በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የአዲስ አበባ አገር ስብከትን ጨምሮ ስድስት የተለያዩ አደረጃጀት ያላቸው ኅብረቶችና ማኅበራት፣ በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያንና አማንያን ላይ እየደረሱ ያሉትን የተለያዩ ዓይነት ጉዳቶችን አስመልክቶ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም. ሊደረግ የነበረው ሰላማዊ ሠልፍ መንግሥት ችግሩን ለማስተካከል ቃል በመግባቱ ተላለፈ፡፡
ማኅበራቱ ሰላማዊ ሠልፉን የጠሩት ለእሑድ መስከረም 4 ቀን 2012 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ ከጳጉሜን 1 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን፣ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተወካዮች ጋር ውይይትና ምክክር ማድረጋቸውን አሳውቀዋል፡፡ ጳጉሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ደግሞ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውንም አክለዋል፡፡ መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ደግሞ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከደቡብ፣ ከሶማሌ ክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ጋር በአካል ተገናኝተው ውይይት መጀመራቸውን ጠቁመው ከሐረሪ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝና ከድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ጋር ለመወያየትም ቀጠሮ መያዛቸውን አስረድተዋል፡፡
ማኅበራቱ እንዳብራሩት መስከረም 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር፣ ከአዲስ አበባ፣ ከኦሮሚያ፣ ከአማራ፣ ከሶማሌ፣ ከቤኒሻንጉል ጉምዝ፣ ከድሬዳዋና ከሐረሪ ፖሊስ ኮሚሽነሮች ጋር ውይይት ተደርጓል፡፡ ማኅበራቱ ወይም ኮሚቴው ይዞ የተነሳውን በቤተ ክርስቲያኗ ላይ እየደረሰ ያለውን ጥቃት ለማስቆም፣ አሥር ቀናት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ ዝርዝር ማስረጃ ቀርቦ ውይይት እንዲደረግበትና ለጥያቄዎቻቸውም ምላሽ እንዲሰጣቸው፣ በቀጣይ የመፍትሔ አቅጣጫዎች ላይ ከክልል ብሔራዊ መንግሥታትና ተወካዮቻቸው ጋር ውይይት በማድረግ፣ የባለቤትነት ችግሩ እንዲፈታ ስምምነት ላይ መደረሱን አስታውቀዋል፡፡
የፌዴራልና የክልል መንግሥታት ላቀረቧቸው ጥያቄዎች በሙሉ ምላሽ ይሰጣሉ የሚል እምነት እንደሌላቸው የጠቆሙት ማኅበራቱ ወይም ኮሚቴው፣ በየደረጃው ያሉ አካላት ከቸልታና ከማናለብኝነት ስሜት ወጥተው ለቤተ ክርስቲያን ዘብ ሲቆሙ መመልከት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡ እያንዳንዱ ከሕግ የተፃረረ ተግባር በተለይም በኦርቶዶክስ ሃይማኖት ላይ የተፈለገው እየተፈጸመ ያላንዳች ጥያቄ የሚኖርበት፣ ሌላው ደግሞ ስለአገርና ስለአንድነት በሚወስደው ኃላፊነት የተሞላበት አካሄድ እየተገፋ፣ ከሌሎች ጋር አብሮ በገነባትና ሲገነባት በኖረባት አገር ላይ ባይተዋር ሆኖ የሚሰደድባት አገር መሆን እንደሌለበት አስምረውበታል፡፡
በኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ እጁን ያነሳ ሁሉ የሚጠየቅበት፣ ጣቱን ከመቀሰር የሚሰበስብበትና ለፍትሕ የሚተጋ መንግሥት ያለባት አገር ሆና መመልከት እንደሚፈልጉም አክለዋል፡፡
ማኅበራቱ ወይም ኮሚቴው እንደገለጹት፣ እየጮሁ ያሉት ለኦርቶዶክስ ሃይማኖት ሰላም መከበር ብቻ ብለው አይደለም፡፡ የእምነት ነፃነት ሰፍኖ በእምነታቸው የተነሳ የተደፉ አንገቶች ቀና ብለው በመከባበር የሚኖሩባት ሰላማዊ አገር ስትሆን መመልከት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በማስመሰል መንፈስ ሳይሆን ከአያት ቅድመ አያቶች በተወረሰው ለፍትሕ የመወገን መንፈስ፣ አገርን ጭምር ለመታደግ የታለመ ቁርጠኝነት ያለው ዓላማ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
በመሆኑም ጥያቄዎቻቸው ሁሉ እስከሚመለሱ ድረስ ትግላቸውን በሰላማዊ መንገድ እንደሚቀጥሉም አስታውቀዋል፡፡ የተጀመረው የኅብረት ጉዟቸው ከገዳም እስከ ከተማ ድረስ ካሉ አባቶች ጋር በመመካከርና በጸሎታቸው በመታገዝ እዚህ መድረሳቸውን ጠቁመው፣ ሕዝቡ ‹‹የመንግሥት አካላት›› ቃል ከመግባት የዘለለ ዕርምጃ ላይሄዱ ይችላሉ የሚል ሥጋት ቢኖረውም፣ ሥጋቱ በእነሱ ውስጥም እንዳለና ጥያቄዎቻቸውን በቅድመ ሁኔታ ጭምር አቅርበው እስከሚወያዩና የሚመጣውን ተግባራዊ ለውጥ ለመመልከት እስከሚበቁ ድረስ፣ ሰላማዊ ሠልፉን በሁለት ወራት በመግፋት የተገባላቸውን ቃል እንደሚጠባበቁ ገልጸዋል፡፡
ጥያቄያቸው ምላሽ የማያገኝ ከሆነ ሰላማዊ ሠልፉን ጥቅምት 30 ቀን 2012 ዓ.ም. እንደሚያደርጉም አስታውቀዋል፡፡ ውይይቱን ከራሳቸው ፍላጎትም ሆነ አንዳንዶች ከሚሠጉት የፍርኃት መንፈስ በፀዳ ስሜት፣ የቤተ ክርስቲያንኗንና የምዕመናኑን ፍላጎትና ጥያቄ ብቻ አስቀድመው የሚቆሙ መሆናቸውን፣ በሕያው እግዚአብሔር ስም ቃል መግባታቸውንም አሳውቀዋል፡፡
ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ስለሚያቀርቡት ጥያቄና ስለሚነጋገሩባቸው ጉዳዮች፣ ከምዕመናኑ ጋር የሚመካከሩባቸው ሰፋፊ መድረኮችን እንደሚያዘጋጁም ጠቁመዋል፡፡ የሚደርጉትን የውይይት ሒደት፣ ውሳኔ፣ ውጤትና ሌሎች ጉዳዮች መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ይፋ እንደሚያደርጉ አስረድተዋል፡፡
ሰላማዊ ሠልፉን ጠርተው የነበሩት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን፣ የአዲስ አበባ አገር ስብከት ካህናት፣ የሰባኪያንና የዘማሪያን ኅብረት፣ የሰንበት ትምህርት ቤት አንድነት የወጣቶችና ጎልማሶች ኅብረት፣ የመንፈሳዊ ኮሌጅ ደቀ መዛሙርት፣ ምሩቃንና የመንፈሳዊ ማኅበራት ተወካዮች ናቸው፡፡