አገሪቱን እንደ ማዕበል ሲንጧትና የተለያዩ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ መስተጋብሮችን ሲያስተጓጉሉ ከቆዩት ሰፋፊ ሕዝባዊ ተቃውሞና አመፆች በኋላ፣ በከፍተኛ የሕዝብ ድጋፍ ታጅቦ ወደ ሥልጣን የመጣው የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ዓመት ከመንፈቅ ሊሆነው አንድ ወር ገደማ ብቻ ይቀረዋል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አስተዳደር ከሞላ ጎደል ከዓመት በኋላ በአገሪቱ እየታዩ ለነበሩ ዘርፈ ብዙ ችግሮች መፍትሔ በመሻትና ለዘላቂነታቸውም መንገድ በመቀየስ እንደቆየ በተደጋጋሚ ሲገለጽ ቆይቷል፡፡ የችግሮቹ ቁልፍ መፍትሔ ተቋማትን ማጠንከር እንደሆነ በመገንዘብም ተቋማዊ ማሻሻያዎችን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እስከ መከላከያና ደኅንነት መሥሪያ ቤቶች፣ እንዲሁም የተለያዩ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ድረስ የዘለቁ ተቋማዊ ማሻሻያዎችን እንዳደረገም ተነግሯል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የዴሞክራሲና የፍትሕ ተቋማት ጠንካራ አቋም እንዲኖራቸው ከመዋቅር እስከ ሰው ኃይል ያላቸው አደረጃጀት እንዲሻሻል ጥረት ማድረጉም፣ በመንግሥት እንደ ስኬትና በአንድ ዓመት ውስጥ ይሆናል ቀርቶ ይታሰባል የማይባል ለውጥ እንደተመዘገበ ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
በእነዚህ ለውጦች ሥር ነቀል መፍትሔዎች ተመዝግበዋል ለማለት ባይቻልም፣ በርካቶች ተስፋ እንዲኖራቸውና ለተወሰኑት የአገሪቱ ችግሮች የማስተንፈሻ መላ መዘየዳቸውን አስተያየት ሰጪዎች ይስማማሉ፡፡
ሆኖም የደቡብ ክልል በሥሩ ከሚያስተዳድራቸው ዞኖች መካከል አሥራ አንድ ዞኖች ከክልሉ በመለየት የየራሳቸውን ክልል ለመመሥረት ያነሱት ጥያቄ ምላሽ ሳያገኝ እስካሁን መቆየቱ፣ ለአዲሱ አስተዳደር እንደ ፈተና ሆኖ የቆየ ጉዳይ እንደሆነ ይጠቀሳል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተዳደር ወደ ሥልጣን በመጣ በአራት ወራት ውስጥ የሲዳማ ዞን ምክር ቤት የክልልነት ጥያቄን በሙሉ ድምፅ አፅድቆና ለክልል ምክር ቤት አቅርቦ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕዝበ ውሳኔ እንዲደረግ ከተመራ በኋላ፣ በተከታታይ ተመሳሳይ ጥያቄዎች በዞን ምክር ቤቶች እየፀደቁ ለክልል ምክር ቤት ቀርበዋል፡፡
የሲዳማ የክልልነት ጥያቄ በምርጫ ቦርድ ዝግጁነት ማነስ የተነሳ ሕዝበ ውሳኔ ሳይከናወን በመቆየቱ ለሰዎች መሞትና ለንብረት ውድመት ምክንያት የሆኑ ብጥብጦች የተስተዋሉ ሲሆን፣ ለአንድ ዓመት ያህል ባልተሰበሰበው የክልል ምክር ቤት ሳቢያ ጥያቄያችን ዘግይቶብናል ያሉ የተለያዩ ዞኖች ደግሞ ፍፁም ሰላማዊ የሚባሉ ሠልፎችን በማድረግ፣ የክልልነት መብታችን ያለ ቅድመ ሁኔታ ይከበርልን የሚሉ ጥሪዎችን ሲያስተጋቡ ተደምጠዋል፡፡
ይሁን እንጂ የክልልነት ጥያቄ ለሚያነሱ ለሁሉም ዞኖች ምላሽ መስጠት በተለያዩ ምክንያቶች ሊፈጸም የሚችል አይደለም በማለት በባለሙያዎች ያስጠናውን ጥናት ይፋ ያደረገው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን)፣ የዚህን ጥናት ውጤት ለተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ማወያየት ይበጃል በማለት በተለያዩ ጊዜያት ከከፍተኛ የፓርቲና የክልሉ አመራሮች አንስቶ እስከ ማኅበረሰብ ተወካዮች ድረስ የዘለቁ ውይይቶችን ሲያደርግ ቆይቷል፡፡
የደቡብ ክልልን ባለበት ማስቀጠል፣ ክልሉን ለሁለት ወይም ከአምስት ባልበለጡ የተለያዩ ክልሎች መክፈል፣ አልያም የክልልነት ጥያቄዎችን በጊዜያዊነት ማቆየት የሚሉ ሦስት ምክረ ሐሳቦችን ያቀረበው ጥናት ከጅምሩ አንስቶ ከፍተኛ ተቃውሞ የገጠመው ሲሆን፣ በተለያዩ ጊዜያት በተደረጉ የጥናቱ ውጤት ውይይቶች ላይ ተመሳሳይ ተቃውሞዎች አስተናግዷል፡፡
በንቅናቄው ማዕከላዊ ኮሚቴና በከፍተኛ አመራሩ ውይይቶች ወቅት ለሲዳማ ክልልነትን በመስጠት ሌላው የክልሉ ክፍል ባለበት እንዲቀጥል ማድረግ የሚል የውሳኔ ሐሳብ የቀረበ ሲሆን፣ ይኼ ውሳኔ ከካፋና ከወላይታ ዞን አመራሮች መረር ያለ ተቃውሞን በማስከተል የተወሰኑ አመራሮች መድረኮቹን ጥለው እንደወጡ ሲነገር ቆይቷል፡፡ ሆኖም ሕዝቡ በጥናቱ መነሻና ግኝቶች ላይ ይወያይ የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ ላይ በተደረገ ስምምነት፣ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን የማወያየት ሥራው ቀጥሎ ቆይቷል፡፡
የእነዚህ ውይይቶች አካል የሆነውና ከመላው ክልል ሞዴል ወጣት፣ ሞዴል አርሶ አደር፣ ሞዴል ነጋዴ፣ እንዲሁም ሞዴል የኢንተራፕራይዝ መሪዎች በሚሉ መሥፈርቶች የተመለመሉ 1,532 ወጣቶችን የሰበሰበው የውይይት መድረክ ከቀድሞዎቹ እምብዛም የተለየ የውይይት መንፈስም ሆነ ውጤት አልታየበትም፡፡ በክልሉ ከሚገኙ ሁሉም ወረዳዎች አምስት አምስት ተወካዮች ተመርጠው በሐዋሳ ከተማ የተደረገው ውይይት፣ ክልል አቀፍ የማኅበረሰብ ውይይት የሚል ስያሜ ተሰጥቶት በሁለት ዋና ዋና አጀንዳዎች ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
የመጀመርያው አጀንዳ አገራዊና ወቅታዊ ሁኔታዎችን የገመገመ ሲሆን፣ ከፀጥታ፣ ከኢኮኖሚና ከፖለቲካዊ ሁነቶች አንፃር ውይይቶች ተደርገዋል፡፡ ይኼ የመጀመርያው አጀንዳ መደበኛ የሚባል ገጽታ ይዞ የተጠናቀቀ ሲሆን፣ ስለክልል አደረጃጀት እየተነሱ ባሉ ጥያቄዎች ላይ የተደረገው ውይይት ግን ከፍተኛ ተቃውሞና ሙግት ያስከተለ እንደነበር ከስብሰባው ተሳታፊዎች ለመረዳት ተችሏል፡፡
የክልልነት ጥያቄዎቹ የሕዝብ ጥያቄዎች ስለሆኑ ሕጋዊ አግባብነታቸውን ብቻ ተከትለው ይመለሱ የሚል አቋም የሚያንፀባርቁት የካፋ ዞንና የወላይታ ዞን ተወካዮች ከሲዳማ ዞን ተወካዮች ጋር በጋራ የተሰበሰቡ ሲሆን፣ ‹እኛ ለብቻ ለምን እንሰበሰባለን የጥያቄያችንን አግባብነት ሌሎችም ይሰሙና ይረዱልን› በማለት ከውይይቱ በፊት ንትርክ ተፈጥሮ እንደነበር ተሰምቷል፡፡
ሆኖም የሌሎች ዞኖች ተወካዮችም በቡድን እየተቀላቀሉ የተሰበሰቡ እንደሆነ ተገልጾ፣ የክልልነት ጥናት ላይ ከአጥኚዎቹ አንዱ በሆኑት ፊልሞን ሀደሮ (ዶ/ር) በቀረበ ሐሳብ ላይ ውይይት ተደርጓል፡፡
‹‹እኛ ክልሉም ጥናቱም አይመለከተንም ነው ያልነው፡፡ ጥያቄያችን ወደ ምርጫ ቦርድ ይሂድ ነው ያልነው፡፡ ክልልነት ለእኛ አዲስ አይደለም፡፡ ካሁን ቀደም የጠቅላይ ግዛትና የአውራጃ ልምድ አለን፤›› በሚል መከራከሪያ ጥናቱንና የጥናቱን ውጤት ሲሞግቱ እንደነበር አንደ የካፋ ዞን የስብሰባው ተሳታፊ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የጥናቱ ውጤት ከቀረበ በኋላ ‹‹የኃይል መድረክ›› በሚል ርዕስ የነበረውን ውይይት አዲስ የተሾሙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳውና የደኢሕዴን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ መርተውታል፡፡ አቶ ሞገስ ስለደኢሕዴን ስኬቶችና ስለደቡባዊ ማንነት፣ እንዲሁም በክልሉ ብሔር ብሔረሰቦች አብሮነት የተገኙ ትሩፋቶችን በማውሳት ላይ ሳሉ፣ ‹‹የመጣንበት ዓላማና ግብ ይኼ አይደለም፣ ውይይቱም አይመጥንነንም፤›› ሲሉ የወላይታና የካፋ ዞን ተወካዮች አዳራሹን ትተው መውጣታቸውም ታውቋል፡፡
ይሁን እንጂ በአካባቢው የነበሩ የፌዴራል ፖሊስ አባላት ተሰብሳቢዎች ተመልሰው ወደ አዳራሹ እንዲገቡ በማድረጋቸው፣ ስብሰባው መቀጠሉን ተሳታፊዎቹ ገልጸዋል፡፡ ስብሰባው በአዲስ መንፈስ እንዲቀጥል ሲሉ አቶ ርስቱ ይቅርታ መጠየቃቸውም ታውቋል፡፡
‹‹የጥናቱን ውጤትና የደኢሕዴንን ውሳኔ እንድንቀበል ከፍተኛ ጫና ያደርጉብን ነበር፤›› በማለት የገለጹት አንድ ተሳታፊ፣ የዚህ ስብሰባ ተሳታፊዎችን ማሳመን ቢቻል ግን የብዙኃኑ ጥያቄ በቀላሉ ይታፈን ነበር ይላሉ፡፡
በጉዳዩ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡት አንድ የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ (ዎብን) ከፍተኛ አመራር ግን፣ ክልሉም ሆነ ደኢሕዴን የክልልነት ጥያቄዎችን ለመመለስ እየሄዱበት ያለው አግባብ የሚያግባባ አይደለም ይላሉ፡፡
‹‹ሕዝቡ ሕገ መንግሥቱን ያውቃል፣ ጥቅምና ጉዳቱንም ጠንቅቆ ይረዳል፤›› ያሉት እኚህ አመራር፣ ‹‹የዎላይታ የክልልነት ጥያቄ እስከ ሕዝቡ ወርዶና ውይይት ተደርጎበት የሕዝብ ጥያቄ መሆኑ ሲረጋገጥ የቀረበ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ጥያቄው በሕገ መንግሥቱ መሠረት ምላሽ እንደሚያገኝ ያውቃል፤›› ብለዋል፡፡
ስለዚህም የተለየ ውጤት ለማያመጣ ነገር ተወያዩ ማለት የሕዝብን ገንዘብ፣ ጊዜና ንብረት ማባከን ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
‹‹ሕጋዊውን መንገድ መከተል ለአገርም ሆነ ለክልሉ ሰላምና ደኅንነት ለማምጣት ይረዳል፤›› ያሉት እኚህ የዎብን ከፍተኛ አመራር፣ ‹‹ለደኢሕዴንም ህልውና የሚበጀው ይህ ነው፤›› በማለት ይከራከራሉ፡፡
በተለያዩ ጊዜያት የተለያዩ ውይይቶች እንደነበሩ በማስታወስ ሕዝቡ ብቸኛው ዋስትናው የክልል አደረጃጀት ብቻ በመሆኑ ምንም የተለየ ውጤት እንዳላመጡ፣ ሕግን ተከትሎ ለጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ብቸኛው መፍትሔ እንደሆነ እንደሚያምኑም ይናገራሉ፡፡ ነገር ግን ይኼ ጥያቄ ኢትዮጵያን ለማፍረስ የሚደረግ ወይም ኢትዮጵያዊ ማንነትን ካለመፈለግ የመነጨ ባለመሆኑ፣ እንዲህ እንደሆነ ተደርጎ የሚታሰብ ከሆነም ስህተት ነው በማለት ያስረዳሉ፡፡
‹‹የክልልነት ጥያቄዎች ከፍትሐዊ ተጠቃሚነት፣ ከልማትና ከመልካም አስተዳደር አንፃር እንጂ አገርን ለማፍረስ ተብለው የተነሱ አይደለም፤›› በማለትም ያክላሉ፡፡
ይሁን እንጂ የሕዝቦችን ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማስጠበቅ የፌዴራል መንግሥት መጠናከርና የእነሱን ችግሮች ማረም እንደሚኖርበት በመጠቆም፣ ‹‹የክልል ሥልጣን የአገር ሥልጣን እስኪመስል ድረስ እየተለጠጠ ነውና ይኼ ለማንም ዋስትና ስለማይሰጥ ጠንካራ የፌዴራል መንግሥት ያስፈልጋል፤›› ሲሉም ያሳስባሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የደቡብ ጉዳይ ከምንም በላይ የፌዴራል መንግሥቱንም ሆነ ሌሎች ክልሎችን ሊያሳስባቸው የሚገባ እንደሆነ በመግለጽ፣ ለዚህ ምክንያቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ክልሉን የሚያስተዳድረው አካል ቅቡልነት እያጣ መሄዱ ነው ይላሉ፡፡
በደኢሕዴን እየተደረገ ያለው ጥረት ክልሉን እንዳለ ማስቀጠል እንደሆነ በመግለጽም፣ ይኼ የሚጠቅም ቢሆን ኖሮ ሕዝቡ ቀድሞውኑ ጥያቄ አያነሳም ነበር ይላሉ፡፡ መጠራጠርና ሽኩቻ ከአመራሩ አልፎ ሕዝቡ ዘንድ እየወረደ በነበረበት ጊዜ ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸውን በማስታወስ፣ ባለፉት 27 ዓመታት አንድነት ላይ ሳይሆን ክፍፍል ላይ በመሠራቱም፣ የአንዱ ሹመት ለሌላው ሥጋት እስከ መሆን ድረስ እንደነበር፣ በዚህም ሳቢያ በልማትም በትስስርም ወደ ኋላ የቀረ ክልል ነበር ይላሉ፡፡
ስለዚህም ደቡብ ክልልን እንዳለ ማስቀጠሉ ለደኢሕዴን ሥልጣን ይጠቅማል እንጂ፣ ሕዝብን ይጠቅማል የሚል እምነት እንደሌላቸው ያስረዳሉ፡፡
የአዲስ ዓመት በዓልን በማስመልከት መግለጫ የሰጡት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ርስቱ ይርዳው፣ በአዲሱ ዓመት በመንግሥት በኩል የነበሩ የአሠራር ክፍተቶችና ከአደረጃጀት ጋር በየአካባቢው የሚነሱ ቅሬታዎችን በአግባቡ በመፈተሽ ምላሽ ይሰጣል ብለዋል፡፡ የሕዝብ ጥያቄዎችና ፍላጎቶችም በሰከነና በሰላማዊ መንገድ ምላሽ እንዲያገኙ፣ መንግሥት ጥረት እንደሚያደርግ አስታውቀዋል፡፡