Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየሰላም ዋጋ

የሰላም ዋጋ

ቀን:

ትልቅ ባለመስታወት ቁም ሳጥን ነው፡፡ የሰው አጽም ሞልቶታል፡፡ የራስ ቅል በአንድ በኩል፣ ሌሎች አጥንቶች በሌላ በኩል ብዙ ናቸው፡፡ የትኛው ከየችኛው ብሔር እንደመጣ፣ የትኛው ከየትኛው ሃይማኖት እንደሆነ፣ የትኛው ቀይ ይሁን ጥቁር፣ የትኛው ሐባሻ ይሁን ፈረንጅ መለየት በፍጹም አይቻልም፡፡ ሁሉም ግን ሰው ሆነው እንዳለፉ አጽማቸው ማሳያ ነው፡፡

ይህ ባለመስታወት ቁም ሳጥን የሚገኘው በቀይ ሽብር ሰማዕታት መታሰቢያ ሙዚየም በአንዱ ክፍል ነው፡፡

ይህ ሙዚየም ያለፈውን ስህተት ማሳያ አሁን ላለው ትውልድ ደግሞ ትልቅ የማስተማሪያ መሣሪያ ነው የሚሉት የብራቭራ አፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ወ/ሮ ሕይወት አዳነ ናቸው፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ስህተት ሳይሠራ አልፎ ቀጣይ የሚመጣው ትውልድ መታሰቢያ ሙዚየም እንዳይገነባ ማድረግ ይኖርበታልም ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአሁኑ ሰዓት ከ70 በመቶ በላይ የሚሆን ወጣት የሚኖርባት አገር ናት፡፡ ወጣት ላይ መሥራት አገር ላይ መሥራት ነው በማለት ቭራቭራ አፍሪካ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የወጣቶችና የበጎ ፍቃድ ማስተባበሪያ ቢሮ ጋር በመተባበር ‹‹ግጭትን በማስወገድ ዘላቂ ሰላምን ማስፈን›› በሚል ርዕስ የፓናል ውይይት ማክሰኞ ነሐሴ 28 ቀን 2011 ዓ.ም. በጊዮን ሆቴል አዘጋጅቶ ነበር፡፡

የፓናሉ ዓላማ ሰላምን ማስፈን እንደሆነ የገለጹት ወ/ሮ ሕይወት፣ ሰላም እንዴት ሊመጣ ይችላል? ሰላም ምን ዓይነት ቦታ አለው? የምናውቀውን ሰላም በሌላ እይታ እንዴት አድርገን ልናየው እንችላለን? እስከመቼ ድረስ ነው መጠፋፋታችንና መጋጨታችን የሚዘልቀው? ላሉብን ችግሮቻችን መፍትሔ የምንሰጥበት ሁኔታዎችን ማመቻቸት አይሻልም ወይ? ያለንበት አዙሪት ወደ ቀድሞው እየመለሰን ስለሆነ ይህንን እንዴት ልንፈታው እንችላለን? የሚለውን  ለመምከርም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ የመገጫጨት፣ የመገዳደል እንዲሁም የመጠፋፋት በቂ ታሪክ አላት፣ ታሪካችን የተመሠረተው አንደኛው አንደኛውን በማሸነፍና በመጉዳት ላይ ነው፡፡ ይህ ትውልድ ያንን እያደረገ በቆየበት ጊዜ ሌላው ዓለም እኛ ያሉንን ዕውቀቶች እየወሰደ እየተጠቀመበት ከፍተኛ ሥልጣኔ ላይ ደርሷል፤›› ብለዋል፡፡

እየተወሰደ ያለውን ዕውቀት በማስቆም፣ ከመጠላለፍ ውስጥ በመውጣት ያሉትን ዕውቀቶች ወደ ተግባር ለመቀየር የሚዘጋጅ ትውልድ መፍጠር መቻል እንደሚገባና ወደ ሥራ የሚገባ ትውልድ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡ ከመገዳደል ማንም እንደማያተርፍም፣ ከዚህ በፊት በነበረው የመገዳደል ታሪክ የተረፈው ቀይ ሽብር ሙዚየም እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዚህ የፓናል ውይይት ሐሳባቸውን ካጋሩት አንዱ ገለታ ሰሚሶ (ዶ/ር) ሲሆኑ፣ በሰላም ጉዳይ ለብዙ ጊዜያት የሠሩ ናቸው፡፡ ዶ/ር ገለታ አንድ ነገር ስናጣው ነው ዋጋውን ምናውቀው በማለት ሰላምም እንዲሁ ሲታጣ ዋጋው እንደሚታወቅ ተናግረዋል፡፡

ትኩረታቸውን ያደረጉት ትውስታ ላይ ሲሆን፣ ‹‹ተባብረን ምናይበት ዕይታ ልክ አይደለም›› ብለዋል፡፡ ትውስታዎቻችን ጀብደኞች ናቸው ያሉት ዶ/ር ገለታ፣ እንደ ምሳሌ ያነሱት መስከረም ሁለት ሲባል ጃንሆን የወደቁበት መወሳቱና ግንቦት 20 ሲባል ደርግ የወደቀበት መታሰቡን ነው፡፡

አርቆ አሳቢነትን መነጠቅ፣ የትውስታ ዋነኛ ጉዳት እንደሆነ፣ እያንዳንዱ ሰው በብሔሩ መኩራት አለበት ሲባል የሌላውን እየጎዳ መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ትልቁ ችግር የብሔር ማንነት የተመሠረተው በጥላቻ መሆኑ ነው፣ ይህንን መቀየር የሚችለው ወጣቱ ነው በማለት ተሳታፊ ለነበረው ወጣት በአደራ መልክ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ‹‹ይህ ካልሆነ ግን መተላለቅ ከፊት ለፊታችን እንደተጋረጠ ይሰማኛል›› ብለዋል፡፡

ከጥግና ጥግ መካከል ክፍተት ይታየኛል የሚሉት ባለሙያው፣ ‹‹ሲያጣላ ምንሊክ ሲያስታርቅ ሉሲ›› በማለት የነበረውን ሰው ፈገግ አሰኝተዋል፡፡ ሁሉም ሲያልፍ ታሪክ ስለሚሆን፣ ለራስ ብሎ ቅን መሆን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡ ሌላው ሐሳቡን ያጋራው የሳይኮሎጂ ባለሙያው አቶ ራፋቶኤል ወርቁ ነው፡፡

አቶ ራፋቶኤል፣ ‹‹ኢትዮጵያውያን ነፃ አይደለንም ነፃ ግን እንሆናለን ስንል  እንደመጣለን ነገር ግን በትክክል ነፃ ነን ወይ? በማለት ጥያቄ አንስተዋል፡፡ የጋራ ንቃተ ህሊናና የግል ንቃተ ህሊናን ምንነት ያስረዱ ሲሆን፣ የግል ንቃተ ህሊና ምንለው የመጣንበትን ማኅበረሰብ ስንረዳ ነው፣ የጋራ ንቃተ ህሊና የራሳችንን ንቃተ ህሊና ተረድተን የሌሎችንም ስንረዳ ነው ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያዊነት በጋራ ሆነን የፈጠርነው ነው ያሉት ራፋቶኤል፣ ከዚህ ቀደም ተደፍሮ የነበረው መሬታችን ቢሆንም፣ አሁን ላይ እየተደፈረ ያለው ንቃተ ህሊናችን መሆኑን፣ ከጋራ ንቃተ ህሊናም የግል ንቃተ ህሊናን እንድናስቀድም ተደርጓል ሲሉ አክለዋል፡፡

በሥርዓተ ትምህርት፣ በፊልም እንዲሁም በተለያዩ ነገሮች ኢትዮጵያውያን ተቀርፀው በተለየ አቋም ተገዝተዋል የሚል አቋም እንዳላቸውም አንፀባርቀዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያዊ በጋራ ምን አሳክተናል ሲሉም ጥያቄን አቅርበዋል፡፡ ኢትዮጵያ መንግሥትን ለመፍጠር የመጀመርያ አገር እንደሆነች በመግለጽ፣ መጽሐፍ ቅዱስንም እንደ ምሳሌ አንስተዋል፡፡

የሕይወት ዘይቤ መምህሩ አቶ ጀምበሩ ኃይሌ ‹‹ልዩነታችን መተኪያ የሌለው መምህራችን ነው›› ይላሉ፡፡ በቀለምና በአቋም የተለያዩ ወፎችን እንደምሳሌ በማሳየት፣ በልዩነታቸው ውስጥ አንድነታቸውን ለማሳየት በመሞከር ሰውም ቢሆን፣ በልዩነቱ ውስጥ አንድነት እንዳለው ለማሳየት ሞክረዋል፡፡

የሰው ልጅ ጠላቱ ማነው? በማለት ጥያቄ ያነሱ ሲሆን፣ የሰው ልጅ ብቸኛ ጠላቱ ድንቁርና፣ እንደሆነ፣ ድንቁርናንም ብረት የሚያስውጥ እልኸኝነት፣ ምኩን ውቅረ አዕምሮ ሲሉ ገልጸውታል፡፡

በመጨረሻም አብሮ መልማት ወይስ አብሮ መጥፋት? በማለት መልሱን ለታዳሚው በመተው አጠናቀዋል፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...