በቁምላቸው አበበ ይማም
ከማይረሱና አስደሳች የሕይወት አንጓዎች አንዱ ለዓመታት የደከሙበትን ትምህርት አጠናቆ ጋዋን ለብሶ ለምረቃ ከተደበላለቀ ስሜትና የሐሳብ ዥዋዥዌ ጋር አዳራሽ መገኘት ነው፡፡ ከዚያም የዕለቱን የክብር እንግዳዎችና ተናጋሪ በጉጉት መጠበቅ፡፡ የፕሪስተን ዩኒቨርሲቲ የምሁራን ታሪከ ፕሮፌሰር አንተኒ ግራፍተን በዩኒቨርሲቲ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ ተናጋሪ መጋበዝ የቆየ ልማድ እንደሆነ ይነግሩንና ተናጋሪዎች ግን፣ እንደ ዛሬው የአገር መሪዎችና ታዋቂ ሰዎች የሚበዙበት እንዳልነበር ያስታውሱናል፡፡ የንግግር ክህሎታቸው ከፍ ያለ አንደበተ ርዕቱ ተማሪዎችም ይጋበዙ እንደነበር ታሪካዊ ሰነዶችን ዋቢ አድርገው ይናገራሉ፡፡ የምረቃ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር አድራጊ እንግዳ መጋበዝ ከዩኒቨርስቲዎች የኋላ ታሪክ ጋር አብሮ የሚወሳ ቢሆንም፣ ዝናው በአለማችን በተናኘው የአሜሪካ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ በክብር እንግድነት ተጋብዘው ለመጀመሪየ ጊዜ እ.ኤ.አ በ1642 ንግግር ያደረጉት የዚያን ጊዜው የማሳቹሴትስ ገዥ ጆን ዊንትሮፕ ነበሩ፡፡
ወደ አገራችን ስንመጣ ግርማዊነታቸው፣ ፕሬዚዳንት መንግሥቱ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይና በርካታ ታዋቂ ሰዎች በዩኒቨርሲቲዎች በክብር እንግድነት በመገኘት ንግግር አድርገዋል፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተማሪዎች የምረቃ ሥነ ሥርዓት ላይ በክብር እንግድነት ተገኝተው ለመጀመርያ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ‹‹. . .በየትኛውም ጉዳይ መከራከርና መሟገት የሚጠበቅ ቢሆንም፣ በአገር ሉዓላዊነትና አንድነት ላይ ግን እንዳትደራደሩ፡፡. . . የዛሬ ምሩቃን ከለውጡ ጎን ብትቆሙ በአጭር ጊዜ አገራችንን ወደ ተሻለ ምዕራፍ ማሸጋገር እንችላለን. . .›› ብለዋል፡፡ ከ1985 ዓ.ም. ወዲህ በተለይ ከ1997 ዓ.ም ምርጫ በኋላ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአካዳሚ ነፃነት ተደፍቆ አንድ ለአምስት ጥርነፋና ለኢሕአዴጋውያን ደኅንነቶችና ካድሬዎች መፈንጫና መናኽሪያ በመሆኑ በተጠየቅ፣ በአመክንዮና በአብርሆት የሚሞግት፣ የሚከራከርና የሚጠይቅ ተማሪም መምህርም ማፍራት አልተቻለም ፡፡ በተቃራኒው የአስገድዶ ማጥመቂያ (indoctrination) ሙት ባህር ሆነ፡፡ እንደ ገሊላ ባህር ውኃ (ሕይወት) ማስገባት ማስወጣቱን ትቶ እንደ ሙት ባህር መቀበል ብቻ ሆነ፡፡
የዩኒቨርሲቲው ማኅበረሰብ በተለይ ምሁራንና ተማሪዎች እንደ ሙት ባህር ተቀባይ ብቻ ሆኑ፡፡ በጣት የሚቆጠሩ እንደ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር)፣ መረራ ጉዲና (ፕሮፌሰር)፣ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውና ሌሎች ግን አሻፈረኝ ብለው እስከ መጨረሻው ሰዓት እንደ ገሊላ ባህር ሕይወት ተቀብለው ሕይወት መስጠታቸውን እንደ ቀጠሉበት ሳይዘነጋ፡፡ ለማንኛውም ዩኒቨርሲቲ እስትንፋሱ ማሰብ፣ መጠየቅ፣ መሞገት፣ መከሰት፣ መግለጥ ነውና፡፡ በተቃራኒው ሞቱ ደግሞ እንደ ሙት ባህር የሰጡትን ብቻ ተቀባይ መሆን ነው፡፡ ለውጡ ከባ‘ተ ከአለፈው አንድ ዓመት ከመፈንቅ ወዲህ ግን ይህ የሙት መንፈስ እያፈገፈገ ይመስላል፡፡ አጥጋቢ ባይሆንም ዩኒቨርሲቲዎቻችን በተለይ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በተመረጡ አገራዊ ርዕሰ ጉዳዮች ፈራ ተባ እያለ የውይይት መድረኮችን ማመቻቸት ጀምሯል፡፡ ልሂቃኑም በአደባባይ መሞገትና መጻፍ ጀማምረዋል፡፡ ከቀሩት የመንግሥትም ሆነ የግል ዩኒቨርሲቲዎችም ይህንን ፈለግ መከተል ይጠበቃል፡፡
በአገር ፍቅርና አንድነት ዙሪያ እንዳይደራደሩ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ምሩቃኑን አደራ ማለታቸው ይታወሳል፡፡ በገደምዳሜ ለእኛ ጭምር በተላለፈው በዚህ መልዕክት አገር ከዘር፣ ከፓርቲ፣ ከፖለቲካዊ አመለካከት፣ ከህሕይወት ፍልስፍና፣ ወዘተ . በላይ መሆኑን አስገንዝበውናል፡፡ በተጠናቀቀው የትምህርት ዘመን አልፎ አልፎ፣ ካች አምናና ከዚያ በፊት ደግሞ በተደጋጋሚ በዩኒቨርሲቲዎች ታውኮና ደፍርሶ የነበረው ሰላም መነሻው ከአገር ይልቅ ማንነትን ተገን አድርጎ በተጎነጎነ የሴራ ፖለቲካ መሆኑን ያስታውሷል፡፡ ዛሬም የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የለውጥ አጀንዳ የራስ ምታት ለአገራችንም የጎን ውጋት ይኼው የማንነት የዘውግ ፖለቲካ ሆኖ ዘልቋል፡፡ የዚህ በሽታ መድኃኒቱ ከማንነት ኢትዮጵያዊነትን ከጎጠኝነት አገርን ማስቀደም ነው፡፡
ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የምረቃ ሥነ ሥርዓት ንግግር በመግቢያዬ ላይ ከተዋስኋቸው ዓበይት መልዕክቶች ስለዩኒቨርሲቲዎቻችን ጠያቂና ሞጋች መሆን አስፈላጊነት ይቺን ታህል ካልኩ፣ ወደ ሁለተኛው መልዕክትና አገራዊ ጥሪን አጣምሮ ወደ ያዘው ሐሳብ ልለፍ፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ9,637 የመጀመሪያ፣ የሁለተኛና የዶክትሬት ምሩቃን ያስተላለፉት፣ ነገር ግን በወቅቱ ብዙ ትኩረትና ቀልብ ያልገዛው ትልቁ መልዕክት ምሩቃኑ በሙሉ ከጎናቸው ለውጡን ደግፈው ቢቆሙ ተዓምር መሥራት እንደሚቻል ያስተላለፉት ጥሪ ነው፡፡ ጥሪው ከተደረገበት ቦታ ዓውድ አንፃር ለምሩቃኑ ብቻ የተደረገ ቢመስልም፣ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ የተደረገ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ለመላ ኢትዮጵያውያን ያቀረበችው የድረሱልኝ ጥሪ፡፡ ዘመኑን፣ ትውልዱን ለመዋጀት የቀረበ ጥሪ፡፡ የማስጠንቀቂያ ደወል ጭምር፡፡ ለውጡን ለመታደግ የቀረበ የተማፅኖ ጥሪ፡፡
አገራችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ልጆቿን ለዘላቂ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት፣ ለፍቅር፣ ለዕርቅ፣ ለመቀባበል፣ ለዘላቂ ሰላም፣ ወዘተ . እየተጣራች ነው፡፡ ይህን ጥሪ ተቀብለው እንደ ገደል ማሚቶ ሳይበርዙ ሳይከልሱ ከአፅናፍ አፅናፍ የሚያስተጋቡና የሚያስተላልፉ የቁርጥ ቀን ልጆች ያስፈልጓታል፡፡ ስለለውጡ የሚመሰክሩ ንፁህ፣ ሀቀኛ ምስክሮች ያስፈልጓታል፡፡ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ጥሪ ከአቶ ብርሃነ መስቀል አበበ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለአርትስ ቲቪ “ዓብይ ጉዳይ” ላይ ቀርበው እንዲህ ሲሉ ከተናገሩት፡፡ ‹‹. . .ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር የካቢኔ አባላት በአደባባይ ወጥተው ስለእርሳቸውም ሆነ ስለለውጡ በልበ ሙሉነት የሚመሰክር፣ ጥብቅና የሚቆም፣ የሚሞግት የለም፡፡ ሁሉም የቢሮ ሥራ የሚሠሩ ፋይል ገፊ ናቸው. . .›› ካሉት ጋር መገጣጠም ለጽሑፌ መነሻ እንደሆነኝ መግለጽ እፈልጋለሁ፡፡ ከአገርና ከሕዝብ ጥቅም ይልቅ ፖለቲካዊ ግ‘ባቸውን ከሚያስቀድሙ ፓርቲዎች፣ በማንነት ስም ከሚነግዱ፣ በአክትቪስት ስም ስውር ደባን ከሚለፍፉ ወይም ከነፈሰው ጋር ከሚነፍሱ ልሂቃን፣ ከአስመሳዮች፣ ከአድርባዮች፣ ወዘተ. የተገኘ ቃል አጥንተው የሚመሰክሩ ሐሰተኛ፣ አስመሳይና ዋሾ የተገዙ ምስክሮችን ሳይሆን በዚህ የጭንቅ የጥብ ሰዓት አገራችን ከምንጊዜውም በላይ እውነትን፣ ፍቅርን፣ ዕርቅን፣ ሰላምን፣ ወዘተ. በልባቸውና በግንባራቸው አትመው በአደባባይ የሚመሰክሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ያስፈልጓታል፡፡
በታላቁ መጽሐፍ ዮሐንስ ራዕይ ላይ እንደ ተመለከተው ፈጣሪ ከእስራኤል 12 ነገዶች ከእያንዳንዳቸው 12 ሺሕ፣ 12 ሺሕ በድምሩ 144 ሺሕ ምስክሮችን ያለ ልዩነት እንዳስነሳው ሁሉ፣ በአገራችንም ከአዲሱ ዓመት ጀምሮ ስለአንድነት፣ ስለፍቅር፣ ስለመነጋገር፣ ስለመደማመጥ፣ ስለመቀባበል፣ ስለይቅርታ፣ ስለሰላም፣ ወዘተ. በድፍረትና በልበ ሙሉነት በአደባባይ የሚመሰክሩ የቁርጥ ቀን ልጆች ያስፈልጋሉ፡፡ በአገራችን ምን ያህል ነገዶችና ጎሳዎች እንዳሉ እያንዳንዳቸው ያላቸውን የሕዝብ ብዛትም የሚገልጽ ወቅታዊና ይፋዊ መረጃ ባይኖርም፣ 10 ሺሕና ከዚያ በላይ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ነገዶች፣ ጎሳዎች ቁጥር 50 ቢሆንና ከየእያንዳንዱ ነገድ፣ ጎሳ ለምስክርነት የሚበቁት 10 ሺሕ ዜጎች ቢኖሩ 500 ሺሕ ምስክሮችን ማብቃት ይቻላል ማለት ነው፡፡ የአገራችን የሕዝብ ብዛት 100 ሚሊዮን ነው ብለን በመቶኛ ብናሰላው 0.5 በመቶ ማለት ነው፡፡ እንደ አስፈላጊነቱ ሰፊ የቆዳ ስፋትና ከፍተኛ የሕዝብ ብዛት ያላቸው ነገዶች፣ ጎሳዎች ከፍ ያለ ቁጥር ያላቸውን ምስክሮች ሊጠሩ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ኮሽ ባለ ቁጥር የማይበረግጉ፣ በአክቲቪስት ተብዬዎች ተነሱ ሲባሉ የማይነሱ ተቀመጡ ሲባሉ የማይቀመጡ፣ በዘውጌአዊ ሚዲያዎች ፉከራ ሽለላ ቀረርቶ፣ ወዘተ. ልባቸው የማይሸፍት፣ ንፋስ ሲጎበኘው ደንገላስ እንደሚመታ ሰብል የማይሆኑ፣ የማያወላውሉ፣ “አቧራ በማስነሳት ሳይሆን አሻር በማኖር” የሚያምኑ፣ ወዘተ. አርዓያነት ያላቸው ዜጎች መሆን አለባቸው፡፡
ከእስራኤል ነገዶች የተመረጡ 144 ሺሕ ምስክሮች ለምስክርነት ወደ አደባባይ የተመሙት ልዑል እግዜአብሔር የሰውን ልጅ ከኃጢያት ሊያስተሰርይ የዘላለም ሕይወት ሊሰጥ አንድያ ልጁን እንደሰጠ ስለሰው ልጅ በደል መተላለፋ፣ መሞቱ፣ በሦስተኛው ቀን ከሙታን መነሳቱን ሊመሰክሩ ከሆነ ግማሽ ሚሊዮን የሚሆኑ የእኛ ምስክሮችስ ስለምንድን ነው የሚመሰክሩት? የሚለውን ከማንሳቴ በፊት በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ከሚመራው የለውጥ ኃይል ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ የማይናወጥ አቋም እንዳለው፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ሉዓላዊ አንድነት ላይ ፅኑና የማይናወጥ አቋም እንዳለው የገባውን ቃል ኪዳን በአዲስ ዓመት እንዲያድስ በታላቅ አክብሮት እጠይቃለሁ፡፡ በማስከተል ምስክሮች ያለ ምንም ልዩነት በአንድ ድምፅ በሁሉም የአገራችን መልካዎች፣ መስኮች፣ ሸለቆዎች፣ ኮረብታዎች፣ ተራሮች፣ ቁልቁለቶች፣ ወዘተ. ክቡራንና ክቡራት አንባቢያን በቀጣይ የምታዳብሩት፣ የምትጨምሩበት ሆኖ የለውጥ ሠራዊቱ፣ ምስክሮችና መልዕክተኞች ስለሚከተሉት የጋራ እውነቶች ለመላ ኢትዮጵያውያን እንዲመሰክሩ እንደ አንድ አገር ወዳድ ዜጋ በአክብሮት እለምናለሁ፡፡
አንድ ካለፈው አንድ አመት ከመንፈቅ ወዲህ እውን የሆነው ለውጥ የሚገባንና የሚዋጀን ከመሆኑ ባሻገር፣ ከእነ አባጣ ጎባጣው ወደ ተራራው ወደ ከፍታው የሚያደርሰን ብቸኛና አቋራጭ መንገድ መሆኑን መመስከር፡፡ ሁለት አንድ ዓይነትነት ሳይሆን አንድነት ከልዩነት ይልቅ ለአገራችንና ለሕዝባችን የሚያተርፍ የሚበጅ መሆኑን መመስከር፡፡
ሦስት የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ለዜጎች እኩልነት፣ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ነፃነት፣ ወዘተ. የማዕዘን ድንጋይ እንደሆነና ለሰው ልጆች ተፈጥሮአዊ ስጦታ መሆኑን በልበ ሙሉነት መመስከር፡፡ አራት ሕዝብ በተለይ የነገ አገር ተረካቢ ወጣት የጥላቻ ፕሮፓጋንዳ፣ የሴራ ፖለቲካ፣ የሐሰተኛ መረጃ ሰለባ እንዳይሆን በሰከነ መንፈስ እውነትንና እውነትን እንዲፈትሽ መመስከር፡፡ አምስት ተቀራርቦ በመነጋገር፣ በመደማመጥ፣ በመቀባበል ዕርቅን ሰላምን ማውረድና በፍቅር ስለመሻገር ለወገን መመስከር፡፡
ስድስት ኢትዮጵያዊነት ከዘውግ ከማንነት በላይና የመደመር ዕሳቤ የማዕዘን ድንጋይ መሆኑን መመስከር፡፡ ሰባት ትውልድ የታሪክ እስረኛ ሳይሆን የመጭው ዘመን አብሪ ኮከብ ስለመሆን ራሱን ከወዲሁ ማዘጋጀት እንዳለበት መመስከር፡፡ ስምንት ብልቶቻችን እርስ በእርስ ካልተንሰላሰሉ፣ ካልተናበቡ፣ ካልተጋገዙ ቆመን መሄድ እነሱም ጤነኛ መሆን እንደማይችሉት ሁሉ፣ እኛ በዘመነ ሉላዊነት ካልተደማመርን ይኼንን ፈታኝ ዘመን መሻገር እንደማንችል መመስከር፡፡ ዘጠኝ ዜጎች በተለይ ወጣቶችና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጥያቄ፣ ቅሬታ ሲኖራቸው ነገ እነሱ የሚረከቡትን ሀብት ከማውደም ኢኮኖሚውን ሽባ ከማድረግ ይልቅ፣ ማንኛውንም ጥያቄ በሠለጠነ መንገድ እንዲያቀርቡ መመስከር፡፡
አሥር ልዩነትን በኃይል ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ በዛፍ ጥላ ሥር፣ በጠረጴዛ ዙሪያ በሰላማዊ ውይይት መፍታት ሰው የመሆን መለያ መሆኑን መመስከር፡፡ አሥራ አንድ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ጀግንነት አልሞ በጥይት በፈጣሪ አምሳል የተፈጠረን ሰው ግንባር መፈርከስ ሳይሆን በአመክንዮ፣ በተጠይቅ፣ በአብርሆት፣ ወዘተ. ሞግቶና ተከራክሮ ማሸነፍ መሆኑን መመስከር፡፡ አሥራ ሁለት በዚህ ሙግት የተረታና የተሸነፈ ቢኖር ሐሳቡ እንጂ የሐሳቡ ባለቤት የሆነው ድርጅት አልያም ብሔር አለመሆኑን መመስከር፡፡
ማጠቃለያ
ሦስቱ አብርሃማዊ እምነቶች ማለትም ክርስትና፣ እስልምና እና አይሁድ ከአፅናፍ አፅናፍ ሊስፋፉ ቢሊዮኖች የሚቆጠሩ ተከታዮችን ሊያፈሩ የቻሉት በደቀ መዛሙርት፣ በሐዋርያትና በተከታዮቻቸው ምስክርነት ነው፡፡ የሒንዱ፣ የቡድሀ፣ የሺንዙ፣ የኮንፊሺየስ፣ ወዘተ. እምነቶችና ፍልስፍናዎች ዕድገትም ሆነ ውድቀት ከዚሁ የተለየ አይደለም፡፡ ወደ ፖለቲካው ስንመጣጣም የማህተመ ጋንዲ ሰላማዊ ትግል የእንግሊዝን ቅኝ ገዥ ከህንዳውያን ትከሻ አሽቀንጥሮ መጣል የተቻለው በደቀ መዛሙርታቸው አማካይነት የየአንዳንዱን ህንድ ልብ ማሸነፍ በመቻላቸው ነው፡፡ የኔልሰን ማንዴላ የፀረ አፓርታይድ ትግል፣ የአፍሪካውያን የፀረ ቅኝ ግዛት ተጋድሎ፣ የማርቲን ሉተር ኪንግ የፀረ ዘረኝነት ትግል፣ ወዘተ. ለድል ለፍሬ የበቁት ባፈሯቸው ተከታዮችና ደቀ መዛሙርት በመታገዝ መሆኑ ታሪክ ሰንዶ አቆይቶናል፡፡ የአንደኛውንና የሁለተኛውን የዓለም ጦርነቶችም ሆኑ ሌሎች ጦርነቶች በአሸናፊነት የተደመደሙት ተከታይን አሳምኖ ከጎን በማሠለፍ ነው፡፡ የቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት በምዕራባውያን አሸናፊነት የተጠናቀቀው በተመሳሳይ ምክንያት ነው፡፡
ስለሆነም በአገራችን የተጀመረው ለውጥ ገዥ ሐሳብ እንዲሆን ከፍ ሲልም አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ በለውጡ መሠረታውያን ሐሳቦች ዙሪያ ማለትም በዴሞክራሲ፣ በፍትሕ፣ በእኩልነት፣ በነፃነት፣ በመደመር ጽንሰ ሐሳብ፣ በዕድገትና ብልፅግና፣ በሰብዓዊ መብቶች መከበር፣ በፍቅር፣ በሰላም፣ በዕር፣ በሕግ የበላይነት፣ ወዘተ. ዕልፍ አዕላፍ ተከታዮችንና ምስክሮችን ማፍራት ይገባል፡፡ እነዚህ ተከታዮችን፣ የለውጥ ሠራዊቶችን፣ የለውጥ መልዕክተኞችን፣ ወዘተ. ከጎጥ እስከ ፌደራል ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ይህ አንድን የፖለቲካ ፓርቲ አልያም መሪ ለመደገፍ የሚደረግ እንቅስቀቃሴ ሳይሆን፣ ለውጡ እንዳይቀለበስ በማድረግ የአገርን ህልውና የማስቀጠል ህልም ነው፡፡ ምክንያቱም ይህን ታሪካዊ አጋጣሚ በማስተዋልና በጥበብ ካልተጠቀምንበት ለውጡም ከእጃችን ካመለጠ ዳግመኛ መልሰን እናገኘዋለን ብዬ አላምንም፡፡ ስለሆነም በምንም ሁኔታ ወደ ጨለማው ዘመን ልንመለስ አይገባም፡፡
እዚህም እዚያም በተስተዋሉ የሕግ የበላይነት ክፍተቶች፣ ለውጡን አስመልክቶ ወጥና ከላይ እስከ ታች የሕዝብ ግንኙነትና የአሕዝቦት ሥራ አለመከናወኑ፣ ገዥውን ፓርቲ ጨምሮ አንዳንድ ተቃዋሚዎች የአክራሪ አክቲቪስቶችን ግንባር ከመመልከት አልፈው ተልዕኮ ተቀባይ መሆናቸው፣ የገዥው ፓርቲ አባል ድርጅቶች ለምርጫ ሲሉ ከአገር ይልቅ ክልላዊ አጀንዳን ወደፊት ለማምጣት መሞከራቸውና የሴራ ፖለቲካ በአናቱ ተጨምሮ ለውጡ እንደ አጀማመሩ መራመድ ተስኖታል፡፡ ስለሆነም የለውጡ ባለድርሻ አካለት ከፍ ብለው የተዘረዘሩ ድክመቶችንና ሌሎችን ውስንነቶችን በባለቤትነት በመውሰድ ነገ ዛሬ ሳይሉ በማያዳግም ሁኔታ በመፍታት፣ ለለውጡ ምስክሮች ጥርጊያ መንገድ ሊያዘጋጁ ይገባል፡፡ ወቅቱ አገርን ከውድቀትና ከቀውስ የምንታደግበት እንጂ፣ ውርስና ባለቤትነት የምንሻማበት ስላልሆነ ማንኛውም አግባብነት ያለው የመንግሥት ተቋም ሆነ የግል ድርጅት ይህን ሐሳብ አሻሽሎና አዳብሮ ሊተገብረው እንደሚችል መግለጽ እወዳለሁ፡፡
ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡