የሪል ስቴት አልሚው ደንበኛው ለሚከፍለው ገንዘብ በባንክ የተረጋገጠ ዋስትና መስጠት አለበት
የሪል ስቴት አልሚው ስለቤቶቹ ማስታወቂያ ለማስነገር ከመንግሥት ፈቃድ ማግኘት ይጠበቅበታል
የሪል ስቴት አልሚዎችን የሚቆጣጠርና የቤት ፈላጊ ደንበኞቻቸውን መብት የሚያስከበር የተለያዩ ግዴታዎችን የሚጥል ረቂቅ ሕግ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት መላኩን፣ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ አመለከተ፡፡
ረቂቅ ሕጉ የተዘጋጀው የሪል ስቴት ልማትና ግብይት ሥርዓቱ የግልጽነትና የተጠያቂነት አሠራር የተከተለ እንዲሆን በማድረግ በዘርፉ የሚታዩትን ሙስናና ብልሹ አሠራሮችን በመከላከል የደንበኞችን ፍላጎት የሚያስጠብቅ ዘርፍ ማድረግ ስለመሆኑ በረቂቅ ሕጉ ተመልክቷል፡፡
በዚህም መሠረት የሪል ስቴት አልሚው ቤቶቹን ለመገንባት የሚያስችለውን የመሬት ይዞታ ማረጋገጫና የግንባታ ፈቃድ ከሚመለከተው አካል ከመረከቡ በፊት፣ ስለግንባታው በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ ማስነገርም ሆነ ሥራውን ማስተዋወቅ፣ ደንበኞችን መመዝገብና ቅድመ ክፍያዎችን መሰብሰብ እንደማይችል ረቂቅ ሕጉ በአልሚዎች ላይ የሚጥለው አንዱ ግዴታ ነው፡፡
የሪል ስቴት አልሚው በሕጋዊ መንገድ የተረከበው መሬት ሊያስተናግድ ከሚችለው ደንበኛ በላይ መመዝገብ እንደማይችል፣ የሪል ስቴት አልሚው ከከተማው ጋር በገባው ውል፣ ባቀረበው ዝርዝር ፕላንና በተሰጠው የግንባታ ፈቃድ መሠረት ቦታውን ለተፈቀደለት አገልግሎት የማዋልና ወቅቱንና ጥራቱን የጠበቀ ቤት ከደንበኞች ጋር በተዋዋለው ውል መሠረት መገንባት፣ ሌሎች በረቂቁ የተካተቱ ግዴታዎች ናቸው፡፡
የሪል ስቴት አልሚው ባቀረበው ዝርዝር ፕላን መሠረት ግንባታውን እያከናወነ መሆኑን ለማረጋገጥ የከተማ አስተዳደሮች የሚመድቧቸው ተቆጣጣሪዎች በማንኛውም ወቅት የኢንስፔክሽን ሥራ ሊያደርጉ እንደሚችሉና አልሚውም ለዚህ ተግባር የመተባበር ግዴታ እንደሚኖርበት በረቂቁ ተካቷል፡፡ በሌላ በኩል የሪል ስቴት አልሚው ስለሚገነባቸው ቤቶች በመገናኛ ብዙኃን ማስታወቂያ ለማስነገር የሚችለው፣ የማስታወቂያውን ኮፒ ለከተማ አስተዳደሩ ከሰጠና የከተማ አስተዳደሩም ማስታወቂያውን እንዲያስነግር ፈቃድ ከሰጠው በኋላ ብቻ እንደሚሆን የረቂቁ ድንጋጌ ያመለክታል፡፡ ማንኛውም ደንበኛ አልሚው ባስነገረው ማስታወቂያ ውስጥ በተካተተ የውሸት ወይም የተሳሳተ መረጃ ምክንያት ኪሳራ ከደረሰበት አልሚው በደንበኛው ላይ የደረሰውን ኪሳራ የማካካስ ግዴታ እንደሚኖርበት፣ ወይም ደንበኛው በዚህ ምክንያት ውል ማቋረጥ ከፈለገ አልሚው የተከፈለውን ቅድመ ክፍያ ሙሉ በሙሉ ሕጋዊ ወለዱን ጨምሮ የመመለስ ግዴታ እንደሚኖርበት በረቂቁ ተካቷል፡፡
ረቂቁ የያዘው ሌላው ድንጋጌ ደንበኛው ለሚከፍለው ገንዘብ የሪል ስቴት አልሚው ሕጋዊ ደረሰኝና በባንክ የተረጋገጠ የዋስትና ማረጋገጫ መስጠት እንደሚኖርበት ያመለክታል፡፡
የሪል ስቴት አልሚው ከደንበኛው ጋር በገባው ውል መሠረት ግንባታውን አጠናቅቆ ቤቱን በተቀመጠው የጊዜ ገደብና የጥራት ደረጃ ለደንበኛው ማስረከብ እንደሚኖርበት፣ በማንኛውም ሁኔታ የማስረከቢያ የጊዜ ገደቡ ሊራዘም የሚችለው በውሉ ከተቀመጠው የጊዜ ገደብ ሃምሳ በመቶ ያልበለጠ የጊዜ ገደብ ውስጥ እንደሚሆን፣ ሌላው በረቂቁ የተካተተ የደንበኞችን ጥቅም የሚያስከብር ድንጋጌ ነው፡፡
የሪል ስቴት አልሚው እያንዳንዱን የግንባታ እርከን በጊዜ ፕሮግራም ከፋፍሎ እስከ ፕሮጀክቱ መጠናቀቂያ ድረስ ለደንበኛው በጽሑፍ ማሳወቅ እንደሚኖርበት፣ በተጨማሪም ግልጽነትን ለማረጋገጥ የሚረዱ ሌሎች ከፕሮጀክቱ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን መረጃዎች ለደንበኛው በጽሑፍ ወይም በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ግልጽ ማድረግ፣ ረቂቁ በአልሚው ላይ የሚጥለው ሌላ ግዴታ መሆኑን ሰነዱ ያስገነዝባል፡፡ በተጨማሪም አልሚው ከደንበኞች ላይ ቅድመ ክፍያ መቀበል የሚችለው ቤት ገንብቶ ለማስረከብ የተደረገ ውል ከተፈራረመ በኋላ ብቻ እንደሚሆን በረቂቁ ተካቷል፡፡
ረቂቅ ሕጉ አልሚውን ከሚመለከቱ ድንጋዎቹ በተጨማሪ፣ የሪል ስቴት ልማት ፈቃድ ለሚሰጡ የፌዴራል ከተማ አስተዳደሮችን የሚመለከቱ ድንጋዎችንም አካቷል፡፡ በዚህም መሠረት ለሪል ስቴት አልሚዎች የግንባታ ቦታን በሊዝ ሕጉ መሠረት በጨረታ ማስተላለፍ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በጨረታ አሸናፊነቱ ለተረጋገጠና የሚጠበቅበትን መሥፈርት አሟልቶ ክፍያ ለፈጸመ አልሚ በ60 ቀናት ውስጥ ቦታውን ማስረከብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በዚህ መሠረት ውል ከተፈጸመ በኋላ ለሪል ስቴት ልማት በተሰጠው ቦታ ላይ ክርክር ቢነሳ ችግሩን የመፍታት ኃላፊነት የከተማ አስተዳደሩ እንደሆነ ይህ የማይቻል የሚሆንበት ሁኔታ ሲያጋጥም በ30 ቀናት ውስጥ ተመሳሳይ ደረጃ ያለው ተለዋዋጭ ቦታ የመስጠት ግዴታ በአስተዳደሩ ላይ ይጥላል፡፡
ረቂቁ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት የተላከ መሆኑንና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አማካይነት በ2012 ዓ.ም. ከሚወጡ አዋጆች መካከል አንዱ እንደሚሆን ሪፖርተር ያገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡