Thursday, November 30, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ዓሹራ ከሐጅ በኋላ ለምን በነጃሺ (በኢትዮጵያ) ይከበራል?

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በሙስሊም የሚከበሩ እንደ ረመዳን፣ ፈጥር፣ ዓረፋ፣ ሐጅ ሁሉ የዓሹራ በዓልም በጾም ከሚከበሩት የሙስሊም በዓላት አንዱ ነው፡፡ የዓሹራ በዓል የሚከበረው በወርኃ ሙሐረም በአሥረኛው ቀን ሲሆን፣ ይህም ከሐጅ ወር ቀጥሎ ከአንድ ወር ከአሥር ቀናት ወይም በአርባኛው ቀን የሚውል ነው፡፡ በዚህ ዓመትም በእኛ ዘመን አቆጣጠር ጳጉሜን 5 ቀን 2011 (ሙሐረም 10 ቀን 1441 ዓመተ ሒጅራ) በመላው ዓለም በልዩ ልዩ ምክንያቶች ተከብሮ ውሏል፡፡ዓሉን በመካከለኛው ምሥራቅና በቱርክ የሚገኙ አይሁዳውያንና ክርስቲያኖችም አብረው ከሙስሊሞች ጋር በመሆን ያከብሩታል፡፡ የዓሹራ በዓል የሚከበርበት ምክንያት ብዙና እንደሁኔታው የሚለያይ ነው፡፡ አንደኛው ምክንያት ነቢዩ ሙሐመድ ከመዲና ወደ በመካ በድል አድራጊነት ከተመለሱ በኋላ ከቁረይሽ ወገኖቻቸው ጋር በመሆን የጾሙበትን ቀን ለማስታወስና የእሳቸውን አርአያ ተከትሎ ለማስቀጠል ነው፡፡ 

የዓሹራ በዓልን በጾም የማክበር አመጣጥ ታሪክ እንደሚያወሳው ደግሞ ነቢዩ ሙሐመድ ከመካ ወደ መዲና ሲመጡ በዚያው ነዋሪ የነበሩት አይሁዶች የዓሹራ በዓልን በጾም ያከብሩት ነበር፡፡ በዚህም ጊዜ እርሳቸውም መጾም ከመጀመራቸውም በላይ ተከታዮቻቸውም እርሳቸውን ተከትለው መጾም ጀመሩ፡፡ ይሁንና በወርኃ ረመዳን መጾም እንደሚገባቸው በፈጣሪ ሲገለጥላቸው የዓሹራ በዓል ግዴታ መሆኑ ቀረና በፈቃደኛነት እንዲሆን ተደረገ፡፡ ይህንም ጉዳይ ኢማሙ ቡኻሪ ትክክል እንደሆነ ገልጠውታል፡፡ ኢብን ዓባስም ከላይ የተጠቀሰውን ያወሱና «አይሁዳውያን ፈጣሪ ነቢዩ ሙሴን ከፈርኦን አገዛዝ ሕዝቡን ነፃ በማውጣትና ፈርኦንም እስከ ሠራዊቱ በቀይ ባሕር እንዲሰምጥ በማድረግ ምልክቱን ያሳየበት ዕለት አድርገው ያከብሩት ነበር፡፡ ስለዚህም ነቢዩ ሙሐመድም ከእነሱ ይልቅ እኔ ለሙሳ እቀርባለሁ» በማለት ቡኻሪንና ሙስሊምን ዋቢ በማድረግ  ይገልጡታል፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ «በሚቀጥለው ዓመት ከኖርኩ የሙሐረምን ዘጠነኛ ቀንንም እጾማለሁ» ብለው የነበሩ ሲሆን ሳይጾሙት አልፈዋል፡፡ ከእርሳቸው በኋላ ግን ዘጠነኛውና፣ አሥረኛው ወይም አሥረኛውና አሥራ አንደኛውን ዕለተ ሙሐረም የሚጾሙ አሉ፡፡ ኢብን ዓባስ እንደሚሉት «በዓሹራ ቀን መጾም በሚቀጥለው ዓመት ከሚፈጸም ኃጢአት ያድናል በሚል ከፍተኛነቱን ያጠናክራሉ፡፡ ኢማም አሕመድ ደግሞ ካለፈው ዓመትና ከሚቀጥለው ነፃ እንደሚያወጣ ያስረዳል፡፡ በዚህ ረገድ የሚጠቀሱ አንዳንድ ሐዲሶች ቢኖሩም ዕለቱን በጾም ከማክበር አኳያ ከጥንታውያን አይሁዶችና ክርስቲያኖች ጋር በተያያዘ በጾም ሲከበር እንደነበረ የሚያወሳው ያስማማል፡፡ በመሆኑም ነቢዩና ተከታዮቻችው የዓሹራን በዓል ከመጾም በስተቀር ሌላ ሥራ ባለመሥራት ያከብሩት ስለነበር እንደ አንደኛ ምክንያት ሆኖ በመከበር ላይ ነው፡፡ ሙስሊም ደግሞ በሐዲሳቸው ዓመት ዓይሻን በመጥቀስ ጭምር የመካ ሰዎች የዓሹራን በዓል በመጾም ያከብሩ እንደነበር በቁጥር 2499 ያወሳሉ፡፡ በዓመት ዓይሻ መሠረት «ቁረይሾች ከኢስላም በፊት የዓሹራን ጾም ይጾሙ የነበረ ሲሆን ነቢዩ ሙሐመድም ከኢስላም በፊት ይጾሙት ነበር፡፡ ወደመዲና በሄዱ ጊዜም የጾሙት ቀደም ሲል ሲጾሙት የነበረውን ይዘው ነው» በማለት ከአይሁዶች የወሰዱት አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ ይህ እንግዲህ ሁለተኛው ምክንያት መሆኑ ነው፡፡

ሦስተኛው ምክንያት ምንም እንኳን ነገሩ በአንዳንድ የሱኒ ሙስሊም ሊቃውንት ተደጋፊነት ባይኖረውም ሺዓዎች ደግሞ ፊታቸውን በጥፊ በመጠፍጠፍ፤ በባና በመፈግፈግ፣ ልብሳቸውን በመቅደድና በጎራዴ ራሳቸውን በማድማት፣ ጀርባቸውን በመግረፍ፣ የነቢዩ ሙሐመድ የልጅ ልጅ የሆኑት ሑሴን 61 ዓመተ ሒጅራ ወይም 680 ዓመተ ኢብን አቢጣሊብ በካራባላ ጦርነት ከከሊፋ ያዚ ጋር በተደረገው ጦርነት በወላጆቻቸው የተገደሉበትን ቀን በማስታወስ በመረረ ሐዘንና ጸጸት ያከብሩታል፡፡ እንዲህ ያለውን ድርጊት የሚቃወሙት ክፍሎች ግን «ያፈነገጣችሁትስ እናንተቢባሉም «ይህንን ለማድረግ የሚያስችል የቁርዓን ወይም የሐዲስ መሠረት ሳይኖራቸው የሚሠሩ» ማለትም ከኢስላማዊ ድርጊት ያፈነገጡ አድርገው ይወስዷቸዋል፡፡ በመሠረቱ የሑሴይንን የመስዋዕትነት ቀንን በዓሹራ ቀን የሚያስታውሱት ሺዓዎች ብቻ አይደሉም፡፡ ለየት ባለ መልኩም ቢሆን ሱኒዎችም «ሙስሊም ድል አድርጎ እምነቱን በጠንካራ መሠረት ላይ የጣለ ነው» ብለው ለድሆች በጎ ነገር በማድረግ፣ በመጸለይ፣ ሕፃናትን፣ አዛውንቶችን በመንከባከብ ያከብሩታል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ልዩ ልዩ ስብሰባዎችን፣ ሴሚናሮችንናልፎችን በማካሄድ ዕለቱን አክብረው የሚውሉ ሱኒዎች አሉ፡፡ በአንዳንድ ሺዓዎች ዘንድ በዓሹራ ቀናት ዕለቱ በሐዘን የሚታሰብ በመሆኑ ይህንን የሚያስረሳ ሙዚቃ ማዳመጥ፣ርግ መደገስ ወይም ደስታን የሚያስገኝ ነገር ማድረግ አይፈቀድም፡፡

አራተኛው ምክንያት ነቢዩ ኖኅ ከጥፋት ውኃ በኋላ ዓለም ተረጋግታ እርሳቸውና ከእራሳቸው ጋር ከጥፋት የዳኑ እንስሳት ከመርከብ የወጡበትን ቀን ለማስታወስ ሲባል የዓሹራ በዓል ይከበራል፡፡ አምስተኛው ምክንያት ከነቢዩ አብርሃም (ኢብራሂም) ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህም የበኩር ልጃቸው ኢስማኤልን በፈጣሪ ጥያቄ መሠረት ለመስዋዕትነት ሲያቀርቡ ታዛዥነታቸውን በማስታወቁ ኮርማ በግ በመልአኩ ገብርኤል አማካይነት እንዳቀረበለት እንዲሁም ለአማኞች የእሳት ሰደድ በለቀቁባቸው ጊዜ ምንም ሳይሆኑ የወጡበትን ምክንያት በማድረግ የሚከበር ዕለት ነው፡፡

በመካ ደግሞ ዓሹራ «ካዕባ» ተብሎ የሚታወቀው ቤተ ፈጣሪ ከሐጅ በኋላ ለአንድ ወር ያህል ተዘግቶ ከቆየ በኋላ ውስጡ በዘምዘም ውኃ ታጥቦና የቤቱ ውጫዊ ግንብ ሙሉ በሙሉ አዲስ ካባ በመልበስ በሩ ለጎብኚዎች የሚከፈትበት ዕለት ነው፡፡ ምንም እንኳን የምሁራን ሙሉ በሙሉ ስምምነት ባይኖርም ወርኃ ሙሐረም ሙስሊሙ ኅብረተሰብ በፈጣሪ የተባረከበት ሙሉ ቀን እንደሆነ ተደርጎ እንደሚወሰድ አብዱልቃድር አል ጀይላኒ (Ghuniyatut Talibin) በሚል ርዕስ ባዘጋጁት ሥራቸው ገልጸውታል፡፡

የዓሹራ በዓል ቀደም ሲል ከተጠቀሱት ምክንያቶች በተጨማሪ ፈጣሪ ምድርንና ሰማይን የፈጠረበት፣ ፈጣሪ አዳምን ከገነት ካባረረው በኋላ መጸጸቱን አውቆ ምሕረት ያደረገበት፣ ፈጣሪ ከነቢዩ ሙሳ (ሙሴ) ጋር የተነጋገረበት፣ ዩኑስ (ዮናስ) በዓሳ ሆድ ሆኖ የዳነበት፣ ኢየሱስ የተወለደበትና ያረገበት፣ ያዕቆብ ከሕመሙ የዳነበት፣ ነቢዩ ኢብራሂም (አብርሃም) ከእሳት ቃጠሎ የዳኑበት፣ ለነቢዩ ሱለይማን (ሰሎሞን) ንጉሥነታቸው የተሰጠበት፣ ያዕቁብና ዩሱፍ (ያዕቆብና ዮሴፍ) የተገናኙበት ዕለት ተደርጎ ጥንታዊውን ሃይማኖት በሚቀበሉ ክርስቲያኖችና አይሁዶችም ጭምር ይከበራል፡፡ ይህም የሚያመለክተው የዓሹራ በዓል ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ታሪካዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ነው፡፡

የዓሹራ በዓል አከባበር በተለያዩ ቦታዎች

የዓሹራ በዓል ሙስሊም ባለበት አገር ሁሉ የሚከበር ሲሆን በተለይም በመካከለኛው ምሥራቅ፣ በሩቅ ምሥራቅና በሰሜን አፍሪካ አገሮች በከፍተኛ ድምቀት ይከበራል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ በተለይም በኢትዮጵያ ከጥንት ጀምሮ ሲከበር የነበረ ሲሆን ይህንንም ለብቻው ርዕስ ሰጥተን የምንመለከተው ይሆናል፡፡ እንደ ኬንያ፣ ታንዛኒያ ባሉ አገሮችም በሙስሊሞች ዘንድ ተከብሮ የሚውል ሲሆን በተለይም በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለብዙ ዓመታት የዓሹራ በዓል ይከበር እንደነበረ ዛሬም በሕይወት ያሉ ሰዎች እንደሚናገሩት «ድሮ በሕፃንነታችን መድረሳ ስንሄድ ኬክ ይሰጠን ነበር፡፡ እንደ ዕድሜያችንም አሥር ሳንቲምና አምስት ሳንቲም እንቀበል ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን እንዲህ ያለው ልማድ እየደበዘዘ ነው፤» ይላሉ፡፡

በአውስትራሊያ በሺዓዎች መስጊድ በከፍተኛ ድምቀት ተከብሮ የሚውል ሲሆን በኢንዶኔዥያ በተለይም ፓሪማን ተብሎ በሚጠራው ስፍራ የካራባላ ጦርነትን የሚያስታውስ ተውኔት እየተተወነ፣ ታስና ዞል የተሰኘ ድቢ እየተመታ ይከበራል፡፡ በሞሮኮ ከፍተኛ የቤተሰብ በዓል ሲሆን በዚህ ዕለት መላው ቤተሰብ ደስ ብሎት እየፈነጠዘ እንዲውል ኩስኩስ ተብሎ የሚጠራው ልዩ ልዩ ጣፋጭ ምግብ ይዘጋጃሉ፡፡ ሞሮኳውያን የዓሹራን በዓል ከቤት ወደ ቤት እየተዘዋወሩ በመጠየቅ ያሳልፋሉ፡፡ ሞሮኳውያን ወጣቶች በዓሹራ በዓል ምሽት «ሻላ» የተባለ የደመራ መብራት በማብራት እያዜሙ ፈጣሪያቸውን ያመሠግናሉ፣ ነቢያቸውንም ያወድሳሉ፡፡ ምንም እንኳን በአሁኑ ጊዜ «መብታችን ተነካ» በሚል ስሜት ተቃውሟቸውን የሚገልጡ ሰዎች በመብዛታቸው ምክንያት እንዲሁም አንዳንድ ባለጌዎች እንደ እንቁላልና ቀለም የመሳሰሉትን በመርጨት ሰዎችን በቆሻሻ ስለሚበክሉ የቀረ ቢሆንም ከጥቂት አሥርት በፊት ሞሮኳውያን በዚህ ዕለት «ዘም ዘም» የሚሉት የውኃ የመራጨት ባህል ነበራቸው፡፡ ሞሮኳውያን በዕለቱ የፍየል፣ የበግ ቆዳ ለብሰው በሠልፍ ወደ አደባባይ ይወጣሉ፡፡ አንዳንዶቹም የእንስሳት ጭምብል ያደርጋሉ፡፡ በሙዚቃም ይታጀባሉ፡፡ አክሮባት መሰል ጭፈራም ይጨፍራሉ፡፡ ሠልፉም በጭብጨባ የተሞላ ይሆናል፡፡ ይህም እስከ ሌሊት ድረስ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ሕፃናት ደግሞ አዲስ ልብሶቻቸውን፣ ሴቶች ከሆኑ ጌጦቻቸውን አድርገው ከቤት ወደ ቤት መንፈሳዊና የሙገሳ ዜማዎችን እያዜሙና እየጨፈሩ በመሄድ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ይቀበላሉ፡፡ በድሮ ጊዜ የሚሰጣቸው እንቁላል፣ምር፣ አልሞንድ የተባለ የፍራፍሬ ዓይነት ይሰጣቸው ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ማንኛውም ስጦታ ወደ ገንዘብ ተለውጧል፡፡

በቱርክና በግብፅም የነቢዩ ኖኅ መቀበያ ተብሎ የሚዘጋጅ ገንፎ ይቀርባል፡፡ ይህንንም ልዩ ገንፎ ለማዘጋጀት እንደ ስንዴ፣ እንደ ባቄላ፣ አተር፣ አደንጓሬ፣ ሽንብራ፣ ኦቾሎኒ፣ ሩዝ፣ በቆሎ፣ ያሉ ጥራጥሬዎች በአንድ ቀን ከተደባለቁ በኋላ በውኃ ተዘፍዝፈው ያድራሉ፡፡ በማግስቱም ሙክክ እስኪሉ ድረስ ይቀቀላሉ፡፡ እየተቀቀሉም በእንጨት ወይም በሌላ ማማሰያ ይገነፋሉ፡፡ በመጨረሻም የገንፎ መልክ ሲኖራቸው ዘቢብ፣ ባሕር ቅመም፣ ስኳርና ሌሎችም ማጣፈጫዎች ተጨምሮባቸው ለአገልግሎት ይውላል፡፡ ገንፎው ከቤተሰብ ተርፎም ወደ ጎረቤቶችና ወዳጅ ዘመድ የሚላክበት ሁኔታ አለ፡፡ ገንፎው ወደ ጎረቤቶችና ወደ ወዳጅ ዘመድ የሚላከው የሃይማኖት ልዩነት ሳይደረግ ሲሆን ማኅበራዊ ግንኙነት በማጠናከር ረገድ የበኩሉን አዎንታዊ ሚና እንደሚጫወትም ይታመናል፡፡ ሐረሪዎች ይህንን ዕለት ከተለያየ የሰብል ዓይነት ተደባልቆ የተፈጨውን ዱቄት ገንፎ በማድረግ እየተመገቡ የነቢዩ ኖኅን ከመርከባቸው የመውረድ ታላቅ ዕለት ያከብሩታል፡፡ ሐረሪዎች ከዚህም በተጨማሪ ለጅቦች ገንፎ በመመገብ «ከአውሬም ጭምር» በሰላም አብሮ የመኖር ቃል ኪዳናቸውን በማደስ ያከብሩታል፡፡ ይህም ሐረር በቱርኮች (ግብፆች ተይዛ በነበረችበት የተወረሰም ይሁን ቱርኮች (ግብፆች ከሐረሪዎች የወረሱት መሆኑን እንድናጠናው የሚያደርገን ነው፡፡  በቱርክና በግብፅ የዓሹራ በዓል ረሃብና እርዛት እንዲሁም ቤት አልባነት እንዲወገድ መላ የሚመታበት ዕለት ሆኖም ይከበራል፡፡ 

የዓሹራ በዓል በኢትዮጵያ

ከብዙ ዓመታት በፊት ወደ ሐጅ የሚኬደው እንደ ዛሬ በአውሮፕላን ወይም በትልልቅ መርከቦች አልነበረም። መንገዱም ውጣ ወረድ የበዛበት፣ ሽፍታ፣ ወንበዴ ወይም ሌላ ዘራፊ መንገድ እየጠበቀ የሚቀማበት፣ ከዚያም በላይ የሚገደሉበት ነበር። ከዚህም በተጨማሪ፣ እንደ ወባና ድንገተኛ በሽታዎች ያሉ የሰውንይወት ይቀጥፉ ነበር። ስለዚህም ኢትዮጵያውያንና የምሥራቅ ሱዳን ሐጃጆች ሐጅ ከመካሄዳቸው ከሦስት አራት ወራት ቀደም ብለው ወደ አንድ መካከል መሰብሰብ አስፈለጋቸው። ያም ማዕከል መንፈሳዊና ማኅበራዊ ፋይዳ ያለው መሆን ነበረበት። ያም ቦታ ነጋሺ ነበር። ነጋሺን ማንኛውም ሙስሊም መዘየር እንዳለበት የኢማም አሕመድ ተከታዮች የሚነግሩን በመሆኑ ቅንጣት ታህል የሚያጠራጥር የለውም።

ይህም በመሆኑ የሦስትና የአራት ወራት ስንቃቸውን የሰነቁ ሐጃጆች በበቅሎ፣ በፈረስ፣ በአህያና በግመል ጭነው በመምጣት ድንኳኖቻቸውን ነጃሺ ላይ ይተክላሉ። ተጓዦች ተጠቃለው ሲመጡም ዱዓ እየተደረገ፣ እንዴት ሐጅ እንደሚደረግ አንዱ ከሌላው ልምድ እየወሰደ፣ ሐጅ መካ መዲና ሲደረስ ብዙ ሕዝብ ስላለ መጠፋፋት እንዳይኖር እየተመከረ፣ መጥፎ ተላላፊ በሽታ ስላለም ምን መደረግ እንደሚገባ ማስጠንቀቂያ በጀምዓ ሶላት ወቅት እየተሰጠ ይሰነብትና በአንድ ላይ ጉዞ ይጀመራል። በሙሐረም አሥር ተጠቃሎ ወደገር ለመመለስም ቀጠሮ ይወሰዳል። በመጨረሻም ስዋንኪን (ዛሬ ሱዳንድሮ ኢትዮጵያ) ወይም ምፅዋ ይደረሳል። እዚያም በቡድን በቡድን እየሆኑ በጀልባ በመሳፈር ወደ ጅዳ መጓዝ ነው። ጅዳ ከደረሱ በኋላ ወደ መካና መዲና አንድም በእግር ሐሩር በረሃውን አቋርጦ መጓዝ ከተቻለም በግመል መሄድ ነው።

መካ ከተደረሰ በኋላም አንድም ድንኳን ተከራይቶ ካለበለዚም ጥግ ይዞ የራስን ምግብ እራስ እያዘጋጁ ሐጂ ማድረግ ነው። በሐጅ ጊዜ መታመም፣ መሞት፣ መጥፋት ሊኖር ይችላል። አጠናቀው ከመካና መዲና ወደ ጂዳ፣ ከዚያም በሄዱበት መንገድ አንድም በምፅዋ ካልሆነም በስዋንኪን ወደ ነጃሺ መምጣት ይጀምራሉ። እስከ ሙሐረም አሥር ሁሉም ተጠቃለው ለመግባት በተሰማሙት መሠረት እዚያ ስለሐጅና ከአመስላማዊ ሕይወት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ሲለዋወጡ ይቆያሉ። ስላመጧቸው ኪታቦችና ምረቃዎች ጭምር። የሞተ የታመመ፣ የጠፋ ወዘተ ከሞላ ጎደል ይታወቃል። በመጨረሻም በአገር ውስጥ ዲናዊ ሥራዎችን ለመሥራት ቃል ገብተው ወደየመጡበት ይመለሳሉ።

ስለዚህ ወደ ሐጂ ሲኬድም ሆነ ከሐጅ ሲመለሱ ነጃሺ የሚገናኙበት መሠረታዊ ምክንያት ለኢስላማዊ ጉዳይ ነበር። ነጃሺ እንደ መካና መዲና ሁሉ የመላው ኢትዮጵያውያን ብቻ ሳትሆን የመላው ዓለም ሙስሊሞች መዲና ናት። የሚገርመው የመዲናም ትይዩ ናት። ሙሐረም አሥር ከመላው ኢትዮጵያ፣ ከሱዳን፣ ከሱማሊያ፣ ከጅቡቲ፣ ከኤርትራ በትንሹም ከሌሎች አገሮች መጥቶ አላህን ማመስገንና ማወደስ የተለመደ ነበር። እንደ ጎንደርና ወሎ ያሉትም ኸልዋ አላቸው። ሌሎችም ነበራቸው። ትልቁ ግን የኤርትራ ነው። የሌላቸውም ሁሉም ነጃሲ የሚገኝ ቤት ሁሉ ቤታቸው ነው። ከፈለጉ ቀኑን በሙሉ እየተዘዋወሩ የተዘጋጀውን ሰደቃ መካፈል ይቻላል። የትግራይ ክልል አስተዳደርላፊነትም ለነጃሺ ጎብኝዎች እንደ ሳዑዲ መሪዎች ሁኔታዎችን ማመቻቸት ነው። ሌሎችም የፓለቲካ ጉዳይ ማድረግ አይጠበቅባቸውም። ነገሩን ለሃይማኖት አባቶች ይተውላቸው።

የዓሹራ ምንዳ

አንዳንድ ሊቃውንት በዓሹራ በዓል መጾም 10,000 ሰማዕት ወይም 10,000 ሰዎች ሐጅና ዑምራ የሚያደርጉ በረከት (ምንዳ) ያህል እንደሚያገኙ ያስተምራሉ፡፡ በዚህ ዕለት 1,000 ጊዜ ‹‹ሱረቱል ኢኽላስ›› መድገም፣ የሚችለውን ያህል ምጽዋት መስጠት፣ ገላውን መታጠብ፣ ጥፍሮቹን መቁረጥ፣ የታመሙ ሰዎችን መጠየቅ አዳምን መጎብኘት እንደሆነም ይገልጻሉ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ውኃ ማቅረብ ከፍተኛ ምንዳ እንዳለው ይነገራል፡፡

በዓሹራ በዓል የሚታዩ ፖለቲካዊ እንከኖች

የዓሹራ በዓል ቀደም ሲል በተጠቀሰው መልኩ በልዩ ልዩ አገሮች የሚከበር ቢሆንም ከእምነት ጋር ብቻ ሳይሆን ከፖለቲካ ጋርም እየተቀናጀ የሚከበርበት ሁኔታ ይኖራል፡፡ በዚህም መሠረት የፖለቲካና የሃይማኖት አባቶች ከሃይማኖታዊነት ይልቅ በፖለቲካ ፋይዳው ጎላ ያለ መልዕክት በማስተላለፍ ይጠቀሙበታል፡፡ ይህም ሃይማኖታዊ ፋይዳውን በማደብዘዝ አሉታዊ ሚናውን በመጫወት ረገድ አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ አልፎ አልፎም ቢሆን ግን ከአመጽና ከሁከት ጋር የሚከበርበት አለ፡፡ በተለይም የሺዓና የሱኒ ውዝግብ ባለባቸው የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች እንዲሁም በአፍጋኒስታንና በአካባቢው አገሮች የመወራከብ ሁኔታ ሆን ተብሎ የሚፈጸምበት ቀን፣ አንዳንድ ጊዜም ንጹሐን ዜጎች የሚገደሉበት ቀን ሆኖ ይውላል፡፡ ከእነዚህም መጥፎ ቀናት ውስጥ 11 ዓመታት በፊት በኢራን በተለይም በኢማም ረዛ አድባር (መቃብር) ይደረግ በነበረው የጸሎት ሥነ ሥርዓት 25 ሰዎች የሞት ሰለባ መሆናቸው፣ ከስምንት ዓመታት በፊት የኢራቅ ሺዓዎች በካራባላ ጸሎት ሲያደርሱ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሙስሊሞች በፈነዳ ቦምብ መሞታቸውና መቁሰላቸው፣ የዛሬ አራት ዓመት በዚችው አገርና በባስራና ናስሪያ 20 ሺሕ ወታደሮች ለጥበቃ ቢሰማሩም 263 ያህል ሰዎች በተፈጠረው ውዝግብ መገደላቸው፣ የዛሬ አራት ዓመት በኢራን በተፈጠረው ግጭት ከፍተኛ ጉዳት መድረሱ ለአብነት ያህል የሚጠቀስ ነው፡፡

የዓሹራ በዓል አከባበር በአገራችን

በአገራችን የዓሹራ በዓል የተጀመረው ከጥንት ጊዜ ጀምሮ እንደሆነ አያጠያይቅም፡፡ ከእነዚህም ውስጥ በትግራይ በተለይም በነጃሺ፣ በሐረሪ ክልል በተለይም በሐረር፣ በኦሮሚያ በተለይም በድሬሸኽ ሑሴን፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች በተለይም በስልጢና በሌሎችም የጉራጌ ዞኖች፣ በአማራ በተለይም በወሎ ያለማቋረጥ የዓሹራ በዓል ሲከበር እንደነበር አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ የትግራይንና የሐረሪን እንደምሳሌ እንውሰድ፡፡

ትግራይ

በትግራይ ውስጥ የውቕሮ ነዋሪ የሆኑትን ሸኽ ማሕሙድ መሐመድ የተባሉ አዋቂና ታዋቂ ነዋሪ እንዲሁም የዓዲግራቱ ተወላጅና የነጃሺና የውቅሮ ነዋሪ የሆኑት ሐጅ ሙሐመድ መሐመድ ሰዒድ እንዳስረዱኝ የጥንት ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች በተለይም የመካከለኛውና የሰሜን ኢትዮጵያ ሙስሊሞች ወደ ሐጅ የሚሄዱት በትግራይና በኤርትራ አድርገው ስለነበር ነጃሽን ጎብኝተው እዚያም ጸሎት አድርገው መሄድና ከሐጅም ሲመለሱ የዓሹራን በዓል እዚያ አክብረው ወደ የክልላቸው መሄድ የተለመደ ነበር፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ከመላው ኢትዮጵያ የተውጣጡ ሙስሊሞች የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮች አጽም ወዳረፈበት ወደ ነጃሺ የዓሹራን በዓል ማክበር የተለመደ ነበር፡፡ በነጃሺ ከልዩ ልዩ ክልሎች ለሚመጡ እንግዶች ማረፊያ ስፍራ (ኻልዋ) ዱሮም የነበረ ቢሆንም የአካባቢው ሙስሊም የፍየልና የበግ ሙክት፣ ሰንጋ በሬና መሲና ላም አርዶ እንጀራ ጋግሮና አዘጋጅቶ እንዲሁም ውኃ አቅርቦ በነፃ ማስተናገድ የተለመደ ነበር፡፡

በነጃሺ የዓሹራ በዓል የሚከበርው በሁለት መንገድ ሲሆን አንደኛው በመብላት ሁለተኛው በመጾም ነው፡፡ የሚበላውም ሆነ የሚጾመው አንዱ የሌላውን ስሜት ከቶ አይጎዳም፡፡ ከአስተናጋጆች በስተቀር ተስተናጋጆች ዋነኛ ሥራቸው የነቢዩ ሙሐመድ ተከታዮችንና ሌሎች ሙስሊሞች የተቀበሩባቸውን ቅዱሳን ሥፍራዎች በመጎብኘት ጸሎት ማድረስ፣ መስገድ፣ በዜማም ለፈጣሪ ምስጋና፣ ለነቢዩ ሙሐመድ፣ ለሃይማኖት አባቶች ውዳሴ ማቅረብ ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የቁርዓንና የሐዲስ ትምህርቶች ይሰጣሉ፡፡ በነጃሺ የዓሹራ በዓል አከባበር ምናልባት በሁለት ከፍሎ ማየት ይቻል ይሆናል፡፡ አንደኛው ከአውሮፕላን መፈጠር በፊት ሁለተኛው ከአውሮፕላን መፈጠር በተለይም መርከብን ከተካ በኋላ ብሎ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ከአውሮፕላን መፈጠር በፊት የመካከለኛውና የሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች ወደ ሐጅ የሚሄዱት በምፅዋ በኩል አድርገው ስለነበር በነጃሺ በኩል አድርገው ይሄዱና ይመለሱ ነበር፡፡ አውሮፕላን ሙሉ በሙሉ መርከብን ከተካ በኋላ ሰው ወደ ሐጅ የሚጓዘው ከአዲስ አበባ በመሆኑ በነጃሺ የመሄዱና የመመለሱ ነገር እንዲቀንስ አድርጎታል፡፡ ስለሆነም ወደ ነጃሺ በዓሹራ በዓል የሚመጡት ከሐጅ መልስ ለመጎብኘት ፍላጎት ያላቸውና የዓሹራን በዓል እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ሙስሊም በነጃሺ ማክበር ያለባቸው መሆኑን የሚያምኑ ናቸው፡፡

የዓሹራን በዓል ለማክበር ወደ ነጃሺ የሚመጡ ሙስሊሞች የሚያርፉት አንድም አያት ቅድመ አያቶቻቸው በሠሩላቸው ኻልዋ ወይም ከነዋሪዎቹ ጋር በአንዱ ወይም በሌላ መልኩ በመጠጋት ሲሆን ካላቸው የራሳቸውን ምግብ ለማዘጋጀት፣ ካልቻሉ ደግሞ ከሌሎች በነፃ ለመመገብ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቢያንስ በአንድ ጊዜ እስከ 500 ሰዎች የሚስተናገዱበት የሐጅ አብዱ ቤተሰቦች ያሠሩት አዳራሽ ሲኖር የወሎና የጎንደር ሙስሊሞችም ዘመናዊ ሕንፃ እያሠሩ ነው፡፡ በተለይም በሐጅ አብዱ ቤተሰቦች የተሠራው ሰፊ አዳራሽ በርካታ ብሔር ብሔረሰቦች የሚገቡበት ስለሆነ ሕያው የብሔረሰብ  ሙዚየም ይመስላል፡፡ ይኸው ለብዙ ዓመታት በአገልግሎት ላይ የሚገኝ በግንብ የተሠራ አዳራሽ እድሳት የሚባል ነገር ዞሮ ያየው ስለማይመስል ከመፈራረሱ በፊት ጉዳዩ የሚመለከታቸው ክፍሎች አስቸኳይ እድሳት ቢያደርጉለት የሚሻል መሆኑን ጸሐፊው በዚህ አጋጣሚ ለመጠቆም ይወዳል፡፡ የዓሹራ በዓል በነጃሺ ሲከበር በርካታ ተመጽዋቾች፣ ልዩ ልዩ ሸቀጣ ሸቀጥ የሚሸጡ ነጋዴዎች፣ ቤት አከራዮች ውኃ አቅራቢዎች ተጠቃሚ የሚሆኑ ሲሆን በተለይም የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ክፍሎች በዚህ ዕለት እጥረት ስለሚታይ ወደፊት የተቀናጀ ዝግጅት ቢደረግ መልካም መሆኑን ጸሐፊው ለማስታወስ ይወዳል፡፡

እስካሁን እምብዛም ትኩረት ያልተሰጠው የነጃሺ መስጊድና የመቃብር ሥፍራ የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ «ኢማም አሕመድ ኢብራሂም» በሚል ርዕስ 2000 ባሳተመው መጽሐፍ (እትም አንድ) እንደገለጸው የመጀመሪያዎቹ የኢስላም ሐዋርያትና የነቢዩ መሐመድ የቅርብ ዘመዶች ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የተቀመጡት በዚሁ ነጃሺ በተባለው ስፍራ እንደሆነ መቃብሮቻቸውና ታሪኮቻቸው ይመሰክራሉ፡፡ በአገራችን በአንዱ ወይም በሌላው ምክንያት ገና ሙሉ ትኩረት ያልተደረገበትና በታሪካዊነቱ ተጠቃሚ ለመሆን ጥረት ያልተደረገበት ቢሆንም የዓለምም ሆነ የአገራችን የኢስላም ታሪክ ከመካ ቀጥሎ በነቢዩ ሙሐመድ አሳሳቢነት ወደ አገራችን በተለይም ወደዚህ ሥፍራ በመጡ የነቢዩ ቤተሰቦች፣ ዘመዶችና ወዳጆች ነው፡፡

ወደ ነጃሺ መሄድ ታሪካዊ መሠረታዊ ምክንያት አለው?

የነቢዩ ጓደኞች ፍዳቸውን የሚያዩበት፣ ነቢዩ ራሳቸው ከሚደርስባቸው አደጋ ለመታደግ የአጎታቸውን የዘመዶቻቸውን ጥበቃ በፈለጉበት ጊዜ፣ ተከታዮቻቸውን በመጥራት «እሱ ባለበት ሁሉ አንዳችም ፍትሕ የማይጓደልበት የሐበሻ ንጉሥ አለ፡፡ አላህ ለሙስሊሞች የተመቻቸ ሁኔታ ፈጥሮ እስክትመለሱ ድረስም ወደ ሐበሻ ሂዳችሁ ተቀመጡ» አሉን፡፡ ይህንንም ስንሰማ ብዙ ሆነን ተሰበሰብን፡፡ ደግመውም «የተባለው ሥፍራ (ሐበሻ) ጥሩ ነው፡፡ እዚያም ያሉ ጎረቤቶቻችን ሃይማኖታችንን ይጠብቁልናል» በማለት ነገሩን ይላሉ፡፡

ነቢዩ ሙሐመድ በፈጣሪ ድጋፍ አሸንፈው በመዲናና በአካባቢው ሰላም መረጋገጥ ሲጀምር ወደ አገራቸው ለመመለስ በቅተው የስደቱን ታሪክ ለነቢዩ ሙሐመድ ተረኩ፡፡ በመሠረቱ በሐበሻው ንጉሥና በነቢዩ መሐመድ መካከል የነበረው ግንኙነት በእጅጉ የጠበቀ ሲሆን የተመሠረተው ቀደም ሲል እንደተጠቀሰው ንጉሡ ከልጆቻቸው አንዱን በእሳቸው ሥር ተኮትኩቶ እንዲያድግ ሲልኩ ነቢዩ መሐመድ ደግሞ የአቡ ሱፍያን ልጅ የሆነችው ሐቢባ 7ኛው ሒጅራ ዓመት ላይ ወደ ሐበሻ መጥታ በነበረችበት ጊዜ ያገቧት (ኒካህ ያሠሩት) ንጉሥ አስሐማ የሳቸው ወኪል ሆነው በመገኘት ነው፡፡ ፊዳአሉል አዕማል ላይ በሰሐቦዎች ታሪክ ምዕራፍ ሠፍሮ እንደምናገኘው፣ በሌላው ተመሳሳይ ትረካ እንደሰፈረው ደግሞ ኻሊድ ኢብን ሰዓድ ኢብን አልዓስ ወደ ሐበሻ ከተሰደዱት አንዱ ሲሆን እሱም «እነዚህ ሱሐባዎች ከበድር ጦርነት በኋላ ከሐበሻ ሲመለሱ የአላህ ነቢይ ተቀበሏቸው፡፡ በበድር ጦርነት ተካፋይ ባለመሆናቸውም ሐዘናቸውን ገለጡላቸው፡፡ የፈጣሪ መልዕክተኛ ግን ከቶ ምን አስጨነቃችሁ እዚህ ያሉት አንድ ጊዜ ወደ ሒጅራ (ስደት) ሲሄዱ እናንተ ግን አንዴ ወደ ሐበሻ፣ ከዚያም ወደኔ ስትመጡ ሁለት ጊዜ ተሰዳችኋል» አሏቸው፡፡

አቡ ሙሳ የተባለ ሶሐባ እንደሚተርከው ደግሞ፣ ከአገራችን 53 ሰዎች ሆነን ወደ ሐበሻው ንጉሥ አገር ተሰደድን፡፡ እዚያው እንደደረስን ጃዕፈር ቢን አቢ ጣሊብን አገኘን፡፡ ከሱም ጋር አብረን ወደ መዲና እስክንመለስ በምድር ሐበሻ ቆየን፡፡ እንደተመለስንም የአላህ መልዕክተኛን ከኸይበር ጦርነት ድል በኋላ አገኘናቸው፡፡  ከዚያ በስፍራው የነበሩ ጥቂት ሰዎች አስማ ቢንት ዑመይላ፣ የነቢዩ ባለቤት ሐፍሳና ዑመር ጨምሮ «እኛ ከአላህ መልዕክተኛ ጋር በመሆን ወደ መዲና የተሰደድን ስንሆን እናንተ ግን ወደ ሐበሻ አገር የተሰደዳችሁ ናችሁ፡፡ ስለዚህ የአላህ መልዕክተኛን የምንቀርበው እኛ ነን፤» አሉ፡፡ ነቢዩ ሲመጡም አንድም ነገር ሳትጨምርም ሳትቀንስም የተባለውን ነገረቻቸው፡፡ እሳቸውም ምን እንደመለሰላቸው ካዳመጡ በኋላ «እናንተ ከእነሱ አትርቁኝም፡፡ እነሱም ከእናንተ አይቀርቡኝም፡፡ ዑመርና ጓደኛቹ የተሰደዱት አንድ ጊዜ ሲሆን እናንተ ግን የተሰደዳችሁት ሁለት ጊዜ ከመሆኑም በላይ በመርከብ ነው፤» በማለት አበሰሯቸው፡፡

በሌላም ሐዲስ አሰማ ቢንት ዑማይስ የአላህ መልዕክተኛን «አንዳንድ ሰዎች ስደትን በሚመለከት ከእኛ የበለጠ ለእርስዎ ቀረቤታ እንዳላቸው አድርገው ይናገራሉ» ብላ ብትጠይቃቸው እናንተ ሁለት ጊዜ ስለተሰደዳችሁ ሁለት ነጥብ አላችሁ» ብለው እንደመለሱላት ተመዝግቧል፡፡ በጥቅሉ የነቢዩ ሙሐመድ የቅርብ ተከታዮች ወደ ሐበሻ ያደረጉት ስደት (ሒጅራ) በኢስላም ታሪክ ታላቅ ቦታ የተሰጠው ክስተት መሆኑና አገራችን ኢትዮጵያም የእስልምና እምነት የሚከተሉ እንግዶችን በማስተናገድ ረገድ ግንባር ቀደም ቦታ ያላት መሆኗን ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡ መሐመድ ኢብን ሐቢብ እንደተረከው የአላህ መልዕክተኛ በአንድ ወቅት «እኔ ራሴን ብሆን የምሰደድባት የቴምር ተክል ያለባትን አገር አይቻለሁ» አሉ፡፡ በዚህ ጊዜ ሐቢብና የስደት ጓዶቻቸው ጃዕፈር ወደ ባሕር ተጓዙ፡፡ (ፈዳኢሉል አዕማል ገጽ 431)

በየጊዜው ወደ ሐበሻ የመጡት ሙስሊሞች በጣም በርካታ ሲሆኑ ሁሉንም ማቅረብ በጣም አስቸጋሪ ነው፡፡ ይሁንና በታሪክ ዐምዶች ትዝታቸው በማይረሳ መልኩ ተጽፈው ከሚገኙት አንዱ ሙስዓብ ነው፡፡ ሌላው አይረሴ ስደተኛ ከቤተሰቡ ማለት የነቢዩ መሐመድ ልጅ ከሆነችው ከሩቂያ ጋር ወደ ሐበሻ/ኢትዮጵያ የተሰደደው ዑስማ ቢን አፋዓን ቃተዳ የተባለው ሶሐባ ነው፡፡ ነዳር ኢብን አናስ ሲናገር እንደሰማሁትም ዑስማን ኢብን አፋን ተሰደደ፡፡ ነቢዩ ሙሐመድ የባልና የሚስቱን ወደ ሐበሻ መሰደድ የሰሙትም ትንሽ ዘግየት ብለው ነበር፡፡ ይህንንም ዜና የሰጧቸው አንዲት የቁረሽ ነገድ አባል የሆኑ አሮጊት ሲሆኑ እሳቸውም «አማችህ ከሚስቱ ጋር በደከመች አህያ ሲጓዝ አይቸዋለሁ» አሏቸው፡፡ እሳቸውም «አላህ ይጠብቃቸው በእውነቱ ዑስማን ከነቢዩ ሎጥ ቀጥሎ ቤተሰቡን ይዞ ለአላህ ሲል የተሰደደ ነው፤» አሉ፡፡

ከላይ ከተጠቀሱት ሶሐባዎች በተጨማሪ በመቶ የሚቆጠሩ ባልና ሚስቶች ከልጆቻቸው ጋር ተሰደዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተወለዱትም ብዙዎች ነበሩ፡፡ ከእነዚህም መካከል የነቢዩ ሙሐመድ ሚስት፣ ልጅና የቅርብ ቤተሰብ አባላት ይገኙበታል፡፡ ከመጡት ውስጥም ሕይወታቸው አልፎ መካነ መቃብራቸው በአገራችን አፈር የሚገኝ በርካታ ናቸው፡፡ ኢድሪስ ሙሐመድ «ኢትዮጵያና እና ኢስላም» በሚል ርዕስ በተረጎሙት መጽሐፍ ውስጥ በስፋት እንደተገለጸው ስማቸው ከሚታወቁት ወንዶች ውስጥ 94 ዝርዝር መረጃ ሲገኝ ከሴት ሶሐቦች መካከልም 26 በዝርዝር ሰፍሯል፡፡ እንደዚሁም ከወላጆቻቸው ጋር የመጡ 13 በሐበሻ ምድር የተወለዱ 20 በድምሩ 33 ሕፃናት ኢትዮጵያዊ ሰብዕና ያላቸው ናቸው፡፡ እንዲሁም በሐበሻ ምድር ሕይወታቸው ያለፈ 14 ወንዶችና ሴቶች ይገኙበታል፡፡ (በተጠቀሰው መጽሐፍ ከገጽ (38-85) ለመሆኑ በዚህ ታሪካችን ምን ያህል ተጠቅመንበታል? ሌላው ሁሉ ቀርቶ በዓለም የሚገኙ ሙስሊሞችን እንዲጎበኙ በማድረግና ኢስላሚክ ቱሪዝም በማስፋፋት በየዓመቱ በቢሊዮኖች የሚቆጠር ገቢ ልናገኝ አንችልም ነበር? ነጋሺ የተባለችውን ስፍራ በዓለም በደማቁ የምታበራ ልናደርጋት አንችልም? ነጋሺ በመብራቷ ሌሎች የኢትዮጵያ ሃይማኖታዊ በረከቶችን ልናይበት አንችልም?

ማጠቃለያ

የዓሹራ በዓል ሃይማኖታዊ ቢሆንም በውስጡ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ እንዳለው አያጠያይቅም፡፡ በዚህም መሠረት ሕዝቦች እርስ በርስ ለመገናኘት፣ ለመወያየት፣ ልምድ ለመለዋወጥ የሚያስችል ከመሆኑም በላይ ብሔራዊ ኩራት እንዲዳብር ያደርጋል፡፡ በትግራይም ይሁን በወሎ፣ በሐረሪም ይሁን በጎጃም፣ በጎንደርም ሆነ በኦሮሚያ ያሉት ኢስላማዊ ማዕከላት የበለጠ እንድንፋቀር፣ የበለጠ አብረን እንድንሠራና እንድንበለጽግ የሚያደርጉን መሆናቸውን ልብ ልንለው  ይገባል፡፡ በሰበበ ዓሹራ ሊሠሩ የሚችሉት የልማት ተቋማት ለሌላ ጊዜ ከፍተኛ ጠቀሜታ ይኖራቸዋል፡፡ ለምሳሌ ነጃሺ በነፋሻነቱ ተመራጭነት ያለው ስፍራ ከመሆኑም በላይ ዙሪያውን ሌሎች ታሪካዊ ስፍራዎችም ያሉበት ስለሆነ ትልልቅ ሆቴሎች ቢሠሩ ያለማቋረጥ የገቢ ምንጭ የሚገኝበት ሊሆን ይችላል፡፡ የሐረሪም፣ ንጉሥም፣ገታም፣ የመርሳም፣ የሆጂራ ፎቂሳም፣ የሐሸንጌም፣ የስልጤው ሐጅ ዓሊየም፣ የአብሬቱም፣ የድሬ ሸኽ ሑሴንም በአጭሩ በሁሉም ክልሎች ያሉ ቅርሶቻችን ጥበቃና ክብካቤ እየተደረገላቸው እንዲቀጥሉ ቢደረግ ጠቀሜታው ከብዙ አንፃር የሚስተዋል ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles