱ ውጤት አለካክከ ቀደመው አለካክ አንፃር ውጤቱን በ3.5 ፐርሰንት ቀንሶታል ማለት ነው፡፡

አዲሱን የውጤት መግለጫ ቀመር መሠረት በማድረግ የኮሌጅ መግቢያ መቁረጫ ነጥብን መገመት ይቻላል?

በመሠረቱ ለዚህ ጥያቄ የቀደመው አለካክ ሥሌትም እንኳን መልስ የለውም፡፡ መልሱ ከአጠቃላይ የተማሪዎች ውጤትና ከዩኒቨርሲቲ የመቀበል አቅም አንፃር ይወሰናል፡፡ ለአንዳንድ ተፈታኞች (ለሴቶች፣ በታዳጊ ክልል ለተፈተኑ፣ ለአካል ጉዳተኛ ተማሪዎች) የሚሰጥ ልዩ ድጋፍም ታሳቢ ይደረግ፡፡ ስለዚህ እርግጠኛ መልስ መስጠት አይቻልም፡፡

ነገር ግን እንደ አጠቃላይ የኮሌጅ ቅበላ ዝቅተኛ ነጥብ (ይህ በመንግሥት ድጎማ በዩኒቨርሲቲ የሚማሩትን ማለት አይደለም) ግምታዊ ሥሌት ለመስጠት እንችል ይሆናል፡፡ ለምሳሌ አምና በነበረው የኮሌጅ የቅበላ ዝቅተኛ ነጥብ (ከ700) 295 ነበር፡፡ ይህ ከዘንድሮው ሥሌት አንፃር አቻ ግምቱ ምን ያህል ይሆናል ብለን ብንጠይቅ መልሱ 295 በ0.5714 በማብዛት የምናገኘው ውጤት ነው፡፡ ይህም 169 ገደማ ይሆናል፡፡ የዘንድሮ የኮሌጅ የቅበላ ዝቅተኛ ነጥብ በቀደመው አለካክ (ከ700 በሚታረም) 300 ቢሆን፣ በአዲሱ የውጤት መግለጫ መሠረት የሚኖር አቻ ውጤት 171 ገደማ ነው ማለት ነው፡፡

በመጨረሻም ተፈታኝ ተማሪዎችና ወላጆቻቸው መልካሙን እንዲገጥማቸው ምኞቴ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፦ ጸሐፊው በጅግጅጋ ዩኒቨርስቲ የኢኮኖሚክስ ረዳት ፕሮፌሰር ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን በኢሜይል አድራሻዎቻቸው [email protected] ወይም [email protected] ማግኘት ይችላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የሰብዓዊ መብት ጉዳይና የመንግሥት አቋም

ሰኔ ወር አጋማሽ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ከፍተኛ የሰብዓዊ...

ከሰሜኑ ጦርነት አገግሞ በሁለት እግሩ ለመቆምና ወደ ባንክነት ለመሸጋገር የተለመው ደደቢት ማክሮ ፋይናንስ

በኢትዮጵያ የፋይናንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ በቀዳሚነት ስማቸው ከሚጠቀሱት ውስጥ ደደቢት...