የኤሌክትሮኒክስ ታክሲ ሥምሪት ሰጪ ድርጅቶች ከሥርዓቱ እንደማይወጡ ማረጋገጫ ሰጠ
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ የኮድ አንድና የኮድ ሦስት ተሽከርካሪዎች፣ በሚፈቀድላቸው ደረጃና መሥፈርት መሠረት ተመዝገበውና የንግድ ፈቃድ አውጥተው መሥራት እንደሚችሉ አስታወቀ፡፡ የንግድ ፈቃድ ሳይኖራቸው በኮድ ሦስት ሲሠሩ የነበሩ ግለሰቦች፣ የንግድ ፈቃድ ማውጣት እንደሚጠበቅባቸውና ወደ ሥርዓት የመግባት ግዴታ እንዳለባቸው አሳስቧል፡፡
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማው የኢኮኖሚ ክላስተር አስተባባሪና የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ሰሎሞን ኪዳኔ (ዶ/ር) ማክሰኞ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ እንዳደረጉት፣ ከነሐሴ 24 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ በኮድ አንድ የታክሲ ትራንስፖርት ወይም በኮድ ሦስት የንግድ ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች፣ በዚሁ አግባብ መሠረት ተመዝገበውና ፈቃድ አግኝተው መሥራት የሚችሉበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ በዚህ መሠረት የኤሌክትሮኒክስ የታክሲ ሥምሪት (ኢታስ) አገልግሎት አሰጣጥ መመርያ ቁጥር 05/2011 ወጥቶ ተግባራዊ መደረግ እንደጀመረ አስታውቀዋል፡፡
አያይዘውም በኢታስ የሚሠማሩ ድርጅቶችና የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችም ሆኑ ማኅበራት ወይም ድርጅቶች፣ በታክሲ ዘርፍ ወይም በመኪና ኪራይ ወይም በንግድ ዘርፍ መሠማራት ይፈቀድላቸዋል በማለት፣ ከዚህ ቀደም ታግዶ የቆየው የኮድ አንድና የኮድ ሦስት የሰሌዳ ቁጥር ፈቃድ አሠጣጥ ሥርዓት በአዲሱ መመርያ መሠረት እንደሚከናወን ገልጸዋል፡፡ በኮድ አንድ የታክሲ አገልግሎት መስጠት የሚፈልጉ የኮድ አንድ ፈቃድ የማውጣትና መኪኖቻቸውን ሰማያዊ በነጭ ቀለም የማስቀባት ግዴታ አለባቸው፡፡ በኮድ ሦስት መሥራት የሚፈልጉም፣ የንግድ ፈቃድ የማውጣት ግዴታ ተቀምጦባቸዋል፡፡ በመሆኑም እንደ ምርጫቸው የታክሲ ወይም የኪራይ ንግድ ዘርፍ ውስጥ ፈቃድ በማውጣት፣ በኤሌክትሮኒክስ ታክሲ ሥምሪት ኩባንያዎች በኩል ተመዝግበው መሥራት እንደሚችሉ ሰሎሞን (ዶ/ር) አረጋግጠዋል፡፡
መመርያው ነባር የኢታስ ድርጅቶችንም ሆነ አዲስ የሚመጡትን እንደማያግድ፣ ይልቁንም የውድድር ሜዳውን ለሁሉም በእኩል ደረጃ ክፍት እንደሚያደርገው ያብራሩት ሰሎሞን (ዶ/ር)፣ በመሥፈርትነት ከተቀመጡት መጠይቆች መካከል በስልክ ጥሪና በመተግበሪያ አማካይነት ትራንስፖርት ሰጪዎችን ከተጠቃሚው የሚያገናኙ የኢታስ ድርጅቶች፣ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ሥር በሚገኘው ትራንስፖርት ባለሥልጣን በኩል መመዝገብና ውል መዋዋል ይጠበቅባቸዋል፡፡ በተዋዋሉት መሠረት የትራንስፖርት ሥምሪት አገልግሎት ለመስጠት ልዩ ፈቃድ ተሰጥቷቸው የሚያገናኟቸው ተሽከርካሪዎች ዝቅተኛውን መሥፈርት ማሟላታቸው ሲረጋገጥ፣ ለሥምሪት የሚጠበቅባቸውን ግዴታዎችና መጠይቆችም ሲያሟሉ ኮድ አንድ ወይም ታክሲ፣ እንዲሁም ኮድ ሦስት የኪራይ ወይም የንግድ ተሽከርካሪዎች አገልግሎት መስጠት እንደሚችሉ አስታውቀዋል፡፡
ይሁን እንጂ በኢታስ ሥርዓት አማካይነት ‹‹የታክሲ አገልግሎት መስጠት የሚችሉት በኮድ አንድ የታክሲ አገልግሎት የተመዘገቡና ፈቃድ ያላቸው ተሽከርካሪዎች ብቻ ናቸው›› በማለት መመርያው ሲያስቀምጥ፣ ይህ ማለት ግን በንግድ ሥራ ዘርፍ ፈቃድ አግኝተው በኮድ ሦስት የተመዘገቡትም በንግድ አሠራር መሠረት ፈቃድ አግኝተውና ተመዝግበው መሥራት እንደሚችሉ ኃላፊው አረጋግጠዋል፡፡
በመሆኑም በኢታስ አገልግሎት ሰጪነት የሚመዘገቡና ውል የሚዋዋሉ ድርጅቶች፣ ለአስተዳደሩ ትራንስፖርት ቢሮ ወይም ለባለሥልጣኑ የኔትወርክ መረጃቸውን የማሳወቅና እስከ አንድ ዓመት የሚቆይ የመረጃ ቋት ሥርዓት የማደራጀትና በተለፈገ ጊዜም ባለሥልጣኑ ለክትትልና ቁጥጥር የሚረዳውን መረጃ ‹‹ሪድ ኦንሊ አክሰስ›› ከኔትወርካቸው ማግኘት የሚችልበት አሠራር እንዲፈጥሩ በመመርያው አስቀምጧል፡፡
እንዲህ ያሉትን መሥፈርቶች ጨምሮ የሚያሠማሯቸው ተሽከርካሪዎችም ዝቅተኛ የሲሊንደር አቅም ወይም የፈረስ ጉልበት ያላቸው፣ ብዛታቸው፣ ዓይነታቸው፣ ቀለማቸውና መሰል ቴክኒካዊ ይዘቶች እንዳሟሉ የሚጠይቁ መረጃዎችን ማቅረብ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ከዚህ ባሻገር በኮድ ሁለት ፈቃድ አውጥተው የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ግለሰቦችና ድርጅቶች ‹‹ሕገወጦች›› ናቸው ያሉት ሰሎሞን (ዶ/ር)፣ በፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ሕግ መሠረት የሰሌዳ ቁጥር አሰጣጥ እንደሚደነግገው፣ የግል አውቶሞቢል ለግል ሥራ ኮድ ሁለት፣ የታክሲ አገልግሎት ለመስጠት ኮድ አንድ፣ እንዲሁም የንግድ ሥራ ለመሥራትም ኮድ ሦስት፣ መፈቀዱን በመጥቀስ፣ በዚህ አግባብ የማይሠሩ አካላት ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል፡፡
ለሁሉም የሚያገለግል አዲስና አንድ ወጥ ታሪፍ በቅርቡ እንደሚወጣ፣ የመኪኖች የአገልግሎት ዘመን ግን በባለሥልጣኑ እንደማይወሰን ያብራሩት ሰሎሞን (ዶ/ር)፣ ይሁንና የትራንስፖርት ቢሮ የሚያወጣውን ታሪፍ በመተላለፍ ከወጣው ታሪፍ በላይ የሚያስከፍሉ የኢታስ መተግበሪያ አገልግሎት ሰጪ ድርጅቶች ቅጣት እንደሚጠብቃቸው አስታውቀዋል፡፡ በመመርያው መሠረትም ከአንድ ሺሕ እስከ ሦስት ሺሕ ብር ቅጣትና የስድስት ወራት ዕገዳ ቅጣት ይጣልባቸዋል፡፡ በየደረጃው ለሚፈጸሙ ሌሎች ጥሰቶችና ጥፋቶች እንደ ደረጃቸው እስከ 15,000 ብርና ፈቃድ እስከማገድ የሚደርሱ ዕርምጃዎች በመመርያው ተደንግገዋል፡፡