እንሽላሊቶች በብዙ ቦታ ተሰራጭተው የሚገኙ ናቸው፡፡ የብስ፣ ጎሬ፣ ውኃ እና ዛፍ ላይ ሁሉ ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ አራት እግርና አጭር ቁመት ሲኖራቸው፣ እግራቸውም እምብዛምም ጠንካራና የዳበረ አይደለም፡፡ እንዲያውም እንደ የመስታወት እንሽላሊት (Glass lizard) አይነቱ ደግሞ እንዲያውም እግር-አልባ ነው፡፡ አብዛኞቹ ተንቀሳቃሽ የዓይን ቆብ ሲኖራቸው የማየት ችሎታቸውም የዳበረ ነው፡፡ እንሽላሊቶች የመስማት ችሎታቸው አነስተኛ ነው፡፡ ሆኖም ውጫዊ ጆሮ አላቸው፡፡ አብዛኞቹም ከሙቀትና ከቃጠሎ አካባቢዎች ጋር ስምሙ ሆነው የሚያኖራቸው ተፈጥሮ አላቸው፡፡
እንሽላሊቶች ለእባቦች በጣም የቀረቡ ቢሆኑም አብዛኞቹ እንሽላሊቶች በደንብ ያደገ እግር ስላላቸው በቀላሉ ልዩነታቸውን ማየት ይቻላል፡፡ እርግጥ ነው እግር-አልባ እንሽላሊቶች አሉ፡፡ በዓለም ላይ 3 ሺሕ ያህል ዝርያዎች አሏቸው፡፡
በመጠን ከትንሹ ትል መሣይ ፍጡር እስከ የኮሞዶ ሞኒተር (Monitors of Komodo) የሚባለው ትልቁ የእንሽላሊት ቤተዘመድ ይደርሳሉ፡፡ ኢጓና (Iguana)፣ ስኪንክ (Skink)፣ ጌኮ (Gecko) እና እስስት (Chamelon) ይገኝበታል፡፡ ከነኚህ ውስጥ ኢጓና (Iguana) የሚደንቅ ነገር ይታይባቸዋል፡፡ አካላቸው ከጎን እስከ ጎን ሰብሰብ ያለ ሲሆን ከጀርባቸው መሀል የሚወርዱ ረጃጅም መስመሮች አሏቸው፡፡ ቁመታቸው 1.8 ሜ. ይሆናል፡፡
ብዙዎቹ እንሽላሊቶች ዕንቁላል ጥለው መሬት ውስጥ ይቀብሩታል፡፡ የዕንቁላሎቹ ሽፋን ቆዳማ መሆኑ ከእባቦቹ ጋር ያመሳስለዋል፡፡ ጥቂት እንሽላሊቶች ዕንቁላል ከመጣል ይልቅ እንደ አጥቢዎች ፀንሰው ይወልዱታል፡፡ ለምሳሌ ቀንዳማ ጓጉንቸሮች (Horned Toads) እዚህ ውስጥ ይመደባሉ፡፡ ይህም አወላለድ ከላይ እንደተጠቀሰው ከአንዳንድ እባቦች ጋር ያመሳስላቸውል፡፡ እርግጥ ከአጥቢዎች የሚለዩበት መንገድ አለ፡፡ ይህም ጽንሱ ከወላጆቹ ምንም ዓይነት ምግብ አለማግኘቱ ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ውስጠ-ቀፍቃፊ ይባላሉ፡፡
ሀ) ምግባቸው
ብዙዎቹ እንሽላሊቶች የተለያየ ዓይነት ሕይወት ያለው እንስሳ ይመገባሉ፡፡ ነገር ግን ዋነኛው ምግብ የሚወሰነው በእንሽላሊቱ የአካል መጠን ነው፡፡ መጠኑ በጨመረ ቁጥር የሚመገበውም እንስሳ መጠን ይጨምራል፡፡
ለምሳሌ፣ ቴጉስ (Tegus) የሚባለው ትልቁ እንሽላሊት ከ1ሜ. በላይ ቁመትና 2.3 ኪ.ግ. የሚሆን ክብደት ሲኖው ሥጋ በል ነው፡፡ ጫጩቶችንም በመብላት ይታወቃል፡፡ የትናንሾቹ ምግብ በዋነኛነት የተለያዩ ሦስት አፅቄዎች ናቸው፡፡ በትሮፒክ አካባቢ የሚገኙ እንሽላሊቶች ጎጂ (ሠብል አውዳሚ) የሆኑ ሦስት አፅቄዎችን በማጥፋት የታወቁና ጠቃሚ መሆናቸውን አንዳንድ ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡ ይህ ጥቅማቸው ከወፎች ጋር የሚመጣጠን ነው ይባላል፡፡
ለ) ከዓይናቸው ደም የሚያመነጩት
ቀንዳማ እንሽላሊቶች (Horned Lizard) የሚባሉት እንሽላሊቶች በሚደነግጡበት ወይም በሚናደዱበት ጊዜ ከአይናቸው ውስጥ ደም ያወጣሉ፡፡ ይህም ይሆናል ተብሎ የሚታሰበው በፍርሃት ወይም በንዴት ጊዜ በሚጨምረው የደም ግፊት አማካይነት ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት ጊዜ ዓይን ስር ያሉ ትናንሾቹ የደም ቧንቧዎች ‹‹ካፒላሪስ›› በመፈንዳት የተወሰነ ርቀት ደም እንዲረጩ ይሆናል፡፡
ሐ) የሚበሩት ወይስ?
ደማቅ ነጠብጣብ፣ ቀይ፣ ቢጫና ጥቁር መልክ ያለው ቢራቢሮ እንሽላሊት (Butterfly Lizard) በዓየር ላይ ለተወሰነ ርቀት መንሳፈፍ ቢችልም በርግጥ አይበርም፡፡ ክንፍ መሳይ ክፍሎቹ ከተንቀሳቃሽ ጎድኑ ጋር የተያያዙና የተጣጠፈ ልል ቆዳ በመሆናቸው አይንቀሳቀሱም፡፡ ድርቅ ያሉም በመሆኑ እንሽላሊት በአየር ላይ ከመሬት ወደ ዛፍ ሲወጣ ተንሳፈፈ እንጂ በረረ ለማለት አይቻልም፡፡ በእርግጥ 18ሜ. ያህል ርቀት መንሳፈፍ ይችላል፡፡ የእንሽላሊቶቹ ቁመት ረጅምና ቀጥ ያለ ጭራቸውን ጨምሮ ከ20-30 ሳ.ሜ ይሆናል፡፡
መ) ባለ ሦስት ጭራዎቹ
ሦስት ጭራ ያላቸው ባላ ባላ መሳይ ጭራ እንሽላሊቶችን ማግኘት የተለመደ ነገር ነው፡፡ የዚህ ምክንያቱም እንሽላሊቶች የተቆረጠ ጭራቸውን ለመተካት በሚደረገው ትክክለኛ ያልሆነ ሂደት ነው፡፡ እንደሚታወቀው እንሽላሊቶች ጭራቸው ቢቆረጥባቸውም መልሰው የመተካት ልዩ ችሎታ አላቸው፡፡ ጭራቸው በሚቆረጥባቸው ጊዜ የቆሰለው ቦታ ላይ ያሉ ህዋሳት ለማደግ ይነቃቃሉ፤ ጭራው ሙሉ በሙሉ እስኪተካም ድረስ ዕድገት ይቀጥላል፡፡ ሆኖም አዲሱ ከዋነኛው ጋር ሲነፃፀር አጭር ነው፡፡ በአብዛኛው ህዋሳት ለማደግ የሚነቃቁት በቁስሉ አንደኛ ወገን ብቻ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ግን ህዋሳት በሁለት ወይም ከዛ በላይ ክፍል ላይ ተነጥለው ማደግ ይጀምራሉ፡፡ በዚህን ጊዜ ሁለትና ከዛ በላይ ጭራ ያበቅላሉ፡፡ አንዳንዴ ደግሞ ጭራው ጉዳት ቢደርስበትም ሙሉ ለሙሉ ለመቆረጥ የማያደርሰው ይሆናል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ጉዳቱ አዳዲስ ህዋሳትን ለዕድገት ማነቃቃት የሚችል ነው፡፡ በዚህን ጊዜ ደግሞ የመጀመሪያው ዋነኛው ጭራ እያለ አንድ ወይም ሁለት ጭራዎች በተጨማሪ ሊበቅሉ ይችላሉ ማለት ነው፡፡
ሠ) ውኃ ላይ የሚሮጡት
ባሲሊከስ (Basilisk) የሚባሉት እንሽላሊቶች ከፊት ይልቅ የኋላ እግራቸው የዳበረ በመሆኑ፤ መሬት ላይ ሲሮጡም የሚጠቀሙት የኋላ እግራቸውን ነው፡፡ ረጅሙን ጭራቸውን ደግሞ ሚዛናቸውን ለመጠበቅ ይጠቀሙበታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ደግሞ ውኃ ላይም በመሮጥ የታወቁ ናቸው፡፡ 400 ኪ.ሜ ድረስ በውኃ ላይ ሳይሰምጡ የመሮጥ ብቃት አላቸው፡፡ እነኚህ እንሽላሊቶች ትልቅ እግሮችና ቀለል ያለ አካል ስላላቸው የውኃ ላይ ሩጫ ይቀላቸዋል፡፡ በሩጫው በፍጥነት ከቀጠሉ አይሰምጡም በመኻል ቆም ካሉ ግን መስመጥ አይቀርላቸውም፡፡ በዋናም በኩል ጥሩ ዋናተኞች ናቸው፡፡
- ማንይንገረው ሸንቁጥ ‹‹አጥቢዎች›› (2004)