Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከ9.1 ቢሊዮን ብር በላይ የአረቦን ገቢ አስመዝግበዋል

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢትዮጵያ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚንቀሳቀሱት 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ከ9.1 ቢሊዮን ብር በላይ የአረቦን ገቢ ያስመዘገቡ መሆኑ ተመለከተ፡፡

በ2011 የሒሳብ ዓመት የአገሪቱን የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ጥቅል ሥራ አፈጻጸም የተመለከቱ መረጃዎች እንዲያመለክቱት፣ 18 የኢንሹራንስ ኩባንያዎች  የሰበሰቡት 9.1 ቢሊዮን ብር የአረቦን ገቢ ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር 8.6 በመቶ ዕድገት የታየበት ነው፡፡ በሒሳብ ዓመቱ 18 ኩባንያዎች ከሰበሰቡት አረቦን ውስጥ መንግሥታዊው የኢትዮጵያ መድን ድርጅት 3.4 ቢሊዮን ብር የሚሆነውን አረቦን በማሰባሰብ ቀዳሚ ሲሆን፣ 17 የግል ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ደግሞ በጥቅል የሰበሰቡት የአረቦን ገቢ 5.7 ቢሊዮን ብር ነው፡፡  

የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ነፃነት ለሜሳ ሰሞኑን የድርጅታቸውን የሥራ አፈጻጸም ተንተርሶ አጠቃላይ የአገሪቱን የመድን ኢንዱስትሪ ቅኝት ባመላከቱበት ሪፖርታቸው እንደጠቀሱት፣ በ2011 የሒሳብ ዓመት ሁሉም የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በጥቅል የአረቦን ገቢ ውስጥ ሕይወት ነክ ካልሆነው የጠቅላላ መድን 8.6 ቢሊዮን ብር አረቦን መሰብሰብ ችለዋል፡፡ 514.3 ሚሊዮን ብር የሚሆነው የተሰበሰበው ደግሞ ከሕይወት መድን ዘርፍ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡

የሕይወት ዘርፍ የመድን ሽፋን ከሌሎች ዓመታት የተሻለ ዕድገት የታየበት መሆኑን ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንድ የኢንሹራንስ ባለሙያ ጠቁመው፣ ነገር ግን አገሪቱ የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ አሁንም በሕይወት የመድን ዘርፍ እያሳየ ያለው አፈጻጸም እጅግ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡

ዘንድሮ ከሕይወት የመድን ዘርፍ የተሰበሰበው የአረቦን ገቢ መጠን የ11.6 በመቶ ዕድገት የታየበት ሲሆን፣ ከዚህ ቀደም ግን የዕድገቱ መጠን በመቶኛ ሲሰላ በ2011 የሒሳብ መት ከተመዘገበው ያነሰ እንደነበር ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡

ይህ ዘርፍ ከጠቅላላው የአገሪቱ የመድን ኢንዱስትሪ ካሰባሰበው አረቦን ውስጥ የሕይወት ኢንሹራንስ ዘርፍ 5.8 በመቶ ድርሻ ይዟል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ መረጃዎች መሠረት ከጠቅላላ የኢንሹራንስ ሽፋን ውስጥ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነው የሕይወት ኢንሹራንስ ነው፡፡ በኢትዮጵያ ግን ይህ በተለየ ሁኔታ በተገላቢጦሽ የሚታይ ሲሆን፣ በሕይወትና ሕይወት ነክ ባልሆነው መካከል ያለው ልዩነት እጅግ የሰፋ ነው፡፡  

የዓለም የመድን ኢንዱስትሪ ከኢትዮጵያ አንፃር ያለው ልዩነት በተለየ መንገድ የሚገለጽ ነው፡፡ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ዋና ሥራ አስፈጻሚ፣ የዓለም የኢንሹራንስ ኢንዱስትሪን ለማመላከት እ.ኤ.አ. የ2018 መረጃን ጠቅሰዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 ዓ.ም. በአጠቃላይ የአረቦን ገቢ 5.2 ትሪሊዮን ዶላር በመድረስ በታሪኩ ከፍተኛ የተባለውን ገቢ ያስመዘገበ ነው ብለዋል፡፡ ይህም ከዓለም ጠቅላላ ኢኮኖሚ ውስጥ ስድስት በመቶ እንዲይዝ ማስቻሉን ጠቁመው፣ ይሁን እንጂ በአጠቃላይ የአረቦን ገቢ ዕድገቱ በቀደመው ዓመት ከነበረው ፍጥነት የተቀዛቀዘ ነበር ብለዋል፡፡  ለዚህም በዋነኛነት የሕይወት ነክ መድን ሽፋኖች ዕድገት መገታት ከፍተኛ ተፅዕኖ ማሳደሩ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በዓለም የመድን ኢንዱስትሪ ውስጥ የሕይወት ነክ የመድን ሽፋኖች ከአጠቅላይ ኢንዱስትሪው 54 በመቶ ድርሻ ሲይዙ፣ ከጠቅላላ መድን ዘርፍ የ46 በመቶ ገቢ እንደማይዙ አቶ ነፃነት አመላክተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት የ2011 ሒሳብ ዓመት የትርፍ መጠኑ ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ ቅናሽ የታየበት ሆኗል፡፡ ድርጅቱ ባለፈው ሳምንት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባዔ የድርጅቱ ዓመታዊ የትርፍ መጠን 854.7 ሚሊዮን ብር መድረሱንና ይህም ከቀዳሚ ዓመት 24 በመቶ ብልጫ ያለው መሆኑን የሚያሳይ ሪፖርቱን ለጋዜጠኞች ማሠራጨቱ ይታወሳል፡፡ ይኼው በድርጅቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ የቀረበው ሪፖርት ከታክስና ከሌሎች ተቀናሾች በፊት የተገኘው ከዕቅዱ ጋር ሲነፃፀር 27.4 በመቶ፣ እንደሁም ካለፈው ዓመት ውጤት ጋር ሲነፃፀር በ24 በመቶ ብልጫ አለው ብሎ ነበር፡፡ ይሁንና ይህ የትርፍ መጠን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ከቀረቡት የ2010 ዓ.ም. ሪፖርት ጋር ሲመሳከር ግን ኩባንያው በጠቀሰው ልክ ትርፉ በ24 በመቶ ባለፈው እንዲሁም የዘንድሮ ትርፍ ከ91 ሚሊዮን ብር በላይ መቀነሱን የሚረጋግጥ ነው፡፡ ባለፈው ዓመት በሥራ አስፈጻሚው በቀረበው ሪፖርት ላይ የኢትዮጵያ መድን ድርጅት ያተረፈው 946.3 ሚሊዮን ብር ነው፡፡ ዘንድሮ ግን ያተረፈው 854.7 ሚሊዮን ብር በመሆኑ የዘንድሮ ትርፉ መቀነሱን ያሳያል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች