መምጫው በትክክል አይታወቅምና ከብዙ ነገሮች ራሱን ጠብቆ ጤናማ ሕይወት የሚኖር ሰው እንኳን በካንሰር ላለመያዝ ዋስትና የለውም፡፡ ሰበቡ ብዙ ነው፡፡ ሲለው በዘር፣ ሲለው በአመጋገብና ከመጠን ባለፈ ውፍረት እንደሚከሰት ይነገራል፡፡ ከመጠን ያለፈ የፀሐይ ብርሃንም የቆዳ ካንሰር ሊያመጣ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ውስብስብ ከሆነው የበሽታው ባህሪ በመነሳት ከአኗኗር ዘይቤ ጋር ተያይዞ የሚከሰት በሽታ ይሉታል፡፡ የበሽታውን መንስዔ ከአኗኗር ዘይቤ ጋር በደፈናው ማያያዙ በትክክል መምጫው የቱ እንደሆነ ለመረዳት አስቸጋሪ በመሆኑም ይመስላል፡፡
በየትኛውም የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙ ሰዎችን ያጠቃል፡፡ ገና መቆምና መቀመጥ እንኳ ያልጀመሩ ጨቅላ ሕፃናትንም አይምርም፡፡ የደም፣ የአንጎል፣ የአንጀት ካንሰር ተጠቂ ለሆኑ ሕፃናት ሕክምና ወጪን ለመሸፈን ዕርዳታ የሚጠይቁ፣ ፈጣሪ በምሕረቱ እንዲምርላቸው ዓለም አብሯቸው ጸሎት እንዲያደርግ የሚለማመጡ ወላጆችን በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ማየትም ተለምዷል፡፡
የተሻለ ኑሮ ከሚኖሩ ጥቂት የዓለም ሰዎች መካከል የሆኑ ከበርቴዎችም በካንሰር ሕይወታቸውን አጥተዋል፣ ወይም ማስታገሻ በሌለው ሕመም እየተሰቃዩ ነው፡፡ ለነገሩ በካንሰር ተይዞ መትረፍ ለጥቂት ዕድለኞች የተሰጠ ፀጋ እስኪመስል ካንሰር ብዙዎችን ሲያረግፍ ይስተዋላል፡፡
በአሁኗ ቅፅበት ውስጥ ይህንን ዓለም በሞት የሚለዩ ብዙዎች መጥፊያቸው ካንሰር ነው፡፡ የዓለም ጤና ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2017 ያወጣው ሪፖርት የሚያሳውም ይኼንኑ ነው፡፡ የተቋሙ ሪፖርት ካንሰር ቀዳሚው ገዳይ በሽታ መሆኑን አረጋግጧል፡፡ ነገር ግን ከመቶ ሰዎች መካከል እስከ 50 የሚሆኑት የሚሞቱት በቀላሉ ሊከላከሉት በሚቻል የካንሰር ሕመም ነው፡፡ በሽታው የአኗኗር ዘይቤን በመቀየር፣ ሌሎች ለካንሰር አጋላጭ ይሆናሉ ተብሎ ከተዘረዘሩ ነገሮች በመራቅ፣ አስቀድሞ መከላከል የሚቻል ነው ይባላል፡፡ ይሁንና እ.ኤ.አ. በ2015፣ 8.8 ሚሊዮን ሰዎች በካንሰር ሞተዋል፡፡ በሌላ አገላለጽ በዚያ ዓመት ከሞቱ ስድስት ሰዎች መካከል አንዱ በካንሰር ሞቷል ማለት ነው፡፡
በካንሰር በሽታ ከሚሞቱ 100 ሰዎች መካከል 70ዎቹ የሚሞቱት መካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የሚኖሩ ዜጎች ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ2018 በካንሰር ምክንያት የሞቱ ወንዶች የሳንባ፣ የጉበት፣ የሆድ ዕቃ፣ ፕሮስቴትና የኮሎሬክታል የካንሰር ዓይነቶች በብዛት ተገኝተውባቸዋል፡፡ በተመሳሳይ ዓመት ለሞቱ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሴቶች ሞት ምክንያት የተባሉትም የጡት፣ የሳንባ፣ ኮሎሬክታል፣ የማኅፀንና የሆድ ዕቃ ካንሰር ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2012 በመካከለኛና ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች ለተመዘገቡት 25 በመቶ የካንሰር ኬዞች በቫይረስ የሚተላለፉ የካንሰር ዓይነቶች እንደነበሩ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያሳያል፡፡ ሒውማን ፓፒሎማ ቫይረስ ለማኅፀን ጫፍ ካንሰር መንስዔ ሲሆን፣ የሂፒታይተስ ቢ ቫይረስ ደግሞ ለጉበት ካንሰር ይዳርጋል፡፡
ለሁለቱ ቫይረሶች ክትባት መስጠት በየዓመቱ የሚከሰቱ 1.1 ሚሊዮን የካንሰር ሕሙማንን ቁጥር መቀነስ ያስችላል፡፡ ሕመሙ ሥር ከመስደዱ በፊት የሚደረግ ሕክምናም በየዓመቱ የሚሞቱ 8.8 ሚሊዮን ዜጎችን ሊታደግ ይችል ነበር፡፡
ነገር ግን ሕክምናውም ክትባቱም ከባድ የካንሰር ጫና ላለባቸው ታዳጊ አገሮች የቅንጦት ያህል ነውና በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውን በማኅፀን፣ በሳንባ፣ በፕሮስቴትና በተለያዩ የካንሰር ዓይነቶች ይሰቃያሉ፣ እስከ ወዲያኛው ያሸልባሉ፡፡ በቀላል ሕክምና መዳን በሚችል በማኅፀን ጫፍ ካንሰር በርካታ እናቶች ሕይወታቸውን አጥተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በብቸኝነት የካንሰር ሕክምና በሚሰጠው በጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የሕክምና ወረፋ እስኪደርሳቸው እየጠበቁ በሽታው ሥር ሰዶባቸው ጎዳና ላይ ወድቀዋል፡፡ ተራ ደርሷቸው ሲደወልላቸውም የሞታቸው ዜና የተሰማላቸው ብዙ ናቸው፡፡
እ.ኤ.አ. በ2017 ዝቅተኛ ገቢ ባላቸው አገሮች የነበረው የካንሰር ሕክምና ተደራሽነት ከ30 በመቶ በታች ነበር፡፡ ባደጉት አገሮች የነበረው የሕክምናው ተደራሽነት ግን ከ90 በመቶ በላይ እንደነበር የድርጅቱ ሪፖርት ያሳያል፡፡ በዓለም ኢኮኖሚ ላይ በየዓመቱ የ1.16 ትሪሊዮን የአሜሪካ ዶላር ተፅዕኖ የሚፈጥረው ካንሰር በሕሙማኑ ላይ ደግሞ መድኃኒት የማያስታግሰው ስቃይ ሲከሰት ኖሯል፡፡
በኢትዮጵያ ሕክምናውን የሚሰጡ ሐኪሞች ቁጥር ከአንድ እንዲበልጥ፣ የተቋማትም ቁጥር ከአንድ ከፍ እንዲል የተለያዩ ሥራዎች ሲሠሩ ቆይቷል፡፡ በዚህ ረገድ የተከናወኑ ተግባራት በተወሰነ መጠን ለውጥ ማምጣትም ችለዋል፡፡ ሕክምናውን በየክልሉ ለማድረስም ሰፊ ጥረት እየተደረገ ይገኛል፡፡ አንድ ለእናቱ የነበረው የጨረር ሕክምና ማሽን ቁጥርም ወደ አምስት ከፍ ብሏል፡፡ ይሁንና ካለው የበሽታው ጫና አንፃር የሕክምናው ተደራሽነት ዓባይን በጭልፋ ያህል ነው፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ የምሥራቅ አፍሪካ የካንሰር ሕክምና ማዕከል በኢትዮጵያ እንዲገነባ እንቅስቃሴ ተጀምሯል፡፡ በምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የሚገኙ 200 ሚሊዮን አፍሪካውያንን የማከም አቅም እንዲኖው ተደርጎ ለሚገነባው ማዕከል 450 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልግ ታውቋል፡፡
ማዕከሉ በምሥራቅ አፍሪካ የልማት በየነ መንግሥታት (ኢጋድ) እንዲገነባ የተወሰነ ሲሆን፣ ለግንባታውም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል መሬት ማዘጋጀቱን፣ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግም የፖለቲካ ቁርጠኝነት ኢትዮጵያ እንዳላት ጤና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ለማዕከሉ ግንባታ የሚውል የገቢ ማሰባሰቢያ ዝግጅትም በአዲስ አበባ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል፡፡
በፍጥነት እንዲገነባ የታዘዘው ማዕከሉ በካንሰር ለሚሰቃዩ ሚሊዮኖች ዕፎይታ ይሆናል፡፡ የታዳጊ አገሮች የካንሰር ሕክምና አቅርቦትም አሁን ካለበት የተደራሽነት ደረጃ አንድ ዕርምጃ ፈቀቅ የሚያደርገው ይሆናል፡፡ ዜጎች የአልጋ ቁራኛ ከመሆን የሚገላግል እንደሚሆንም ይጠበቃል፡፡