Friday, October 7, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - ማስታወቂያ -
  - ማስታወቂያ -

  ቶታል ኢትዮጵያ በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ የሞተር ዘይት መለወጫ ጣቢያዎች እንደገነባ አስታወቀ

  - ማስታወቂያ -

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  ላለፉት 69 ዓመታት በኢትዮጵያ የነዳጅ ማከፋፈል ዘርፍ ተሰማርቶ የቆየው ቶታል ኢትዮጵያ፣ በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ 52 የተሽከርካሪዎች የሞተር ዘይትና የቅባት መለዋወጫ ጣቢያዎች በአዲስ አበባና ክልል ከተሞች መገንባቱን አስታወቀ፡፡

  ባለፉት ሁለት ዓመታት በአዲስ አበባ 32፣ በክልል ከተሞች 20 የሞተር ዘይትና የቅባት መለወጫ ጣቢያዎችን ከሽያጭ ወኪሎች ጋር በመተባበር በ40 ሚሊዮን ብር ወጪ ገንብቶ ወደ ሥራ ማስገባቱን ኩባንያው አስታውቋል፡፡ እያንዳንዱ ጣቢያ በአማካይ ለአሥር ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተገልጿል፡፡

  ቶታል ኢትዮጵያ በአዲስ አበባ መገናኛ አካባቢ አቶ ኤርሚያስ ይስሃቅ ከተባሉ የሽያጭ ወኪል ጋር በመተባበር በአራት ሚሊዮን ብር ያስገነባውን የሞተር ዘይትና የቅባት ሽያጭ ማዕከል፣ ማክሰኞ መስከረም 6 ቀን 2012 ዓ.ም. አስመርቋል፡፡

  በሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት የቶታል ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ሚስተር ቲቦ ለሲዩኧር ቶታል ኢትዮጵያ ያስገነባቸው የሞተር ዘይትና ቅባት ሽያጭ ማዕከላት፣ አሽከርካሪዎች ጥራት ያላቸው ምርቶች ከተያያዥ አገልግሎቶች ጋር እንዲያገኙ እንደሚያስችላቸው ተናግረዋል፡፡ ኩባንያው በመጪው ሁለት ዓመታት ተጨማሪ አንድ መቶ የዘይትና የቅባት መሸጫ ጣቢያዎች እንደሚከፍት የገለጹት ለሲዩኧር፣ ደንበኞች ጥራት ያላቸው ምርቶች ከማግኘታቸውም በላይ ለኢትዮጵያውያን የሥራ ዕድል እንደሚፈጥሩ ተናግረዋል፡፡

  ቶታልና ሌሎች የነዳጅ ኩባንያዎች የሞተር ዘይትና ቅባት ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ እጥረት እየገጠማቸው እንደሆነ ለሲዩኧር ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

  የውጭ ምንዛሪ እጥረት አጠቃላይ አገሪቱ የገጠማት ፈተና እንደሆነ ገልጸው፣ የነዳጅ ኩባንያዎች ለትራንስፖርት ዘርፍ ቁልፍ ሚና የሚጫወቱትን የዘይትና የቅባት ምርቶች ለማስገባት የሚያስፈልገውን የውጭ ምንዛሪ ማግኘት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ፣ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክና ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ኃላፊዎች ጋር በመመካከር ላይ እንደሆኑ ጠቁመዋል፡፡ ‹‹ቶታል ኢትዮጵያ ችግሩን ለመፍታት ከሚመለከታቸው የመንግሥት ኃላፊዎች ጋር ጥረት ያደርጋል እንጂ ሕገወጥ አማራጮች አይጠቀምም፤›› ብለዋል፡፡ በተፈጠረው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ሳቢያ የሞተር ዘይትና የቅባቶች ዋጋ መናሩ ይታወቃል፡፡

  እ.ኤ.አ. በ1950 የተመሠረተው ቶታል ኢትዮጵያ ላለፉት 69 ዓመታት የነዳጅ ውጤቶች፣ ዘይትና ቅባት ሲያከፋፍል ቆይቷል፡፡ በ2006 ዓ.ም. የሞቢል ኩባንያ ከኢትዮጵያ ሲወጣ የኩባንያውን ንብረቶችና ንግዱን ጠቅልሎ መግዛቱ ይታወሳል፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ 153 የነዳጅ ማደያዎች ሲኖሩት፣ 17 በመቶ የገበያ ድርሻ እንዳለው ለማወቅ ተችሏል፡፡

  - Advertisement -spot_img

  የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች