Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበሰኔ 15 ግድያ በሽብር የተጠረጠሩ 21 ግለሰቦች አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ለፍርድ...

በሰኔ 15 ግድያ በሽብር የተጠረጠሩ 21 ግለሰቦች አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ለፍርድ ቤት አቀረቡ

ቀን:

በባህር ዳርና በአዲስ አበባ ከተሞች ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. ከተፈጸመው ከፍተኛ የመንግሥት አመራሮች ግድያ ጋር በተያያዘ፣ በሽብርተኝነት ተጠርጥረው በእስር ላይ የሚገኙ 21 ግለሰቦች አካልን ነፃ የማውጣት ክስ ለፍርድ ቤት አቀረቡ፡፡

ሁሉም ተጠርጣሪዎች ታስረው የሚገኙት በአዲስ አበባ ከተማ ፖሊስ ኮሚሽን እስረኛ ማቆያ ጣቢያ ሲሆን፣ የጠረጠራቸው ደግሞ የፌዴራል ፖሊስ ነው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ አቶ ጀማል ሐሰን፣ አቶ አስጠራው ከበደ፣ አቶ ፋንታሁን ሞላ፣ ፶ አለቃ አምባ ገላዬ፣ አቶ በዕውቀቱ አግደው፣ አቶ ሞላልኝ መለሰና አቶ ሲሳይ አልታሰብን ጨምሮ 21 ናቸው፡፡ ተጠርጣሪዎቹ ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ፍትሐ ብሔር ተረኛ ችሎት ያቀረቡት አካልን ነፃ የማውጣት አቤቱታ፣ የፌዴራል ፍርድ ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ቁጥር 25/88 አንቀጽ 5 (10፣ 11 እና 14)፣ እንዲሁም የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 15 (2ቀ)፣ 177 (3) እና አንቀጽ 205 ድንጋጌዎችን ተከትለው መሆኑን በአቤቱታቸው አስታውቀዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ሰኔ 15 ቀን 2011 ዓ.ም. በተገደሉት ርዕሰ መስተዳድሩ አምባቸው መኮንን (ዶ/ር)፣ ዋና ዓቃቤ ሕግ አቶ ምግባሩ ከበደና የፕሬዚዳንቱ አማካሪ አቶ እዘዝ ዋሴ፣ እንዲሁም በተቀራራቢ ሰዓት በአዲስ አበባ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው በተገደሉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹም ጄኔራል ሰዓረ መኮንንና ጓደኛቸው ሜጀር ጄኔራል ገዛዒ አበራ ግድያ ጋር በተያያዘ፣ በሽብር ተግባር ወንጀል ጠርጥሮ እንደያዛቸው አስታውሰዋል፡፡፡ ፍርድ ቤት አቅርቧቸውም በአዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 20 ድንጋጌ መሠረት 28 ቀናት ለምርመራ አስፈቅዶባቸዋል፡፡ ፖሊስ በተሰጠው 28 ቀናት ውስጥ በተጠርጣሪዎቹ ላይ የሽብር ተግባር ስለመፈጸማቸው የሚያስረዳ ወይም ለጥርጣሬው መነሻ የሚሆን ማስረጃ ማቅረብ ባለመቻሉ፣ የፌዴራል የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት ሐምሌ 23 ቀን 2011 ዓ.ም. በዋስ እንዲወጡ ብይን መስጠቱን በአቤቱታቸው ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል መጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ብይን የተቃወመው የፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ ቡድን ለፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ይግባኝ በማለቱ፣ ተጠርጣሪዎቹም መቃወሚያቸውን ዘረዝረው ማቅረባቸውን ገልጸዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ያቀረቡትን የመቃወሚያ ሰነድና ክርክር ሳይመረምርና ሳይተነትን፣ ይግባኙን በመቀበልና የመጀመርያ ደረጃ ፍርድ ቤትን ብይን በማገድ የ48 ቀናት የምርመራ ጊዜ ለፖሊስ መፍቀዱን አስረድተዋል፡፡

ከፍተኛው ፍርድ ቤት ሳይመረምርና ትንታኔ ሳይሰጥ የሥር ፍርድ ቤትን ብይን ማገዱ ብቻ ሳይሆን፣ የፀረ ሽብር አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 20 ድንጋጌ ከሚፈቅደው ውጪ 48 ቀናት መፍቀዱ የተቋሙንም ሆነ የዳኝነት ሥራውን ግምት ውስጥ የሚጥል መሆኑን በመግለጽ፣ ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ይግባኝ ሰሚ ችሎት ማመልከታቸውንም አሳውቀዋል፡፡ ይግባኝ ሰሚው ችሎትም ያስቀርባል ካለ በኋላ፣ መዝገቡን መርምሮና አከራክሮ በሰጠው ፍርድ ከፍተኛው ፍርድ ቤት የሰጠው ፍርድና ትዕዛዝ ተገቢ እንዳልሆነ፣ 28 ቀናት ቢፈቅድ እንኳን ተጠርጣሪዎቹን ፍርድ ቤት ማቅረብ ያለበት ወይም ምርመራውን ማጠናቀቅ ያለበት ነሐሴ 14 ቀን 2011 ዓ.ም. በመሆኑ፣ ከዚያ በኋላ ያለው እስር ሕገወጥ መሆኑን በመግለጽ ውሳኔ ማሳለፉን ገልጸዋል፡፡

የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ውሳኔውን የሰጠው ነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. በመሆኑ፣ ወደኋላ የታሰሩበት ጊዜ ዋጋ ስለሌለው ውሳኔው ከተሰጠበት ከነሐሴ 27 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ባሉት ቀናት፣ ከቦታ ቦታ የመዘዋወር ነፃነታቸው መገፋቱንና በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጠላቸው የአካል ነፃነት መብታቸው መጣሱንም አስረድተዋል፡፡

በመሆኑም የታሰሩት ያለ ፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሆኑን በመግለጽ በጠበቆቻቸው አማካይነት አቤቱታቸውን አቅርበዋል፡፡ ፍርድ ቤቱም መርምሮ ብይን ለመስጠት ለሰኞ መስከረም 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...