ካለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት ጀምሮ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ለኅብረተሰቡ የነበረው አበርክቶ ‹‹መጥፎ ጎኑ›› ካልሆነ ይህ ነው የሚባል ነገር አልነበረውም፡፡ ስፖርቱ በእነዚህ ዓመታት ማበርከት ከነበረበት ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ፋይዳ በተቃርኖ የማንነት ማቀንቀኛ ዓይነተኛ መሳሪያ ሆኖ ለዜጎች ሕይወት መጥፋትና ጉዳት እንዲሁም ለንብረት ውድመት መንስዔ ሲሆን ታይቷል፡፡ ችግሩን ሁሉም ወገኖች ‹‹ውግዝ ከመ አርዮስ›› ቢሉትም በመድረክና ከመድረክ ጀርባ ያሉ አካሄዶች ለየቅል እየሆኑ መድረኮቹ በተከናወኑ ማግስት የአንድ ከተማ ቡድን ወደ ሌላው የከተማ ቡድን ሄዶ እግር ኳሳዊ ድርሻውን መወጣት የማይችልበት ‹‹አዋጅ›› በማወጅ የመፍትሔው ቁልፍ ሊገኝ አልቻለም፣ በሁሉም ዘንድ የተበዳይነት ስሜት ካልሆነ ለሚበጀው ጊዜ ሳይኖረው የቁልቁለት ጉዞው እንደቀጠለ ይገኛል፡፡ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑን በማስተዳደር ላይ የሚገኘው የአቶ ኢሳያስ ጅራ ስብስብ ለችግሩ መፍትሔ ያለውን ሁሉ አድርጓል፣ እያደረገም ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል በብሔራዊ ፌዴሬሽኑ አወዳዳሪነት ቀጥሎ የቆየው ውድድር ከ2012 ጀምሮ ሊጉ ክለቦች ያመኑበት ራሱን የቻለ አወዳዳሪ አካል እንዲኖረው የዕቅድ ዝግጅት መጠናቀቁን ይፋ አድርጓል፡፡ እንደ ፌዴሬሽኑ ከሆነ ይህ ዕቅድ በቅርቡ በሚጠራው መደበኛ ጠቅላላ ጉባዔ ቀርቦ ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ሌላው እግር ኳሱ በአሁኑ ወቅት እያጋጠመው ላለው ትልቅ ተግዳሮት በአማራጭነት ለጉባዔው እንደሚያቀርበው የሚጠበቀው፣ የፕሪሚየር ሊጉን ተሳታፊዎች ቁጥር ወደ 24 ከፍ በማድረግ በሁለት ምድብ ከፍሎ ማጫወት የሚለው ይጠቀሳል፡፡ ይህም በሊጉ ሲያጋጥም የቆየውን ማለትም በትግራይና በአማራ ክለቦች፣ በደቡብ ክልል በሲዳማና በወላይታ ክለቦች፣ በትግራይ በመቐለ 70 እንደርታና አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ክለቦችና የአዲስ አበባዎቹ ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የማይገናኙበት የውድድር ሥርዓት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡ ይሁንና ፌዴሬሽኑ በአማራጭነት የያዛቸው እነዚህና ሌሎችም ሕግ ሆነው ተግባር ላይ የሚውሉት ለጉባዔው ቀርበው ውይይትና መግባባት ላይ ሲደረስ እንደሆነ የሚናገሩ አስተያየት ሰጪዎች ጉዳዩ ይሁንታ ባያገኝ የእግር ኳሱ ቀጣይ ዕጣ ፈንታ ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ቀላል እንደማይሆን ያላቸውን ሥጋት ያስቀምጣሉ፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንትና የሊግ ኮሚቴ ሰብሳቢ ኮሎኔል አወል አብዱራሂም ምንም ይሁን ምን መፍትሔ የሌለው ችግር ሊኖር እንደማይችል ያምናሉ፡፡ በእነዚህና ሌሎች ተያያዥ ወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ደረጀ ጠገናው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡– አዲሱ የውድድር ዓመት ሊጀመር የተቃረበበት የዝግጅት ወቅት ነው፡፡ እንደሚታወቀው ያለፈው ዓመት መርሐ ግብር ከጠንካራ ጎኑ ይልቅ ክፍተቱ ጎልቶ የታየበት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ተቋሙ በ2012 የውድድር ዓመት እነዚህን ከመሰሉ ችግሮችና አለመግባባቶች ተላቆ፣ በእግር ኳሱ የሚፈለገው ለውጥ ይመጣ ዘንድ በፌዴሬሽኑ በኩል ምን የታቀደ ነገር አለ?
ኮሎኔል አወል፡– አንዱና ትልቁ ነገር እኔ ክለብ በምመራበት ወቅትም ሳነሳውና ሳቀነቅነው የነበረው ክለቦች የራሳቸውን ሊግ ራሳቸው ማስተዳደር የሚችሉበትን ሥርዓት መፈጠር አለበት የሚል ስለነበረ አሁንም ይህ ጉዳይ ከግቡ መድረስ እንዳለበት የፀና እምነቴ ነው፡፡ የሚገርመው እኔን ጨምሮ ወደ ኃላፊነት የመጡት የሥራ ባልደረቦቼ የሁሉም እምነት ሆኖ አግኝቸዋለሁ፡፡ በመሆኑም ከ2012 የውድድር ዓመት ጀምሮ ክለቦች ሊጋቸውን እንዲያስተዳሩና እንዲመሩ ይደረጋል፣ እንደ ተቋምም ይህን ተግባራዊ ለማድረግ ዕቅዱ ተጠናቆ የጉባዔውንና የባለድርሻ አካላት ይሁንታ ብቻ እየጠበቀ ነው፡፡ ከዚህም በላይ ክለቦች ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን የሚያሳድጉበትና ዘርፉንም ወደ ቢዝነስ በመለወጥ ተጠቃሚ እንዲሆኑና ሊጉም ተወዳጅ ሆኖ እንዲቀጥል የሚያደርግ በ‹‹ቢዝነስ ካምፓኒ›› ደረጃ እንዲቋቋም ዕቅዱ በፌዴሬሽኑ ተዘጋጅቷል፡፡
ሪፖርተር፡– ፕሪሚየር ሊጉ ከስያሜው እስከ መዋቅራዊ ቁመናው በብዙ ክፍተቶች የተተበተበ መሆኑ ይታወቃል፡፡ የቢዝነስ ኩባንያ ሲባል እንዴትና በምን አግባብ ዕውን ለማድረግ ነው የታቀደው?
ኮሎኔል አወል፡– ከቢዝነስ ካምፓኒው ስያሜው ስንነሳ በአጭሩ ‹‹ኢትዮ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር›› የሚል ነው፡፡ ሌላው የፌዴሬሽኑ መተዳደሪያ ደንብ ሁሉም እንደሚያውቀው ይህ ቀረሽ የማይባል ክፍተት ያለበት ነው፡፡ ለዚህም ፌዴሬሽኑ ደንቡ ማሻሻያ ይደረግለት ዘንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ ሥራውን በአጥጋቢ ሁኔታ እያከናወነ ነው፣ በአጋጣሚም የዚህ ጥናት ቡድን ሰብሳቢ እኔ ነኝ፡፡ ጥናቱ ከተጠናቀቀ በኋላ በአጀንዳ መልክ ተይዞ ሥራ አስፈጻሚው ለጠቅላላ ጉባዔ እንዲያቀርበው ይደረጋል፣ ከዚያ በፊት ግን አጀንዳው ለክለቦች ተልኮ በግብዓትነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ሰነዱ ቀድሞ እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡
ሪፖርተር፡– የመተዳደሪያ ደንቡ ክፍተት የሚሏቸውን ዋና ዋናዎቹን ቢጠቅሱልን?
ኮሎኔል አወል፡– ከብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ኃላፊነቶች ጀምሮ አንድ ተቋም ሊኖረው የሚገባው የሕግ ማዕቀፍና አሁን በዚህ መድረክ እንዲህና እንዲያ ማለት የማንችላቸው በርካታ ክፍተቶች ያሉበት ነው፡፡
ሪፖርተር፡– የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ጽሕፈት ቤትና የሙያተኞች የአቅምና የክህሎት ውስንነት አሁን ተቋሙ እተገብረዋለሁ ለሚለው እንቅፋት እንዳይሆን ሥጋት ያላቸው አሉ።
ኮሎኔል አወል፡– እውነት ነው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጽሕፈት ቤቱን ለማዘመንና ለማሻሻል ሙሉ ቁርጠኛ ሆኖ እንቅስቃሴ ጀምሯል፡፡ ምክንያቱም ይህ ክፍል የተቋሙ ሞተር እንደመሆኑ እንደ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴም ለጉዳዩ ትኩረት መስጠት የጀመርነው ኃላፊነቱን ከተረከብንበት ሰዓት ጀምሮ ነው፡፡ እስካሁን የተሠሩ ሥራዎች ደካማና ጠንካራ ጎኖች ተገምግመዋል፣ ከዚህ መውሰድ የተቻለው ለፌዴሬሽኑ ተቋማዊ አደረጃጀት የአካዴሚክ ዕውቀት እንደተጠበቀ፣ ሌሎች ልምዶችንም ከነባራዊው ሁኔታ ጋር በማቀናጀት ማዋቀር ይቻል ዘንድ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ ምክንያቱም ሰሞኑን ከብሔራዊ ቡድን የጉዞ ዕቅድ ጋር ተያይዞ ሲነሱ የነበሩትን ብንመለከት፣ ከዚህ ክፍል የሚነሳ ድክመት እንዳለ በግልጽ እንረዳለን፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ጉዞ መስተጓጎል ጽሕፈት ቤታችን አሁንም ምን ያህል ደካማ እንደሆነ አይተንበታል፡፡ እዚህ ላይ አንዳንዶች ችግሩን ቀላል የሚያደርጉት አሉ፣ በግሌ በዚህ አልስማማም፡፡ ብሔራዊ ቡድን የአንድን አገር ብሔራዊ ኃላፊነት ይዞ የሚንቀሳቀስ አካል ነው፣ ለዚህ አካል ከጉዞ ጀምሮ ዕቅዶች ቀድመው ሊዘጋጁለት ይገባል፡፡ የጉዞ ዕቅድ ለአንድ ተቋም መሠረታዊ ነው፣ ምክንያቱም መነሻህን ቀድመህ ስታቅድና ስታውቅ ነው መጨረሻህ የሚሰምረው፡፡
ሪፖርተር፡– ከሊግ ካምፓኒው ጋር በተገናኘ፣ ክለቦች በዚህ ጉዳይ የጠራ ግንዛቤ እንዲኖራቸው በእናንተ በኩል ምን ጥረት ተደርጓል?
ኮሎኔል አወል፡– ከ2011 የውድድር መርሐ ግብሮች ጎን ለጎን የተለያዩ መድረኮች ተፈጥረው ውይይቶች ሲደረጉ ቆይቷል፡፡ ክለቦች አፈጻጸሙ ላይ ካልሆነ ሊግ ካምፓኒው ላይ ያን ያህል ግርታ የለባቸውም፡፡ በዚያ ላይ በጥናት ቡድኑ የተዘጋጀው ሰነድ ከነመመሥረቻና መተዳደሪያ ደንቡ ጭምር ተልኮላቸዋል፡፡ ክለቦች ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ያላቸውን ሐሳብ ለጉባዔው እንዲያቀርቡና በእዚያም ላይ ውይይት የሚደረግበት ነው የሚሆነው፡፡ የካምፓኒው መመሥረቻ ጉባዔ መስከረም 13 ቀን 2012 ዓ.ም. በኢትዮጵያ አየር መንገድ አዲሱ ስካይ ላይት ሆቴል ይደረጋል፡፡ በዕለቱ የሚኖሩት ሁለት አጀንዳዎች አንደኛው የካምፓኒው መመሥረቻና መተዳደሪያ ደንብ ላይ ተወያይቶ ማጽደቅ ሲሆን፣ ሁለተኛው የካምፓኒው የቦርድ አመራሮች ምርጫ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡– በካምፓኒው የፌዴሬሽኑ ድርሻና ኃላፊነት ምንድነው?
ኮሎኔል አወል፡– ካምፓኒው ሙሉ በሙሉ ራሱን ችሎ የሚንቀሳቀስ እንደመሆኑ እዚህ ላይ የፌዴሬሽኑ ድርሻ እንደ አንድ ባለድርሻ ካልሆነ ሌላ ሚና ሊኖረው አይችልም፣ ልክ እንደ አንድ ክለብ ማለት ነው፡፡ ተቋሙ እንደ ባለድርሻ በአንድ ሼር ይወከላል፣ ይህ ማለት ግን የኢትዮጵያን ሕጎች መመሪያና ደንቦች ከማክበር አኳያ የበላይ አካል መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ የካፍና ፊፋ ደንቦችና መመሪያዎች ተግባራዊ መሆን አለመሆናቸውን ይቆጣጠራል፣ ያስፈጽማል፣ ይከታተላል፡፡
ሪፖርተር፡– ባለፈው የውድድር ዓመት ከውድድር የተዟዙሮ ጨዋታ (ፎርማት) ጋር በተያያዘ ቅሬታ የነበራቸው ክለቦች ነበሩ፣ አሉም፡፡ ፌዴሬሽኑ እዚህ ላይ ያለው አቋም እስካሁን ግልጽ አይደለም፣ ምክንያቱ ምንድነው?
ኮሎኔል አወል፡– የሚባለው በወሬ ደረጃ ካልሆነ በተጨባጭ ለፌዴሬሽኑ የቀረበ ነገር ስለሌለ ምንም ማለት አልችልም፡፡
ሪፖርተር፡– የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጰያ ቡና ክለቦች ጥያቄ እንዳለ አያውቁም?
ኮሎኔል አወል፡– በስፖርት ጋዜጠኞች አማካይነት በአንዳንድ ኤፍ ኤሞች ካልሆነ ክለቦቹ በተጨባጭ እንዲህ እንዲህ ዓይነት ችግር ስላለብን ብለው ለፌዴሬሽኑ ያቀረቡት ነገር የለም፡፡
ሪፖርተር፡– ፕሪሚየር ሊጉ በነበረው የተዟዙሮ ጨዋታ በ2012ም ይቀጥላል እንበል?
ኮሎኔል አወል፡– በእኔ እምነት እንደሚቀጥል ነው የማውቀው፣ የብዙኃኑ ክለቦች ፍላጎትና ዝግጅትም ይህንኑ ታሳቢ ያደረገ መሆኑን ነው የማውቀው፡፡
ሪፖርተር፡– ከፎርማቱ ጋር በተገናኘ መንግሥት በጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ ጋር እየተነጋገረበት መሆኑ ጭምር የሚናገሩ አሉ፣
ኮሎኔል አወል፡– የፌዴሬሽኑ ምክትል ፕሬዚዳንት እንደ መሆኔ በዚህ ጉዳይ የትኛውም የመንግሥት አካል ፌዴሬሽኑን ያናገረበት ወቅት አልገጠመኝም፣ ፌዴሬሽኑ ከመንግሥት አካል ጋር አልተነጋገረም፡፡
ሪፖርተር፡– ፌዴሬሽኑ ባለፉት የውድድር ዓመታት ሲከሰቱ ለነበሩ ስፖርታዊ ጨዋነት ጥሰት መፍትሔ ይሆናል በሚል የፕሪሚየር ሊጉን ቁጥር ወደ 24 ከፍ እንዲል በማድረግ የ2012 የውድድር መርሐ ግብሩን በሁለት ምድብ ከፍሎ ለማከናወን ዕቅድ እንዳለ አመራሩም ጉዳዩን ሙሉ በሙሉ ደግፎት በዝግጅት ላይ መሆኑ ተሰምቷል፣ እውነት ነው?
ኮሎኔል አወል፡– እንደ ፌዴሬሽን ባለፉት ዓመታት ከነበረው የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ጋር ተያይዞ የታየውን አለመግባባት ለማስወገድ፣ የአጭር ጊዜ መፍትሔ ብለን የፕሪሚየር ሊጉን ቁጥር በመጨመር በሁለት ምድብ በመክፈል ውድድሩን ለማስኬድ ፌዴሬሽኑ ውሳኔ ላይ ደርሷል፡፡ የወደፊቱን በሚመለከት ግን በቅርቡ ይመሠረታል ተብሎ በዕቅድ የተያዘው ሊግ ካምፓኒ ውሳኔ የሚሰጥበት ነው የሚሆነው፡፡
[ዝርዝሩን በሚመለከት ምክትል ፕሬዚዳንቱ ባያብራሩትም፣ በ2011 የውድድር ዓመት ወደ ታችኛው ሊግ የወረዱት መከላከያ፣ ደደቢትና ደቡብ ፖሊስ በፕሪሚየር ሊጉ እንዲቀጥሉ፣ ካደጉት ከሆሳዕና ከተማ፣ ከሰበታ ከተማና ከወልቂጤ ከተማ በተጨማሪ በከፍተኛው ሊግ ጥሩ ሁለተኛና ሦስተኛ በመሆን ካጠናቀቁት መካከል ማለትም ከጥሩ ሁለተኛ አርባ ምንጭ ከተማ፣ ለገጣፎና ኢትዮጵያ መድን ሲሆኑ፣ ጥሩ ሦስተኛ ከሆኑት ውስጥ ደግሞ ባስመዘገቡት ነጥብ መሠረት ኢኮስኮና ለቀምት ከተማ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ እንዲካተቱ በማድረግ ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› ምድብ በሚል ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ለማስቀጠል ዕቅድ እንዳለው ታውቋል፡፡]