Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርችግራችንን ለመፍታት ከፖለቲከኞች የተቃረመ አጀንዳ አንከተል

ችግራችንን ለመፍታት ከፖለቲከኞች የተቃረመ አጀንዳ አንከተል

ቀን:

በእስክንድር መርሐ ፅድቅ

ተወልጄ ያደግሁት ኦሮሚያ ውስጥ በመሆኑ ከኦሮምኛ ውጪ ሌላ ቋንቋ የማያውቁ በርካታ ወገኖቻችን በማያውቁት ቋንቋ ሲሰበክላቸው፣ ሲቀደስላቸው ወይም ሲፀለይላቸው እንደነበር አውቃለሁ፡፡ ይህን የተገነዘቡ እንደ ባሌው ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሰላማ (ነፍሳቸውን ይማረውና) እና ማኅበረ ቅዱሳን ያሉ ተቆርቋሪዎች ሥርዓቱን ከፖለቲካ ጋር ሳይለውሱ ብዙ መንገድ እንዳስኬዱት ማንም ሳይነግረን ራሳችን እናውቃለን፡፡ ያን አካሄድ የሕግ ድጋፍ አስይዞ ለማራመድ ጠቅላይ ቤተ ክህነት የጀመረው ነገር ቢኖርም፣ የሚፈለገውን ያህል እንዳልሄደ ደግሞ ሰሞኑን ‹‹የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ይቋቋም›› ባዮች ነግረውናል፡፡

‹‹በቋንቋው ይቀደስለት›› ‹‹በቋንቋው ይፀለይለት›› ‹‹በቋንቋው ይተዳደር›› ‹‹በቋንቋው ይሰበክለት›› ጥያቄ ጤነኛና ለኦሮሞው ብቻ ሳይሆን ለጋምቤላውም፣ ለትግራዩም፣ ለጉራጌውም፣ ለሁሉም የሚጠቅም ነው፡፡ ጎጂ የሚሆነው ግን የሰለቸንና ያላኗኗረን ፖለቲካ ሲገባበት ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በቋንቋ የተዋቀረ ፌዴራሊዝም እያወዛገበ ባለበት፣ አከላለል በብሔር መሆኑ፣ እያናከሰንና እያሳደደን በሚገኝበት፣ መፍትሔው በቅን መሪዎች ሲበጅ ጥላቻን ያነገቡ አቻዎቻቸው እየበጠበጡ ውጤቱን ያዘገዩበት ሁኔታ ባልጠራበት የቤተ ክርስቲያን ወገኖች መንግሥትን መካሪ ሆነው መቅረብና ስለሰላም መፀለይ ሲገባቸው፣ ከፋፋይ ፖለቲካ ቋንቋን ከተገቢው ጥያቄ ጋር መለወሳቸው አንገትን ያስደፋል፡፡ ቂምንና የራስ ስሜትን ያረገዘው አካሄድ ‹‹እንትን ተባልክ›› ‹‹ባህልህና ወግህን አራከሱብህ›› ወዘተ. በሚሉ አነሳሽ መልዕክቶች መታጀቡ በፖለቲካው ጉዞ ተጫርሶ ለተረፈው ዜጋ ሌላ የሞት ድግስ ማዘጋጀት ነው፡፡

እስካሁን ከዘራፊ ጋር ሲዘርፉ ታግሰናል፣ ከትዕቢተኞች ጋር ሆነው የተበደለ ደሃን ሲንቁና ሲያስንቁ ዝም ብለናል፣ ቤተ ክርስቲያንን ሲያራቁቱ ‹‹የሾመ አምላክ የእጃቸውን ይስጣቸው›› ብለን ዘመናትን ተሸክመናቸዋል፡፡ አሥርቱን ትዕዛዛት እንዳይጣሱ ከማስተማር ይልቅ ራሳቸው እየጣሱ አስተማሪ ሲያስፈልጋቸው እንዳላየ አልፈናቸዋል፡፡ የአሁኑ ግን ጫን ያለው ነውና ቤተ ክህነት አካባቢ የሚገኙ የነዚህ ርኩሰት አራማጆች አደብ ቢገዙ መልካም ነው፡፡ ምክንያቱም ዛሬ በአገርም፣ በቤተ ክርስቲያንም ላይ ለመጣው የጥፋትና የመከፋፈል ደመና ከዋነኞቹ ተጠያቂዎች አንዱ ናቸውና!

ይልቁንስ አስፈላጊም ከሆነ ሌላ ሲኖዶስና ቤተ ክህነት ማቋቋም ትናንት በቤተ ክርስቲያን ፍርፋሪ አድገው ዛሬ ሙልጭ ያሉ ሌቦች ለሆኑት ለአዲስ አበባና ዙሪያዋ ሌባ ‹‹አገልጋዮች›› ነው፡፡ ካስፈለገ ቤተ ክህነትስ መቋቋም የሚገባው የአዲስ አበባና ዙሪያዋና የሌብነትና የዘረኝነት ሩጫ ልምድን እንደ መልካም ተግባር ቀስመው ቤተ ክርስቲያናችንን የሰውም ሆነ የገንዘብ ደሃ እያደረጓት ላሉ ከተሞች ‹‹አገልጋዮች›› ነው፡፡

የዛሬ 16 ዓመት ቤንሻንጉል ጉምዝ በነበርኩበት ጊዜ የማኅበረ ቅዱሳን ወጣቶች የጉምዝ ልጆችን ሰብስበው ወንጌልን በቋንቋቸው ሲያስተምሩ፣ በተደጋጋሚ አይቻለሁ፡፡ ያንን አጠናክሮ መጓዝ ከአናት ያሉት ቁልፍ የሃይማኖቱ መሪዎች ተግባር ቢሆንም፣ በጥቃቅን ስህተቶች ማኅበሩን ማዋከብና የራሳቸውን ኪስ ለማድለብ ዝርፊያ ላይ በማትኮራቸው ይኸው በቀዳዳችን የገቡ የቤቷ ልጆች ምንም እንኳ በቋንቋ መገልገል መብት ቢሆንም፣ ካድሬያዊ አቀራረብና ይዘት አንግበው እንዲነሱ አደረሷቸው፡፡

አካሄዱ ምናልባትም የፖለቲካ እንቅስቃሴው ያልሆነላቸው ሰዎች ግፊት እንዳለው የሚያስጠረጥረን የገለጹባቸው መንገዶችና የተጠቀሙባቸው ሚዲያዎች ሚዛን የጎደለው አቀራረብም ነው፡፡ ከዚህ ሌላ ከፖለቲከኞቻችን በቀላወጡትና እነርሱም አብረው ሲያቦኩት በነበረው አካሄድ ያሰቡት ካልተሳካ ቤተ ክርስቲያን ትልቅ ቀውስ ውስጥ እንደምትገባና እንደምትከፋፈል የተነገረን ማስፈራሪያም ተጨማሪ ነው፡፡ ይህ አካሄድ አይደለም ኦሮሞን ከአማራውና ከሌላውም፣ እርስ በርሱም ሊያጋጨው ይችላልና ሰከን ተብሎ ቢታሰብበት፡፡

አለመታደል ሆኖ እንጂ እኛ ብንስማማ እነ / ዓብይ ያቀራረቡት ሲኖዶስ ተግባር በእኛው አባቶች ቢካሄድ መልካም ነበር፡፡ ከዚህም በላይ ደግሞ እሳትና ጭድ የሆኑትን ፖለቲካ ድርጅቶች መክሮ ማስማማትም የሃይማኖት መሪዎች ሚና ነበር፡፡ የተገላቢጦሽ ነገር ሆኖ አስታራቂው ማስታረቅ ባለበት ወገን ተሸመገለ፡፡ ለዚህም ዘመቻ የእነ ዶ/ ዓብይ ሽምግልናም ተፈለገ፡፡ ይህ ለሃይማኖት መሪዎቻችን ሞት ነው፡፡ እነሱ ሞተው እኛም አንገታችንን እንድንደፋ አደረጉን፡፡ ሞትነቱ እነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ማስማማታቸው ሳይሆን ልጅ አባቱን የሚያስታርቅበት የሚና ማሊያውን መለዋወጥ ነው፡፡

አሁን ለእኛ የሚያስፈልጉን ለእስልምና ሃይማኖት አንድነት በመትጋት ስማቸው ጎልቶ የሚመሰገኑት ተቀዳሚ ሙፍቲ ሀጂ ዑመር እንድሪስና በምርጫ 97 ወቅት አምባገነኖች እንደ ልባቸው ሲጋልቡ፣ ‹‹እኛም መንግሥት መንግሥት አንሽተት፣ እናንተም ዕጣን ዕጣን አትሽተቱ!›› ብለው ያወገዙትን የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያን መሪ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ዓይነት አባቶች እንጂ፣ ከፖለቲካው የተረፈውን ፍርፋሪ የሚመግቡንንና በሙዳየ ምፅዋት ግልበጣ በመካን የሚዘርፉንን አይደለም፡፡

በመጨረሻም አንድ ነገር ላሳስብ፡፡ የሰሞኑን ጥያቄ ያነሱትን ወገኖች መዘርጠጥና ማዋረድ አይገባም፡፡ ተገቢው ነገር ከፖለቲካው ጋር ተለውሶ የቀረበውን አንጥሮ በመለየት ምዕመናን የሚቸገሩበትን ችግር ሐሳቡ ላይ ብቻ በማትኮር መቅረፍ ነው፡፡ የሰው ልጅ እሱ ሲነካ ብቻ የሌሎችን በደል መሣሪያ በማድረግ የስሜቱ አጃቢ ለማድረግ የሚማስን ቢሆንም ‹‹ማን አመጣው?›› ትተን በጨዋነት ለመፍትሔው በፀሎትም፣ በተግባርም እንትጋ፡፡ ከዚህ ጋር ደግሞ የጉዳዩ ባለቤቶችን በስፋት ማወያየት ይገባል፡፡ እነዚህን መንገዶች ስንከተል ከፖለቲከኞቹ የተቃረመን አጀንዳ ሳንከተል መሆን አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

‹‹በየቦታው ምርት እየገዙ የሚያከማቹ ከበርቴ ገበሬዎች ተፈጥረዋል››

አቶ ኡስማን ስሩር፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር...

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...