Friday, September 22, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየስሜን ተራሮች በረከት

የስሜን ተራሮች በረከት

ቀን:

ወደ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ጉዟችንን ለማድረግ ከጠዋቱ አንድ ሰዓት ወደ ጎንደር የሚያቀናውን አውሮፕላን ለመሳፈር የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአገር ውስጥ  በረራ በሚካሄድበት ቅጥር ግቢ ውስጥ ተሰባሰብን፡፡

የመብረሪያ ሰዓታችን ከጠዋቱ ሁለት ሰዓት ከአሥር ስለነበር፣ ቀድሞ በነበረን የአንድ ሰዓት ቆይታ ከዚህ ቀደም ወደ ፓርኩ ሄደው ለማየት ዕድል የነበራቸው ጋዜጠኞች ስለ ፓርኩ ምድራዊ አቀማመጥ፣ ስለ አካባቢው ሰዎች፣ ስለ አየሩ ሁኔታ እንዲሁም ስለ ብርቅዬ እንስሳት እያወጉን ሰዓቱን ገፋነው፡፡ ሁለት ሰዓት ሲሆን፣ ወደ ተዘጋጀልን አውሮፕላን እንድንገባ በተነገረን መሠረት ወደ ጎንደር ወደሚበረው አውሮፕላን ተሳፈርን፡፡ በ24 ሺሕ ጫማ ከፍታ ከአዲስ አበባ ጎንደር አንድ ሰዓት በፈጀ በረራ አፄ ቴዎድሮስ አየር ማረፊያ ደረስን፡፡

ቀጣይ ጉዟችን ቀጥታ ወደ ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ ስለነበር ከጎንደር ወደ ፓርኩ ሊወስደን ወደ ተዘጋጀው መኪና አመራን፡፡ ፓርኩ ከጎንደር ከተማ በስተ ስሜን ምሥራቅ አቅጣጫ 120 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ጉዟችንን ከታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ጀመርን፡፡ ጎንደር በ1624 ዓ.ም. የተመሠረተች ከተማ ስትሆን፣ ከ5,500 ሄክታር በላይ የቆዳ ስፋት አላት፡፡ በጎንደር እምብርት የሚገኘው የፋሲለደስ ግንብም እስከ ዛሬ ድረስ የብዙ ቱሪስቶችን ቀልብ ስቧል፡፡ ይህን ታሪካዊ ቦታ አልፈን አምባ ጊዮርጊስን አገኘን፡ አምባ  ጊዮርጊስ ከጎንደር ከተማ 40 ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል፡፡ አምባ ጊዮርጊስ ስሜን ጎንደር የሚገኝ አለት ፍልፍል ቤተ ክርስቲያን ነው፡፡ የተሠራውም በ13ኛው ክፍለ ዘመን ነው፡፡ አምባ ጊዮርጊስን ስናልፍ ዳባት ወረዳን አገኘን፡፡ ዳባት ከጎንደር 75 ኪሎ ሜትር ርቆ የሚገኝ ሲሆን፣ ወረዳው በአብዛኛው በስሜን ተራራ ይሸፈናል፡፡ ከኢትዮጵያ ከፍተኛው ቦታ፣ የራስ ዳሸን ጫፍ እዚህ ወረዳ ይገኛል፡፡ አረንጓዴውን ዳባት ወረዳ አልፈን ከጎንደር ከተማ 100 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኘውን ደባርቅ ወረዳን አገኘን፡፡ ደባርቅ በ2,850 ሜትር ከፍታ ላይ ይገኛል፡፡ የሊማሊሞ ገደል የሚያልፈው ይህን ወረዳ ሰንጥቆ ነው፡፡

ከደባርቅ ቀጥሎ ማረፊያችን ወደ ሆነው ስሜን ሎጅ አቀናን፡፡ ስሜን ሎጅ የፓርኩ መግቢያ አካባቢ፣ በ3,260 ሜትር ከፍታ ላይ፣ ከጎንደር ከተማ 122 ኪሎ ሜትር ርቆ ይገኛል፡፡

በጣም ቀዝቃዛ ቦታ ነው፡፡ የስሜን ሎጅ ለዓይን ማራኪ ነው፡፡ ባህላዊ መልክና ይዘትም አለው፡፡

የተያዘልን አልጋ እዚያው ሎጅ ውስጥ ስለነበር ቦርሳችንን በየክፍላችን አስቀምጠን ለምሳ ተገናኘን፡፡ ከምሳ በኋላ ቀጣይ ጉዞችን ወደ ሳንቃበር እንደሆነ ተነገረን፡፡ ዋናው የመጣንበት ዓላማም ይኸው ነበር፡፡ የጉዞው አዘጋጅ ሃይኒከን ኢትዮጵያ በዋልያ ብራንድ ስም በቅርቡ ከኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጋር ባደረገው የሁለትዮሽ ትብብር ፊርማ የመጀመሪያ ድጋፍ ለማድረግ ያለመ ጉዞ ነው፡፡

ሃይኒከን ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሚዲያ የተውጣጡ ጋዜጠኞችን በማሳተፍ ያደረገው ጉዞ፣ ቁጥሩ እየቀነሰ የመጣውን ዋልያ ቁጥር እንዲጨምር እንስሳው የሚመገባቸውን ተክሎች ለመትከል እንዲሁም ለፓርኩ ጠባቂዎች አልባሳት የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ የታሰበ እንደሆነ የሃይኒከን ኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቃዱ ባሻህ ገልጸዋል፡፡ ሳንቃበር ለመድረስ በመኪና 20 ደቂቃ ከሎጁ ተጓዝን፡፡ ይህ ቦታ የተለያዩ እንስሳት መገኛ ሲሆን ድኩላ፣ ነብር እንዲሁም ጭላዳ በሰፊው ይገኛሉ፡፡ ታዋቂው ሳንቃበር ካምፕ ሳይትም ይገኛል፡፡ ቦታው ኃይለኛ ንፋስ የሚነፍስበት ቦታ በጉም የተሸፈነም ነው፡፡ እዚህ የመጣነው ችግኝ ለመትከል ሲሆን፣ በቦታውም የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ አቶ አበባው አዘናው ተገኝተው ነበር፡፡

እንደ አቶ አበባው ገለጻ፣ አሁን የሚከናወነው የችግኝ ተከላ ለአምስተኛና ለመጨረሻ ጊዜ ነው፡፡ ቀደም ሲል በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጥሪ መሠረት ሐምሌ 22 ቀን 2011 ዓ.ም. አገር አቀፍ የችግኝ ተከላ ቀን እንደነበር አስታውሰው ‹‹እኛ ከሐምሌ 22 አንድ ወር በፊት በደባርቅና ስሜን ጎንደር በሚገኙ ወረዳዎች በዘመቻ መልክ አከናውነናል፡፡ ከዚያ በኋላም ከሐምሌ ስምንት ጀምሮ ለአራት ጊዜ ከፍተኛ የሆነ የችግኝ ተከላ ዘመቻ አካሂደናል፤›› ብለዋል፡፡

አሞቻ፣ ወይራ፣ ውጨናን እንዲሁም የኮሶ ዛፍ ዝርያዎችን ጨምሮ ስድስት ዓይነት የሚሆኑ 38,200 የሚደርሱ አገር በቀል ችግኞችን ፓርኩ አካባቢ እንደተተከሉም ገልጸዋል፡፡ እኛም በሥፍራው በተገኘንበት የችግኝ ተከላ ፕሮግራም ግራር ተክለናል፡፡

በዚሁ ፕሮግራም ላይ የዋልያ ቢራ አምባሳደር ሲራክ ስዩምን ለመተዋወቅ ዕድል አግኝተን ነበር፡፡ ሲራክ ስዩም የኤቨረስት ተራራን የወጣ የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ በወጣቶቹ ዕድሜ ላይ የሚገኘው ሲራክ፣ ነዋሪነቱ በአሜሪካ ካሊፎርኒያ ነው፡፡

ሲራክ የስሜን ተራሮችን ሳቢ ሆኖ እንዳገኛቸው ከሪፖርተር ጋር በነበረው ቆይታ ገልጿል፡፡ እንደ ሲራክ አተያይ በስሜን ብሔራዊ ፓርክ ብዙ ምልክቶችን በመትከል ሰው ቦታዎችን በቀላሉ እንዲረዳ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ሥፍራው ቀላል እንዲሁም መካከለኛ ተብሎ ቢገለጽ፣ ሰው ምልክት እያየ እንደየአቅሙ ተራራዎችን እንዲወጣ ማድረግ እንደሚገባ ገልጿል፡፡ ‹‹እንዲህ በሚሆንበት ጊዜ ሰው በፕሮግራም ለመንቀሳቀስ ምቹ አጋጣሚ ይፈጠርለታል፤›› ብሏል፡፡

በማኅበራዊ ገጽም፣ ብዙ ቢሠራና የሚከፈለው ገንዘብ መጠን፣ የአየሩ ሁኔታ፣ ስንት ሰዓት እንደሚፈጅ የተከለከሉና ያልተከለከሉ ሥፍራዎች፣ ጉዳት የሚያደርሱ እንስሳት ያሉባቸውና የሌሉባቸው፣ የትና በየትኛው አቅጣጫ ምን ዓይነት እንስሳት ማየት እንደሚቻል ሙሉ መረጃ እዚያ ላይ ቢቀመጥ ብዙ የሚጎበኙ ሰዎችን መሳብ ይቻላል ብሎ እንደሚያስብም አክሏል፡፡ ይህ በማኅበራዊ ገጽ ብቻ ሳይሆን ተራሮቹ ላይ ጭምር አቅጣጫን ጨምሮ አመላካች ሆነው እንዲቀመጡም አክሏል፡፡

ከቀኑ 11 ሰዓት ሲሆን እዚያ የነበረንን የችግኝ ተከላ ሥነ ሥርዓት ጨርሰን ወደ ማረፊያችን ተመለስን፡፡ በነጋታው አመሻሽ ላይ ወደ አዲስ አበባ ስለምንመለስ በጠዋት ተነስተን ቦታዎቹን እንድንጎበኝና ዋልያዎችን ለማየት ዕድል እንዲኖረን ዕቅድ ይዘን ወደየማረፊያችን ተለያየን፡፡

ሐሙስ ነሐሴ 16 ቀን 2011 ዓ.ም. ጠዋት 1 ሰዓት ተኩል ላይ እዚያው ሎጁ ግቢ ውስጥ ተገናኝተን፣ ዋልያን ለማየት ጉዞ ጀመርን፡፡ ቅድሚያ ሳንቃበርን አገኘን፣ ከዚያ አምባ ራስን አየን ቀጥለን ግጭን አገኘን፡፡ ግጭን ስናልፍ ጨነቅን አገኘን ከዚያም ዋልያዎቹ ከሚገኙበት ቧይት ደረስን፡፡ ዋልያ እዚህ ፓርክ ውስጥ ብቻ የሚገኝ ብርቅዬ የዱር እንስሳ ነወ፡፡

በአሁኑ ሰዓት ወደ 1,000 የሚጠጉ ዋልያዎች በፓርኩ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ የዋልያ ዝርያ ከፍየልና ከበግ ይመደባል፡፡ ቀንዱ ወፈር ብሎ ረዘም ያለ ነው፡፡ የቆዳው ቀለም ጠቆር ያለ ቡኒ ነው፡፡ በአብዛኛው የወንዱ ዋልያ ኪሎ 125 ሲሆን፣ ሴቷ ደግሞ 80 ኪሎ ግራም ትመዝናለች፡፡ ሴቶቹ ፈካ ያለ ቡኒ ቀለም ሲኖራቸው፣ ወንዶቹ ደግሞ ጠቆር ያለ ቡኒ ቀለም አላቸው፡፡

እኛ እዚያ በደረስን ሰዓት ቆመው ነበር፡፡ ግን ወዲያው ሸሹ፡፡ ከጭላዳ ባቡን ጋር አንድ ላይ የሚሆኑት ዋሊያዎች፣ ሰው በሚመጣ ጊዜ ጭላዳዎቹ የሆነ ምልክት ይሰጧቸውና ዋልያዎቹ እንዲሸሹ ያደርጋሉ፡፡

በዚህ እየተደነቅን እዚያው ቧይት ላይ ሆነን 4543 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኘውን የራስ ዳሸን ተራራን ከርቀት አየነው፡፡ ይህ ተራራ በጠፋው ለዘር፣ አባ ያሬድ፣ ቀዳዳው ዋሻ፣ ወይናበር፣ አናሎ፣ ቧሂት ተራሮች መካከል ከፍ ብሎ ይታያል፡፡

በራስ ዳሸንና አባ ያሬድ ተራሮች መካከል ቅዱስ ያሬድ ዜማ ያስተማረበትና በመጨረሻም የተሰወረበት የዋሻ ገዳም ይገኛል፡፡ ተራራው ጥቅጥቅ ያለ ደን ነው፡፡ ቧሂት በ4,200 ሜትር ከፍታ ላይ የሚገኝ ተራራ ሲሆን፣ በጣም ከባድ ቅዝቃዜ አለ፡፡ እዚያ በነበርበን ሰዓት ኔጌቲቭ ሁለት ደርሶ ነበር፡፡ ግን የቦታው ማራኪና ሳቢ መሆን ቅዝቃዜውን ከቶ የሚያስረሳ ነው፡፡ ያየነውን አዕምሮአችን ላይ ከትበን ጉዟችንን ወደ መጣንበት ጀመርን፡፡

በዚሁ መሀል ከቦታ ቦታ ለጉዞው የሚረዱ መኪኖችን ያዘጋጀልንን የቶን ሬቭ አስጎብኚ ድርጅት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አሰፋ አስራት ከሪፖርተር ጋር በነበረው ጥቂት ቆይታ ስሜን ብሔራዊ ፓርክ ለአስጎብኚ ድርጅቶች በጣም ጠቃሚና አለ የሚባል ቅርስ እንደሆነ አወጋን፡፡

‹‹ሀገር ውስጥ ያለው ቱሪስት እንደጨመረ ይምጣ እንጂ በቂ አይደለም›› የሚለው ሥራ አስኪያጁ፣ በአብዛኛው የሚሠሩት የኮንፍራንስ ቱሪዝም እንደሆነ ገልጿል፡፡ ‹‹ከኅዳር እስከ ጥር ያሉት ወራት የቱሪስት ቁጥር ይጨምራል፣ በዚህም ጊዜ በአማካይ እስከ 15 ቀን ለሚቆዩ ቱሪስቶች በቀን ከ1500 ዶላር እስከ 2,000 ዶላር እናስከፍላለን፤›› በማለት የቱሪስት ቁጥር እንደወቅቱ እንደሚለያይ አቶ አሰፋ ገልጿል፡፡

ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ 412 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ስፋት አለው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1966 የተመሠረተው ይህ ፓርክ፣ በ1969 በነጋሪት ጋዜጣ ታውጆ ሕጋዊነቱን አገኘ፡፡ ባለው አስደናቂ መሬት አቀማመጥና ብዝኃ ሕይወት ብሎም በውስጡ አቅፎ ከያዛቸው ብርቅዬ ዱር እንስሳት አንፃር ታይቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለውን ፋይዳ በመገንዘብ እ.ኤ.አ. በ1978 በዩኔስኮ ተፈጥሯዊ የዓለም ቅርስ ተብሎ ተመዘገበ፡፡ በዚህ ጊዜ ግን 230 ኪሎ ሜትር ስኰዌር ስፋት ብቻ ነው የነበረው፡፡ የተለያዩ ጥናቶች ከተደረጉ በኋላ ግን ሊማሊሞ ገደልን፣ ራስ ዳሸን ተራራን የዋልያ የቀበሮና የጭላዳ ዝንጀሮ መራቢያ ሥፍራዎችን ጨምሮ ወደ 412 ኪሎ ሜትር ስኩዌር እንዲሆን ተደርጎ ዳግም ክለላ ተሠርቶ እ.ኤ.አ. በ2000 እንደገና በነጋሪት ጋዜጣ ታወጀ፡፡

ነገር ግን በዚህ መሀል እ.ኤ.አ. በ1991 በነበረው የእርስ በርስ ጦርነት የፓርኩ አስተዳደር በጣም ተዳክሞ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ አደን፣ እሳት ቃጠሎ ሕገወጥ እርሻ፣ ቤት ግንባታ ተንሠራፍቶ የነበረ ሲሆን በፓርኩ ያሉ ብርቅዬ እንስሳት ቁጥር በእጅጉ ተመናምኖ ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት እ.ኤ.አ.1996 ፓርኩ በዓለም የአደጋ መዝገብ ውስጥ ገብቶ ነበር፡፡ በዚህን ወቅት የጭላዳ ቁጥር በጣም ወርዶ የዋልያ ቁጥር 150 ደርሶ ነበር፡፡ ቀይ ቀበሮም ወደ 20 ወርዶ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ለኢትዮጵያ መንግሥትና ለአካባቢው ማኅበረሰብ በተሰጠው የቤት ሥራ ጥበቃው በመጠናከሩና በሕገወጥ የሰፈሩ ሰዎች በፈቃደኝነት (በተመጣጣኝ ካሳ) ወደ ሌላ አካባቢ ሄደው በመስፈራቸው ፓርኩ መልሶ ማገገም ችሏል፡፡ ዩኔስኮ የጠየቀውን ጥያቄ ከሞላ ጎደል የኢትዮጵያ መንግሥትና የአካባቢው ማኅበረሰብ በመመለሱ እ.ኤ.አ. በ2017 ከነበረበት የአደጋ መዝገብ አውጥቶታል፡፡

አፈጣጠሩ በእሳት ጎሞራ ምክንያት እንደሆነ የሚነገርለት ይህ ፓርክ፣ አሜሪካ ውስጥ ካለው ግራንድ ካንየን ጋር ብዙዎች ያመሳስሉታል፡፡ በዓለም ከተመዘገቡት አራት የተፈጥሮ ቅርሶች ስሜን ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ አንዱ ነው፡፡

ኢትዮጵያ ውስጥ አሉ ከተባሉ ሰባት አጥቢ እንስሳት (ብርቅዬ እንስሳት) አራቱ ስሜን ብሔራዊ ፓርክ ውስጥ ይገኛሉ፡፡ እነሱም ዋሊያ አይቤክስ፣ ቀይ ቀበሮ፣ ጭላዳ ባቡን (ጭላዳ ዝንጀሮ) እንዲሁም የምንሊክ ድኩላ ናቸው፡፡

ፓርኩ አምስት ወረዳዎችን የሚያዋስን ሲሆን፣ እነሱም ደባርቅ፣ ጃናሞራ፣ በየዳ፣ አደርቃይ እንዲሁም ፀለምት ናቸው፡፡ እነዚህ አምስት ወረዳዎች 42 የቀበሌ ገበሬ ማኅበራት ያዋስኗቸዋል፡፡ በእነዚህ ማኅበራት ከ50,000 በላይ የሚሆኑ አባወራዎችና እማወራዎች ይኖራሉ፡፡

ፓርኩ የአየር ሚዛንን በመጠበቅ ረገድ አገራዊ ፋይዳ አለው፡፡ በፓርኩ አካባቢ ያሉ ሥፍራዎች ከሌላ ቦታ ለየት ባለ መልኩ ጊዜውን ጠብቆ ዝናብ የማግኘት ዕድል አላቸው፡፡

በፓርኩ ዙሪያ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችም የውኃ መገኛቸው  ከስሜን ተራሮች በሚፈልቁ ምንጮች (ገባር ወንዞች) ነው፡፡ በአገራችን ያሉ ትልልቅ ፕሮጀክቶችም የውኃ ምንጫቸው የስሜን ተራሮች ናቸው፡፡ ወልቃይት ስኳር ፋብሪካና ተከዜ ሃይድሮ ኤልክትሪክ ግድብን እንደ አብነት መጥቀስ ይቻላል፡፡

በዚህ ዓመት 32,400 ቱሪስቶች ፓርኩን የጎበኙ ሲሆን፣ ከመግቢያ ክፍያ ሰባት ሚሊዮን ብር እንደተገኘ የፓርኩ ዋና ሥራ አስኪያጀ አቶ አበባው አዝናው ገልጸዋል፡፡ ማኅበረሰቡ በመንገድ መሪነት፣ በምግብ አብሳይነት፣ በበቅሎ ጫኝነት እንዲሁም በአጃቢነት ደረሰኝ በመቁረጥ ወደ 33 ሚሊዮን ብር ገቢ መገኘቱንም አክለዋል፡፡

ፓርኩ በየዓመቱ በደረሰኝ ገቢ ብቻ ወደ 40 ሚሊዮን ብር ለመንግሥትና ለማኅበረሰቡ እንደሚያስገባም ተናግረዋል፡፡ 

አቶ አበባው እንደገለጹት፣ ጎብኚዎች እዚህ መጥተው ቃል በሚገቡት መሠረት በዚህ ዓመት ሰባት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ሁለት ትምህርት ቤቶች እንደተከፈቱ፣ በባለፈው ዓመት አምስት ሚሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ትምህርት ቤት በደባርቅ እንደተገነባ ተናግረዋል፡፡ ጤና ኬላዎችም በተመሳሳይ እየተገነቡ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

90 በመቶ የሚሆኑ በስሜን ተራሮች ዙሪያ የሚገኙ ነዋሪዎች የኑሮ መሠረታቸው እርሻ ነው፡፡

በበየዳ፣ ፀለምትና ጃናሞራ በኩል ፓርኩ ምንም እንዳልተነካ የገለጹት አቶ አበባው፣ እስካሁን ቱሪስት የተጠቀመበት ወይም ያየው ከፓርኩ 20 በመቶ ያህሉን እንደሆነ ገልጸዋል፡፡በ2011 ዓ.ም. መጋቢትና ሚያዝያ አካባቢ በፓርኩ ድንገተኛ የእሳት ቃጠሎ መነሳቱ የሚታወስ ነው፡፡ በእሳት ቃጠሎው ፓርኩ ከያዘው 41,200 ሄክታር ውስጥ 1,040 ሄክታር በሳምንት ልዩነት ሁለቴ የእሳት አደጋ ደርሶበት ነበር፡፡

የፓርኩ ሥራ አስኪያጅ እንደገለጹት፣ ሁሉም አካላት ባደረጉት ርብርብ ሊደርስ የነበረውን ከፍተኛ ጉዳት መቆጣጠር ተችሏል፡፡ ‹‹የተጎዳው የፓርኩ ክፍል ሙሉ ለሙሉ እያገገመ ነው፡፡ ከተወሰኑ ዕፅዋቶች ውጪ አብዛኛው ዕፅዋትና ሳር ከክረምት መግባት ጋር ተያይዞ ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት እየመለሰ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ሪፖርተርም በቦታው ሆኖ ለማየት እንደሞከረው አብዛኛው የፓርኩ ክፍል በጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል፡፡   

የስሜኑን ትዝታ በልባችን ውስጥ አኑረን ጉዞ ወደ አዲስ አበባ ቀጠልን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ባለሙያዎች ኮሚሽን ሪፖርት ምን ይዟል?

ለአሜሪካ ድምፅ አማርኛ ዝግጅት የስልክ አስተያየት የሰጡ አንድ የደንበጫ...

መንግሥት በአማራ ክልል ለወደሙ የአበባ እርሻዎች ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በአማራ ክልል የተፈጠረው ግጭትና አለመረጋጋት በቢዝነስ...

አምናና ዘንድሮ!

እነሆ መስከረም ጠብቶ በአዲስ መንፈስ ተሞልተን መንገድ ጀምረናል። ‹‹አዲስ...