Wednesday, February 8, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናበፓርላማ በሚፀድቁ ሕጎች ላይ የሕዝብ ተሳትፎ ዝቅተኛ ስለሆነ ታማኝነት እንደሌላቸው በጥናት ተመለከተ

በፓርላማ በሚፀድቁ ሕጎች ላይ የሕዝብ ተሳትፎ ዝቅተኛ ስለሆነ ታማኝነት እንደሌላቸው በጥናት ተመለከተ

ቀን:

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚፀድቁ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ አዋጆችና ሌሎች አዋጆች ላይ የሕዝቡ ተሳትፎ የለም በሚባል ደረጃ በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ያላቸው ተቀባይነትና በተፈጻሚነታቸው ላይ ያለው እምነት በጣም ዝቅተኛ መሆኑን አንድ ጥናት አመላከተ፡፡

በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠያቂነት በሦስት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሕዝብ አስተዳደር መምህራን በአጠቃላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሠራርና የአባላት ውክልናን በሚመለከት ላለፉት ስድስት ወራት ሲደረግ በነበረ ጥናት የተረጋገጠው፣ ፓርላማው የአሠራር ችግር እንዳለበት መሆኑን አጥኚዎቹ ማክሰኞ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በግሎባል ሆቴል ለግማሽ ቀን ባዘጋጁት የጥናቱ ግኝት ማብራሪያ ላይ አሳውቀዋል፡፡

በጥናቱ ከተሳተፉት መካከል አቶ ጫላ አምዲሳ ስለጥናት እንዳብራሩት፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት ‹‹የፓርላማ ቁጥጥርና ክትትል ምን ይመስላል?›› የሚል ጥናት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ላይ ሠርተው ነበር፡፡ የዚያ ጥናት ውጤት ጥሩ ሆኖ በመገኘቱ በድጋሚ ስለዴሞክራሲና በዴሞክራሲ ሥርዓት ውስጥ የፓርላማ አባላት የሕዝብ ውክልና ምን እንደሚመስል ላለፉት ስድስት ወራት ጥናት ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በዚህ ዘመን ቀጥተኛ ዴሞክራሲ እንደሌለና ሕዝብ በሆነ ነገር ላይ በፈለገበት ጊዜና ቦታ ተነስቶ አንድ ውሳኔ መወሰን እንደማይችል የገለጹት አቶ ጫላ፣ ያለው የዴሞክራሲ ሥርዓት የውክልና ዴሞክራሲ (Representative Democracy) መሆኑን አስታውሰዋል፡፡

የውክልና ዴሞክራሲ ባይሳካ ደግሞ የዴሞክራሲ ሥርዓትም እንደማይሳካ፣ ምክንያቱ ደግሞ የሥልጣን ባለቤት ሕዝብ በመሆኑና እሱን የወከለው አካል ካልተሳካለት ማለትም በፓርላማ ሕዝቡን ወክሎ ካልተናገረ፣ በተለያዩ ውሳኔዎች ላይ አብሮ ካልወሰነ የሥልጣን ባለቤት እንደማይሆንም አክለዋል፡፡ በመሆኑም ተወክሏል የሚባለው አካል ሕዝቡን ወክሎ ለሕዝቡ ካልሠራና ሕዝቡ የሚፈልጋቸው የሕግና የፖሊሲ ማስፈጻሚያ አዋጆች ላይ ተሳትፎ ከሌለው የዴሞክራሲ ሥርዓቱ እንደማይሠራም ጠቁመዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ውስጥ የሕዝብ ውክልና (Representation) ምን ያህል ውጤታማ ይሆኗል?›› በሚለው ጥያቄ መነሻ ጥናታቸውን በጥልቀት ማድረጋቸውን የተናገሩት አቶ ጫላ፣ ውክልና በየትኛውም ዓለም የራሱ ችግር አለው ብለዋል፡፡ አንድ የምክር ቤት አባል የወከለውን ሕዝብ ፍላጎት ሙሉ በሙሉ ማሟላት እንደማይችልና የሕዝብን ችግር ለመፍታት በዓለም ደረጃ እንደ አማራጭ የተያዘው፣ ሕዝብን ያሳተፈ የፓርላማ ውሳኔ ማሳለፍ (Parliamentarian Public Engagement) መሆኑንም አስረድተዋል፡፡ ሕዝቡ የሚወክለው አባል የአምስት ዓመታት የፓርላማ ውክልናው እስከሚያልቅ ድረስ እጁን አጣጥፎ መመልከት እንደሌለበት፣ የፖሊሲ ማስፈጸሚያ አዋጆችና አዳዲስ አዋጆች ሲወጡ ከመፅደቃቸው በፊት መሳተፍና ግብዓት መስጠት እንዳለበት ተናግረዋል፡፡ ፓርላማው ሕዝብ የወከለበትን ምክንያት በማጥናትና በማየት የሕዝብ ድምፅ መሆን እንዳለበትም አክለዋል፡፡

በጥናታቸው በፓርላማው ውስጥ በርካታ ክፍተቶች እንዳገኙ የጠቆሙት ባለሙያው፣ በምክር ቤቱ ላይ ሕዝብ ያለው አመኔታ በጣም ዝቅተኛ መሆኑንና የምክር ቤቱ አባላትም ‹‹ፓርቲዬ ለሚወክለው ሕዝብ ከእኔ የተሻለ ያውቅለታል፤›› የሚል አመለካከት እንዳላቸው ለማወቅ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ኢሕአዴግ የሚከተለው ወይም የሚያራምደው ‹‹ዴሞክራሲዊ ማዕከላዊነት›› በማዕከል የተወሰነውን ውሳኔ ሌላው የፓርቲ አባል ሊቃወመው እንደማይችልና ያቀረበውን የፖሊሲ ማስፈጸሚያም ሆነ ሌላ አዋጅ ሲያቀርብ ዝም ብሎ ማፅደቅ መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ ይህንን በጥናታቸው ማረጋገጣቸውን ተናግረዋል፡፡ በመሆኑም ‹‹ዴሞክራሲዊ ማዕከላዊነት ኢዴሞክራሲያዊነት ነው፤›› ብለዋል፡፡

የምክር ቤቱ አባል የሚሰማው የመረጠውን ሕዝብ ሳይሆን ፓርቲው ያለውን መሆኑንም አክለዋል፡፡ ያ የሚሆነው ደግሞ የምርጫ ዘመኑ ሲጠናቀቅ ለመሾም ወይም በሌላ ሥር ላይ ለመመደብ የሚጠቅመው የሕዝብ ድምፅ ሳይሆን፣ ፓርቲ በመሆኑ ፓርላማው ጥርስ የሌለው አንበሳ መሆኑን በጥናታቸው ማረጋገጥ መቻላቸውን አስረድተዋል፡፡ በዚህ ምክንያት ሕዝብን ወክሎ በፓርላማ ተፅዕኖ መፍጠር እንዳልተቻለም ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ የፓርላማው ችግር የአሠራር መሆኑን በጥናቱ መረጋገጡን የገለጹት አቶ ጫላ፣ ሌላው ችግር ደግሞ የሎጂስቲክስ እጥረት ስላለበት የምክር ቤት አባላቱ ወደ መረጣቸው ሕዝብ መሄድ የሚችሉት በዓመት ሁለት ጊዜ ማለትም በየካቲት ወር ለዕረፍት ሲዘጋና በክረምት ሲዘጋ ብቻ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አንድ የምክር ቤት አባል የመረጠውን ሕዝብ አወያይቶ ሲመለስ ለምክር ቤቱ ሪፖርት ቢያደርግም፣ በእያንዳንዱ አባል ሪፖርት ላይ ውይይት እንደማይደረግ በጥናቱ መታወቁን የገለጹት ባለሙያው፣ ተመሳሳይ ጥያቄዎች ተጣምረው ለቋሚ ኮሚቴ እንደሚቀርቡም ጠቁመዋል፡፡ ከቋሚ ኮሚቴ ወደ አፈ ጉባዔ ጽሕፈት ቤት ይላክና ከዚያ ደግሞ ወደ አስፈጻሚ ይላካል፡፡ በጠያቂውና በሥራ አስፈጻሚ መካከል ባለው ርቀት ጥያቄው ይዘቱን ቀይሮ እንደሚቀርብና አስፈጻሚም ምላሽ ሳይሰጥ የሚቀርበት አሠራር እንዳለ ተናግረዋል፡፡ ምክር ቤቱ አሠራር ዘርግቶ ከሕዝብ ለተነሳው ጥያቄ አስፈጻሚ ተገቢውን ምላሽ መስጠት አለመስጠቱን ማረጋገጥ ቢኖርበትም፣ ያንን የሚያደርግበት አሠራር እንደሌለ አስረድተዋል፡፡

በዚህ ምክንያት የምክር ቤት አባል ከዓመታት በኋላ ተመልሶ ወደ ሕዝቡ ሲሄድ፣ ‹‹አምና በቀረብንልህ ጥያቄ ምላሽ ሳትሰጠን አሁን ለምን መጣህ?›› የሚል ጥያቄ እንደሚያቀርብና በውክልናው ላይ እምነት እንደሌለው በጥናቱ ተጠቁሟል፡፡ የፓርላማው የአሠራር ሥርዓት ዝግ ከመሆኑም በተጨማሪ፣ ተወካዮቹ በፓርላማው አዋጅ ማውጣት ሒደት ውስጥ የእነሱ ውክልና ለፓርቲው፣ ሕዝቡ የመረጣቸው ደግሞ የፓርቲያቸውን ፕሮግራም እንዲያስፈጽሙ መሆኑን ብቻ እንደሚያውቁ ባለሙያው ተናግረዋል፡፡  

ሌላው በፓርላማውና በአስፈጻሚ መካከል ያለው የሥልጣን ምጣኔ (Power Balance)፣ ምክር ቤቱ በአስፈጻሚው ላይ ተፅዕኖ  መፍጠር በማይችልበት ደረጃ ላይ መሆኑንም በጥናቱ ማወቅ መቻሉን አቶ ጫላ ገልጸዋል፡፡

በአጠቃላይ ችግሩ የኢሕአዴግ የዴሞክራሲ ማዕከላዊነት ችግር መሆኑን የገለጹት ባለሙያው፣ በፓርቲው ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን ላይ ያሉ ሰዎች ከፓርላማው በላይ ሥልጣን እንዳላቸውም ተናግረዋል፡፡ ምድባቸው አስፈጻሚ ውስጥ በመሆኑና የምክር ቤቱ አባላት ዘመናቸው ሲጠናቀቅ የግል ጥቅማቸውና ፍላጎታቸው የሚወሰነው በእነዚሁ ባለሥልጣናት በመሆኑ፣ ፓርላማው ውስጥ እንደፈለጉ ለመናገር ትልቅ ተፅዕኖ እንዳለ አብራርተዋል፡፡

ይኼንን ችግር ለማስወገድ ወደ ፓርላማ የሚገቡ የምክር ቤት አባላት ከተለያዩ ፓርቲዎች ማካተት መሆን እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ ፓርላማው የሚያስተላልፋቸውን ውሳኔዎችና የሚያፀድቃቸውን ሕጎች በአንድ ቋንቋ ብቻ ከማድረግ፣ በድረ ገጹ ላይ በአምስትና ከዚያም በላይ ቋንቋዎች መጠቀም እንዳለበት አስረድተዋል፡፡

ከመገናኛ ብዙኃን ጋር ተቀራርቦ መሥራት እንዳለበትና ሕዝብ ስለፓርላማው ዕውቀትና ቅርበት እንዲኖረው ማስተዋወቅ እንዳለበትም፣ በጥናታቸው የመፍትሔ ሐሳብ ማስቀመጣቸውን ባለሙያው ተናግረዋል፡፡        

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ጥቁር የመልበስ ውዝግብና የእምነት ነፃነት በኢትዮጵያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ኅዳር ወር ላይ በፓርላማ...

የኢንሹራንስ ዘርፉን የሚቆጠጠር ገለልተኛ ተቋም ለመመሥረት እንቅስቃሴ ተጀመረ

ከ70 በላይ አዳዲስ የፋይናንስ ተቋማት ዘርፉን ሊቀላቀሉ ነው የኢትዮጵያ ብሔራዊ...

እስቲ አንገፋፋ!

እነሆ መንገድ። ጊዜና ሥፍራ ተጋግዘው በውስንነት ይዘውናል። መፍጠን ያቃተው...