Thursday, November 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የማይከብድ ነገር ለምን ይከብደናል?

ሰላም! ሰላም! በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የደረሰብኝን ልንገራችሁ፡፡ በቅርቡ እነ አምታታው በከተማ መኪና እንጭንልሃለን ብለው ሙልጭ አድርገው የበሉት ወዳጄ፣ ከፀበል መመለሱን ሰማሁና ልጠይቀው ሄድኩ። ገና ሲያየኝ እግሬ ሥር ወድቆ ምን ቢለኝ ጥሩ ነው? ‹‹አደራህን ሰው አትመን፣ የዘንድሮ ሰው ገንዘብህን ቢያጣ ቀልብህን መስረቁ አይቀርም፤›› አይለኝ መሰላችሁ? ወይ እንባና ሳቅ? እኔም ምንተ እፍረቴን፣ ‹‹አይዞህ እኔ ባንተ የደረሰው አይደርስብኝም. . .›› ብዬው ተለያይተን ወዲያው ስክለፈለፍ ለውዴ ማንጠግቦሽ የበዓል ወጪ የሚሆን ገንዘብ ፍለጋ ወደ ባንክ ሄድኩ። የሰው ልጅ ውጣ ውረድ፣ የማግኘትና የማጣት እኩል በረከተ መርገም እያብሰለሰለኝ ፈዝዣለሁ። ለማንጠግቦሽ ሳልነግራት ዝም ብዬ አንድ አሥር ሺሕ ብር ላውጣ? ደግሞ በኋላ ያነሳት እንደሆነስ? እያልኩ ጭንቅ ጥብብ ብሎኛል። የዘንድሮ ገንዘብ አገባቡ እንጂ አጠፋፉ ስለማይታወቅ መቼም ማሳበቢያ አይጠፋም። ለማንኛውም በበዓል ምድር ውድ ባለቤቴ የፈቀደችውን ታደርግበት ዘንድ አስቤ የገንዘቡን መጠን መጨመር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ ሺሕ ዓመት አይኖር፡፡ የነገውን የፈጠረን ያውቃል ብዬ ወደ ባንኩ ተንደረደርኩ፡፡

እንዲሁ የባጥ የቆጡን እያሰብኩ የወጪ ማዘዣ ፎርም ላይ 15,000 ብር ብዬ ጻፍኩ። ስጽፍ የቁልፍ መያዣዬን ከእነ ቁልፎቹ ጠረጴዛው ላይ መርሳት። ኋላ አንዲት ወይዘሮ፣ ‹‹ማን ነው ቁልፍ የረሳው?›› ብላ መጮህ። ሐሳብ ይዞኝ የለ? የእኔ ነው ሳልል ልቀበላት ስጠጋት ቁልፉን ወረወረችው። አሁንም ቀልቤ ከሰው ልጅ ውጣ ውረድ የተሞላበት ኑሮ ላይ እንጂ አኳኋኗን አላጠናሁም። ገና ቁልፌን ከማንሳቴ ወረደችብኛ። ‹‹የዘንድሮ ሰው ምሥጋና እንኳን ጠፋ. . .›› ቅብጥርሴ እያለች በባንክ ቤቱ ሠራተኞችና ደንበኞች ዓይን በትዝብት አጉላላችኝ። በሐሳብ መናወዜ እንጂ ለምሥጋና የምለግም ከንቱ አልነበርኩም፡፡ ‹‹ምነው እህቴ ወረድሽብኝ እኮ! ስንቶች አገርን እያሳቀቁ መላ ቅጣችንን ሲያጠፉ እያየሽ በልበ ዝንጉነት ውስጥ ያለሁትን ወንድምሽን አሳቀልሽኝ፣ ይቅር በይኝ. . .›› ስላት ሁኔታዬ አሳዘናት መሰል፣ ‹‹ይቅርታ ወንድሜ!›› ብላኝ በሰላም ተለያየን፡፡ ስንቶቻችን እንሆን እንዲህ ፀብን ወደ ሰላም መቀየር የምንችለው የሚለውን ሳስብ፣ የዘመናችን ሰው ጉዳይ አልያዝ አልጨበጥ አለኝ፡፡

መቼስ ጉድ አንድ ሰሞን ነው። ያቺን 15,000 ብር አውጥቼ አምስቱን በቀኝ አሥሩን በግራ ኪሴ ከትቼ እጓዛለሁ። ጎንበስ ብዬ ጫማዬን ሳየው ቆሽሿል። ቆይ ላስቦርሽ ብዬ ሊስትሮ ዘንድ ቁጭ አልኩ። በኋላ ሳስበው ነው ላዳዋን ባንክ ቤቱ አካባቢ ማየቴ ትዝ የሚለኝ። ከመቀመጤ ወዲያው አራት ሰዎች የጫነች ላዳ ታክሲ መጥታ ከሊስትሮው አጠገብ ቆመች። ጋቢና የተቀመጠው ይለፈልፋል፣ ለውዝም እየፈለፈለ ይበላል። እናም በወሬ መሀል ሳያስበው አስመስሎ አፉ ውስጥ ያለውን ለውዝ ወደ እኔ ተፋው። እኔ ከመደንገጤ በፊት እሱ ክው አለ። ወዲያው ሁለቱ ዘለው ከላዳዋ ወረዱ። ‹‹ይቅርታ አለቃ. . . ማረኝ እባክህ. . . ወይኔ. . . ወይኔ. . .›› እየተባባሉ ከተቀመጥኩበት አስነስተው ያራግፉኝ ጀመር። ትህትናቸው ልቤን ጭልጥ አድርጎት እጨነቃለሁ፣ እነሱ ግን አንዱ ተንበርክኮ ሌላው አጎንብሶ በከፍተኛ ትጋት ትፋቱን ይጠርጉልኛል፡፡ አንደኛው ደግሞ በሁለት እጄ ያስጨበጠኝን የታሸገ ውኃ እየከፈተልኝ በይቅርታ ያጨናንቀኛል፡፡

እኔ ይኼ ሁሉ ሲሆን መርበትበታቸው አሳዝኖኝ፣ ‹‹ግዴለም በቃ. . .›› ብዬ በግድ ገፍቼ ከሸኘኋቸው በኋላ ነው ግራ ኪሴን እንደ ቀለለኝ የታወቀኝ። አሥር ሺው የለም። ወዴት ልሩጥ? ማንን ልጥራ? ምን ልሁን? ምን ልጨብጥ? ‹‹እሪ. . .›› አልኩ። ጅብ ከሄደ ሆነና ነገሩ የአላፊ አግዳሚው መሳቂያ ሆንኩ። ወይ አዲስ አበባ? ወይ እኔ አንበርብር ምንተስኖት? እንዲህ ከፊት ጀምረን ከኋላ እንቅር? ማለቴ ይህችን ይህችን እንኳን መጠርጠር ያቅተን? እና ይኼውላችሁ ለበዓል የቤት ወጪ ብዬ ያወጣሁት አሥር ሺሕ ብር ለእኔ ማልቀሻ፣ ለሌቦቹ ያልታሰበ ሲሳይ ሊሆን ሄደ። እኔም አውጥቼ አውርጄ ሳበቃ ‹ጦሴን› ብዬ ዝም አልኩ። አዲስ ዓመትን በደስታ ለመቀበል ስዘጋጅ ይህ ውርጅብኝ ቢደርስብኝም፣ እኔ ግን ተስፋ አልቆርጥምና የጠፋውን ለመተካት ታጥቄ ተነስቼ ተፍ ተፍ ማለት ነበረብኝ፡፡ ለማን ደስ ይበለው ብዬ ነው ባለፈ ነገር እየተብሰለሰልኩ ነገዬን የማበላሸው!

ሳይደግስ የማይጣላው አምላክ መቼስ ደግ ነውና ወዲያው ስልኬ ጠራ። ብድግ ሳደርገው፣ ‹‹ሰባት ሚሊዮን ብር የሚገመት ያበደ ዘመናዊ መኖሪያ ቤት አለና ገዥ ፈልግ፤›› ብሎ አንድ ወዳጄ ቱስ አለኝ። እኔም ያችን አሥር ሺሕ በነበረችበት ለማየት ተፍ ተፍ ስል ውዬ ከሰዓት በኋላ አካባቢ አንድ አዛውንት ደወሉ። ‹‹ማን ልበል?›› ስላቸው ያ ስለቤቱ የነገረኝ ወዳጄ ቤት መግዛት የሚፈልጉ መሆናቸውን አውቆ የእኔን ስልክ እንደሰጣቸው ያጫውቱኛል። ተመልከቱ እንግዲህ የሰው ልጅ በሁለት ምድብ ተከፍሎ ገበጣ ሲጫወት። እንግዲህ ከዚህም ሆነ ከእነዚያ ሌቦች ወንድሞቼ ጋር በሥጋ አንገናኝም። ሰው በመሆን ግን አንድ ነን። የምርጫ ጉዳይ ሆኖ እነዚያ ያልለፉበትንና ያልደከሙበትን በመንጠቅ ሲያምኑ፣ እዚህ ግን ቤቱንም ገዥውንም አሳልፎ የሚሰጥ ወዳጅ እግዜር ከጎኔ አስቀምጧል። ይኼን አስቤ ስለእህል ውኃና ስለነፃ ፈቃድ ማሰብ ጀመርኩ። ውሎ አድሮ ከምሁሩ የባሻዬ ልጅ ጋር ስናወራ፣ ‹‹ዕጣ ፈንታ የሚባል ነገር የለም፣ ያለው ነፃ ፈቃድ ብቻ ነው፤›› አለኝ። ልቤ በመቀበልና ባለመቀበል መሀል ቢዋልልም ዕጣ ፈንታ የለም ለማለት ግን የምደፍር ግብዝ አይደለሁም፡፡

ይኼ የባሻዬ ልጅ እያደር እኔን ግራ በማጋባት ሱስ ተጠምዷል ልበል እያልኩ፣ ‹‹ያው አይደለም ወይ ምንም ዓይነት ሕይወት ለመኖር ነፃ ፈቃዱ እጃችን ላይ ካለ ዕጣ ፈንታም እኮ አብሮ ነው፤›› ስለው አንድ ታሪክ አጫወተኝ። ‹‹ንጉሥ አርተር ይባላል. . .›› አለ ሰውዬው። ‹‹ኋላ ነው ንጉሥ የተባለው። በግማሹ ሮማዊ በግማሹ ደግሞ እንግሊዛዊ ነው። በዘመኑ ሕግ ማንኛውም ሰይፍ ለማንሳት የደረሰ የበኩር ልጅ ሁሉ ከያለበት ተለቅሞ ለ15 ዓመታት የሮም መንግሥት ልዩ ወታደር እንዲሆን ይመለመላል። አርተር ወደ ሮም የሚመለስበትን ቀን እየናፈቀ ለ15 ዓመታት በእንግሊዝ አገር አሳለፈ። ኋላ ግዴታውን ጨርሶ ሂድ ሲባል እግሩም ልቡም እንቢ አሉት። ነፃነት ከውስጥ እንጂ ከውጭ እንደማይወሰን ገባው። እናም. . .›› አለኝ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ሰዎች በሚመርጡት የአኗኗር ዘዬ የታሰሩ ወይ የተፈቱ ናቸው። ዕጣ ፈንታ የምትለው እሱ ነው፤›› ሲለኝ ነቃሁ። የዘንድሮ ሰው ደግሞ ያቃተው ነገር ቢኖር መምረጥም አለመምረጥም ሆኗል። ሆሆ!

መቼስ ያለ ምክንያት ሰው ይብላኝ እንደማይባል ታውቃላችሁ። በእነ አምታታው በከተማ በጠራራ ፀሐይ ገንዘቡን ተበልቶ፣ ወይ ሽማግሌ ወይ ሕግ ያላስመለሱለት ካልሆነ በቀር ማለቴ ነው። ይኼን ስላቸው ለአዛውንቱ ባሻዬ፣ ‹‹እህል እንጂ ገንዘብ ይበላል እንዴ?›› ብለው ለአገሩ እንግዳ ሆኑብኝ። ይኼኔ ልጃቸው ደለብ ያለ መጽሐፍ እያነበበ ፈንጠር ብሎ ተቀምጦ ነበር። ምን ቢል ጥሩ ነው? ‹‹በእህሉ ፈንታ ገንዘቡ በየቦታው ተዝረክርኮ ሲገኝ ታዲያ ሰው ምን ይብላ?›› አለና አረፈዋ። ባላየ ባልሰማ ባልነበረ ቡና ሳላከትም ወጥቼ ላጥ ስል፣ ማኪያቶ 30 ብር እየሸጠ የዋይፋይ ‘ኔትወርኩን’ መሰብሰብ ያቃተው ገጽታ ገንቢ ፎቅ ሥር ቆሜያለሁ። እንጃ ለምን እንደቆምኩ። ምናልባት ከገጽታ ግንባታው ያጋባብኝ ይሆናል ብዬ ይሆናላ። የሚሉንን ቀርቶ የምንለውን አጥርተን ማወቅ ያቃተን ጊዜ ላይ መሆናችንን ረሳችሁት? መቼ ይሆን ግን መርሳት ራሱን የሚረሳው? እንደ ዘበት የተረሳሳነው በዛን እኮ! እንደ ዘበት በአደባባይ ነሁላዩ ሲጨምር፣ ገፊ ሲደነፋ፣ ተገፊው ሲበዛ ዓይተን እንዳላየን ሆነ እኮ ሥራችን።  ለዚህም ኔትወርክን ሰበብ እናደርግ ይሆን?

 በሉ እንሰነባበት። ኪሴ በገንዘብ ተወጣጥሮ ሊቀደድ ደርሷል። ሳይደግስ አይጣላም አላልኩም? መጀመርያ የበዓል ወጪ ለውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ፣ ለቢራ የሚሆነኝን ቆንጥሬ አንስቼ፣ የቀረውን ባንክ ቤት ቀርቅሬ ወደ ተለመደችዋ ግሮሰሪ አመራሁ። እንደ ገባሁ በሩቁ ያየሁት ምሁሩን የባሻዬን ልጅ ነው። ቀን ስላናደደኝ ለንቦጬን ጥዬ ሄጄ አጠገቡ ተቀመጥኩ። መናገር ሲጀምር አቋረጥኩትና ያማረለት ከመሰለው እንደ ተሳሳተ አስረዳሁት። ‹‹ምንም ቢሆን ያለኸው ሦስተኛው ዓለም ነው፤›› ሲል አንዱ ከሩቅ ውሎአችንን እንደሚያውቅ ሁሉ ሲናገር ሁለታችንም ክው አልን። ለካስ ሰውዬው ሌላ ጨዋታ ይዞ ነው። ዕፎይ ከማለታችን የባሻዬ ልጅ በጥሞና አንድ የግሪክ አፈ ታሪክ አጫወተኝ።

‹‹ሲሲፈስ በግሪክ አፈ ታሪክ የኦሊምፒያ አማልክት ዋና አለቃ በሚባለው ዚውስ የተፈረደበት ግዞተኛ ነው። ዚውስ የፈረደበት የባህር አምላክን ሴት ልጅ ጠልፎ ሲያስወስዳት ሲሲፈስ ዓይቶ ለባህር አምላክ ስለነገረው ነው። ፍርዱ ምን ይመስልሃል ታዲያ? አንበርብር?›› አለኝ። እንዲህ በተረትና በምሳሌ ሲያጫውተኝ ደስ ስለሚለኝ፣ “ምኑን አውቄ?” አልኩት ፈታ እያልኩ። ‹‹ፍርዱ አንድ ረጅም ተራራ ጫፍ ላይ እንደ ኳስ የሚንከባለል ግዙፍ ቋጥኝ እየገፋ ማድረስ ነው። አደረስኩት ሲል ቋጥኙ ተመልሶ ይንከባለላል። በአጠቃላይ የእኛም ነገር እንደ ሲሲፈስ ሲሆንብኝ እየተናነቀኝ ነው፤›› ሲለኝ ተረዳሁት። በተለይ በተለይ፣ የተበላሹ ስሞቻችን ካልተስተካከሉ ትውልድ የሲሲፈስን ታሪክ ሲቀባበል እንደሚኖር ተገለጸልኝ። ‹የተማረ ይግደለኝ› እንዳልል በዚህ ዘመን ያልተማረው ነው ተሽሎ የተገኘው። የተማረው ማይም ይመስል አሳፋሪ ድርጊት ሲፈጽም፣ ያልተማረው ደግሞ ፈጣሪ በሰጠው አስተውሎት መካሪ ዘካሪ ሆኖ አገር ይጠብቃል፡፡

‹‹ሌብነት በዝቷል፣ እሴት ያለው ሕይወት የሚኖር ሰው አንሷል፣ እያዩ እንዳላዩ ማለፍ ባህል ሆኗል፣ በአጠቃላይ ስማችን ተበላሽቷል፣ ታዲያ ምን ይሻላል? የሚሻለውማ ኩሩ ሆኖ በጨዋነት መኖር ነው. . .›› የሚለኝ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ‹‹ነገሩ መልካም ቢሆንም ጨዋነት ብቻውን ምን ይፈይዳል?›› የእኔ ጥያቄ ነበር፡፡ ዘመኑ እኮ ብዙ ያናግራል! አይደለም እንዴ? ‹‹የጨዋነት ፋይዳው ዕኩይ ድርጊቶችን ተፀይፎ መልካም ተግባራትን ማከናወን ነው፡፡ ሌብነትን ማጥፋት፣ ክፋትን ማስወገድ፣ የዘመናት የጋራ እሴቶችን መንከባከብ፣ መከባበር፣ መፋቀር፣ መተዛዘን፣ ትውልዱን ማነፅ፣ አገርን ከድህነት ውስጥ በጋራ መንጭቆ ማውጣትና ማበልፀግ፣ ነፃነት፣ ፍትሕ፣ እኩልነት ማንገሥ. . .›› እያለ ሲነግረኝ ለራሴ ቃል እየገባሁ ነበር፡፡ የገባሁት ቃልም ጥሩ ሰው መሆን አለብኝ የሚል ነበር፡፡ መልካም መሆን አያቅትማ፡፡ አገርንና ወገንን መውደድ ከባድ አይደለማ፡፡ የማይከብድ ነገር ለምን ይከብደናል? መልካም ሰንበት!   

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት