Saturday, January 28, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሉህ (ለውህ) ከአገራችን ተጨባጭ ቅርሶች አንዱ

በተሾመ ብርሃኑ ከማል

በአገራችን ለቁጥር የሚያታክቱ ብዙ ተጨባጭ ቅርሶቻችን ጠፍተዋል፡፡ ዳግም ላይታወሱ ተረስተዋልም፡፡ ለምሳሌ ኢትዮጵያ ከብዙ አገሮች በፊት የራሷ የፊደል ቅርስ ያላትና በርካታ የዓለማችን ፊደላት ከእኛ የተወሰዱ እንደሆኑ ሲታወቅ፣ ነገር ግን ከ3,000 እና 4,000 ዓመታት በፊት ተማሪዎች ወይም ጸሐፍት በምን ላይ ይጽፉ እንደነበር አይታወቅም፡፡ አክሱም ሐውልት ላይ በግልጽና ውብ በሆነ ፊደል በጻፈች አገር የማስተማሪያና የመማሪያ ሒደቱ ምን እንደነበረ የሚገልጽ መረጃ ቢኖር እንኳ ስለመኖሩ የሚቀርብ መረጃ የለም፡፡ ያለፉትን አምስት መቶና ስድስት መቶ ዓመታት ታሪካችንን ስንመለከት የኦሪትም ሆነ የወንጌል ትምህርት ይሰጥ የነበረው በቃል ሲሆን፣ ጸሐፊ የሚሆነው አንድ ትልቅ የትምህርት ደረጃ ላይ ከተደረሰ በኋላ ነው፡፡ ስለሆነም ብዙዎቹ የቆሎ ተማሪዎች ማንበብ እንጂ መጻፍ ይቸግራቸው ነበር፡፡

‹‹ይህ ለምን ሆነ?›› ብለን ስንጠይቅ ‹‹የመማሪያው ማስተማሪያው ተዘጋጅቶ የተቀመጠ ብራና ሲሆን፣ ብራናውም በአብዛኛው ከአስተማሪው እጅ አይወጣም፡፡ በዕውቀቱ እጅግ የላቀና የተከበረ ተማሪ ከመሀል ሲወጣ ግን እርሱ እጅግ በጣም ጥንቃቄ በተመላበት ሁኔታ እንዲገለብጠው ይደረጋል፡፡ በብራና ላይ መጻፍ ብዙ ፍየል ብቻ ሳይሆን ብዙ ጊዜ የሚወስድና አድካሚ ሥራ የሚሆነው የፊደልም ሆነ የቃላት ስህተት ቢፈጠር ስህተቱን አጥፍቶ ማረም አስቸጋሪ በመሆኑ ነው፡፡ የድሮ ትምህርት ቤቶችም ሆነ የቆሎ ተማሪዎች አካባቢያቸውን ለቀው ስለሚመጡ እንኳንስ በየጊዜው ፍየል ሊያርዱ የዕለት ምግባቸውን የሚያገኙትም በልመና ነበር፡፡ እንዲህ እየሆነ ዕውቀት ሲተላለፍ መምጣቱ ሲታይ ከተዓምር የሚቆጠር ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያ ከነበሯትና በመጥፋት ላይ ከሚገኙት ተጨባጭ ቅርሶቿ አንዱ ለውህ (ሉህ) ነው፡፡ ሉህ ምን ያህል በኦሪት ወይም በወንጌል ትምህርት በአገልግሎት ላይ እንደነበር ጸሐፊው የሚያውቀው ባይኖርም በቁርዓን ግን ከጥንት ጀምሮ በአገልግሎት ላይ እንደዋለ እንረዳለን፡፡ በኢንሳይክሎፒዲያ ኢትዮፒካልም መጠነኛ ማብራሪያ ተሰጥቶታል፡፡

የዚህ ጽሑፍ መሠረታዊ ዓላማ ከጥንት ቅርሶቻችን አንዱ የሆነው ለውህ (ሉህ) አሠራርና ጥቅም ለማያውቀው ለማሳወቅ ሲሆን፣ በዚህም ጽሑፍ የሉህ ታሪክ ከጽሑፍ ታሪክ አንፃር፣ ሉህ ወይም ለውህ ምንድነው፣ የለውህ አዘገጃጀት፣ የሉህ ጥቅም፣ ለውህን ለጽሑፍ ማዘጋጀት፣ የመድ (በለውህ ላይ የሚጻፍበት ቀለም) አዘገጃጀት፣ የቀሰም (መጻፊያ፣ ብርዕ) አዘገጃጀት፣ በለውህ የሚጽፍ ማነው? ሲጻፍ የሚደረግ ጥንቃቄ የሚሉ ሐሳቦች ተካተዋል፡፡

የሉህ ታሪክ ከጽሑፍ ታሪክ አንፃር

በብዙ የሥነ ጽሑፍ የቀረቡ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት የተጀመረው ሰዎች ለሰዎች ሐሳባቸውን በምልክት፣ ወይም ቀስ በቀስ በመጣ ጽሑፍ መግለጽ ከጀመሩበት ጊዜ ነው፡፡ ከታሪክ በፊት የነበሩ ሰዎች ይህንንም መልዕክት ያስተላልፉት የነበረው መሬት ላይ፣ በድንጋይ ላይ፣ በሸክላ ላይ ሲያስተላልፉ ነበር፡፡ ሐሳብን በሰሌዳ፣ በብራና፣ በወረቀት፣ በብረት፣ በነሐስ፣ በብር፣ በወርቅ… ጽሑፍ መግለጽ ከተጀመረበት ጊዜ ወዲህ ደግሞ የራሱን ዕድገት ቀጥሏል፡፡  ከ3,000 – 6,000 ዓመታት (ቅክ) በነበረው የታሪክ ሒደት ጥንታዊት ኢትዮጵያን፣ ሱሜሪያን (ደቡብ ሜሶፖታሚያ)፣ ጥንታዊት ግብፅ፣ ግሪክ፣ ሮማ፣ ቻይና ይወሳሉ፡፡

በተለይም የኢትዮጵያ ፊደላት የአብዛኛዎቹ አገሮች ፊደላት እናት ተብሎ እንደሚጠራ በዚህ አጋጣሚ ማውሳት ተገቢ ነው፡፡ ስለሆነም ለጽሑፍና ለሥነ ጽሑፍ የሚያገለግሉን ፊደላት የአሁኑን ቅርፅ ለመያዝ 6,000 ዓመት እንደወሰደባቸውና ወደፊትም ለውጡ እንደሚቀጥል ይታወቃል፡፡ የጽሑፍ ዋነኛ አገልግሎት መረጃን ለዘመኑና ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ ሲሆን፣ በዚህ ረገድ ጽሑፉ የሚያርፍባቸው ሰሌዳዎችም ከፊደል ያልተናነሰ አስተዋጽኦ እንዳላቸው እንረዳለን፡፡ ከእነዚህም የመጻፊያ ሰሌዳዎች መካከል ለውህ አንዱ ነው፡፡ የታሪክ መረጃዎቻችንን ፈልገንና አፈላልገን እስክናገኝ ድረስ ለጊዜው በለውህ ማለትም በጠፍጣፋ ድንጋይ ወይም ሸክላ ወይም ጣውላ መጻፍ በኢትዮጵያ መቼ እንደተጀመረ ማወቅ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ በግብፅ ግን ከ3,000 (ቅክ) ዘመን በፊት እንደ ተጀመረ አንዳንድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡

ሉህ ወይም ለውህ ምንድነው?

ሉህ ወይም ለውህ የሚለው ቃል ከቁርዓን ንባብ ጋር በተያያዘ ትርጉሙ ሕፃናት ቁርዓን ቤት ሲገቡ ከዓረብኛ ፊደል ጀምሮ እስከ መጀመርያው ክፍል ድረስ (ቁርዓን 114 ምዕራፎችና 30 ክፍሎች አሉት) እየጻፉ የሚጠቀሙበት ከጣውላ የተሠራ ሠሌዳ ነው፡፡ ጣውላው ከልዩ ልዩ ዕፅዋት መሥራት የሚቻል ሲሆን በአገራችን ከወይራ፣ ከዋንዛ፣ ከዝግባና ከመሳሰሉት ዛፎች ይዘጋጃል፡፡ የለውህ መጠን እንደ ሕፃናቱ አቅም ወይም እንደ ወላጆች አቅርቦት የሚለያይ ቢሆንም፣ በአብዛኛው ቁመቱ እስከ 50 ሳንቲ ሜትር (አንድ ክንድ)፣ ወርዱ ደግሞ እስከ 25 ሳንቲ ሜትር ወይም አንድ ስንዝር ከጋት ሊሆን ይችላል፡፡ ውፍረቱም ከሦስት እስከ አምስት ሳንቲ ሜትር ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ የሚሰፋ ወይም የሚጠብ ሊሆን ሲችል ሕፃናት ከሆኑ መጠኑ 30 20 ሳንቲ ሜትር ሊሆን ይችላል፡፡ የለውሁ መስፋትና መጥበብ በሚጻፈው የቁርዓን አንቀጾች ላይ ተፅዕኖ ሊያደርግ ይችላል፡፡ ማለትም ትንሽ ከሆነ ትንሽ ይጻፍበታል፡፡ ትልቅ የሆነ ደግሞ ብዙ ይጻፍበታል፡፡

የለውህ አዘገጃጀት

ለውህ ለቁርዓን መጻፊያ አገልግሎት ከመዋሉ በፊት ጥሩ ጣውላ ሊወጣው የሚችል ቀጥ ያለ ግንድ ይመረጣል፡፡ ያም ግንድ በግማሽ ሜትር ልክ ይቆረጥና ይሰነጠቃል፡፡ አንድ ጉራጅ እንደ አንድ ግንዱ ትልቅነትና አዘጋጁ ችሎታ አራትም አምስትም ሊወጣው ይችላል፡፡ አንዱ ስንጣቂም በሰላጤ (መጥረቢያ) ቅርፊቱ፣ ጎባጣ አካሉ (ዛፍ የክብነት ባህርይ እንዳለው ልብ ይሏል) ይጠረባል፡፡ ከዚያ ሲፈለጥ ወይም ሲተረተር የሚፈጥረው አባጣ ጎባጣ ይስተካከላል፡፡

ለውህ ተጠርቦ ለመዝጊያ ወይም ለሌላ አገልግሎት ከተዘጋጀ ጣውላም እንደ አስፈላጊነቱ ሊዘጋጅ ይችላል፡፡ ከተዘጋጀ ጣውላ የሚሠራ ከሆነ አስቀድሞ መታየት የሚኖርበት የጣውላው ባህርይ ነው፡፡ ቀለም የሚበትን ከሆነ አያገለግልም፡፡

ለውህ ከላይ ራስ፣ ከታች እግር የሚሠራለት ከሆነ አስቀድሞ ወይም ሁሉም ነገር ከተስተካከለ በኋላ ሊበጅለት ይችላል፡፡ ከላይ አንገት ያለው ወይም የሌለው ራስና ከሥር አንድ እግር የሚደረግለት ዋነኛ ምክንያት በራሱ ለማንጠልጠል፣ በእግሩ ቁርዓን የተጻፈበት ለውህ መሬት እንዳይነካ ሲሆን ራስም ሆነ እግር የሌለውም ሊሆን ይችላል፡፡

የለውህ መልክ ከያዘ በኋላ የመጨረሻ ሥራ በቀለም እየተጠቀሰ ለመጻፍ የሚያስችል እስኪሆን ድረስ፣ በባልጩት ድንጋይ፣ በጠርሙስ ሱፋጭ፣ በቢላዋ ወይም በሌላ ብረት ነገር ልሙጥ እስኪሆን ድረስ ይለሰልሳል፡፡ በመጨረሻም ራስ ካለው ራሱ ይበሳና የክር መንጠልጠያ ይደረግበታል፡፡ በመጨረሻም ክው ብሎ ይደርቃል፡፡

የሉህ ጥቅም

ለውህ መሠረታዊ አገልግሎቱ አንድን ጽሑፍ ከመገኛ ምንጩ (በማተሚያ ቤት ከታተመ ቁርዓን ወይም ከብራና፣ ወይም ከተራ ወረቀት) የሚገለበጥበት ነው፡፡ በራሱ በተማሪው ወይም በአስተማሪው ወይም በተማሪው ረዳት የተገለበጠው ጽሑፍንም ተማሪው ደጋግሞ እንዲያነበው በማድረግ ያጠናበታል፡፡ ስለሆነም በለውህ ላይ የተጻፈ ጽሑፍ አስተማሪው በበቂ ሁኔታ ተጠንቷል ብሎ አስተማሪው ወይም አስጠኝው ሲያምን የተጻፉትን አንቀጾች በማጠብ ይጠፋና ሒደቱን ተከትሎ ሌላ ይጻፍበታል፡፡

የለውህ ሌላው አገልግሎቱ ወጪን የሚቆጥብ መሆኑ ነው፡፡ ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው ለውህ የሚሠራው ከጣውላ ሲሆን፣ ይህም ጣውላ በጥንቃቄ ከተያዘ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሊተላለፍ ይችላል፡፡

የሚቀለመው በነጭበረቅ ወይም በኖራ ወይም ልም በሆነ ነጭ አመድ ስለሆነና ቀለሙም በራሱ በተማሪው የሚዘጋጅ ስለሆነ ወጪው አነስተኛ ነው፡፡ ይህን በወረቀት ብንተምነው ብዙ ደብተሮችንና እስክሪፕቶዎችን የሚጠይቅ ነው፡፡ ደብተሩና ቀለሙ በገንዘብ ሲሰላ ምን ያህል ሊሆን እንደሚችል እንደ ዘመኑ ማስላት ይቻላል፡፡

ለውህ በአንድ ገጽ የሠፈረ ጽሑፍ ተደጋግሞ የሚጠናበት በመሆኑ አዕምሮን በአንድ አቅጣጫ አሰባስቦ በቃል ለመያዝ ጠቀሜታ አለው፡፡ ስለሆነም አንድ ልጅ በመጽሐፍ ቢያጠና ሌሎች አስፈላጊ ያልሆኑ ገጾችን በማገላበጥ የሚያባክነውን ጊዜ ለመቆጠብ ይረዳዋል፡፡

በአሁኑ ጊዜ የቁርዓን ተማሪዎች የሚጠቀሙት ራሱን ቁርዓኑን ሲሆን፣ ልጆች በመሆናቸው በሚገባው ክብርና ጥንቃቄ የማይዙት ከመሆናቸውም በላይ በአንድ ቀን ሊቀዳድዱት ይችላሉ፡፡ አንድ ቦታ ሲጫወቱ ካስቀመጡበት ረስተውት ከሄዱ አንድም ከማይገባው እጅ ይገባል ሁለትም ይጠፋና ሌላ ወጪ ያስወጣል፡፡

ለውህን ለጽሑፍ ማዘጋጀት

የተዘጋጀው ለውህ እንደዛፉ ባህርይ ጥቁር፣ ቀይ፣ ወደ ቢጫ ያደላ፣ ወዘተ ሊሆን ስለሚችል በጣም የላመ ኖራ (limestone) ይቀባል፡፡ አንዳንድ ልጆችም ልም የሆነ ነጭ አመድ ሊቀቡት ይችላሉ፡፡ ከተገኘ በኖራ ቢቀባም ይሆናል፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቢሆን ነጭ የብረት ቀለም ቀብቶ ለብዙ ጊዜ መገልገል በተቻለ ነበር፡፡ በኖራና በመሳሰሉት የሚቀባው ግን በአቀባቡ ምክንያት ቀለም እንዳያወርድ ወደ ጎን የሚሄድ መስመር ማበጀት አስፈላጊ ሊሆን ይችላል፡፡ ኖራ ከተቀባ በኋላ ክው ብሎ እስኪደርቅ ይጠበቃል፡፡ ምናልባት በደንብ ያልላመ ኖራ እንዳይኖርና መጻፊያውን (ቀሰሙን) በቀላሉ ለመጻፍ እንዲያስችለው በእጅ መወልወል ይኖርበታል፡፡ ይህ ከሆነ በኋላ ቀለም (መድ) እያጠቀሱ በቀሰሙ መጻፍ ነው፡፡ እዚህ ላይ መጠቀስ የሚገባው ጠቃሚ ነገር መስመር በሌለው ሰሌዳ መጻፍ፣ በተለይም ለሕፃናት ቀላል ባለመሆኑ ብዙ ጊዜ በግራ በኩል መዛባት ሊከሰት ሲችል ጠንቃቃ ጸሐፊዎች ግን ቀጥ ባለ መስመር ይጽፋሉ፡፡

ይሁንና በሉህ ላይ የሚጻፈው የፈጣሪ ቃል እንደመሆኑ መጠን ከተጠና በኋላ የተለየ ንፁህ ቦታ ተመርጦ ይታጠባል፡፡ በተገኘው ቦታ ሁሉ ማጠብ አይቻልም፡፡ ብዙ ጊዜም የተጻፈውን በመላስ ማጥፋት ይችላል፡፡ ይህም የሚደረገው አዕምሮ ያሰፋል፣ ልቦናን ብሩህ ያደርጋል በሚል ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎችም ከብዙ ሕመም ይፈውሳል ብለው ያምናል፡፡

መድ (በለውህ ላይ የሚጻፍበት ቀለም) አዘገጃጀት

መድ የሚባለው ቀለም ሲሆን ይህም ቀለም የሚዘጋጀው በራሱ በቁርዓን ተማሪው ነው፡፡ መድ አንድም ከጥላሸት ማለትም ከብረት ምጣድ ከሚጠረግ፣ ወይም የኩራዝ ጥላሸት ከሚጠራቀምበት ተወስዶ፣ ወይም ከሰል አድቅቆ በመቀጥቀጥ ወይም በባትሪ ድንጋይ በሚገኝ ከሰል ወይም ገብስ አሳርሮ በመፍጨት፣ በትንሽ ሰርዲን ቆርቆሮ ወይም ከሸክላ በውኃ ይበጠበጥና በቀላሉ እንዳይለቅ ሙጫ ይደረግበታል፡፡ በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ሦስት ቃላት ለዚህ ትውልድ፣ በተለይም ለከተማ ነዋሪው ግልጽ ላይሆኑ ይችላሉ፡፡ እነርሱም የብረት ምጣድ ጥላሸት፣ የኩራዝ ጥላሸትና ሙጫ የሚሉት ናቸው፡፡ የብረት ምጣድ (ከላሜራ ወይም ከበርሜል ቁራጭ የሚሠራ ክብ የሆነ ምጣድ) ለቆሎ መቁያ ወይም ለቂጣ መጋገሪያ ይጠቅማል፡፡ ጥላሸት የሚባለው እንጨት በማንደድ ቡናና ቆሎ የሚቆላበት፣ ቂጣ የሚጋገርበትና አስፈላጊም ከሆነ እንጀራ የሚሞቅበት ጊዜ በሚፈጠር ጭስ (ካርቦን) የብረት ምጣዱ ጀርባ ይጠቁራል፡፡ ጥቁረቱም በየጊዜው ይቀጥልና ጥቁር ግግር ሊፈጥር ይችላል፡፡ ይህ የጢስ ግግር ጥላሸት ሲባል ይህም ጥላሸት አንድም በሸምበቆ ስንጣቂ ወይም በእንጨት ፍላጭ እየተገፈፈ (እየተላጨ ወይም እየተጠረገ) ይጠራቀማል፡፡

ከኩራዝ የሚገኝ ጥላሸትም እንዲህ እንደ ዛሬ ኤሌክትሪክ ወይም የሶላር ኃይል ሳይፈጠር ሰዎች በጨለማ መብራት የሚጠቀሙት ከትንንሽ ጣሳዎች በተሠሩ ኩራዞች ናፍጣ (ነጭ ጋዝ፣ ጋዞሊን) ይከቱና ክሩ እንዲነከር ያደርጋሉ፡፡ ያ ክር የእስክሪፕቶ ቅርፅ ባለው የቆርቆሮ ዘንግ እንዲወጣ በማድረግ በክብሪት ይለኮሳል፡፡ ጋዝ የተነከረው ክር ሲቃጠል ብዙ ጭስ ስላለውና ቤቱን ስለሚሞላ ግድግዳ ላይ ከኩራዙ ከፍ ያለ በእንቁላል ቅርፅ መቀመጫ ይሠራለታል፡፡ ምናልባት ቀላል ይሆን እንደሆነም የሾርባ መጠጫ መጠነኛ ሸክላ የሆነ ጎድጓዳ ሰሃን ግድግዳ ላይ በጭቃ ይሠራል ማለት ነው፡፡ በዚህም መሠረት ኩራዙ ጋዝ የተነከረው፣ የጋዙ ክር ሲድ የሚያወጣው ጭስ ከመቀመጫው የላይኛ ክፍል ይጠራቀማል፡፡ የኩራዝ ጥላሸት ሲጠራቀም ተዘቅዝቆ የተለጠፈ ስኒ ሊመስል ይችላል፡፡ ለወጣቱ ምሁር ስታላክታይትስ (Stalictites) የሚመስል ማለት የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡

ከሁሉም የጥላሸት ወይም የከሰል ውጤቶች የተገኘውን ቀደም ሲል ልም መሆኑን አስቀድሞ በማረጋገጥ በመያዣ በመበጥበጥ ሙጫ መጨመር ነው፡፡ ሙጫ (Resin) ከዛፍ ቅርፊት በላይ የሚገኝ የማጣበቅ ባህርይ ያለው ሲወጣ፣ በፈሳሽ መልክ ማለትም በፋብሪካ የመዘጋጀውን ሙጫ (ገም) መስሎ በኋላም ቀስ በቀስ እንደ ዕጣን የሚደርቅና የዕጣንና የከርቤ ዝርያ ነው፡፡ ብዙ ጊዜም ተመራጭነት የሚኖረው የግራር ሙጫ መሆኑን ጸሐፊው ከሕይወት ልምዱ ዓይቶታል፡፡ ከርቤም ቀለሙ በሰሌዳው ላይ ሲጻፍ እንዳይለቅ በማድረግ ረገድ በጣም ተመራጭ ነው፡፡

የቀሰም (መጻፊያ፣ ብርዕ) አዘገጃጀት

ቀሰም (መጻፊያ፣ ብርዕ) የሚዘጋጀው የእስክሪብቶ መጠን ያለው ለጋ ሸንበቆ፣ በአንድ በኩል ተቀርፆ የመንጎል ወይም ቀለም እየጠጣ የሚጻፍበት ብዕር ቅርጥ ይዞ ይዘጋጃል፡፡ ወይም የትልቅ ሸንበቆ አንድ አንጓ ለአምስት ስድስት ከተሰነጠቀ በኋላ በጦር ቅርፅ ተቀርፆ መሀሉን በመሰንጠቅ ለመጻፊያ አገልግሎት ይውላል፡፡ ከቀሰም የሚሠራው መጻፊያ አንድም ከደረቀ ሸንበቆ ይሠራል፡፡ ያለበለዚያም ቅርፅ ከወጣለት በኋላ ሊደርቅ ይችላል፡፡ የብርዕ ጫፍ እንደ ጸሐፊው ፍላጎት ወይም ለውሁ ሊይዝ በሚፈለገው መጠን እንዲይዝ ሊወፍር ወይም ሊቀጥን ይችላል፡፡ ወፍራም ከሆነ በአንድ ከቀኝ ወደ ግራ የሚጻፍ መስመር ከአምስት እስከ ስድስት ቃላት መጻፍ ሲቻል ቀጭን ከሆነ ግን እስከ አሥር መስመር መጻፍ ይቻላል፡፡ ከላይ እስከ ታች (ከራስ እስከ እግሩ) የሚይዘውም በዚያው መጠን ሊያንስና ለጨምር ይችላል፡፡

በለውህ የሚጽፍ ማነው?

የቁርዓን ትምህርት ከሕፃንነት ዕድሜ ማለትም ከአራትና አምስት ዓመት ዕድሜ ጀምሮ ወደ ቁርዓን ቤት ተኪዶ የሚቀራ ሲሆን፣ ሕፃናት በመጀመርያ የዓረብኛ ፊደላት እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ከዚያም አቀራሩን ይማራሉ፡፡ ወደ መጻፍ ከመሄዳቸው በፊት የተወሰነ የቁርዓን ምዕራፍ በቃላቸው እንዲያጠኑ ይደረጋል፡፡ ከዚም በለውህ ላይ የተወሰኑ አንቀጾችን እየጻፉ ማንበብ ይጀምራሉ፡፡ ጥናት የሚጀመረው ከቁርዓን አነስተኛ ምዕራፎች ማለትም ከአንድ መስመር፣ ሁለት መስመር፣ ሦስት መስመር እያለ እስከ ብዙ መስመር የሚያድግ በመሆኑና ቀስ በቀስ ከአዕምሯቸው ዕድገት ጋር እየተጣጣመ የሚሄድ በመሆኑ ለልጆች አይከብድም፡፡ እንዲያውም ጎበዞች ማለትም በቃል የመያዝ (ሐፊዝ የመሆን ችሎታ ካላቸው) በቃል የጀመሩትን፣ በጽሑፍም እስከ መጨረሻው ሊቀጥሉ ይችላሉ፡፡ በቃል እንዲማሩ ከሚደረግባቸው ምክንያቶች አንዱ አቀራሩን እንዲለማመዱ ለማድረግ ነው፡፡ የቃል ጥናቱ ከ30ዎቹ ክፍለ ቁርዓኖች አንዱን እንዲይዙ ቢደረግ 29ኙን በሚገባው ዓይነት ድምፅ የመቅራት እንዲችሉ ይረዳቸዋል፡፡

ሲጻፍ የሚደረግ ጥንቃቄ

በለውህ ላይ የሚጻፍበት ምክንያት እንዲጠና ማለትም በቁርዓኑ ላይ በተጻፈው ድምፀት መሠረት ጭምር እንዲታወቅ፣ በልቦና እንዲያዝ፣ የፈጣሪን ቃል በትክክል ለመቀበልና ለማስተላለፍ ተብሎና ታስቦ የሚዘጋጅ እንደመሆኑ የሚጻፈውም የዚያን ያህል ጥንቃቄ ተደርጎ ነው፡፡ ሆኖም የድምፅ የማስረዘሚያ፣ የማሳጠሪያ፣ የማጥበቂያ፣ የማላሊያ፣ የማስቆሚያና ሳይቆሙ የመቀጠያ (አያይዞ በማንበብ) ምልክቶች በቁርዓን ላይ ቢኖሩም ተማሪዎቹ ሕፃናት በመሆናቸው፣ በሰለሌዳው ላይ ሁሉንም ነገር ማስፈር ስለማይችሉ አነባበቡን የሚማሩት ከተመደቡላቸው በትምህርታቸውና በዕድሜያቸው ከፍ ካሉ ተማሪዎች ወይም ከአቅሪዎቹ (አስተማሪዎቹ/ኡስታዞቹ) አማካይነት ነው፡፡ ስለሆነም ተማሪዎቹ ከቁርዓን ወደ ሰሌዳው የሚያጠኑትን ክፍል መጠን ከጻፉ በኋላ አንድም ወደ ተመደቡላቸው አስተማሪዎች ወይም ወደ ዋናው ሸኽ በመሄድ አቀራራቸው ጥሩ መሆኑና አለመሆኑ፣ ወይም ቀጥሎ በሚብራራው መንገድ ማለትም በተጅዊድ መሠረት መነበቡን ያረጋግጣሉ፡፡ በቃላቸው ለመያዝ ጮክ ብለው ሲቀሩ የድምፅ ስህተት ከፈጠሩ ሸኹ (አስተማሪው/ኡስታዙ) ሰምተው ያስተካክላሉ፡፡ ሸኾች ተማሪዎቻቸቸው ሲሳሰቱ ሰምተው የማረም ችሎታቸው ከፍተኛ ብቻ ሳይሆን አስገራሚ ነው፡፡  ለመሆኑ ተጅዊድ ምንድነው?

ተጅዊድ ማለት በአጭሩ ቁርዓንን በጅብሪል (ገብርኤል) አማካይነት ለነብዩ ሙሐመድ (ሱዓወ) እንደወረደ በትክክል፣ ደግሞም ውብ በሆነ ድምፅ በተሟላ መልክ ለማንበብ የሚያስችል ሥርዓት ማለት ሲሆን፣ ይህም ማለት መቶ በመቶ አቀራሩ ይመጣል ማለት አይደለም፡፡ አብዛኛውን ጥሩ ቁርዓን ቀሪ ከመቶ ሲሰላ ሃምሳ በመቶ ቢሆን እጅግ በጣም የተራቀቀ ዕውቀት ያላቸውም ቃሪኦች ከ90 በመቶ ማለፍ ይቸግራቸዋል፡፡ መቶ በመቶ መቻላቸውን ማረጋገጥ የሚችልም (ከነብዩ በስተቀር) የለም፡፡ ስለዚህም ተጅዊድ ወደ ጥራት የሚወስድ መንገድ እንጂ የሚያደርስ አይደለም ማለት ይቻላል፡፡

በቁርዓን ትምህርት ቤት የተጅዊድ ሥርዓት መዘርጋት ያስፈለገበት ምክንያት ዓረብኛ ቃላት ተመሳሳይ ፊደላት ቢኖራቸውም ሲጠብቁና ሲላሉ፣ ረዘም ብለው ሲነበቡና አጠር ብለው ሲነበቡ፣ አያይዞ ሲነበቡና በሐረጎች መካከል ቆም ተብሎ ሲነበቡ የተለያየ ትርጉም ስለሚኖራቸው ነው፡፡

ተጅዊድ ከዚህም በተጨማሪ የጉሮሮና የላንቃ ቃላት በትክከል መውጣት እንዳለባቸው የሚያስተምር መሣሪያ ነው፡፡ ለምሳሌ ሀ እና ሓ፣ አ እና ዓ፣ ከ እና ኸ፣ ዘ (ዛል) እና ዘ (ዘይ)፣ (ዳል) እና ደ (ዷድ)፣ (ሳእ)፣ (ሲን)፣ (ሷድ)፣ (ቃፍ) እና ቐ (ቓይን) ወዘተ ድምፀታቸው ይለያያል፡፡ ምናልባት በቀላል ምሳሌ መግለጽ ይቻል እንደሆን የግዕዝ ፊደላትን በግዕዝ፣ በዓማርኛ፣ በትግርኛና በሐረሪኛ ስንጠቀምባቸው እንደሚለያዩት ማለት ነው፡፡ ይህም ሆኖ በአገራችን  የቁርዓን ተማሪዎች ምን ያህል በትክክል እንደሚያነቡ የሚገልጽ ጥናት ተደርጎ ከሆነ የወጣ መረጃ ይኖር እንደሆን ገና ወደ አደባባይ አልወጣም፡፡ ከሌለ ግን ማጥናት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊው አንጋፋ ጋዜጠኛ፣ ደራሲ፣ የእስልምና ጉዳዮች ተመራማሪ፣ እንዲሁም የታሪክ አጥኚ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእሳቸውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles