የመንግሥት ፕራይቬታይዜሽንን ውሳኔ ከግራ ቀኙ ሲያነጋግር በዋለው የማኅበራዊ ጥናት መድረክ፣ በተለይ የኢንሽየቲቭ አፍሪካ መሥራችና ኃላፊ አቶ ክቡር ገና እና የገንዘብ ሚኒስቴር ከፍተኛ አማሪ ብሩክ ታዬ (ዶ/ር) ያደረጉት ክርክር ድረስ ሙግት በመድረኩ ታዳሚዎች ላይ ተጋብቶ ነበር፡፡ መድረኩ መንግሥት በከፊልም ሆነ ሙሉ ለሙሉ ወደ ግል በሚያዛውራቸው የልማት ድርጅቶች ጉዳይ ላይ ለመምከር የተጠራ ሲሆን፣ የመንግሥት አካላት፣ አንጋፋ የየዘርፉ ባለሙያዎችና ሌሎች ተሳታፊዎች መንግሥት ሊሸጥ ያቀረባቸው ድርጅቶች መሸጥ እንደሌለባቸው፤ ቢሸጡ እንኳን አሁን ጊዜው እንዳልሆነ የሚሞግቱ ሐሳቦች ሲያቀርቡ፣ የለም መሸጣቸው ተገቢ ነው ከሚሉ ወገኖችም የመንግሥትን አቅጣጫ ደግፈው የተከራከሩ ነበሩ፡፡ ምናልባትም መድረኩ በፕራይቬታይዜሽን ዙሪያ ጠንከር ያሉ ሙግቶች የቀረቡበት ነበር፡፡