Wednesday, April 17, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹የባንካችን ዓላማ በሁሉም ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ቤት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው›› አቶ ጌታሁን ናና፣ የጎህ የቤቶች ባንክ ዋና አደራጅና ሰብሳቢ

በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዳዲስ ነገሮች እየታዩ ነው፡፡ በ2012 ዓ.ም. በአማራጭነት የሚታዩ የባንክ አገልግሎቶችን ለመስጠት የተሰናዱ አዳዲስ ባንኮች ገበያውን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በተለየ አገልግሎት ወደ ኢንዱስትሪው ለመግባት እየተዘጋጁ ካሉት ውስጥ ‹‹ጎህ የቤቶች ባንክ›› የሚል ስያሜ የተሰጠው ባንክ ይጠቀሳል፡፡ በአሁኑ ወቅት በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚታየውን ክፍተት በመመልከት፣ እንዲሁም ከቤቶች ግንባታ ጋር ተያይዞ ያለውን የፋይናንስ አቅርቦት አናሳነትና የመኖሪያ ቤት ፍላጎትን በማጤን፣ እንዲህ ያለውን ስፔሻላይዝድ ባንክ ማቋቋሙ እጅግ አስፈላጊ በመሆኑ ወደዚህ ሥራ መገባቱን የባንኩ አደራጆች ያስረዳሉ፡፡ በተለይ ከመኖሪያ ቤት ችግር ጋር ተያይዞ ያለውን ችግር ለመፍታት እንዲህ ያሉ ባንኮች የሚኖራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነ በመታመኑ፣ ‹‹ጎህ የቤቶች ባንክ››ን ለማቋቋም እንዳነሳሳቸውም ለመረዳት ተችሏል፡፡ ከዜጎች መሠረታዊ ፍላጎት ጋር የተያዘውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለመፍታት ደግሞ፣ የባንኩ አደራጆች በጥንቃቄ መመረጣቸውም ይነገራል፡፡ ከዚህ ባንክ አደረጃጀት ጋር በተያያዘ በተለይ የሚታየው ደግሞ፣ ከአሥሩ አደራጆች አምስቱ በአገሪቱ የተለያዩ ባንኮች ውስጥ በፕሬዚዳንትነት ያገለገሉ መሆናቸው ነው፡፡ ይህንን ባንክ ለማቋቋም በሐሳብ አፍላቂነት፣ በዋና አደራጅነትና ሰብሳቢነት የሚጠቀሱት የቀድሞ የብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥና ከዚያም የኢትዮጵያ ልማት ባንክ ፕሬዚዳንት በመሆን ያገለገሉት አቶ ጌታሁን ናና ሲሆኑ፣ የባንኩን የምሥረታ ሒደትና አጠቃላይ አሠራሩን በተመለከተ ዳዊት ታዬ አቶ ጌታሁንን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥ አንጋፋ የምትባሉ ባለሙያዎች በግል ደረጃ ያልተሞከረ ባንክ ለማቋቋም እየተንቀሳቀሳችሁ ነው፡፡ ጎህ ቤቶች ባንክ የሚል ስያሜ የሰጣችሁትን ባንክ ለማቋቋም እንዴት ተነሳሳችሁ?

አቶ ጌታሁን፡- እንዲህ ያለውን ለየት ያለ ባንክ ለመመሥረት ያነሳሱን የተለያዩ ምክንያቶች ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባም ሆነ በክልል ከተሞች ያለው መኖሪያ ቤት ችግርና ለቤቶችና ለግንባታ ሥራዎች ራሱን የቻለ ፋይናንስ የሚያደርግ ተቋም አለመኖሩ አንዱ ነው፡፡ በአጭሩ ወደዚህ የገባነው ያለውን ችግር በመመልከት፣ እንዲሁም የችግሩን ስፋትና ጥልቀት በጥናት ጭምር በመለየታችን ነው፡፡ በከተሞች እስከ 1.2 ሚሊዮን ቤቶች እጥረት አለ፡፡ ከ100 እስከ 300 ሺሕ ቤቶች በየዓመቱ መሠራት አለባቸው፡፡ ቤት ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎቶች አንዱ ነው፡፡ 70 በመቶ የሚሆኑ ቤቶች ፈርሰው እንደገና መሠራት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ለመኖሪያ ምቹ አይደሉም፡፡ ለመኖሪያ ምቹ ማለት ሳሎን፣ መኝታ፣ ማዕድ ቤት፣ መታጠቢያ ቤት ያለው ማለት ነው፡፡ ያነሳሳን ይህንን ችግር ለመፍታት የራሳችንን አስተዋጽኦ ለማሳደግ ነው፡፡ ራዕያችን በአገራችን ሁሉም ሰው ምቹ የመኖሪያ ቤት እንዲኖረው ማድረግ ወይም ኖሮት ማየት ነው፡፡ ይህንን ራዕይ ለማሳከት ሐሳቡን ተቀብለው የሚተገብሩ ባለሙያዎች መሰባሰብ ነበረባቸው፡፡ በመሆኑም በባንኩ ዘርፍ የረዥም ጊዜ አመራርና ትግበራ፣ በምሕንድስናው ዘርፍ ሰፊ የጽንሰ ሐሳብና የተግባር፣ በሕግ፣ ፋይናንስና በኢንቨስትመንት ልምድ ያላቸውን አባላት በማሰባሰብ አደራጅ ኮሚቴ ተዋቅሯል፡፡ በባንክ ዘርፍ ትልቁ ነገር በሕዝብ ዘንድ አመኔታና ተቀባይነት ማግኘት ነው፡፡ የእኛ ስብስብ ደግሞ ይህንን የሚያሟላ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ሁሉም ለአገር ዕድገትና ብልፅግና የሚያስቡ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የገቡትን ቃል ለመፈጸም የሚጨነቁና ክብራችንን ለመጠበቅ የሚተጉ ናቸው፡፡ በመጨረሻ በግላቸውም ይህንን ልዩና ታሪካዊ ባንክ በማቋቋም ጠንካራና ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ማድረግ ነው፡፡  እንደ አንድ ዜጋ የአገር ችግር የሆነውን የመኖሪያ ቤት ችግር ለማቃለል ያግዛል ያልነውን ሐሳብ ዛሬ በመጀመር፣ የነገው ትውልድ ደግሞ የበለጠ እያጠናከረውና የበለጠ እያዘመነው ይሠራል፡፡ እኛም እንደ ዜጋ ይህንን መሠረት በመጣል ኃላፊነታችንን ለመወጣት ዕድል ይሰጠናል፡፡

ሪፖርተር፡- ባንኩ ለየት ያለ አገልግሎት የሚሰጥ በመሆኑ፣ እንዲሁም በዚህ ኢንቨስትመንት ላይ ያለው ግንዛቤ እምብዛም ከመሆኑ አንፃር የምትፈልጉትን ካፒታል ለማሰባሰብ አልተቸገራችሁም? አሁን በምን ደረጃ ላይ ናችሁ?

አቶ ጌታሁን፡- በባንኩ አደራጆች እምነት ባንኩን የማቋቋሙ ሐሳብ በጣም ትልቅ ጉዳይ ነው፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት በተለይ በከተሞች ያለው የቤቶች ችግር ግዙፍ ነው፡፡ ችግሩ አገራዊ ነው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ሁሉም የአገሪቱ ዜጎች እንደሚረባረቡ እርግጠኞች ነን፡፡ ሐሳቡን መጀመርያ መሸጥ የሞከርነው ለመንግሥት ነው፡፡ በዚህ ረገድ የሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት የሰጡን ድጋፍ እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡ ትግበራውን እንድናፈጥነው እያበረታቱን ነው፡፡ ቀጥሎ በቅርብ ለምናውቃቸው ባለሀብቶች ሐሳቡን አካፍለን ያገኘነው ግብረ መልስ እጅግ በጣም የሚደንቅና ወደፊት እንድንገፋበት ያደረገን ነው፡፡ አንዳንድ ባለሀብቶች ከባንኩ የሚያገኙት ትርፍ እንደተጠበቀ ሆኖ የአገርን ችግር መፍታት ከፍተኛ ቦታ እንዳለው ያምናሉ፡፡ በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ እንደ መምታት ማለት ነው፡፡ ባንኩ ትርፍ ይገኛል፡፡ ከዚህ ባሻገር ደግሞ የአገርን ችግር የሚፈታ በመሆኑ፣ የዚህ ባንክ ሥራ መጀመር እያተረፍክ አገርን ማገልገል ነው፡፡ ስለሆነም በባለሀብቶች በኩል በቂ ገንዘብና ካፒታል ለማሰባሰብ በሚያስችለን ሁኔታ ላይ ነን ብለን እናምናለን፡፡ እስካሁን በቅርብ ከምናውቃቸው ባለሀብቶች ውጪ አክሲዮኖችን ለመሸጥ አልተንቀሳቀስንም፡፡ ከመስከረም 8 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ግን በይፋ ወደ ገበያው እንወጣለን፡፡ አክሲዮኖችን የመሸጡ ሥራ በሰፊው ይካሄዳል፡፡ ያኔ ሁሉም ዜጋ አክሲዮኖቹን ለመግዛትና በዚህ ታሪካዊ ባንክ ምሥረታ የራሱን አሻራ ለማኖር ይረባረባል ብለን እናምናለን፡፡ ችግሩ አገራዊ ነው፡፡ መፍትሔውም መምጣት ያለበት ከሁሉም የአገሪቱ ዜጎች በመሆኑ፣ የባንኩ ባለአክሲዮን መሆን የሚያስገኘውን ጥቅም በመረዳት ዜጎች የዚህ ባንክ ባለቤት ይሆናሉ ብለን እናምናለን፡፡ ‹‹ጋን በጠጠር ይደገፋል›› እንዲሁ፣ ሁሉም ሰው የባንኩን አክሲዮኖ በመግዛት የባንኩ ባለቤት እንዲሆን፣ የራሱን ቤትም እንዲሠራ፣ ጠቀም ያለ ትርፍ እንዲያገኝና የአገርን ችግር እንዲፈታ በዚህ አጋጣሚ ልንገልጽ እንወዳለን፡፡

ሪፖርተር፡- የዚህ ባንክ መመሥረት ጠቀሜታው በተለየ የሚታይ ነው ካሉ፣ እንዲህ ያሉ ባንኮች ጠቀሜታ እንዴት ይገለጻል? አጠቃላይ አሠራሩን በተመለከተ አሁን በገበያው ውስጥ ካሉት ባንኮች የሚለየውና የሚያመሳስለው ምንድነው?

አቶ ጌታሁን፡- ከሌሎች ጋር ያለው ልዩነትና ተመሳሳይነት ከላይ እንደተገለጸው፣ የባንካችን ዓላማ በሁሉም ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች የመኖሪያ ቤት እንዲኖራቸው ማድረግ ነው፡፡ ጠቀሜታውም የሚታየው ከዚህ አንፃር ነው፡፡ ሁሉም ዜጋ የመኖሪያ ቤት እንዲኖረው ማድረግ ማለት፣ ሁሉም ሰው የቤት ባለቤት እንዲሆን ማድረግ ማለት አይደለም፡፡ ቤት ተከራይቶ መኖር የሚፈልግ ሰው የኪራይ ቤት በቀላሉና በተመጣጣኝ ዋጋ ማግኘት መቻል አለበት፡፡ ለዚህም ባንኩ ቤት ገንብተው የሚያከራዩ ባለሀብቶች የሚያስፈልጋቸውን የግንባታ ወጪ ለመሸፈን የሚያስችላቸው የገንዘብ ድጋፍ ያደርጋል፡፡ ድጋፍ ደግሞ የሚጀምረው ብድር በማቅረብ ነው፡፡ በተመሳሳይ የቤት ባለቤት ለመሆን ለሚፈልጉትም ባንኩ የብድር ድጋፍ ያደርጋል፡፡ መኖሪያ ቤት ለሚገዙ ወይም መኖሪያ ቤት ያላቸው ሆነው ቤቱን ለመጠገን፣ ለማስፋፋት ወይም ለማሻሻል ለሚፈልጉትም የብድር ጥያቄያቸውን ባንኩ ያስተናግዳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪም የአገሪቱ የቁጠባ ባህል እንዲያድግ ቤት ገንቢዎች፣ ገዥዎችና ማስፋፋት የሚፈልጉ ሰዎች ገንዘብ እንዲቆጥቡ የተለያዩ ተስማሚ የቁጠባ አገልግሎቶችን ይሰጣል፡፡ ቤት ለመገንባት፣ ለመግዛት ወይም ለማስፋፋት ቁጠባ የግድ ነው፡፡ ባንኩ ቤት ለመግዛት ወይም ለመገንባት የሚስያፈልገውን ሙሉ ወጪ ራሱ ሊሸፍን አይችልም፡፡ ይልቁንም ከ70 እስከ 80 በመቶ በባንኩ የሚሸፈን ሲሆን፣ ቀሪው ከ20 እስከ 30 በመቶ የሚሆነው በተበዳሪ መሸፈን አለበት፡፡ በመሆኑም ተበዳሪው ከባንኩ ብድር ከመውሰዱ በፊት፣ ከ20 እስከ 30 በመቶ መቆጠብ የሚኖርበትን አሠራር ልንከተል እንችላለን፡፡ ሌሎች አማራጮችም ይታያሉ፡፡

ከሌሎች ባንኮች ጋር ያለውን ልዩነትና ተመሳሳይነትን በሚመለከት፣ እንደሚታወቀው የአንድ ማንኛውም ዓይነት ባንክ ዋና ሥራ ገንዘብ በተለያዩ መንገዶች ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ አገር ሰብስቦ ማበደር ነው፡፡ ገንዘብ በማሰባሰቡና ብድር በመስጠቱ ላይ በጥቅሉ ሲታይ የእኛ ባንክ ከሌሎች ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ ነገር ግን ብድሩ ለማንና ለየትኛው ዘርፍ ነው የሚሰጠው በሚለው ላይ፣ የእኛ ባንክ አሁን በሥራ ላይ ካሉት ባንኮች ይለያል፡፡ እነዚህ ባንኮች በአብዛኛው ጊዜ በተለያየ መጠን የሚያበድሩት በአጭር ጊዜ ለሚመለስ የቢዝነስ ሥራ ነው፡፡ የእኛ ባንክ ግን በአብዛኛው ብድር የሚሰጠው በረዥም ጊዜ ለሚከፈል የቤቶች መግዣ፣ ግንባታ፣ ማስፋፊያና ጥገና ነው፡፡ ይህ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ በክፍያ ሥርዓቱ፣ በውጭ ምንዛሪ ገበያው፣ በዓለም አቀፍ ንግድና በመሳሰሉት የምናደርገው እንቅስቃሴ ከሌሎች ባንኮች ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡

ሌላው መሠረታዊ ልዩነት የእኛ ባንክ ከሌሎች ባንኮች ጋር ሲተያይ ከውድድር ይልቅ በትብብር መርህ ላይ መመሥረቱ ነው፡፡ ጎህ የቤቶች ባንክ የሚያስበው የብድር ዘርፍ ሌሎች ባንኮች በአብዛኛው ለመግባት የሚፈልጉት አይደለም፡፡ በመሆኑም እነዚህ ባንኮች ከጎህ ጋር በመሆን አብረውና ተባብረው ወደዚህ ዘርፍ እንዲገቡ ያበረታታል፡፡ ለምሳሌ አንድ ለመኖሪያ ቤት አፓርትመንት ኪራይ የሚውል ሰማይ ጠቀስ ሕንፃ በባለሀብት መገንባት ቢያስፈልግ፣ ጎህ የቤቶች ባንክ የዚህን ሕንፃ ግንባታ ወጪ ለመሸፈን ከአንድ በላይ የሆኑ ሌሎች ባንኮች ወይም የመድን ኩባንያዎች ወይም ሁለቱም በአንድ ላይ ተባብረው ወጪውን እንዲሸፍኑ ሊያደርግ ይችላል፡፡ በተመሳሳይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች በመንግሥት ወይም በሌሎች አጋዥ ድርጅቶች ዕገዛ በአነስተኛ ወጪ ቤት በብድር መሥራት ቢያስፈልግ፣ እንዲህ ዓይነት ትንንሽ ብድሮች አስተዳደራዊ ወጪያቸው ከፍተኛ በመሆኑ ከአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋር በመተባበር ባንኩ የቤት ብድር ለዝቅተኛው የኅብረተሰብ ክፍል እንዲደርስ ያደርጋል፡፡ ይህ ከሌሎች ባንኮች፣ ከመድን ኩባንያዎችና ከአነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት ጋር አብሮና ተባብሮ የመሥራት ልምድ ከዚህ በፊት በአገሪቱ ያልነበረና በእኛ ባንክ ግን የሚበረተታታ ይሆናል፡፡ የእኛ መርህ ‹‹ኬኩን ያሸነፈው ሁሉ ይውሰደው›› ሳይሆን፣ ‹‹ኬኩን በጋራ አሳድገንና አስፋፍተን ሁላችንም እንደ ሚናችን የየድርሻችን እንካፈል›› ነው፡፡ እንዲህ ሲሆን ሁላችንም ተጠቃሚ እንሆናለን፡፡ ሁላችንም የውድድሩ አሸናፊ እንሆናለን፡፡ አጥፊና ጠፊ አይኖርም፡፡

ሪፖርተር፡- አንዳንድ ወገኖች በቤትና በግንባታ ሥራዎች ላይ የሚያተኩር ባንክ ከፍተኛ ካፒታል ስለሚፈልግ አሠራሩም ጥንቃቄ የሚሻ እንደሆነ ያሳስባሉ፡፡ ከዚህ አንፃር የእናንተ ዝግጅትና ዕቅድ ምንድነው?

አቶ ጌታሁን፡- ከፍተኛ ካፒታል ማስፈለጉና የእኛ ዝግጅት ማድረግ እርግጥ ነው፡፡ የቤቶች ፋይናንስ ሥራ ከፍተኛ ገንዘብና ጥንቃቄ ይፈልጋል፡፡ የባንክ አንዱና ዋና ሥራ ካፒታል ማሰባሰብ ነው፡፡ በእኛ እምነት ተገቢ የሆነ የገንዘብ ማሰባሰቢያ ዘዴ ከተዘረጋ፣ በአገራችን ኢኮኖሚ ውስጥ ያለውን ገንዘብ፣ ካፒታል ማሰባሰብ ይቻላል፡፡ በዓለም ባንክ በተደረገው ጥናት መሠረት ለአካለ መጠን ከደረሱ የአገሪቱ ዜጎች ውስጥ 62 በመቶ የሚሆኑት በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ገንዘብ ይቆጥባሉ፡፡ ነገር ግን ይህ ቁጠባ በአብዛኛው የሚደረገው ከፋይናንስ ተቋማት ውጪ ነው፡፡ ስለዚህ ተስማሚ የሆነ የቤት የቁጠባ አገልግሎት በመስጠት ወደ ባንካችን እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል (ሁሉን ሳይሆን ከፍተኛ ግምት የሚሰጥ መጠን)፡፡ በተመሳሳይ በየማኅበራቱ ተከማችቶ ለሥራ የተቀመጠ ገንዘብን ለቤት ሥራ ማሰባሰብ ይቻላል፡፡ ከመንግሥት ጋር በመተባበርም የረዥም ጊዜ የቤት ሥራ ፈንድ መመሥረት ይቻላል፡፡ በርካታ ዓለም አቀፍና ተቋማትና የውጭ መንግሥታት፣ እንዲሁም የውጭ ኢንቨስተሮች የካፒታል ምንጭ ሊሆኑ እንደሚችሉ ፍላጎታቸውን እያሳዩ ይገኛል፡፡ አሁን ገና በምሥረታ ሒደት ላይ እያለን እንኳ አንድ የውጭ ዕርዳታ ሰጪ ድርጅት የባንኩን የአሠራር (ኦፕሬሽን) ስትራቴጂ እያዘጋጀልን ከመሆኑም በተጨማሪ፣ አክሲዮኖች በገበያ ለመሸጥ የሚያስፈልገውን ወጪ እየተጋራ ይገኛል፡፡ በአጭሩ ትክክለኛ ስትራቴጂ ከተነደፈ ካፒታል ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ማሰባሰብ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በተለይ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት አሁን እናንተ ለማቋቋም እየተሰናዳችሁበት እንዳለው ዓይነት ስፔሻላዝድ ባንክ ነበሩ፡፡ ከዚያም በኋላ የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክም ነበር፡፡ እነዚህ ባንኮች አሁን የሉም፡፡ በነበሩበት ወቅት የሥራ እንቅስቃሴያቸው እንዴት ይታይ ነበር? ከእነሱ የምትወስዱት ልምድ ይኖራል?

አቶ ጌታሁን፡- በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት በቤቶች ፋይናንስ ዘርፍ የተወሰኑ ሁለት ተቋማት ነበሩ፡፡ አንዱ “Imperials Saving and Home Ownership Public Association (ISHOPA)” ሲባል ሌላው፣ “Saving and Mortgage Corporation of Ethiopia” ይባል ነበር፡፡ የደርግ መንግሥት መምጣትን ተከትሎ እነዚህ ሁለት ተቋማት እ.ኤ.አ. በ1975 ዓ.ም. ተቀላቅለው የቤቶችና ቁጠባ ባንክን መሠረቱ፡፡ በኢሕአዴግ መንግሥት ደግሞ የዚህ ባንክ ስያሜ ወደ ኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ ተቀየረ፡፡ በመጨረሻም ይህ ባንክ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር ተቀላቅሏል፡፡ እነዚህ ተቋማት በዘመናቸው ለቤቶች ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ዛሬ በአዲስ አበባ ውስጥ በእነዚህ ተቋማት የተገነቡ ብዙ ቤቶች አሉ፡፡ በወቅቱ በርካታ ሰዎች የቤት ባለቤት እንደሆኑ አድርገዋል፡፡ የእኛ ባንክ ከእነዚህ ተቋማት የሚማረው የቤት ፋይናንስ ባንክ ዜጎች የቤት ባለቤት እንዲሆኑ ከፍተኛ ዕገዛ እንደሚያደርግ፣ ቀጣይነት ባለው መንገድ ትርፋማ ሆኖ ሥራውን ማከናወን እንደሚችል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች የኮንስትራክሽንና ቢዝነስ ባንክ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ጋር የተቀላቀለው ስለከሰረ ነው ይላሉ፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ሁለቱ ባንኮች የተቀላቀሉት በመንግሥት ውሳኔ እንጂ በኪሳራ ምክንያት አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት እንደ አዲስ አበባ ባሉ ከተሞች ከፍተኛ የሆነ የመኖሪያ ቤት ችግር አለ፡፡ ባንካችሁ ደግሞ በዋናነት በቤት ግንባታ ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር እንደ መሆኑ፣ የቤት ግንባታዎችን እንዴት እንደግፋለን ብላችሁ ታምናላችሁ? በተጨባጭ የእኛ ድርሻ ይኼ ነው ብለው ሊገለጽልኝ የሚችሉት ነገር አለ?

አቶ ጌታሁን፡- ቀደም ሲል እንደተገለጸው በአገሪቱ ባሉ ዋና ዋና ከተሞች ከፍተኛ የመኖሪያ ቤት እጥረት አለ፡፡ ችግሩን ለመፍታት አዳዲስ ቤቶች መገንባት አለባቸው፡፡ የባንኩ ዋና ዓላማ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚውል ብድር ለአልሚዎች መስጠት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ ከቤት ግንባታ ጋር በተያያዘ ሁለት ተጓዳኝ ተግባራት ይኖሩታል፡፡ አንዱ ሊገነባ የታቀደው ቤት በአነስተኛ ወጪ፣ በዲዛይኑ መሠረት በጥራትና በተፈቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ ነው፡፡ ሌላው ለቤት ገዥዎች የማማከር አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ባንኩ ስለመኖሪያ ቤቶች ግንባታ፣ ጥራትና ወጪ የሚያጠና የተጠናከረ የጥራትና ምርምር የሥራ ክፍል ይኖረዋል፡፡ የዚህ የሥራ ዘርፍ የጥናት ውጤቶች እንደ ሁኔታው እየተገመገሙ፣ በአነስተኛ ዋጋ ጥራት ያላቸው ምቹ ቤቶች በታቀደው የግንባታ ጊዜ እንዲጠናቀቁ በሚያስችል መንገድ ሥራ ላይ ይውላሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ለቤት ግንባታ የሚውል ኢንቨስትመንት በቀጥታ ከግንባታ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ስለዚህ ካለው ልምድ አኳያ ግንባታዎች በቶሎ መጠናቀቅ ካልቻሉ ልትፈተኑ አትችሉም?

አቶ ጌታሁን፡- በአገራችን በአሁኑ ጊዜ ግንባታን በታቀደለት ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ ፈታኝ ነው፡፡ ብዙ ጊዜ የተለያዩ ግንባታዎች የተራዘመ ጊዜ ይወስዳሉ፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ባንኩ የተመረጡና የታመኑ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን፣ የላቀ የሥራ ክንውንና ልምድ ያላቸውን የውጭ የኮንስትራክሽን ኩባንያዎችን መጠቀም ድረስ ይሄዳል፡፡ የአገር ውስጥ ኮንትራክተሮች በጊዜ ሥራቸውን እንዲያጠናቅቁ በባንኩ በኩል አስፈላጊው ድጋፍ ይደረጋል፡፡ ለምሳሌ የኮንትራክተሮቹ ችግር የውጭ ምንዛሪ ከሆነ ይህንን ለመፍታት ባንኩ ይጥራል፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ደግሞ የቤት ግንባታዎችን የሚያቀላጥፉ አዳዲስ አሠራሮችና ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀማል፡፡

ሪፖርተር፡- እርስዎ በባንክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ረዘም ያለ ጊዜ ከመቆየትዎ አኳያ የአገሪቱን የፋይናንስ ዘርፍ እንዴት ይገልጹታል?

አቶ ጌታሁን፡- በእኔ እምነት የአገራችን የፋይናንስ ሥርዓት ገና በማኮብኮብ ላይ ያለ ዘርፍ ነው፡፡ የፋይናንስ ሥርዓቱን በሦስት ክፍሎች ከፋፍሎ ማየት ይቻላል፡፡ አንደኛ የፋይናንስ ተቋማት ከኢሕአዴግ ወደ ሥልጣን መምጣት ጀምሮ በቁጥርም ሆነ በአቅም ከፍተኛ ዕድገት አሳይተዋል፡፡ በርካታ የግል ባንኮች፣ የመድን ድርጀቶች፣ አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትና የካፒታል ዕቃ አቅራቢዎች ተቋቁመው በአገሪቱ ገበያ ውስጥ በመሥራት ላይ ናቸው፡፡ ነገር ግን አሁንም ተጨማሪ ተቋማት የፋይናንስ ዘርፉን ለማዳበርና ለማጠናከር መቋቋም ይኖባቸዋል፡፡ ለምሳሌ ዛሬ ሳይሆን ትናንት መቋቋም የነበረበት ይህ እኛ የምንመሠርተው በቤቶች ፋይናንስ ላይ የሚያተኩር ዓይነት ልዩ ባንክ ነው፡፡ የክፍያ ሥርዓቱን ሊያዘምኑ የሚችሉ የክፍያ ባንኮች፣ የውጭ ምንዛሪ ቢሮዎች፣ በአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ላይ የሚተኩሩ ባንኮች፣ ወዘተ መቋቋም ይኖባቸዋል፡፡

ሁለተኛው የፋይናንስ ሥርዓት የፋይናንስ ገበያ አካል ነው፡፡ በኢትዮጵያ የተደራጀ የፋይናንስ ገበያ የለም፣ ወይም እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡ የተደራጀ የአክሲዮንና የቦንድ ገበያ የለም፡፡ በባንኮች በኩል የሚደረግ የገንዘብ ልውውጥ ገበያም በተመሳሳይ የለም ማለት ከሚቻልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ሦስተኛው የፋይናንስ ሥርዓቱ አካል የፋይናንስ አገልግሎቶችና ምርቶች ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ የፋይናንስ ገበያ ውስጥ ያሉት የፋይናንስ አገልግሎቶችና ምርቶች የተለመዱና ውስን ናቸው፡፡ አዳዲስ የፋይናንስ አገልግሎቶችና ምርቶች በአገሪቱ በመስፋፋት ላይ ያሉት የኢኮኖሚያችንን ዕድገትና ዓለም አቀፉን የፋይናንስ ሥርዓት ባላገናዘበ መንገድ፣ እጅግ በጣም ዘገምተኛ ሆነው ነው፡፡ ዛሬም ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን የምንለዋወጠው አብዛኛውን ጊዜ ከመቶ ዓመት በፊት የነበሩ ቅድመ አያቶቻችን ሲያደርጉት እንደነበረው፣ ጥሬ ገንዘብ ቆጥረን በመክፈልና ቆጥረን በመቀበል ነው፡፡ ዘመናዊው ዓለም ግን ጥሬ ገንዘብን ከገበያ እያስወጣ በአብዛኛው በኤሌክትሮኒክስ የክፍያ ዘዴ እየተካ ነው፡፡ የፍጆታ ብድር የሚሰጥ ባንክ የለም፡፡ የዓለም ባንክ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ለአካለ መጠን ከደረሱ ሰዎች ውስጥ ከፋይናንስ ተቋማት ብድር መውሰድ የቻሉት ብዛት ከ11 በመቶ አይበልጥም፡፡ የሕይወት መድን ሽፋን ዕድገት ዘገምተኛ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ የኢትዮጵያ የፋይናንስ ሥርዓት ገና በማደግ ላይ ያለ፣ በብዙ ረገድ ለአገራችን ኢኮኖሚ ከሚጠበቅበት በታች አስተዋጽኦ እያደረገ ያለ ዘርፍ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት መንግሥት ለፋይናንስ ዘርፍ የወጡ ሕግጋትን በማፍታታቱ፣ የአገሪቱ ባንኮች ቁጥር እያደገ መጥቷል፡፡ ይህ ብዙም አስፈላጊ አይደለም የሚሉ አሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ አሁንም መበርከት እንደሚኖርባቸው ያምናሉ፡፡ እርስዎስ?

አቶ ጌታሁን፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩት የፋይናንስ ዘርፉ በኢኮኖሚያችን ውስጥ መጫወት ያለበትንና የሚጠበቅበትን ሚና በመወጣቱ ረገድ ውስንነት አለበት፡፡ ከዚህ ውስንነት ለመውጣትና የፋይናንስ ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚጠበቅበትን አስተዋጽኦ ማበርከት ካለበት፣ የፋይናንስ ተቋማት በይበልጥ መስፋፋት ይኖርባቸዋል፡፡ የፋይናንስ ገበያውም መቋቋምና መጠናከር አለበት፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አሁን በአገሪቱ ያለው የፋይናንስ ተደራሽነት ከ35 በመቶ አይበልጥም፡፡ ይህ ማለት 65 በመቶ የፋይናንስ አገልግሎት ፈላጊ ሕዝብ አገልግሎቱን እያገኘ አይደለም ማለት ነው፡፡ ታዲያ በምን እሳቤ ነው በአገራችን የፋይናንስ ተቋማት በበቂ ሁኔታ ተስፋፍተዋል የምንለው? ለአካለ መጠን ከደረሱ የአገሪቱ ዜጎች ውስጥ ከፋይናንስ ተቋማት (አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማትን ጨምሮ) የብድር አገልግሎት የሚያገኙት ከ11 በመቶ አይበልጡም፡፡ ይህ ቁጥር የባንክ ዘርፉ በቂ ተቋማት ገብተውበታል ለማለት ያስችላል? አያስችልም፡፡ ቁጥሮቹ የሚነግሩን ገና ብዙ ባንኮች መቋቋም እንዳለባቸው ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጎህ የቤቶች ባንክን ለማቋቋም ስትነሱ ያደረጋችሁት ጥናት ይኖራል፡፡ እንዲህ ባለው ባንክ ኢንቨስት ማድረግ ምን ያህል አዋጭ ነው?

አቶ ጌታሁን፡- ጎህ የቤቶች ባንክን ለመመሥረት ሰፊ የአዋጭነት ጥናት ተደርጓል፡፡ በዚህ ጥናት መሠረት ባንኩ ከጀመርያው ዓመት ጀምሮ ትርፍ ያስመዘግባል፡፡ በአምስተኛው ዓመት ባለሀብቶች ለባንኩ ምሥረታ የከፈሉትን ገንዘብ መልሰው ያገኛሉ፡፡ ይህ በማናቸውም መለኪያ ፕሮጀክቱ ጥሩ የኢንቨስትመንት አማራጭ መሆኑን ያሳያል፡፡ በመሆኑም የባንኩን አክሲዮኖች መግዛት ጠቀሜታው ላቅ ያለ ነው፡፡ የባንኩ መመሥረት ግን ከትርፍ እሳቤ ብቻ ወጣ ባለ መልክ መታየት አለበት፡፡ የሚመሠረተው የሕዝብ ባንክ ነው፡፡ ዓላማውም ከአገሪቱ ቁልፍ ችግሮች አንዱን ለመፍታት የራሱን ሚና መጫወት ነው፡፡ ችግሩ አገራዊ እንደ መሆኑ መጠን መፍትሔውም ለጥቂት አገር ወዳዶች ብቻ የሚተው አይደለም፡፡ በመሆኑም ባንኩን ለመመሥረት የሁሉም ርብርብ አለበት፡፡ በባንኩ መመሥረትና ወደ ሥራ መግባት ተጠቃሚ የሚሆኑት ሁሉም ባለድርሻ አካላት ናቸው፡፡ ኢንቨስተሩ ከባንኩ ላቅ ያለ ትርፍ ያገኛል፡፡ ቤት ፈላጊው በአንድ ወይም በሌላ መንገድ የሚፈልገውን ቤት እንደ አቅሙ ያገኛል፡፡ በመጨረሻም መንግሥትና ኅብረተሰቡ በጋራ አገራዊ ችግሩን ይፈታሉ፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹የሥራ አጦች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ መጨመርና መከማቸት ለትግራይ ክልል ሰላምና ደኅንነት ትልቅ ሥጋት ይፈጥራል›› አትክልቲ ኪሮስ (ዶ/ር)፣ የፋይናንስ ባለሙያ

በሰሜን ኢትዮጵያ የተደረገው ጦርነት ከፍተኛ ውድመት አስከትሏል፡፡ ለማኅበራዊ ቀውስ ምክንያትም ሆኗል፡፡ በጦርነቱ ሕይወታቸውን ያጡ፣ ለአካል ጉዳት የተዳረጉና ሀብት ንብረታቸው የወደመባቸው ዜጎች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ናቸው፡፡ ...

‹‹በሌሎች ክልሎች ያለው የሰብዓዊ ዕርዳታ ፍላጎት ከትግራይ አንፃር አነስተኛ ነው ብዬ ለመግለጽ አልችልም›› ራሚዝ አላክባሮቭ (ዶ/ር)፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የኢትዮጵያ ተወካይና የሰብዓዊ ዕርዳታ...

በኢትዮጵያ የሰብዓዊ ዕርዳታ የሚያቀርቡ ዓለም አቀፍ የረድዔት ድርጅቶችና ሠራተኞች በአገሪቱ በሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞች፣ ድርቅ፣ ጎርፍና ጦርነት ምክንያት ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእጅጉ ተፈትነው ነበር። በኮቪድ-19...

‹‹የውጭ ዜጎች ንብረት እንዲያፈሩ መፍቀድ ከፍተኛ ጥቅም አለው›› ቆስጠንጢኖስ በርሃ (ዶ/ር)፣ የኢኮኖሚ ባለሙያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋር ተከታታይ ውይይት እያደረጉ ነው፡፡ ከእነዚህ የውይይት መድረኮች መካከል ከከፍተኛ የግብር ከፋዮች ወይም ታማኝ ግብር ከፋዮች...