ምርጫ 2012 በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ የሚካሄድ ከሆነ የቀረው የወራት ዕድሜ ብቻ ነው፡፡ በቀሩት እነዚህ ወራት ውስጥ በርካታ ክንዋኔዎች የሚጠበቁ ሲሆን፣ አሁን ግን አገሪቱ በወራት ውስጥ ምርጫ የምታካሂድ አትመስልም፡፡
ምርጫ 2007 በተደረገበት ወቅት ቢያንስ ከምርጫው አንድ ዓመት አስቀድሞ በርካታ ሥራዎች በመከናወናቸው፣ የምርጫው ጉዳይም በአብዛኛው የመገናኛ ብዙኃንን ሽፋን ያገኘ ነበር፡፡
ዘንድሮ በወርኃ ግንቦት ይካሄዳል ተብሎ የሚጠበቀው ምርጫ ግን ለወራት በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሄድ አለመካሄዱ ካልሆነ በቀር፣ በጉዳዩ ላይ ከዚህ ቀደም ይካሄዱ እንደነበሩ ዓይነት ምርጫዎች የመገናኛ ብዙኃን ዓብይ አጀንዳ መሆን አልቻለም፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) አስተዳደር ሥልጣን ከያዘ ወዲህ በርካታ የማሻሻያ ሥራዎች የተከናወኑ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን መልሶ ማቋቋምን ያካተተ ነበር፡፡ በዚህ የመልሶ ማቋቋምና የማሻሻያ ሒደትም ቦርዱ አዳዲስ የቦርድ አባላት ተሰይመውበት የማቋቋሚያ አዋጁም ተሻሽሏል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የአገሪቱን የምርጫና የፖለቲካ ፓርቲዎች አዋጅ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአስቸኳይ ስብሰባው አፅድቆታል፡፡ ይህ የፀደቀው አዋጅ ከዚህ ቀደም በአገሪቱ ይወጡ የነበሩ ሕጎችና አዋጆች ይገጥማቸው የነበረው ዓይነት ከፍተኛ ተቃውሞ አስከትሏል፡፡
ይህ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት በአገሪቱ የሚንቀሳቀሱ 107 ፓርቲዎች በፈረሙት የቃል ኪዳን ሰነድ አማካይነት በተቋቋመው የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ እንዲሁም በተናጠል የተቃውሞ ፖለቲካው ተዋናዮች ከምርጫ ቦርድ ጋር ስለአዋጁ ይዘት የተለያዩ ውይይቶች አካሄደው ነበር፡፡
አሁን በከፍተኛ ሁኔታ ተቃውሞአቸውን እያሰሙ ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎችም የተቃውሞ ምንጫቸውም ሆነ ቅሬታቸው፣ ከቦርዱ ጋር በተደረጉ ውይይቶች ወቅት ያነሷቸው ነጥቦች በአዋጁ አልተካተቱም የሚል ነው፡፡
አዲሱ አዋጅ ከፍተኛ ተቃውሞ ማስከተሉና በግንቦት ወር ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው ምርጫ፣ ከብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል እንደ ከዚህ ቀደም ይደረጉ የነበሩ የምርጫ ዝግጅቶች ስለመጀመራቸው በይፋ የተገለጸ ነገር አለመኖሩ፣ የምርጫው መካሄድ አለመካሄድ ቁርጥ ያለ ውሳኔ አለማግኘቱን ይጠቁማል በማለት የሚገልጹ በርካቶች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ቦርዱ ከምርጫ 2012 አስቀድሞ ዓብይ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ የሚገኘው በኅዳር ወር እንደሚካሄድ በተገለጸው የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ላይ መሆኑን በመጥቀስ፣ የቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫ ዕጣ ፈንታ ተወስኗል ማለት እንደማይቻል ይገልጻሉ፡፡
በቅርቡ መግለጫ የሰጡት የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ሚደቅሳ በመግለጫው ወቅት ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ የሲዳማ ሕዝበ ውሳኔ ሒደትን አስመልክቶ መሆኑን ከግምት በማስገባት ከላይ ለተጠቀሱት መከራከሪያዎች ማጠናከርያ የሚሆን ሐሳብ ነው፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በመግለጫው ወቅት የተነሱት ጉዳዮች የክልል ምርጫ ቦርድ አደረጃጀትንና የክልል የምርጫ ኃላፊዎች ምልመላን የተመለከተ መሆኑ፣ ምርጫ ቦርድ ምርጫ 2012 ለማከናወን ከፍተኛ የቤት ሥራ ከፊቱ እንደሚጠብቀው የሚያመላክት ነው፡፡
የክልል ምርጫ ቦርድ አደረጃጀትና የክልል የምርጫ ኃላፊዎች ምልመላ እየተካሄደ መሆኑን የተገለጸ ሲሆን፣ ይህም የሆነበት ምክንያት በዋና መሥሪያ ቤት ደረጃ የተጀመረውን ውስጣዊ የአደረጃጀት ማሻሻያ በክልል ደረጃም ለማስፋት እንደሆነ ተነግሯል፡፡
‹‹የዚህ ሥራ ዋናው አካል የክልል የምርጫ ኃላፊዎችን እንደ ሥራ አመራር ቦርዱ አመራረጥ ሁሉ የሚመለከታቸው አካላት የተሳተፉበት እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ በዚህም መሠረት በዘጠኙ ክልሎችና በሁለቱ የከተማ አስተዳደሮች በዕጩነት ለመወዳደር የሚፈልጉና የተቀመጠውን መሥፈርት የሚያሟሉ ግለሰቦች የአመላመል ሒደት፣ እንዲሁም በመጨረሻ ይህን የክልል ቅርንጫፍ መሥሪያ ቤት ዋና ኃላፊነትን አስመልክቶ የሚሰጠው የቅጥር ውሳኔ በሚዲያ በይፋ የተገለጸ እንዲሆን ማድረግ አስፈልጓል፤›› በማለት፣ የክልል ምርጫ ቦርድ አደረጃጀትንና የክልል የምርጫ ኃላፊዎችን በተመለከተ የተሰጠው መግለጫ ይገልጻል፡፡
ከዚህ አንፃር ለመካሄድ የወራት ዕድሜ የሚቀረውን ምርጫ 2012 ለማከናወን የክልል የምርጫ ኃላፊዎች አለመሰየም፣ እንዲሁም የክልል የምርጫ ቦርድ አደረጃጀት ገና ሒደት ላይ መሆኑ በራሱ ሌላ ጥያቄ ነው፡፡ በሚዲያ በይፋ ይገለጻል የተባለው የቅጥር ውሳኔስ በምን ያህል ጊዜ ውስጥ ተጠናቆ ነው የተመለመሉት ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን የሚረከቡትና ቀጣዩ ጠቅላላ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስችሉ ሥራዎችን የሚሠሩት የሚለውም፣ እንዲሁ ራሱን የቻለ ተጨማሪ ጥያቄ ነው፡፡
እነዚህንና መሰል ጥያቄዎች እየሰነዘሩበት ያለው ቀጣዩ የምርጫ ዝግጅት እንቅስቃሴ፣ እንዲህ ያሉ አስቸኳይ ምላሽና ኃላፊነት የሚጠይቁ ቢሆንም ምላሾቹ ግን እስካሁን አልተሰሙም፡፡
ከእነዚህ ጥያቄዎች ባለፈ ደግሞ የምርጫው ተዋናዮች፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ፓርቲዎችና የምርጫ ጉዳዮችን በሚዳኘው አዲሱ አዋጅ ላይ ከፍተኛ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡
ፓርቲዎቹ በተለያየ ደረጃ ተቃውሞ እያሰሙ ነው፡፡ በመጀመርያ የ33 ፓርቲዎች ስብስብ ተቃውሞውን ገልጾ ነበር፡፡ በመቀጠል የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ታቃውሞውን እንዲሁ አሰምቶ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ 65 ተቃዋሚ ፓርቲዎች ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡
የፓርቲዎቹ ዋነኛ የተቃውሞ ድምፅ ደግሞ በአዋጁ ላይ እንዲካተቱና በአዋጁ ይዘት ላይ እንዲቀነሱ የሰነዘሯቸው ሐሳቦች ሳይካተቱበት እንዲሁ በወከባ የወጣ አዋጅ ነው የሚል ነው፡፡
በዚህም መሠረት አዋጁ ከመውጣቱ በፊት 33 ተቃዋሚ ፓርቲዎች በአዋጁ ውስጥ እንዲካተቱ የሰነዘሯቸው ሐሳቦች ስላልተካተቱ፣ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት የሚመለከታቸው አካላት ዳግም እንዲወያዩበትና የተሰነዘሩት ሐሳቦችን ያካተተ አዋጅ እንዲወጣ ጠይቀው ነበር፡፡
ሆኖም ጥያቄያቸው ምላሽ ሳያገኝ አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት በመፅደቁ፣ ይህ ማለት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ወደ ምርጫ የሚገቡት በአዋጁ ይካተቱ ያሏቸው ሐሳቦች ምላሽ ሳያገኙ ነው ብለዋል፡፡ ይህም በራሱ ከአጠቃላይ የፖሊሲና የርዕዮተ ዓለም ክርክሮች ይልቅ፣ በቀጣይ ሊደረጉ በሚችሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ክርክር ወቅት ዋነኛ አጀንዳ ሊሆን ይችላል የሚል ሥጋት ያላቸው አካላት እንዲፈጠሩ አድርጓል፡፡
የአዋጁን መፅደቅ ተከትሎ ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት፣ አዋጁ በተለያዩ ጊዜያት ባደረጋቸው ውይይቶች ወቅት የተነሱ ሐሳቦችን ሳያካትት በመፅደቁ ተፈጻሚ እንዳይሆን ጠይቋል፡፡
እነዚህ መሰል የተቃውሞ ድምፆች ከዚህ ቀደም ይወጡ የነበሩ አዋጆችና ሕጎች የሚያስተናግዱት ዓይነት የተቃውሞ ድምፅ እያስተናገደ ሲሆን፣ በተለይ ደግሞ አፋኝ የሆኑ ሕጎችን ለማሻሻል እየተሠራ እንደሆነ ከመገለጹ አንፃር ተመሳሳይነት ያለው ጥያቄ በመሆኑ ጉዳዩ ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ነው በማለት የሚተቹም አሉ፡፡
ከዚህ ጋር በተያያዘ ደግሞ የአዋጁ መውጣትን ተከትሎ በኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) ቢሮ ውስጥ መግለጫ የሰጡት 65 ፓርቲዎች ይህንን ሐሳብ አንፀባርቀዋል፡፡
ፓርቲዎቹ በጋራ በሰጡት መግለጫ፣ ‹‹ትናንት በኢትዮጵያ ሕዝብና በታጋይ ልጆቹ እንቢተኝነት ተገፍቶ ሳይወድ በግዱ ጥፋትና ስህተቱን አምኖ አገርና ሕዝብን ይቅርታ ጠይቆ ከመፍረስና ከመበታተን የዳነው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግና በእሱ የሚመራው ምክር ቤት ለአገርና ለሕዝብ ሰላምና ደኅንነት፣ ለሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብት መከበር፣ ለዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ከምንም በላይ ቅድሚያ ሰጥቼ እደራደራለሁ ሲል በአደባባይ የገባውን ቃል ሽሮ ሁላችንም ለሰላም፣ ለዴሞክራሲ፣ ለፍትሕ፣ ለእኩልነትና ለአንድነት በጋራ እንሠራለን ብለን የሰነቅነውን ተስፋ ከማጨለሙም በላይ፣ አምርረን ስንታገለውና ስንጠላው የነበርነውን ኢዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መልሶ የመትከል ጉዞ መጀመሩን በሕግ ሽፋን በገሃድ እያረጋገጠ ይገኛል፤›› በማለት፣ ባለፉት ወራት በአገሪቱ የታየው የለውጥ ተስፋ መልሶ እየከሰመ እንደሆነ በመግለጫቸው ገልጸዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም አዋጁ ውስጥ ከተካተቱት የመመሥረቻ ፊርማዎች ማሰባሰብ ጋር በተያያዘ የተነሱት ጥያቄዎች ከበርካታ ጥያቄዎች መሀል የሚጠቀስ ሆኖ ሳለ፣ በጉዳዩ ላይ በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን የሚቀርበው ዘገባ ሆን ተብሎ ፓርቲዎችን ከጥቅምና ከቁጥር ጋር ማያያዝ ተገቢ አለመሆኑን በማውሳት ተቃውሞአቸውን አሰምተዋል፡፡
‹‹የእኛ ጥያቄ የገንዘብና የጥቅም አይደለም፡፡ የእኛ ጥያቄ መሠረታዊ የዴሞክራሲ፣ የሰላም፣ የእኩልነትና የፍትሕ ነው፡፡ ስለሆነም ጥያቄያችንን መንግሥትም ሆነ የሚመለከታቸው ተቋማት የቁጥርና የጥቅም ጥያቄ አድርገው ለማሳየት መሞከራቸው የሥርዓቱንና በሥርዓቱ የሚገነቡ ተቋማት የተንሸዋረረ ዕይታና የተዛባ ቁመናን የሚያመላክት ወይም የሚያሳይ ነው፤›› በማለት፣ ጥያቄያቸው አጠቃላይ የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታውን የተመለከተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
አዲሱ አዋጅ በፖለቲካ ፓርቲዎች አማካይነት ከፍተኛ ተቃውሞ ቢያስተናግድም፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ግን የተሰነዘረውን ተቃውሞ እንደማይቀበለው አስታውቋል፡፡
የቦርዱ ሰብሳቢ ወ/ሪት ብርቱካን ነሐሴ 29 ቀን 2011 ዓ.ም. ሰጥተውት በነበረው ጋዜጣዊ መግለጫ ወቅት፣ ‹‹ከፓርቲዎቹ ጋር ወደ ሦስት የሚሆኑ የምክክር መድረኮች ነበሩን፡፡ ይህ በቂ አልነበረም ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ሕጉን አላየሁትም ማለት ውሸት ነው፤›› ሲሉ ምላሽ መስጠታቸው ይታወሳል፡፡
እዚህ ላይ ግን አዋጁን የተቃወሙት ፓርቲዎች ጥያቄያቸው፣ ‹‹አዋጁን አላየነውም የሚል ሳይሆን፣ አዋጁን ለማውጣት በተደረጉ ውይይቶች ወቅት ያነሳናቸው ነጥቦች አልተካተቱም የሚል ነው፤›› ሲሉ የመኢአድ ተወካይ አቶ ሙሉጌታ አበበ የሰብሳቢውን ምላሽ ተችተዋል፡፡
በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ከተከናወነ ምርጫ 2012 የሚቀረው የስምንት ወራት ዕድሜ ያህል ነው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሆኑት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ጨዋታው የሚመራበትን ሕግ በከፍተኛ ሁኔታ እየተቃወሙት ነው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ሥልጣን ሲይዙ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተቃዋሚ ሳይሆን ተፎካካሪ የሚል ስም ሰጥተዋቸው ነበር፡፡ አሁን እነዚህ ተፎካካሪ የተባሉት አካላት መሠረታዊ የዴሞክራሲ፣ የሰላም፣ የእኩልነትና የፍትሕ ጥያቄዎች አሉን እያሉ እየጠየቁ ከመሆናቸው አንፃር እነዚህ መሠረታዊ የተባሉ ጥያቄዎች ምላሽ ሳያገኙ ምን ዓይነት ፉክክር ሊኖር ይችላል የሚለው ጥያቄ የበርካቶች ነው፡፡ እነዚህ ጥያቄዎች በቀሪው አጭር ጊዜ ምላሽ አግኝተው ፉክክሩ የእኩል ይሆናል ወይ የሚለውም እንዲሁ ሌላ ምላሽ የሚሻ ጥያቄ ነው፡፡