Saturday, April 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜና‹‹ኢሕአዴግ አሁን ባለው ቁመና እንደማይቀጥል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ...

‹‹ኢሕአዴግ አሁን ባለው ቁመና እንደማይቀጥል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል›› ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)

ቀን:

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ሰሞኑን ከሸገር 102.1 ኤፍኤም ሬዲዮ ጣቢያ ጋር ባደረጉት ሰፊ ቃለ ምልልስ፣ ኢሕአዴግ አሁን ባለው ቁመና እንደማይቀጥል እርግጠኛ ሆኖ መናገር እንደሚቻል አስታወቁ፡፡

ከሬዲዮ ጣቢያው አዘጋጅ ከቀረቡላቸው በርካታ ጥያቄዎች መካከል በምርጫ 2012 እሳቸው የሚመሩት ኢሕአዴግ መካሄድ እንዳለበት አቋሙን መግለጹ፣ የምርጫ ቦርድ እንደገና መቋቋሙ መልካም ቢሆንም በቂ ጊዜ ስለመኖሩ፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች መብዛትና ዝግጅታቸው ደካማ መሆኑ፣ የአክቲቪስቶች ሚናና ወሰን አለመታወቅ፣ በየሥፍራው ባሉ አለመረጋጋቶች ሳቢያ ሰላማዊ ምርጫ ለማካሄድ ማዳገቱ፣ ውጤቱም  አገሪቱ ወደ ብጥብጥ ሊያመራት እንደሚቻል፣ ሁለቱ የኢሕአዴግ ድርጅቶች ወደ ፓርቲ የመቀየር ምልክት ቢያሳዩም፣ ግንባሩ ግን የቅርፅ ለውጥ አለማሳየቱና ከግንባርነት ወደ ፓርቲ መለወጥን በተመለከተ የቀረቡት ተጠቃሽ ናቸው፡፡

ከኢሕአዴግ ጉዳይ በመነሳት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰጡት ምላሽ ኢሕአዴግ በጉዳዩ ላይ እየተወያየ መሆኑን ገልጸው፣ በቅርቡ አቋሙን እንደሚያስታውቅ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ኢሕአዴግ አሁን ባለው ቁመና እንደማይቀጥል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል፤›› ብለው፣ አሁን ባለው አወቃቀር አይቀጥልም ሲሉ አስታውቀዋል፡፡

‹‹ምን ይሆናል? እንዴት ይሆናል? እንዴት ይጀመራል? እንዴት ይፈጸማል? እየተወያየን ነው፡፡ ዴሞክራሲን በውስጥ ካልተለማመድነው በውጭ ልንተገብረው ስለማንችል በውይይት፣ በምክክርና በንግግር የምንወጣው ነው፡፡ ግን በጥቂት ጊዜ ውስጥ ውይይታችንን ቋጭተን አንድ ዜና ይዘን እንወጣለን ብለን እናስባለን፤›› ብለዋል፡፡ ዜናው በመጨረሻ ምን ይሆናል የሚለውን የሚወስነው ውይይቱ ስለሆነ፣ ቀድመው መልኩን ወይም ቅርፁን መናገር እንደማይችሉ አስረድተው፣ ‹‹ግን የሆነ ለውጥ ማድረጋችን አይቀርም ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፤›› ብለዋል፡፡

ምርጫን በተመለከተ ደግሞ ምርጫን እንከንና ችግር አልባ አድርጎ ማሰብ ከመጀመሪያው ያለ መገንዘብ እንደሆነ ገልጸው፣ ምርጫ ውድድር ያለበት መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ ነገር ግን ከልክ ያለፈ ከሆነ ደግሞ መበላላት እንደሚያመጣ አመላክተዋል፡፡

‹‹ፉክክሩ እንዳለ አያስፈልግም ካልን ደግሞ ያየነውን ችግር ያስከትላልና ምርጫ ያስፈልጋል፡፡ ምርጫ ሪስክ (አደጋ) አለው፤›› ካሉ በኋላ፣ ኢትዮጵያውያን አደጋውን ማስቀረትና መቆጣጠር እንደሚችሉና ቢያንስ አምስት ምርጫዎች ማካሄዳቸውን፣ በምርጫ ውስጥ ዝም ብለው ያለፉበትም ጊዜ መኖሩንና ከምርጫ በኋላ ተጋድለው የሞቱበትም ጊዜ እንደነበረ አስታውሰዋል፡፡

‹‹ከምርጫ በኋላ ያለ ግጭት ሰው ይገላል እንጂ መቀጠላችን አይቀርም፡፡ አገር ማስቀጠሉና መንግሥት መቀጠሉ ላይ ችግር የለም፡፡ ሰው ነው የሚሞተው፡፡ ሰው እንዳይሞት ነው ኮንሸስ (ንቁ) መሆን የሚያስፈልገው፡፡ ምርጫ ያስፈልጋል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ምርጫ የሚያስፈልግበት ዋናው ምክንያት ቅድም የተነሱትን ችግሮች በሙሉ በሕዝብ ዕይታና መንግሥትም ኃላፊነት ወስዶ እንዲመልሳቸው ዕድል ስለሚሰጥ ነው ብለው፣ አሁን ባለው ሁኔታ ቢራዘም የሚሉ ሰዎች በጣም ራሽናል (ምክንያታዊ) ሐሳብ እንዳላቸውና ለዚህም ሰላምንና ግጭት ያነሳሉ ብለዋል፡፡ አይራዘም የሚሉትም ሰዎች ሕጋዊ ነገር እንደሚያነሱ፣ ‹‹ዋናው ጉዳይ ግን ሁለት ሦስት አራት ዓመት ብናራዝመው ያ የሚባለው ተቋም ይፈጠራል ወይ? እኛ በባህላችን በአጠረ ጊዜ ነገርን ኤግዝኪውት (መፈጸም) የማንችል ሆነን ስናበቃ፣ ይህንን ምርጫ ግማሽ መንገድ የሚወስድ አድርገነው መጠቀም ነው ያለብን፡፡ ሁሉን ችግር የሚፈታ ሊሆን አይችልም፡፡ ግን ግማሽ መንገድ እንዲወስደን አድርገን መሠራት አለበት፡፡ ይህ እንዲሆን ጋዜጠኞች፣ የሙያ ማኅበራት፣ በምርጫ የሚወዳደሩ ፓርቲዎች ሪስፖንስቢሊቲ (ኃላፊነት) አለባቸው፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡

‹‹አሁን ያሉ ፓርቲዎች አሥር አሥር ወንበርን እንኳን ቢያሸንፉ (ማክሲመም ማለት ነው) መንግሥት መሆን አይችሉም፡፡ አንድ ፓርቲ የሚወዳደረው መንግሥት ለመሆን ነው፡፡ ቢያንስ ራሱ ካልቻለ ደግሞ ከሌሎች ሰዎች ጋር ሆኖ ነው መንግሥት መፍጠር የሚፈልገው፡፡ መቶ ፓርቲ ካለ አሥር አሥር ወንበር ምንም ማለት አይደለም፡፡ አሥር ሰዎች ሥራ ያስይዛል፣ የፓርላማ አባል ያደርጋል እንጂ መንግሥት አያደርግም፡፡ ማሰብ ያለብን ነገር ሰብሰብ ማለት ነው፡፡ ሰብሰብ ስንል በዚያው ልክ መደመጥ፣ በዚያው ልክ በሥልጣን ውስጥ ቦታ ማግኘት፣ የማድረግ አቅማችንና  በዚያው ልክ የማስተዳደር አቅማችን ያድጋል፡፡ ለምሳሌ 10 ሺሕ፣ 100 ሺሕ፣ 20 ሺሕ፣ አንድ ሚሊዮን አባል ያላስተዳደረ ፓርቲ የሆነ ቦታ ሰጥተን ግዛ ብንለው ከየት ያመጣዋል? ልምምድም ስለሆነ ሰብሰብ ማለት አስፈላጊ ነው፤›› ሲሉ አክለዋል፡፡

ምርጫውን የኢትዮጵያ ሕዝብ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ይመራዋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረው፣ ‹‹እኛ ከሎው ኢንፎርስመንት (ሕግ ከማስከበር) አንፃር አስፈላጊውን ዝግጅት እናደርጋለን፡፡ ዘንድሮ የነበረው የመንጋ ጨዋታ አይቀጥልም፡፡ ሥርዓትና ሕግ የሚከበርበት መንገድ የግድ ነው እሱ፡፡ ለዚያ የሚያስፈልገውን ከፍተኛ ዝግጅት እያደረግን ነው ያለነው፡፡ ፀጥታ እናስከብራለን፡፡ ሕዝቡ ይተባበረናል፡፡ ይኼ ሆኖ ሲያበቃ አክቲቪስቶችም በሕግ፣ ፖለቲከኞችም በሕግ፣ ወጣቶችም ነገሩን ከዘላቂ ጥቅም አንፃር እያዩት ከሄዱ መፍትሔው ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ካልሆነስ? በ1997 ዓ.ም. እንዳየነው ሰዎች ይሞታሉ፣ ሰዎች ይጎዳሉ፣ ቤተሰብ ይጎዳል፣ እናት ታለቅሳለች፣ የሚቀየር ነገር አይኖርም፡፡ ወደዚያ ዓይነት ስህተት መግባት የለብንም፡፡ በኢሕአዴግ በኩል እናድርግ ብሎ ብቻ ሳይሆን፣ ምርጫው በተቻለ መጠን ዴሞክራሲያዊ እንዲሆን፣ ነፃና ገለልተኛ እንዲሆን ማክሲመም (በከፍተኛ ደረጃ) እንሠራለን፡፡ በምርጫው ብንሸነፍም በፍቅር እናስረክባለን፡፡ ብናሸንፍና ብንመረጥ ደግሞ በኃላፊነት እንሠራለን፡፡ ሁለቱ የዴሞክራሲ መንገድ ነው፡፡ ውድድርም፤›› ብለዋል፡፡

ለዚህ ሁሉም ዝግጁ መሆን እንዳለበትና ችግሩ ይመጣል ብለው እንደማይሠጉና ትምህርትም እንደተወሰደበት ገልጸው፣ ‹‹ቆስለን እናውቃለን፣ ተጎድተን እናውቃለን፣ ያ ይደገማል ብዬ አላስብም፡፡ በዚህ ዓመት (2011 ዓ.ም.) በጣም በርካታ ፈተናዎች አልፈናል፡፡ ሶማሌ ካጋጠመን ችግር፣ ሲዳማ ካጋጠመን ችግር፣ ቡራዩና ወለጋ ካጋጠመን ችግር፣ አሁን በአማራ ክልል ካጋጠመን ችግር የተለየ ነገር አያጋጥመንም፡፡ ካጋጠመም እናልፈዋለን፡፡ በዚህ ነው የማየው፡፡ ችግር አለ ወይም የለም ብዬ ሳይሆን ሊያጋጥም ይችላል፡፡ እንዴት እናልፈዋለን? እንዴት ብናደርግ ሰላማዊ ይሆናል? ከሕዝባችን ጋር እንዴት እንወያይ? ብለን በምክክር የምናደርገው ይሆናል፤›› ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢያደርጉ ደስ የሚላቸውን ሲያስረዱም ሰብሰብ ማለት ነው ብለዋል፡፡ ሁለተኛ ሐሳብ ማደራጀት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹አሁን እንዳለፈው እናንተ አስራችኋል፣ ተሳድባችኋል፣ እናንተ ምናምን ናችሁ፣ እናንተ ኦሮሞ ናችሁ እየተባለ ምርጫ አይሆንም፡፡ ምርጫ ሐሳብ ነው፡፡ ፖለቲካን እንዲህ ነው የምናስበው፣ ኢኮኖሚውን እንዲህ ነው የምናስበው ብለው ይህንን አድርገን ኢትዮጵያን እናሻግራለን የሚል ኦልተርኔቲቭ ቶውት (አማራጭ ሐሳብ) ካላመጡ ዝም ብሎ በወቀሳና በክስ ለማሸነፍ መሄድ ብዙ የሚያዋጣ አይመስለኝም፡፡ በጣም ብዙ ሰው እየነቃና እየተማረ ስለሆነ፣ ሁሉም ተዘጋጅቶ በሐሳብ ከሆነ ግን አንዳንድ ሐሳቦቹ በምርጫ ባሸነፈው ፓርቲ ውስጥ ገብተው ሥራ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ ሐሳብን ወደ ሐሳብ፣ ወደ እምነት፣ ወደ ሠለጠነ መንገድ ካመጣነው ጥሩ ይሆናል ብዬ አስባለሁ፤›› በማለት አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተወግዘው የነበሩ ሦስቱ ሊቀጳጳሳትና 20 ተሿሚ ኤጲስ ቆጶሳት ውግዘት ተነሳ

_ቀሪዎቹ ሦስት ህገወጥ ተሿሚዎች የመጨረሻ እድል ተሰጥቷቸዋል ​ ጥር 14...

በሕወሓት አመራሮች ላይ ተመስርቶና በሂደት ላይ የነበረው የወንጀል ክስ ተቋረጠ

በቀድሞ የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት ደብረጽዮን ገብረሚካኤ,(ዶ/ር)ና ባለፈው ሳምንት በተሾሙት...

[የምክር ቤቱ አባል ላቀረቡት ጥያቄ በተሰጣቸው ምላሽ አቤቱታቸውን ለክቡር ሚኒስትሩ እያቀረቡ ነው]

ክቡር ሚኒስትር እየሆነ ያለው ነገር ትክክል ነው? ምነው? ምክር ቤቱም ሆነ...

የጉራጌ የክልልነት ጥያቄ ትኩሳት

ቅዳሜ መጋቢት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. በጉራጌ ዞን ወልቂጤ...